ኢየሱስ በገዛ ሕዝቡ ማለትም በናዝሬት በሚኖሩ አይሁዶች ተገፋ (ሉቃስ 4፡14-30)

ኢየሱስ ከተጠመቀና ከተፈተነ በኋላ አገልግሎቱን በይፋ ለመጀመር ተዘጋጀ። በአገልግሎት ስላሳለፈው የመጀመሪያው ዓመት ብዙም የምናውቀው ነገር የለም። ሉቃስ ይህንን ጊዜ ያጠቃለለው፥ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ማስተማርና መፈወስ መጀመሩን በመግለጽ ነው። አሁንም ሉቃስ እኛም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሥራት እንዳለብን ያስገነዝበናል።

ከዕለታት በአንዱ ቅዳሜ ምናልባትም አገልግሎቱን ከጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ፥ ኢየሱስ ወዳደገባት ወደ ናዝሬት ተመለሰ። አይሁዶች በአምልኮአቸው መጨረሻ ላይ አዲስ መምህራንን የመጋበዝ ልማድ ነበራቸው። ከአይሁዳውያን የአምልኮ ልማዶች መካከል አንድ የብሉይ ኪዳን ክፍል ማንበብ አንዱ ነበር። ይህም ከሙሴ ሕግና ከትንቢት መጻሕፍት የሚቀርብ ምንባብ ነበር። ብዙውን ጊዜ አዲሱ መምህር ከነቢያት የምንባብ ክፍል ይሰጠውና ክፍሉን አንብቦ አንዳንድ አሳቦችን ያካፍላል። አይሁዶችም ኢየሱስን ይህንኑ እንዲያደርግ ጋበዙት። ከኢሳይያስ ምዕራፍ 61 ላይ እንዲያነብ የጠየቁት መንፈስ ቅዱስ ስለ መራቸው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ቁጥሮች ብቻ ካነበበ በኋላ፥ የመጽሐፉን ጥቅልል መልሶ ሰጣቸው። ከዚያም እንደ አይሁድ መምህራን ልማድ ኢየሱስ ቁጭ ብሎ አጭር ማብራሪያ አቀረበ። ማብራሪያውም እነዚህ ትንቢታዊ መልእክቶች በእርሱ አገልግሎት እንደ ተፈጸሙ የሚያመለክት ነበር።

ሉቃስ ይህንን ታሪክ የመረጠው በሁለት ምክንያቶች ነበር። አንደኛው፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት በድሆች፣ እስረኞችና ዐይነ ስውራን ላይ እንዳተኮረ ያመለክታል። ምንም እንኳ ኢሳይያስ እነዚህን ቃላት የተጠቀመው የሕዝቡን መንፈሳዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ለማመልከት በሚያስችል ተምሳሌታዊ አገላለጽ ቢሆንም፣ ሉቃስ ኢየሱስ ለድሆች የሰጠውን አገልግሎት እንደሚያጠቃልል ያስረዳል። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አብዛኛቹ ምእመናን ድሆች ስለ ነበሩ፣ ሉቃስ ምንም እንኳ ዓለም ብትንቃቸውም ኢየሱስ እንደሚወዳቸው በመግለጽ ያጽናናቸዋል። ይህ ክርስቲያኖችም በድሆች ላይ ያተኮረ አገልግሎት ማድረግ እንደሚገባቸው የሚያመለክት ማስጠንቀቂያ ነው። በሀብታሞችና በኃያላን ላይ በማተኮር፥ ድሆችን መርሳት ኢየሱስ ያገለገለበትን መንገድ ለመከተል አለመፈለግ መሆኑን አሳስቧል።

የውውይት ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እያገለገለ ቢሆን፣ አገልግሎቱ በእነማን ላይ የሚያተኩር ይመስልሃል? ለ) አንተና ቤተ ክርስቲያንህ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተናቁትን ለማገልገል የምታደርጉትን ተግባራት ዘርዝር። ሐ) ድሆችን ዘንግቶ በምሑራን፣ በሀብታሞችና በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ማተኮሩ ቀላል የሚሆነው እንዴት ነው?

ሁለተኛው፣ ሉቃስ በታሪኩ ውስጥ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን ለመፈጸም እያገለገለ መሆኑን ለማሳየት ይፈልጋል።

ኢየሱስ ስብከቱን በጨረሰ ጊዜ አይሁዶች እርስ በርሳቸው ይወያዩ ጀመር። በመጀመሪያ አንዳንዶች ኢየሱስ መልካም ንግግር እንዳቀረበ በመግለጽ ድጋፋቸውን ሰጥተው ነበር። ወዲያውኑ ግን ኢየሱስ ከእነርሱ አንዱ እንደሆነ ተገነዘቡ። የአናጺው የዮሴፍ ልጅ እንደሆነ አስታወሱ። በዚህ ጊዜ ድጋፋቸው ወደ ጥርጣሬ ተለወጠ። ኢየሱስ አገልግሎቱ በናዝሬት ላይ እንዲያተኩር በመፈለጋቸው ራስ ወዳዶች መሆናቸውን ገለጻ። ኢየሱስ ለሌሎች ሳይሆን ለእነርሱ ብቻ ተአምራትን እንዲያደርግ ነበር የፈለጉት። ይህንን ሲጠይቁ ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን ተገንዝበው በእርሱ ለማመን እንደፈለጉ እየገለጹ አልነበረም። ኢየሱስ በቅድሚያ ፍላጎታቸውን እንዲያሟላላቸው ብቻ ነበር የፈቀዱት።

በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በብርቱ ወቀሳቸው። በብሉይ ኪዳን ዘመን እስራኤል ከእግዚአብሔር ገሸሽ ብላ ነበር። ኤልያስ ምንም ያህል ተግቶ ቢያገለግላቸውም፣ ከአምልኮተ ጣዖት ለመራቅ ፈቃደኞች አልነበሩም። ስለሆነም እግዚአብሔር ነቢዩን ወደ ሁለት አሕዛብ ላከው፡፡ ኤልያስ በእስራኤል ከነበሩት ብዙ መበለቶች ይልቅ የሲዶንን መበለቶች አገለገለ። በእስራኤል አገር ከነበሩት ብዙ ለምጻሞች ይልቅ ኤልያስ ሶርያዊውን ንዕማንን ፈወሰው። ኢየሱስ አይሁድ በእርሱ የማያምኑ ከሆነ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አሕዛብ እንደሚመልስ እያስጠነቀቃቸው ነበር። አሁንም ሉቃስ እግዚአብሔር አሕዛብን የበረከቱ ተካፋዮች ለማድረግ እንደወጠነ አመልክቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እኛ ክርስቲያኖችስ በራስ ወዳድነት መንፈስ ተይዘን እግዚአብሔር የእኛን ቤተ ክርስቲያን ወይም ቤተ እምነት ብቻ እንዲባርክ ልንጠይቅ የምንችለው እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ ዓለማዊ ወይም ራስ ወዳድ በምንሆንበት ጊዜ እግዚአብሔር በረከትን ከእኛ ነሥቶ ለሌሎች ሊሰጥ የሚችለው እንዴት ነው?

እግዚአብሔር ከአይሁዶች ይልቅ አሕዛብን እንደሚባርክ መነገሩ በናዝሬት የነበሩትን አይሁዶች በጣም ስላስቆጣቸው፣ በመካከላቸው ያደገውን ኢየሱስን ለመግደል ተነሣሱ። ነገር ግን ኢየሱስ በእግዚአብሔር ፈቃድ ይሠራ ስለነበር፣ እግዚአብሔር አዳነው። የሚሞትበት ጊዜ ገና ስላልደረሰ ምንም ጉዳት ላይመጣበት ተለይቷቸው ሄደ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: