የመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ (ሉቃስ 1:57-80)

በዚህ ታሪክ ሉቃስ የኢየሱስ መንገድ ጠራጊ ወደሆነው ወደ መጥምቁ ዮሐንስ መወለድ ይመለሳል። በአይሁድ ባህል መሠረት፣ ዮሐንስ ስምንት ቀን ስለ ሞላው ከተገረዘ በኋላ ስም የማውጣት ሥነ ሥርዓት ተካሄደ። አይሁዶች ብዙ ጊዜ ልጅን በአባት ወይም በዘመድ ስም ይጠሩ ስለ ነበር፣ ጎረቤቶቻቸው ዘካርያስ ብለው ሊሰይሙት ፈለጉ። ነገር ግን ኤልሳቤጥ ልጁ ዮሐንስ መባል እንዳለበት ታውቅ ነበር። ስለዚህ ዘካርያስም ልጁ ዮሐንስ መባል እንዳለበት በጽሑፍ ገለጸ። ሰዎቹ እግዚአብሔር ተአምር እንደ ሠራ ያውቁ ስለ ነበር፣ ዮሐንስ ታላቅ ሰው እንደሚሆን ባይጠራጠሩም፥ ነገር ግን ልባቸውን ለመሢሑ የሚያዘጋጅ ታላቁ ኤልያስ መሆኑን አላወቁም ነበር።

ዘካርያስ የልጁ ስም ዮሐንስ እንደሆነ ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ እግዚአብሔር አፉን ከፈተለት። በዚህም ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ በመዝሙር ትንቢት ይናገር ጀመር። (ይህ በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ሁለተኛው መዝሙር ነው) ዘካርያስ እግዚአብሔርን ያመሰገነው ስለ ልጁ ሳይሆን፥ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ስለሚፈጸመው ነገር ነበር። ዘካርያስ እግዚአብሔር በጥንት ዘመን የተነገሩ ትንቢቶችን እንደሚፈጽም ይገነዘብ ነበር። በተጨማሪም የዮሐንስና የመሢሑ መምጣት የእግዚአብሔርን አገዛዝ የሚያመለክት መሢሓዊ ዘመን መሆኑን ያውቅ ነበር። እስራኤላውያን አሁን ከኃጢአታቸው ብቻ ሳይሆን ለአሕዛብ ተላልፈው ከተሰጡበት ባርነትም ነፃ ይወጣሉ፥ ጠላቶቻቸውም ይሸነፋሉ። የሰዎች ልብ ተለውጦ ያለ ፍርሃት፣ በቅድስናና በጽድቅ ያገለግላሉ። ምንም እንኳ ዘካርያስ ልጁ መሢሕ እንዳልሆነ ቢያውቅም፣ እግዚአብሔር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጠቀምበት ይገባው ነበር። ዮሐንስ የልዑል እግዚአብሔር ነቢይ እንደሚሆን ተረድቶ ነበር። ሥራውም ሰዎች ከኃጢአታቸው ተመልሰው የእግዚአብሔርን ይቅርታ እንዲጠይቁ በማድረግ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ለመሢሑ እንዲዘጋጁ ማድረግ ነው። ዘካርያስ የተገነዘበው ልጁ ከሁሉም የሚልቅ ታላቅ ሰው እንደሚሆን ሳይሆን የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደሚሆን ነበር።

መሪዎች ቅንዓትና ኩራትን ከሚያሳዩባቸው መንገዶች አንዱ፥ የልጆች አያያዝ ነው። ለልጆቻችን ከሁሉም የተሻለውን እንመኝላቸዋለን። ብዙውን ጊዜ ይህ ማለት ደግሞ እኛን የሚተኩ መሪዎች እንዲሆኑ እንሻለን ማለት ነው። ልጆቻችን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሚገቡበትን ወይም የወጣት ማኅበራት መሪዎች የሚሆኑበትን መንገድ ለማመቻቸት እንጥራለን። ይህ ለቤተ ክርስቲያን በጣም አደገኛ ነገር ነው። ትልቁ ምኞታችን የእግዚአብሔር ክብር እንጂ የልጆቻችን መሆን የለበትም። ስለሆነም በአመራር ስፍራ ላይ ካለን መሪ መሆን የሚገባቸው የመሪነት ስጦታ ያላቸው (በእግዚአብሔር የተመረጡ) ሰዎች ብቻ ሊሆኑ እንደሚገባ መገንዘብ አለብን። እግዚአብሔር የሌላውን ሰው ልጅ ለመሪነት ከመረጠው፣ የእግዚአብሔርን ምርጫ በማክበር ደስ ልንሰኝ ይገባል። እግዚአብሔር በመንግሥቱ ውስጥ ለሁሉም ሰው የተለያዩ ስጦታዎችን ስለሚሰጥ፣ ለልጆቻችንና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች መመኘት የሚገባን ሁላችንም የየራሳችንን ልዩ ስፍራ ለይተን ለእግዚአብሔር ክብር እንድናውለው ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንደዚህ ማሰቡ አስቸጋሪ እንደሆነ የምታስበው ለምንድን ነው? ለ) የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን እንዲከተሉ ከማድረግ ፈንታ፥ አንድ መሪ ልጁን ወደ መዘምራን ወይም ወደ ሌላ የተለየ አገልግሎት ለማስገባት በሚሞክርበት ጊዜ ምን ዐይነት ችግሮች ሲከሰቱ አስተውለሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: