ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ከሚኖሩበት አካባቢ በሰሜን በኩል ራቅ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ምናልባትም 15 ወይም 16 ዓመት የሚሆናት አንዲት ልጃገረድ ትኖር ነበር። ይህች ልጃገረድ ለዮሴፍ የታጨች ነበረች። መልአኩ ገብርኤል አንድ ቀን መጥቶ መልካም ዜና ባበሠራት ጊዜ አባባሉ አሳብ ላይ ጣላት። ገብርኤል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስማቸው ከተጠሩ ሁለት መላእክት መካከል አንዱ ነው። ሌላው በስሙ የተጠራው ሚካኤል ነው (ዳን. 10፡21)። ገብርኤል ወሳኝ የሆኑ መልእክቶችን ከእግዚአብሔር ወደ ሕዝብ የሚያደርስ ልዩ መልአክ ነው (ዳን. 8፡16፤ 9፡21-22 አንብብ።) ማቴዎስ፥ ማርያም መልአኩን በሕልምዋ እንዳየች ሲናገር፣ ሉቃስ ግን ፊት ለፊት እንደ ተነጋገሩ ይገልጻል። ማቴዎስ ስለ ኢየሱስ ልደት የተረከው ከዮሴፍ እይታ አንጻር ሲሆን፣ ሉቃስ ታሪኩን ያቀረበው ግን ከማርያም አንጻር ነው።
ገብርኤል ለማርያም ያስተላለፈው መልእክት በጣም ግልጽ ነበር። እግዚአብሔር በዓለም ታሪክ ውስጥ ልዩ ለሆነ ዓላማ መርጧታል። ልጅ ትወልዳለች። የልጁም ስም ኢየሱስ ይባላል። ይህም ኢያሱ ከሚለው የዕብራይስጡ ስም ጋር ተመሳሳይ ስያሜ ነው። የሁለቱም ስሞች ፍች፥ “እግዚአብሔር ያድናል» ወይም «እግዚአብሔር ደኅንነት ነው» የሚል ነው። ይህም የኢየሱስ ትልቁ አገልግሎት ለሰው ልጆች ደኅንነትን ማስገኘት እንደሆነ ያመለክታል። ኢየሱስ «የልዑል ልጅ» እንደሚባል ገብርኤል ለማርያም ገልጾላታል። አብዛኞቹ አይሁዶች «እግዚአብሔር» የሚለውን ቃል ለመጥራት ስለማይደፍሩ ይህ «የእግዚአብሔር ልጅ» ለሚለው አገላለጽ ሌላው አማራጭ ነበር። ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠው መሢሕና በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀውጥ ንጉሥ ነበር። ከዳዊት በተለየ አኳኋን የኢየሱስ አገዛዝና መንግሥት ዘላለማዊ ነው።
ሉቃስ ማርያም ከሌሎች ሴቶች ሁሉ በላይ ቅድስት መሆኗን አይነግረንም። ይልቁንም እግዚአብሔር ትምህርትን፣ ዘርን፥ ሀብትን መሠረት ሳያደርግ ሰዎችን ለዓላማው እንደሚመርጥ የሚያመለክት ምሳሌ ነው። ከሰው አስተሳሰብ አንጻር እግዚአብሔር የተማረችውንና ከልዩ ዘር የተወለደችውን ሀብታም ሴት ይመርጣል ብለን እናስብ ይሆናል። የገጠር ገበሬ ልጅ እንደ መሆኗ፣ ማርያም ከእነዚህ መስፈርቶች አንዱንም አታሟላም ነበር። ስለ ማርያም የምናውቀው ነገር ቢኖር እግዚአብሔርን የምትወድ ሴት መሆኗ ነበር። ይህ ታሪክ ባለን ስጦታ ተመክተን እንዳንታበይ ያስጠነቅቀናል። የመዝሙር ስጦታ ቢኖረን ይህ የሆነው በራሳችን ችሎታ ሳይሆን ከእዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ነው። ቁሳዊ በረከት፣ ጥሩ ቤተሰብ፣ ልዩ ችሎታ፣ ውበትና መልካም ገላ ቢኖረን፣ ይህንን ሁሉ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት እንደሌለ መገንዘብ ይኖርብናል። ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፤ ትምክህት እንዳይገዛንና ከእኛ የተሻሉ ናቸው ብለን በምናስባቸው ሰዎች እንዳንቀና ይህንን ማስታወስ አለብን። ይህ የእግዚአብሔር ምርጫና ስጦታ እንጂ የእኛ እንዳልሆነ መገንዘብ አለብን።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እኛ ልንቆጣጠራቸው በማንችላቸው እንደ ዘር፥ ትምህርት፣ ሀብት፣ ውበት በመሳሰሉት ነገሮች የምንታበየው እንዴት ነው? ለ) ከእኛ በተሻሉ ሰዎች ላይ የምንቀናው ለምንድን ነው? ሐ) ስንታበይ ወይም ስንቀና እግዚአብሔር በሕይወታችን ላይ ስላለው ሉዓላዊ ፈቃድ የምንዘነጋው ነገር ምንድን ነው? መ) የአንተን ሕይወት ከምታውቀው አንድ ለማኝ ጋር አነጻጽር። የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ምርጫና ለጦታ ባይኖር ኖሮ፥ እንደዚያ ሰው ልትሆን ትችል የነበረው እንዴት ነው?
ባለን አንድ ልዩ ስጦታ መታበይ ወይም በሌላው ሰው መቅናት ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ናቸው። ሁለቱም መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የስጦታዎች ሁሉ ምንጭ እንደሆነ ከሚያስተምረው አሳብ ውጭ ናቸው። እነዚህ ኃጢአቶች ካሉብህ አሁኑኑ ንስሓ ግባ። እግዚአብሔር ስለ ሰጠህ ስጦታ የሚያመሰግን ልብ እንዲሰጥህ ጸልይ። ስጦታዎችህን ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዳታነጻጽርና ትሑት እንዲያደርግህ እግዚአብሔርን ለምን።
«ይህ እንዴት ይሆናል?» የሚለው የማርያም ምላሽ፥ ከዘካርያስ ጥርጣሬ ጋር ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን መልአኩ ዘካርያስን የቀጣው ሲሆን፣ ማርያምን ግን አልቀጣትም። ለምን? ምናልባትም ከጥርጣሬያቸው በስተ ጀርባ የተለያዩ አመለካከቶች ሊኖሯቸው ይችላሉ። የዘካርያስ አቀራረብ ልጅ ለመውለድ እንደማይችል በማሰብ እግዚአብሔርን እንደ ተጠራጠረ የሚያመለክት ይሆናል። የማርያም አቀራረብ ግን እግዚአብሔር የሚሠራበትን መንገድ ለማወቅ የጠየቀች ይመስላል። ያላገባች ልጃገረድ እንደ መሆኗ ከወንድ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት አድርጋ አታውቅም። እስክታገባ ድረስ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ እንደማትችል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል። በታሪክ ደግሞ ከወንድ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሳታደርግ ያረገዘች ሴት ኖራ አታውቅም። እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጅ በማርያም ማሕፀን ውስጥ ሊፀነስ የሚችለው እንዴት ነው? የመልአኩ መልስ ለማርያም ትርጉም የሚሰጥ አይመስልም። መንፈስ ቅዱስ በሰውነቷ ውስጥ ተአምር በመሥራት ከወንድ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሳታደርግ የምትፀንስበትን ተግባር እንደሚፈጽም ነበር የገለጸላት።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ልጅህ በመንፈስ ቅዱስ ተአምር አርግዣለሁ ብትልህ ምላሽህ ምን ይሆናል? ታምናታለህ? ለምን? ለ) ያላገባች የቤተ ክርስቲያናችሁ አባል አርግዛ ብትገኝ ከቤተሰቧ፣ ከጓደኞቿና ከቤተ ክርስቲያን የሚገጥማት ችግር ምን ሊሆን ይችላል? ሐ) የማርያም ምላሽ በእግዚአብሔር ላይ ያላትን አስደናቂ እምነት የሚያሳየው እንዴት ነው?
ማርያም ገና ወጣት ብትሆንም፣ «እኔ የጌታ ባሪያ ነኝ። እነሆም፥ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ» በማለት የሚያስገርም መንፈሳዊ ብስለት አሳይታለች። በእዚህም ማርያም ከቤተሰቧ ለመፈናቀል ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻለች። ምክንያቱም በዚያን ዘመን ከጋብቻ ውጭ ያረገዘች ሴት ልጅ ለቤተሰቡ ትልቅ ሐፍረት እንደምትሆን ይታመን ነበር። ከጋብቻ በፊት የወለደች ሴት የሚያገባ ሰው ስለማይኖር፣ ያለ ጋብቻ ለመኖር ወስናም ነበር። በመላው ሰዎች ሊሰድብዋት ከፈለጉ ሳይከፋት በገሊላ የዲቃላ እናት ተብላ ለመጠራት ዝግጁ ነበረች። ለዚህም ምክንያቱ ለእግዚአብሔር ያላት ፍቅርና ታዛዥነት ነበር። እግዚአብሔር ነገሮችን እንዴት እንደሚሠራ ባታውቅም፣ ስለ እግዚአብሔር መነቀፍን መርጣለች።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)