- የኢየሱስ አገልግሎት ምሳሌዎች በገሊላ (ሉቃስ 4፡31-44)
ሉቃስ የኢየሱስን አገልግሎት ሦስት ምሳሌዎችና የሕዝቡን ምላሽ ገልጾአል።
ሀ. የኢየሱስ የማስተማር አገልግሎት፡- ሉቃስ በቅፍርናሆም የነበሩ አይሁዶች የሰጡትን ምላሽ በናዝሬት ከነበሩት ጋር በማነጻጸር አቅርቧል። በናዝሬት የነበሩ አይሁዶች ሲቃወሙት በቅፍርናሆም የነበሩት ግን ኢየሱስ በሚያስተምርበት ሥልጣን ተደንቀዋል።
ለ. ኢየሱስ አጋንንትን አስወጣ፡- አጋንንት ኢየሱስ «ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ» እንደሆነ ያውቁ ነበር። «የናዝሬቱ ኢየሱስ» በማለት ጠርተውታል። በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ይህ ስም ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል። ኢየሱስ ተብለው የሚጠሩ ሌሎች ብዙ አይሁዶች ስለ ነበሩ፣ «የናዝሬቱ ኢየሱስ» የሚለው እርሱን ከሌሎች ለመለየት አይሁዶች የሚጠቀሙበት ዘዴ ነበር። ስለሆነም አጋንንትን ለማስወጣት የእግዚአብሔርን ልጅ ሥልጣን የጨበጠው የቅፍርናሆሙ ኢየሱስ ሳይሆን፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነበር። ጥቂት ቃል ብቻ ሲናገር አጋንንት ኢየሱስን ይታዘዙት ነበር።
ሐ. ኢየሱስ ሕሙማንን ፈወሰ፡– ከጴጥሮስ አማት ጀምሮ ኢየሱስ ብዙ በሽተኞችን ፈውሷል።
ምንም እንኳ ኢየሱስ ሰዎችን ቢፈውስና አጋንንትን ቢያስወጣም ተቀዳሚ አገልግሎቱ ግን ይሄ አልነበረም። ከሰማይ ወደ ምድር የወረደው ፈዋሽ ወይም አጋንንት አውጭ ብቻ ለመሆን አልነበረም። እነዚህን ነገሮች ያደረገው ከርኅራኄው የተነሣ ነበር። ተቀዳሚ አገልግሎቱ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል መስበክ ነበር። ኢየሱስ እያደገ የመጣው ዝና በአንድ አካባቢ እንዲወሰን አላደረገውም። ይልቁንም ሌሎች ብዙ ሰዎች መልካሙን ዜና ለመስማት ዕድል እንዲኖራቸው ጥሯል።
ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች በአገልግሎታቸው ላይ አለማተኮሩ ቀላል ነው። አንዳንዶች በፈውስ፣ ሌሎች የማኅበረ ምእመናኑን ፍላጎቶች በማሟላት ወዲያ ወዲህ በማለት ሊንከራተቱ ይችላሉ። ኢየሱስ ዋነኛ በሆነው አገልግሎታችን ማለትም ወንጌልን ላልሰሙ ሰዎች በመመስከር ተግባር ላይ እንድናተኩር ይፈልጋል። ነገር ግን ብዙም ሳንቆይ ወደ ራስ ወዳድነት እንሸጋገራለን። ራስ ወዳድ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ለረዥም ጊዜ የእግዚአብሔርን በረከት ልትቀበል አትችልም።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወይም አብያተ ክርስቲያናት ከዋነኛ ተልእኮአቸው ሲያፈነግጡ የተመለከትህባቸውን አጋጣሚ ግለጽ። ለ) ቤተ ክርስቲያን ራስ ወዳድ በመሆን መልካሙን የምሥራች ለማዳረስ እንደ ተጠራች ልትዘነጋ የምትችለው እንዴት ነው?
- ኢየሱስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ (ሉቃስ 5፡1-11)
ሁላችንም የኢየሱስ ደቀ መዝሙሮች እንደሆንን ለመጽናት እንጥራለን። የአሮጌውን ሕይወት ጥሪ ተቀብለን ወደ ኋላ የምንመለስበት ጊዜ አለ። ከዚያም ኢየሱስ እንድንከተለው ይጠራናል። በኢየሱስ ይፋዊ አገልግሎት ወቅት፣ ጴጥሮስን፣ እንድርያስንና ዮሐንስን ጨምሮ በርካታ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን ለመከተል ወሰኑ (ዮሐ 1፡35-42)። ወዲያው ግን ደቀ መዝሙርነታቸውን ትተው ወደ ዓሣ ማጥመድ ሥራቸው ተመለሱ። ይህ በሉቃስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው ታሪክ፥ በማቴ. 4፡18-20 ከቀረበው የተለየ ከሆነ፣ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለአጭር ጊዜ ከተከተለው በኋላ ወደ ዓሣ ማጥመዱ ሥራ ተመልሷል ማለት ነው። ከኢየሱስ ስቅለት በኋላም ጴጥሮስ እንደገና ወደ ዓሣ ማጥመዱ ሥራ ሲመለስ እንመለከታለን (ዮሐ 21፡1-5)። የዓለም ኃይል የዋዛ አይደለም። እኛም ለራሳችን ወደሚመቸን አቅጣጫ ለመመለስ እንፈልጋለን፡፡ ሁልጊዜ የኢየሱስ ተከታይ ሆኖ ለመኖር ከፍተኛ ቆራጥነትንና ትጋትን ይጠይቃል። እግዚአብሔርም የሚጠራን ይህንኑ እንድናደርግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለማወቅ ሁልጊዜ ራሳችንን እንድንመረምር የሚጠይቀንም ለዚሁ ነው (2ኛ ቆሮ.13፡5)።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በሕይወትህ ኢየሱስን ከመከተል ለማፈግፈግ የቃጣህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሆነህ ለማደግ ምን እያደረግህ ነው?
ይህ በሉቃስ ወንጌል ውስጥ የቀረበው ታሪክ በማቴ. 4፡18-22 ላይ ከተጠቀሰው ታሪክ ጋር ተመሳሳይ መሆን አለመሆኑን አስመልክቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን አንድ ዐይነት አቋም የላቸውም፡፡ ምንም እንኳ ታሪኩ አንድ ክስተት ሊሆን ቢችልም፣ አያሌ ልዩነቶች አሉት። በሉቃስ ወንጌል ውስጥ እንደምናነበው ጴጥሮስና እንድርያስ ዓሣ ሲያጠምዱ ቆይተው መረቦቻቸውን እያደረቁ ነበር፣ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ግን ከሐይቁ ዳር ቆመው በመረቦቻቸው ዓሦችን እያጠመዱ ነበር። በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ወደ ታንኳቸው ገብቶ ሲያስተምር እናነባለን። በማቴዎስና በማርቆስ ወንጌሎች ውስጥ ግን ኢየሱስ ይህንን እንዳደረገ የሚያሳይ ምልክት የለም። ወደ ሐይቁ ገብተው ብዙ ዓሣ ማጥመዳቸውን የገለጸው ሉቃስ ብቻ ነው።ሉቃስ ይህንን ታሪክ የጨመረው ስለ ደቀ መዝሙርነት አንዳንድ ጠቃሚ እውነቶችን ለማስተማር ነው።
ሀ. ኢየሱስን መከተል ማለት ነገሮች አመክኒዮአዊ በማይመስሉበት ጊዜም እንኳ እርሱን መታዘዝ ማለት ነው። ጴጥሮስና እንድርያስ በዓሣ ማጥመድ ሙያ የተካኑ ሲሆኑ፤ ኢየሱስ ግን በሰው እይታ ስለ ዓሣ ማጥመድ ምንም ነገር የማያውቅ አናጺ ነበር። ሌሊቱን ሁሉ ዓሣ ሲያጠምዱ ነበር። ይህ ደግሞ ዓሣ ለማጥመድ ከሁሉም የተሻለው ጊዜ እንደሆነ ያውቁታል። ነገር ግን ምንም ዓሣ አልያዙም። ቀን ቀን ዓሣ ማግኘቱ አስቸጋሪ ነበር። ነገር ግን ከተለመደው አሠራር ውጭ ኢየሱስን ታምነው ስለ ታዘዙ፣ ከዚህ ቀደም ይዘው የማያውቁትን ያህል ዓሣ ለመሰብሰብ ችለዋል።
ለ. ደቀ መዝሙርነት የሚጀምረው ኢየሱስን በማወቅ ነው። ስለ ኢየሱስ ማንነት የተሻለ ግንዛቤ ሲኖረንና ይህም ግንዛቤ ሕይወታችንን ሲለውጥ፣ የሚያስከፍለው ዋጋ ምንም ያህል ከባድ ቢሆንም እንታዘዘዋለን። ጴጥርስ ኢየሱስ በተአምር ዓሣ ሊሰጣቸው እንደ ቻለ ሲመለከት፣ ጌትነቱን ተገነዘበ። ከዚህ በኋላ አሮጌ ሕይወቱን ትቶ በአዲስ ሕይወት ኢየሱስን ለመከተል ወሰነ፡፡
ሐ. ኢየሱስን ይበልጥ ስናውቀው፣ የራሳችንን ኃጢአተኛነትና ደካማነት እንገነዘባለን። ብዙውን ጊዜ ከእኛ የበለጠ ኃጢአት ከሚሠሩት ሰዎች የተሻልን እንደሆንን በማሰብ እንታበያለን። ይሁንና ራሳችንን ልናነጻጽር የሚገባን ከሰዎች ጋር ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ጋር ነው። ራሳችንን ከእግዚአብሔር ጋር በምናነጻጽርበት ጊዜ ብርሃን ባልነበረበት ቤት ውስጥ ድንገት ብርሃን ቢበራ በቤቱ ውስጥ ያለውን ቆሻሻ ማየት እንደሚቻል ሁሉ፥ የእኛም እድፍና ጉድፍ ቁልጭ ብሎ ይታያል። ደቀመዝሙር ሆነን ለመከተል ከፈለግን፣ ኢየሱስ ብቻ ቅዱሳን አድርጎ ሊጠብቀን እንደሚችል በመገንዘብ በትሕትና ልንመላለስ ይገባል።
መ. የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ትልቅ ውሳኔ ነው እርሱን ለመከተል ሁሉንም ነገር እንድንተው የሚጠይቅ በመሆኑ ሥር ነቀል ለውጥ ነው። ዓለምንና ኢየሱስን ልንከተል አንችልም። ሁለቱ መንገዶች የማይገናኙ ተቃራኒዎች ናቸውና። ሉቃስ ሥራችንን እንድንተው እያስተማረ አይደለም። ይህ የልብ ጉዳይ ነው። በልባችን ለእኛ ታላላቅ ናቸው የምንላቸውን ነገሮች ለምሳሌ ዝናን፥ ሀብትን፥ ትምህርትን፥ ሌላውንም ለኢየሱስ ስንል መተው ይገባናል። ለእኛ ከምንም ነገር በላይ ውድ መሆን ያለበት ኢየሱስ ብቻ ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆንህን ለመገንዘብ ሕይወትህን መርምር። ከእነዚህ አራት አቅጣጫዎች የደከምህባቸው ወይም ደቀ መዝሙር ያልሆንህባቸው የትኛቹ ናቸው? ለ) ሁሉንም ነገር ትተህ እንድትከተለው ያደረጉህን የኢየሱስን ባሕርያት ግለጽ። ሓ) ከልብህ ልታስወግዳቸው የሚገቡህን ኃጢአቶች ዘርዝር። መ) እግዚአብሔር እርሱን ለመከተል ሁሉንም ነገር ለመተው እንዲረዳህ በመጠየቅ በንስሐና ጸሎት የተወሰነ ጊዜ አላልፍ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)