ማርያም ኤልሳቤጥን ጎበኘች (ሉቃስ 1፡39-56)

መልአኩ በቅርቡ ስለሚፈጸመው ሁለተኛው ተአምራዊ ልደት ለማርያም ነግሯት ሲሄድ፥ ማርያም በልቧ ውስጥ የሚጋጭ ስሜት እንደ ፈጠረባት ልንገምት እንችላለን። ማርያም ስለዚሁ ጉዳይ ለመነጋገር በመፈለጓ ምክንያት ብዙ ኪሎ ሜትር ተጉዛ ወደ ዘመዷ ወደ ኤልሳቤጥ ዘንድ ሄደች፡፡ በአይሁድ ባሕል ወጣት ሴቶች ከቤታቸው ወጥተው ሩቅ መንገድ ለመሄድ ስለማይችሉ፣ ይህንን ማድረጉ ለማርያም ቀላል አልነበረም።

እግዚአብሔር አንድ ከባድ ነገር እንድናደርግ ሲጠይቀን፥ አብዛኛውን ጊዜ የሚያበረታታንን ነገር ያደርጋል። ማርያም ኤልሳቤጥን በጎበኘች ጊዜ መጥምቁ ዮሓንስ በኤልሳቤጥ ማሕፀን ውስጥ ዘለለ። በዚያን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በኤልሳቤጥ ላይ በመውረዱ፥ ማንም ሳይነግራት ማርያም ታላቅ ልጅ እንዳረገዘች አወቀች። አሁንም ኤልሳቤጥ የሆነውን በትክክል መገንዘቧ አጠራጣሪ ነው። እግዚአብሔር እንዴት ሰው ሊሆን ይችላል? ምንም እንኳ ግሪኮች እንዲህ ዓይነት አፈ ታሪክ ቢኖሯቸውም፣ ይህ ለአይሁዳውያን ስድብ ነበር። ይሁንና የማርያም ልጅ አምላክ እንደሆነ ኤልሳቤጥ ተገንዝባ ነበር።

ሉቃስ በመጽሐፉ ውስጥ ካካተታቸው ልዩ ነገሮች መካከል፥ በዚህ ወቅት ሰዎች የሰጡትን ምላሽ ያንጸባረቁዋቸውን ምላሾች በመዝሙር መልክ መጻፉ ነበር። በዚህ ክፍል አራት መዝሙራት ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም የመጀመሪያው የማርያም ነው። ማርያም ይህንን የማጽናኛ ቃል ከተቀበለች በኋላ በርካታ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች የሚገኙበትን መዝሙር ለመዘመር ችላለች። የተዋረደችውን ልጃገረድ እግዚአብሔር ስለ መረጠ አመሰገነች። ይህ ከታላቅነቷ ወይም ከኃጢአት-የለሽነቷ የተነሣ (ካቶሊኮችና ኦርቶዶክሶች እንደሚያስተምሩት ሳይሆን)፣ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ እንደሆነ ተገንዝባ ነበር። ምሕረት ታላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሲሆን፣ ፍችውም እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ የማይገባንን ነገር እንዳደረገልን የሚያመለክት ነው። የማርያም መዝሙር እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ከሰዎች በተለየ አቅጣጫ የሚሠራበትን ሁኔታ ያመለክታል። ሰዎች ለባለጠጎችና ለኀያላን ሲያሸረግዱ፣ እግዚአብሔር እንዴት ገዥዎችን እንደሚያዋርድ፣ ባለጠጎችን ባዶአቸውን እንደሚሰድድና ሰዎች የሚኩራሩበትን ነገር እንደሚያፈርስ ማርያም በመዝሙሯ ገልጻለች። በአንጻሩም፣ እግዚአብሔር እንደ ማርያም ያሉ የተዋረዱ ሰዎችን ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ ያከብራል። እንደ ማርያም ያሉ ድሆችን ይመግባል፥ ይባርክማል። ማርያም ስለ መሢሑ የተረዳችው ከብሉይ ኪዳን የነቢያት መጻሕፍት ነው።

ሉቃስ ማርያም ከኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወር እንዳሳለፈች ገልጾአል። ኤልሳቤጥ በዚህ ጊዜ የስድስት ወር እርጉዝ ስለ ነበረች፤ ማርያም መጥምቁ ዮሐንስ እስኪወለድ ድረስ እዚያው ቆይታለች ማለት ነው። ማርያም ወደ ዮሴፍ ዘንድ የመጣችው የሦስት ወር እርጉዝ ሆና ምናልባትም ከኤልሳቤጥ ዘንድ ከተመለሰች በኋላ ሳይሆን አይቀርም።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: