ሉቃስ 3፡1-4፡13

ሀ. የኢየሱስ መንገድ ጠራጊ የሆነው የመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት (ሉቃስ 3፡1-20)። ሉቃስ አሁንም ስለ መጥምቁ ዮሐንስና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት አጠቃላይ ታሪካዊ ገለጻ ይሰጠናል። ጢባርዮስ ቄሣር ለ15 ዓመታት ንጉሥ ሆኖ ገዝቷል። ምሑራን ይህ ጊዜ ከ25-26 ዓ.ም. እንደሚሆን ይገምታሉ። ጴንጤናዊ ጲላጦስ የይሁዳ አውራጃ ገዥ ነበር (26-36 ዓ.ም.)። በዚህ ጊዜ ይሁዳ በሄሮድስ ዘመዶች ሳይሆን በሮማውያን ትገዛ ነበር። ሄሮድስ አንቲጳስ (ከ4 ዓ.ዓ.-39 ዓ.ም.) ኢየሱስ በነበረበት በገሊላ አካባቢ ገዥ ሆኖ ያስተዳድር ነበር። ሄሮድስ ፊልጶስ (ከ4 ዓ.ዓ–39 ዓ.ም.) የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ ገዥ ነበር። ሊሳኒዮላ የሳቢላኒስ ገዥ ነበር። ሐናንያ ሊቀ ካህን ሆኖ ከ6-15 ዓ.ም. ድረስ ያገለገለ ሲሆን፣ ከ18-36 ዓ.ም. ከአማቹ ጋር አብር ሠርቷል።

ዮሐንስ ያገለገለው በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ነበር። ሉቃስ የዮሐንስን አገልግሎት «ለኃጢአት ይቅርታ የሚሆን የንስሐ ጥምቀት» በማለት ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል። የኃጢአትን ይቅርታ የሚያስገኘው ጥምቀት አይደለም። ይልቁንም ጥምቀት ሰዎች ንስሐ ገብተው የኃጢአት ይቅርታ እንዳገኙ የሚያሳይ ውጫዊ ምልክት ነው። ሉቃስ ዮሐንስ በኢሳ. 40፡3-5 ላይ የተነገረውን ትንቢት እንደ ፈጸመ ያውቅ ነበር። ሉቃስ ኢየሱስ ለአይሁዶችም ሆነ ለአሕዛብ የሚሆነውን የእግዚአብሔርን ማዳን እንደሚያመጣ አብራርቷል።

ማቴዎስ፥ ዮሐንስ በፈሪሳውያን ላይ የሰነዘራቸውን ከባድ ቃላት ሲጠቅለ (ማቴ. 3፡7-10፣ ሉቃስ ግን እነዚህ የተግሣጽ ቃላት ሁሉንም ሰው የሚመለከቱ መሆናቸውን ገልጾአል (ሉቃስ 3፡7-9)። መጥምቁ ዮሐንስ መጭውን ፍርድ መፍራትና መጠመቅ ብቻ በቂ እንዳልሆነ አስጠንቅቋል። ሕዝቡ ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ መለወጥ ያስፈልገዋል። ሉቃስ በምን በምን ረገድ መለወጥ እንዳለባቸው በሚገባ ዘርዝሯል። ሀብታሞች (ሁለት ልብስ ያላቸው) ለድሆች (ምንም ለሌላቸው) ማካፈል ያስፈልጋቸዋል። ቀራጮች ራስ ወዳድነትን አስወግደው የሮም መንግሥት ካወጣው ታሪፍ በላይ ማስከፈላቸውን ማቆም ይኖርባቸዋል። ጉቦ በመቀበልና በፍጥነት ራሳቸውን ሀብታም ከማድረግ መቆጠብ አለባቸው። ወታደሮች ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ከሕዝቡ ገንዘብ ከመሰብሰብ ይልቅ በሚያገኙት ደመወዝ መተዳደር እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አምስት የሥራ ዘርፎችን ዘርዝር። ዮሐንስ ኢየሱስን ለመከተል የሚፈልጉ ሰዎች እንዴት መኖር እንዳለባቸው የሚያስብ ይመስልሃል?

ዮሐንስ ኀላፊነቱን በሚገባ ያውቃል። እርሱ መሢሑ አይደለም። ከመሢሑ እንደማያንስና ባሪያው እንኳ ሊሆን እንደማይገባው ገልጾአል። በአገልግሎቱም ዮሐንስ ሰዎችን በውኃ ከማጥመቅ ያለፈ ሥልጣን ስላልነበረው ከመሢሑ ያንስ ነበር። መሢሑ ግን የብሉይ ኪዳንን የተስፋ ቃሎች በመፈጸም (ኢዩኤል 2፡28-29 አንብብ) በመንፈስ ቅዱስና በፍርድ እሳት ያጠምቃል።

በመጨረሻም ንጉሥ ሄሮድስ አንቲጳስ የወንድሙን ሚስት በማግባቱ ምክንያት ስለ ገሠጸው መጥምቁ ዮሐንስን እንዳሰረው በመግለጽ ይፋዊ አገልግሎቱ እንደ ተፈጸመ ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል።

ለ. የኢየሱስ መጠመቅና የዘር ሐረጉ (ሉቃስ 3፡21-38)። ሉቃስ ስለ ኢየሱስ መጠመቅ ያቀረበው ዘገባ ከሌሎቹ የወንጌላት ትንታኔ ሁሉ አጠር ያለ ነው። ሉቃስ ኢየሱስ ይፋዊ አገልግሎቱን የጀመረው በሠላሳ ዓመቱ አካባቢ እንደሆነ ገልጾአል። ይህንን መረጃ የሰጠን ኢየሱስ ከጉልምስና ዕድሜ ላይ እንደ ደረሰና በአይሁዶች ባህል ሰዎች እግዚአብሔርን ለማገልገል ከሚችሉበት ትክክለኛ ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ ለመግለጽ ስለ ፈለገ ይሆናል (ዘኁል. 4፡47 አንብብ።) ሉቃስ ኢየሱስ ለይፋዊ አገልግሎቱ የተዘጋጀበትን ሁኔታ በመግለጽ፣ ዮሐንስ ኢየሱስን እንዴት እንዳጠመቀው አስረድቷል። እዚህ ላይ ሉቃስ አንድ አስገራሚ ነገር አክሏል። ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ይጸልይ ነበር። ሲጸልይ ሰማይ ተከፍቶ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ወረደ። ወዲያውም እግዚአብሔር አብ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወደው ልጁ እንደሆነ ገልጾአል። እዚህ ላይ ሉቃስ ከመጽሐፉ ጭብጦች መካከል አንዱ ስለሆነው ስለ ጸሎት ይነግረናል። ኢየሱስ በጸሎት የሰማይን በሮች እንደ ከፈተለት ሁሉ፣ እኛም የኢየሱስ ተከታዮች እንደ መሆናችን በጸሎት ልንተጋ ይገባል። መንፈስ ቅዱስ በጸሎታችን አማካይነት ይሠራል።

ሉቃስ ስለ ኢየሱስ መፈተን ከመግለጹ በፊት፣ ስለ ኢየሱስ የዘር ሐረግ ይነግረናል። ማቴዎስና ሉቃስ ባቀረቧቸው የኢየሱስ የዘር ሐረግ ዝርዝሮች ውስጥ አያሌ አስገራሚ ልዩነቶች አሉ። አንደኛው፥ ማቴዎስ ከአብርሃም ወደ ኢየሱስ ሲዘረዝር፣ ሉቃስ ግን ወደ ኋላ በመመለስ ከኢየሱስ ወደ አዳም ይዘረዝራል። ሁለተኛው፣ ማቴዎስ የአይሁዶች አባት ከሆነው ከአብርሃም ሲጀምር፣ ሉቃስ ዝርዝሩን የቋጨው የመጀመሪያው ሰው በሆነው አዳም ነው። ሦስተኛው፣ ከአብርሃም እስከ ዳዊት ድረስ ሁለቱም የዘር ሐረግ ዝርዝሮች ተመሳሳይ ናቸው። ከዳዊት በኋላ ግን ይለያያሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት ማቴዎስ የኢየሱስ ሕጋዊ አባት በሆነው ዮሴፍ አማካይነት የዳዊትን ሕጋዊ ንግሥና ለማሳየት ስለፈለገ ሳይሆን አይቀርም። ሉቃስ ግን የዘር ሐረጉን ያደረገው በማርያም በኩል ነው። አራተኛው፣ ሉቃስ የዘር ሐረጉን ቆጠራ የሚያበቃው በአዳም (እግዚአብሔር ስለ ፈጠረው የእግዚአብሔር ልጅ ተብሏል) በመሆኑ፥ የኢየሱስን ሰው መሆን አጉልቶ አሳይቷል። ይህም ኢየሱስ እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ የአዳም ዘር መሆኑንም ይገልጻል።

ሐ. የኢየሱስ በምድረ በዳ መፈተን (ሉቃስ 4፡1-18)። ሉቃስ ኢየሱስ በተፈተነ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንደ ነበረበት ያስረዳል። ኢየሱስ ክርስቶስ ፈተናውን ወደሚቀበልበት ምድረ በዳ የተወሰደው በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ሲሆን፣ ሕይወቱም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ነበር። አሁንም ሉቃስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በተቀበሉትና በራሱ በኢየሱስ ሕይወት የመንፈስ ቅዱስ ተሳትፎ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ በአጽንኦት ሲገልጽ እንመለከታለን። ሉቃስ ሊያስገነዝበን የፈለገው ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ሳለ፥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ካለው፣ እኛም ይህንኑ ልናደርግ እንደሚገባን ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መመሥረት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) እስካሁን ከተመለከትነው በመነሣት ሉቃስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ተሳትፎ የተናገራቸውን ዘርዝር። ከዚህ ስለ መንፈስ ቅዱስ ልዩ ልዩ ሥራ ምን እንረዳለን?

ሉቃስ ኢየሱስ ለ40 ቀን እንደ ተፈተነ ገልቆአል። ፈተናው እንዳበቃ ሰይጣን ሌላ ምቹ አጋጣሚ እስኪያገኝ ድረስ ለጊዜው ከኢየሱስ ፈቀቅ አለ። የተጠቀሱት ሦስቱ ፈተናዎች የፈተናው ጊዜ እንዳበቃ የሚያመለክቱ መደምደሚያ ብቻ ናቸው። ምናልባትም ሉቃስ የኢየሱስ ፈተና ከባድ መሆኑን የገለጻው ሰይጣን ሁልጊዜ ደቀ መዛሙርትን እንደሚፈትን ለማሳየት ነው። ይህ ልንገነዘበው የሚገባ ቀጣይ ሂደት ነው። ነገር ግን በእያንዳንዱ ፈተና ኢየሱስን የረዳው መንፈስ ቅዱስ ከእኛም ጋር እንዳለ መገንዘብ አለብን። ለሰይጣን ጆሮአችንን በመስጠት ራሳችንን ለውድቀት መዳረግ አይገባንም። ሉቃስ የሁለተኛውንና የሦስተኛውን ፈተና ቅደም ተከተል ለዋውጧል። ማቴዎስም ሆነ ሉቃስ ታሪኩን በትክክለኛ ቅደም ተከተል አላቀረቡትም።

የኢየሱስ ሦስቱ ፈተናዎች እያንዳንዳችን በተለይም በመምራት አገልግሎት ላይ ያለን ክርስቲያኖች የምንጋፈጣቸው ናቸው።

  1. ድንጋይን ወደ ዳቦ መለወጥ፡- ሰይጣን ኢየሱስ የሌሎችን ፍላጎት ከማሟላት ይልቅ በሥልጣኑ ተጠቅሞ በራስ ወዳድነት የራሱን ፍላጎት እንዲያሟላ ጠይቆታል። እንዲህ ዐይነቱ ፈተና በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ላይ ጎልቶ ይታያል። እግዚአብሔር መሪ አድርጎ የሾማቸው የምእመናኑን ሁሉ ፍላጎት እንዲያሟሉ ነው። ሰይጣን በእጃቸው የገባውን ሥልጣን በመጠቀም የራሳቸውን ወይም የቤተሰባቸውን ሕይወት እንዲያሻሽሉ ይፈትናቸዋል። ነገር ግን በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ አመራር ሌሎችን ለማገልገል የምንጠቀምበት ነው። ስለዚህ ይህ ሥልጣን በራስ ወዳድነት የምንጠቀምበት አይደለም።
  2. የዓለምን መንግሥት ለማግኘት ሰይጣንን ማምለክ፡- ሰይጣን በምድር መንግሥታት ላይ ጊዜያዊ ሥልጣን እንዳለው ያውቃል። ሥልጣኑ የእግዚአብሔር ወይም የኢየሱስ እንደሆነ ይገነዘባል። አንድ ቀን ኢየሱስ እነዚህን መንግሥታት እንደሚወስድበት ያውቃል። ነገር ግን ሰይጣን ለኢየሱስ በአቋራጭ ሹመት ለመስጠት ፈለገ። እግዚአብሔር በማይፈልገው መንገድ የሥልጣን በትር እንደሚያስጨብጠው ተናገረ። ኢየሱስ ወደ መስቀሉ የሚወስደውን ረዥም ጉዞ ከመከተል ይልቅ፥ ለሰይጣን አንድ ጊዜ ብቻ ቢሰግድ ከእግዚአብሔር ባላጋራ አንዱ ያደርገው ነበር። ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው ኀጢአት የሌለበት መሥዋዕት ነው፤ ደግሞም ሰዎችን ለመዋጀት የሚችለው ኀጢአት የሌለበት ኢየሱስ ብቻ ነው። ኢየሱስ በምድራዊ መንግሥት ላይ ትኩረት ቢያደርግ ኖሮ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ መንግሥት ይዘነጋ ነበር።

ሰይጣን እኛም አቋራጭ መንገድ እንድንከተል ይፈትነናል። ይህ ለእኛም መልካም ሊመስል ይችላል። ጥሩ ትምህርት እንፈልግ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ሰይጣን በፈተና ላይ አጭበርብረን የምንፈልገውን ጥሩ ውጤት እንድናገኝ ይፈትነናል። ወይም ደግሞ ቁሳዊ በረከቶችን እንፈልግ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ ጉቦን፣ ስርቆትን፣ ቀረጥ አለመክፈልን፣ እግዚአብሔርን ከማገልገል ይልቅ በገንዘብ ላይ ማተኮርን ከፊታችን ሊደቅን ይችላል። ሰይጣን ሌሎችን በተሰጠ መንፈስ አገልግለን የክብር አክሊል እንዳንቀዳጅ ሥልጣን የሚያስገኘውን ጥቅማ ጥቅም እንድናሳድድ ይፈትነናል። እንዲሁም ሰይጣን አንድን ነገር ወይም ሰው እግዚአብሔርን ከምንወደው በላይ እንድንወድ በማድረግ እንድናመልከው ይፈልጋል። በዚህም ከእርሱ ጋር የእግዚአብሔር ጠላቶች እንሆናለን።

  1. ራሱን ከቤተ መቅደሱ ጫፍ መወርወር፡- እግዚአብሔር መላእክቱን በመላክ ኢየሱስን ሊያድነው ይችል እንደሆነ ለመፈተን ሰይጣን እየጠየቀው ነበር። ሰይጣን ኢየሱስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመኖር እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበትን ነገር ብቻ ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። ደግሞም በእግዚአብሔር ፍጹም ፈቃድ ውስጥ፣ እግዚአብሔር የእርሱ ፈቃድ ካልሆነው ከማንኛውም ነገር ኢየሱስንም ሆነ እኛን እንደሚጠብቀን ያውቃል። ነገር ግን ተገቢ ያልሆነ ነገር እያደረጉ እግዚአብሔር እንዲጠብቀን መጠየቁ እግዚአብሔርን መፈታተን ይሆናል።

እግዚአብሔርን በምንፈትንበት ጊዜ ኃጢአትን እንሠራለን። እግዚአብሔር ከኃጢአት ውጤቶች እንደምንጠበቅ ዋስትና አልሰጠንም። እግዚአብሔር እንደሚጠብቀን የተናገረው እርሱን ስንታዘዝ ብቻ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር ከፈቃዱ ውጭ ለእኛ ወይም ለቤተ ክርስቲያናችን አንድን ነገር እንዲያደርግ በምንጠይቅበት ጊዜ፣ የእግዚአብሔርን ሥልጣን እየተቀናቀንን እንጂ ለፈቃዱ እየተዝን አይደለንም። እግዚአብሔር እንዲፈውሰን፣ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራልን፣ ወይም አላግባብ መኪናችንን እያሽከረከርን እግዚአብሔር እንዲጠብቀን ስንጠይቅ፣ እግዚአብሔርን እንፈትናለን። ይህ ደግሞ ኃጢአት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ለእነዚህ ሦስት ዐይነት ኃጢአቶች ለእያንዳንዳቸው ማብራሪያዎችን በማቅረብ፣ ዛሬ እኛ እንዴት ልንፈጽማቸው እንደምንችል ግለጽ።

ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣንን ያሸነፈው እንዴት ነው? ሥልጣንና ኃይሉን በመጠቀም ነው? አይደለም! ኢየሱስ የተጠቀመው የራሱን ሥልጣን ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ቃል ነው። ሰይጣንን የምናሸንፈው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእግዚአብሔርን ቃል ስንጠቀምበት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስ መጽሐፍ ቅዱስን ስለሚያውቅ የሰይጣንን ፈተና ለመቋቋም ተጠቅሞበታል። መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል ለማወቅና የሰይጣንን ፈተና ለማሸነፍ ምን ታደርጋለህ? ለ) በቅርቡ ስለ ገጠመህ ፈተናና ፈተናውን እንዴት እንዳለፍህ ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: