የሉቃስ ወንጌል የተጻፈበት ጊዜና ቦታ

የሉቃስ ወንጌል መቼ እንደ ተጻፈ ለመገመት የሌሎቹን ወንጌላትና የሐዋርያት ሥራን ቅደም ተከተል መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ፣ ሉቃስ የማርቆስን ወንጌል ከምንጮቹ እንደ አንዱ አድርጎ ተጠቅሞ ይሆን? የሐዋርያት ሥራ የተጻፈው መቼ ነው? በሐዋርያት ሥራ 1፡1 ላይ ሉቃስ ስለ መጀመሪያው መጽሐፉ ማለትም ስለ ሉቃስ ወንጌል ስለሚጠቅስ፣ የሐዋርያት ሥራ ከሉቃስ ወንጌል በኋላ እንደ ተጻፈ አያጠራጥርም። የሐዋርያት ሥራ የሚያበቃው ጳውሎስ ከሮም ወኅኒ ቤት ይወጣል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው። ሉቃስ ስለ ጳውሎስና ስለ አሟሟቱ ምንም ዓይነት ተጨማሪ አሳብ ስላልጻፈ፥ የሐዋርያት ሥራን ጽፎ የጨረሰው ጳውሎስ ከእስር ቤት ከመውጣቱና እንደገና ከመታሰሩ በፊት ሳይሆን አይቀርም። ስለሆነም የሐዋርያት ሥራ በ63 እና 64 ዓ.ም. መካከል እንደ ተጻፈ ይገመታል። ይህም የሉቃስ ወንጌል ከዚያ በፊት እንደ ተጻፈ ያመለክታል። ስለሆነም ሉቃስ ወንጌሉን ከ59-63 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ እንዳጠናቀቀ ይገመታል።

ሉቃስ የማርቆስን ወንጌል እንደ ምንጭ ተጠቅሟል የሚሉ ምሑራን፥ መጽሐፉ የተጻፈበትን ዘመን ወደ 70 ዓ.ም. ያመጡታል። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት፣ ይህን ወንጌል እንደ አንዱ ምንጭ አድርጎ ሉቃስ ከመጠቀሙ በፊት፥ የማርቆስ ወንጌል ተጽፎ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እስኪሰራጭ ድረስ ጊዜ ሳይወሰድ እንዳልቀረ ይናገራሉ። ነገር ግን የማርቆስ ወንጌል ቀደም ብሎ ተጽፎ ተቀባይነትን ካገኙት ወንጌላት እንደ አንዱ ሆኖ ካገለገለባት በኋላ፥ በሮም የራሱን መጽሐፍ ጽፎ ይሆናል ብለው ይገምታሉ። ሉቃስ ከ63 ዓ.ም. በኋላ ጽፎታል የሚለው ግምት ግን ይህን ያህል ተቀባይነት አላገኘም።

ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው በየት ስፍራ እንደሆነ በውል አይታወቅም። በአማራጭነት የሚጠቀሱት አገሮች ፣ ሉቃስ ብዙ ጊዜ ያሳለፈባት ፊልጵስዩስ፣ 2) ጳውሎስ ለሁለት ዓመት የታሰረባት ቂሣርያ፥ ወይም 3) ጳውሎስ ታስሮ የቆየባት ሮም ናቸው። ከእነዚህ በአንዱ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል። ሆኖም ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው ቂሣርያ ወይም ሮም በቆየባቸው ጊዜያት ይመስላል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ሊያውቋቸውና ከሕይወታቸው ጋር ሊያዛምዷቸው የሚገቧቸው እውነቶች ምንድን ናቸው? ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከእነዚህ እውነቶች አብዛኞቹ የሚገኙት የት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: