የሉቃስ መግቢያ

አስፋው የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበር። አንድ ቀን መምህሩ፡ «እናንተ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ በሮማውያን የተገደለ ጥሩ ሰው እንደ ነበረ እንጂ አምላክ እንዳልነበረ ማወቅ አለባችሁ። ሌላው ነገር ሁሉ ሰዎች የጻፉት ነው። ስለ ኢየሱስ ተአምራት፣ ስለ አምላክነቱና ስለ ትንሣኤው የሚነገረው ሁሉ፥ የጥንት ተከታዮቹ በዚህ አስቸጋሪ ዓለም ውስጥ መጽናኛ እንዲሆንላቸው የተናገሩትና የጻፉት ታሪክ ነው» ሲል ተናገረ።

የውይይት ጥያቄ:- ያመንነው ነገር ሁሉ በአፈ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ እምነታችን ምን በሆነ ነበር? ኢየሱስ ክርስቶስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፈው መሠረት እንደነበረና ስለ እርሱ የሚናገሩ ታሪኮች እውነት መሆናቸውን ማወቁ ለምን ይጠቅማል? ለ) 1ኛ ቆሮ. 15፡12-19 አንብብ። ጳውሎስ ኢየሱስ ከሞት ካልተነሣ የክርስትና እምነት ምንድን ነው ይላል? ሐ) ሉቃስ 1፡1-4 አንብብ። ሉቃስ በወንጌሉ ውስጥ የጠቀሳቸው ታሪኮች፥ እውነት እንጂ አፈ ታሪክ አለመሆናቸውን የሚያሳይ ምን ነገር ተናገረ?

ኢየሱስ ክርስቶስ ከ2000 ዓመታት በፊት የኖረ እውነተኛ አምላክና እውነተኛ ሰው እንደሆነ በትክክል ማወቁ አስፈላጊ አይደለም ብለው የሚያስቡ፥ አንዳንድ ክርስቲያኖች አሉ። በእርሱ ካመንንና ስለ እርሱ የሚናገሩ ታሪኮች የሚያበረታቱን እስከ ሆኑ ድረስ፣ እነዚያ ታሪኮች በሰዎች የተጻፉ ቢሆኑም እንኳ አሳሳቢ አይሆንም ብለው ያስባሉ። ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ ከላይ እንደ ምሳሌ የተጠቀሰው የዩኒቨርስቲ መምህር ያቀረበውን ዓይነት አሳብ ቢስማሙበትም፥ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይሆን ወይ? የሚለው ጥያቄ አያስጨንቃቸውም፡ «ይህ ምሑራን የሚያቀርቡት ክርክር ነው፡፡ — እኛ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየዘመርን ለመደሰት እንፈልጋለን። ጥሩ ስሜትም ይፈጥርልናል» ብለው ይናገራሉ።

ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ከመሆኑም በላይ ፈቃዱንም የሚገልጽ እውነተኛ መጽሐፍ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስን የምንጠራጠር፥ ዐበይት ስሕተቶችና በሰዎች የተጻፉ ታሪኮች ያሉበት መጽሐፍ እንደሆነ አድርገን የምናስብ ከሆን፣ እምነታችን የተመሠረተው ባለማስተዋል ላይ ነው ማለት ነው። ይህን የምናደርግ ከሆነ ከሌሎች የዓለም ሃይማኖቶች ከሚባሉት በምንም አኳኋን እንደማንለይ መረዳት ይኖርብናል።

ከልብ ማወቅ ያለብን ክርስትና ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ብቸኛ ሃይማኖት መሆኑን ነው። ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው አሳብ ሁሉ እውነት እንደሆነና ሰዎች ከአእምሮአቸው አፍልቀው ያልጻፉት መሆኑን ያምናሉ። እምነታችን የተመሠረተው ተአምራትን በሠራውና ወደ እግዚአብሔር የሚወስደውን መንገድ ባስተማረው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነው። ይህ ኢየሱስም በመስቀል ላይ ሞቶአል፥ ተቀብሯል፥ ከሙታንም ተነሥቷል። ከእነዚህ ነገሮች አንዱም እንኳ ልብ ወለድ ሲሆን፥ እምነታችን ስሜታዊ ብቻ በሆነ ነበር። ባዶ ከበሮ ከፍተኛ ድምፅ እንደሚሰጥ፥ እኛም ጮክ ብለን ልናመልክ ብንችልም፣ ነገሩ ባዶ አየር ከመሆን አያልፍም።

በየዘመኑ የተነሡ በክርስቶስ የማያምኑ ሰዎች ስለ እርሱ የሚናገሩ ታሪኮች በተለይም ከሞት መነሣቱ እውነት እንዳልሆነ ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ለማቅረብ ሲሞክሩ ቆይተዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ማልከም ማግሪጅ የተባለ የብሪታኒያ ሪፖርተር ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት እንዳልተነሣ ለማረጋገጥ ሞክሮ ነበር። ለብዙ ወራት በጥንቃቄ ሲያጠና ቆይቶ፥ የክርስቶስ ትንሣኤ እውነት መሆኑን ለማመን በመገደዱ ጠንካራ ክርስቲያን ለመሆን በቅቷል። ክርስትና ትርጉም የሚሰጠው ተአምራትን ያደረገ፣ ስለ እግዚአብሔር ያስተማረ፣ የሞትና ከሞት የተነሣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚባል ሰው እንዳለ ስናውቅ ብቻ ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ የጥንት ደቀ መዛሙርት ለምን ብለው ለዚህ እምነት ይሠዉ ነበር? ደግሞም ታሪኩ ውሸት ቢሆን ኖሮ ለዚህ እምነት ከመሞት መካዱ አይቀላቸውም ነበር? ጆሽ ማክዶውል የተባለ አንድ አሜሪካዊ የሕግ ባለሙያ እንዳመለከተው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ የሚናገረው እውነት እንደሆነ አምኖ ከመቀበል ውጭ ለክርስትና ሌላ አመክንዮአዊ ትንታኔ ማቅረብ አይቻልም። ክርስትና ለሰዎች ጥሩ ስሜት በሚሰጡ አፈ ታሪኮች ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት አይደለም። ክርስትና በጽኑ ታሪካዊ እውነቶች ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት ነው፤ ተምረናል የሚሉትና ነገሩንም ተረት ተረት ነው የሚሉ ሰዎች የክርስቶስን ታሪክ በሳይንሳዊ መንገድ ለማብራራት አልሞከሩም። ስለሆነም፣ ስለ እምነታችን የምናፍርበት ወይም ሳይንሳዊና ታሪካዊ አይደለም ብለን የምንሸማቀቅበት ምክንያት የለም!

የሉቃስ ወንጌል የተጻፈው ሉቃስ በተባለ ጥንታዊ የታሪክ ምሑር ነው። ሉቃስ የእርሱም ሆነ የሌሎች ክርስቲያኖች እምነት በፈጠራ ታሪክ ላይ እንዲመሠረት አልፈለገም። እርሱም ከክርስቶስ ሕይወት መጀመሪያ እንሥቶ ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ መርምሮ እንደጻፈ ገልጾአል። ዓላማውም ቀደም ሲል የተነገሩት አሳቦች እውነት መሆናቸውን ማረጋገጥ ነበር። አንድ የታሪክ ጸሐፊ ኢየሱስ በሞተበት የመጀመሪያዎቹ ሠላሣ አምስት ዓመታት ክልል ውስጥ ታሪኩን የሚያረጋግጡ በርካታ የዓይን ምስክሮች ባሉበት ዘመን ከጻፈ፥ እርሱም ሆነ ሌሎች የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ስለ ክርስቶስ የሚነግሩንን አምኖ ለመቀበል ፍጹም ድፍረት ይኖረናል። ታሪኩ እውነት ባይሆን ኖሮ፥ በዚያን ዘመን የነበሩት ሰዎች ይቃወሙት እንደነበር አይጠረጠርም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ስለ ሉቃስ የተጻፈውን አንብብ። ስለ መጽሓፉ ደራሲና ስለ ሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮች የቀረበውን አሳብ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። ለ) ቆላ. 4፡14፤ 2ኛ ጢሞ. 4፡11፤ ፊልሞና 1፡24 አንብብ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ ሉቃስ ምን ያስተምሩናል? ሐ) የሐዋ. 16፡11-13፤ 20፡6-7፤ 21፡1-6፤ 28፡16 አንብብ፡፡ እነዚህ ጥቅሶች ስለ ደራሲውና ከጳውሎስ ጋር ስላሉት ተግባራት ምን ያሳዩናል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: