የሉቃስ ወንጌል ዓላማ

አዲስ ኪዳን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች ላይ በማተኮር፣ ስለ ማንነቱ፣ ስላስከተላቸው ለውጦች በሕይወታችን ውስጥ እንዴት ልናስከብረው እንደሚገባን ያብራራል። መልእክቶች ሁሉ እውነትን ተግባራዊ የሚያደርጉት ከኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት አንጻር ነው። ለመሆኑ የጥንት ክርስቲያኖች እምነታቸውንና ተግባራቸውን የመሠረቱት በምን ላይ ነበር? በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ላይ ነበር። እያንዳንዱ መልእክት ከግምት ውስጥ የሚያስገቡት ነገር አለ። ይኸውም እያንዳንዱ ክርስቲያን ስለ ኢየሱስ የሚናገሩትን ታሪኮችና ተከታዮቹም ሕይወታቸውን እንዴት መምራት እንደሚገባቸው ያውቃል። መልእክቶች ኢየሱስ ማን እንደሆነ ይበልጥ ያብራራሉ። ክርስቲያኖች የክርስቶስን ትምህርት ራሳቸው ከሚገኙባቸው ሁኔታዎች ጋር ያዛምዱታል። መልእክቶች ስለ ኢየሱስ ፍጹም አዲስ ትምህርት አያስተምሩም፡፡ ነገር ግን ከወንጌላት ውስጥ ስለ ክርስቶስ ጥልቅ ጥናት የሚያደርጉ ክርስቲያኖች ብዙዎች አይደሉም። መልእክቶችን ማንበብ እንወዳለን። ይህም አንድ አባል የሚስቱን ባሕርይ ለማወቅ ከጓደኞቿ ጋር እንደሚናገር ማለት ነው። ነገር ግን ከራሷ ጋር በመነጋገር ስለ ባሕሪዋና ምን እንደሚያስፈልጋት እስካልተገነዘበ ድረስ፥ ሚስቱን በትክክል ሊያውቃት አይችልም። በዚሁ መሠረት ኢየሱስን እንደ ጳውሎስ ባሉት ሌሎች ሰዎች አማካይነት ልናውቅ አንችልም። ግን በወንጌላት ውስጥ እንደተገለጸው በቀጥታ ኢየሱስን መመልከት አለብን። ኢየሱስ የእምነታችን መሠረት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌላት ውስጥ የተገለጸበትን ሁኔታ እስካልተገነዘብን ድረስ በእምነታችን ልንጠነክር አንችልም።

ስለ ክርስቶስ የተለያዩ ታሪኮች ይነገሩ እንደነበር አይጠረጠርም። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ እውነት ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ግን ውሸትና የተጋነኑ ነበሩ። ስለሆነም፤ ሉቃስ እያንዳንዱ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው ፈልጓል። ሉቃስ ይህንን መጽሐፍ ሲጽፍ አያሌ ዓላማዎች ነበሩት፡-

  1. ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ግልጽ ታሪካዊ ዘገባ ማቅረብ። ሉቃስ ሌሎችም ሰዎች የኢየሱስን ታሪክ እንደ ጻፉ ገልጾአል። ምናልባትም የማርቆስ ወንጌል መኖሩን ያውቅ ይሆናል። ሰዎች ከጻፉዋቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ብቃት የጎደላቸው ወይም የተሳሳቱ ሊይሆኑ ይችላሉ። ሌሎች የኢየሱስን ሕይወት ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ አላቀረቡም ወይም በቂ መረጃ አልሰጡም ይሆናል። ወይም ሉቃስ እንደ ታሪክ ጸሐፊ ከታሪኮቹ በአንዳንዶቹ ላይ ብቁ የምርምር ሂደት እንደ ተካሄደ አላመነም ይሆናል። ታሪክ ጸሐፊው ሉቃስ፥ ለዘመናት ሁሉ የሚሆን ትክክለኛ የኢየሱስ ታሪክ መጻፍ እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። መንፈስ ቅዱስም ሉቃስ ተጨማሪ ወንጌል እንዲጽፍ ቀሰቀሰው።
  2. ክርስቲያኖች ማንን እንዳመኑ እንዲያውቁ። ለዚህም ነው ለቴዎፍሎስና ለሌሎችም፣ «ይህንንም የማደርገው የተማርኸው ነገር እውነተኛ መሆኑን እንድታውቅ ነው» ሲል የገለጸው (ሉቃስ 1፡4)። የእምነታችን ጥንካሬ የሚለካው ያመንነውን ነገር ባወቅነው መጠን ነው። በስደት ጊዜ ታማኞች ሆነን እንድንጸና ከተፈለገ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነና እርሱን መከተል ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሰዎች ክርስቶስን የሚክዱት በእርሱ ላይ ያላቸው እምነት ስላልጠነከረ ይሆን? መልስህን አብራራ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: