የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሉቃስ 1፡1-4 እና የሐዋ. 1፡1-2 እንብብ። ሉቃስ ወንጌሉን ለማን እንደ ጻፈ ነው የገለጸው? ለ) የሐዋ. 28፡30-31 አንብብ። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው የመጨረሻው ክስተት ምንድን ነው?
በሉቃስም ሆነ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ደራሲው መጽሐፉን የጻፈው፥ «ቴዎፍሎስ» ለሚባል ሰው ነው። «ቴዎፍሎስ» ማለት «የእግዚአብሔር ወዳጅ» ማለት ስለሆነ አንዳንድ ሰዎች ይህ «የእግዚአብሔር ወዳጅ ለሆኑ ክርስቲያኖች» የተጻፈ ነው ብለው ያስባሉ። ይህ ግን ትክክል አይመስልም። ቴዎፍሎስ ሉቃስ በደንብ የሚያውቀው ከአሕዛብ ወገን የሆነ ሰው ሳይሆን አይቀርም። አንዳንድ ምሑራን ቴዎፍሎስ ሉቃስ ወደ ክርስቶስ ያመጣው አማኝ ክርስቲያን ሳይሆን እንደማይቀር ያስባሉ። ሉቃስ «ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ» ብሎ ስለሚጠራውና ይህም የሮማውያን የማዕረግ ስም ስለሆነ፣ ቴዎፍሎስ አሕዛብ ምናልባትም ሮማዊ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ። ምናልባትም ሀብታም የሮም ባለሥልጣን ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ምሑራን ቴዎፍሎስ ለሉቃስ ገንዘብ በመስጠት የሉቃስ ወንጌልና የሐዋርያት ሥራ ታትሞ በዓለም እንዲሰራጭ እርዳታ አድርጓል በማለት ይናገራሉ። ይህ በጥንት ዘመን የተለመደ አሠራር ነበር። አንዳንድ ምሑራን ሉቃስ ቴዎፍሎስን ለማሳመን ወይም አዲስ ክርስቲያን ስለ ማድረጉና ክርስቶስን ስለ መከተል ለማስተማር ሲል መጽሐፉን እንደ ጻፈ ይገምታሉ።
ቴዎፍሎስ የሉቃስ ወንጌል የመጀመሪያው ተቀባይ ቢሆንም፣ ሉቃስ መጽሐፉ በብዙ ሰዎች እንደሚነበብ ያውቅ ነበር። ሉቃስ መጽሐፉን የጻፈው የአይሁድን ባሕል ለማያውቁ አሕዛብ ነው። እርሱም በመጽሐፉ ውስጥ ወንጌል አሕዛብን ጨምሮ ለሰዎች ሁሉ መሰበክ አለበት በሚለው እውነት ላይ ያተኩራል። አንዳንድ ምሑራን ሉቃስ የቀድሞ አምልኮአቸውን ትተው እግዚአብሔርን በመፍራት ለሚኖሩ አሕዛብ እንደ ጻፈ ያስባሉ። እነዚህ አሕዛብ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተገለጠውን አንድ አምላክ ለመቀበል ፈቃደኞች ቢሆኑም፥ ተገርዘው አይሁድ ለመሆን ግን አልፈለጉም ነበር ( የሐዋ. 13፡16)። ምንም እንኳ የሉቃስ ወንጌል ክርስቲያኖችን ለማስተማር የተጻፈ ቢሆንም፣ ክርስትና በአፈ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው ለሚለው ክስም መልስ ይሰጣል። አንዳንድ ምሑራን ሉቃስ ክርስትና ሕጋዊ ሃይማኖት ሊሆን የሚገባው እንጂ፥ ስጋትን እንደሚያስከትል ተቆጥሮ መሰደድ እንደ ሌለበት ለአሕዛብ ለማሳየት የተጻፈ ነው ይላሉ።
ምንም እንኳ ጳውሎስ ከማንም በላይ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ መጻሕፍትን ቢጽፍም፣ በገጽ ብዛት ግን ሉቃስን የሚወዳደር የለም። የሉቃስ ወንጌልና የሐዋርያት ሥራ በአንድነት ቢደመሩ የጠቅላላው አዲስ ኪዳን ሲሶ ይሆናሉ። የሉቃስ ወንጌል በአዲስ ኪዳን ውስጥ በርዝመቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሲሆን፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ከሌሎች ሁሉ ጠለቅ ያለ መልእክትን ያስተላልፋል።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)