- ኢየሱስ ለምጻሙን ሰው ፈወሰ (ሉቃስ 5፡12-16)
ሉቃስ ኢየሱስ እንደ ለምጻሙ ሰው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንደሚራራ ያሳያል። ኢየሱስ በሰማይ ብቻ የሚኖር የሩቅ አምላክ ሳይሆን፣ የሚከብዱንን ነገሮች የሚያውቅና ችግሮቻችንንም የሚያቃልልልን ርኅሩኅ አምላክ ነው። ድንቅ ፍቅሩን እየተለማመድን ስንሄድ፣ እርሱን መከተል ቀላል ይሆንልናል።
ኢየሱስ የፈውስ አገልጋይ ሆኖ ለመታወቅ አልፈለገም ነበር። ብዙውን ጊዜ ሰዎችን ከፈወሰ በኋላ ለማንም እንዳይናገሩ ያስጠነቅቃቸው ነበር። ሰዎቹ ግን እርሱ እንደ ፈወሳቸው በመናገራቸው፣ ኢየሱስ የሰዎችን ፍላጎት በማሟላትና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በመስበክ መካከል ያለውን ሚዛናዊነት ለመጠበቅ ታግሏል። የሰዎች ፍላጎቶች ደግሞ ማለቂያ አልነበራቸውም። ኢየሱስ በሰብአዊነቱ ችግሮቻቸውን ሁሉ ለማቃለል አይችልም ነበር። የፈውሱ አገልግሎት ያለውን ጊዜና ጉልበት ሁሉ ስለሚወስድበት ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ ለማስተማር የሚተርፍ ጊዜ አልነበረውም። ኢየሱስ የሰዎችን ፍላጎት ለማሟላትና ወንጌልን ለመስበክ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ጥሪ ሚዛናዊ አድርጎ የፈጸመው እንዴት ነበር? ሉቃስ ለዚህ ቁልፉ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት መገናኘቱ እንደሆነ ይገልጻል። አመለካከቱ ሊጠራ የሚችለው በዚህ ጊዜ ብቻ ነበር። በሁካታ መካከል እግዚአብሔርን ለመስማት አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ በሚጸልይበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ድምፅ በጥንቃቄ ለመስማት ይችል ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡– የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ክርስቲያኖች በእምነታቸው ጠንክረው ላልዳኑት እንዲመሰክሩ ከማድረግ ይልቅ፥ በሰዎች አንገብጋቢ ችግርች ላይ በማተኮር ሚዛናዊነትን ለመጠበቅ የሚቸገሩት እንዴት ነው? ለ) ሕይወትህ ሚዛናዊ እንደሆነና እግዚአብሔር የሚፈልገውን እንደምታደርግ ለማረጋገጥ በግልህ ከእግዚአብሔር ጋር የምትገናኝባቸውን መንገዶች ዘርዝር።
- ኢየሱስ ሽባውን ሰውዬ ፈወሰ (ሉቃስ 5፡17-26)
ኢየሱስ አገልግሎቱ ለዎችን በመርዳትና በመፈወስ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ለማድረግ ይችል ነበር። ነገር ግን የመጣው አዳኝ ለመሆን ነው። ኢየሱስ ሰዎች የኃጢአታቸው አዳኝ እንደሆነ እንዲገነዘቡለት ለማድረግ ሞክሯል። ብዙውን ጊዜ ግን ከተአምራቱ ሌላ አክለው ለማየት አልቻሉም። እንደ ፈሪሳያውንና (የደኅንነትን ሕግጋት በመጠበቁ ላይ የሚያተኩሩ አጥባቂ ሃይማኖተኞች) ጸሐፍት (የሥነ መለኮትና የብሉይ ኪዳን ሊቃውንት) ያሉት ሰዎች ተአምራቱን ቢመለከቱም ሊያምኑበት አልቻሉም። ተራውም ሕዝብ ሲከተለው የነበረው ለግል ጥቅሙ ነበር፤ የሃይማኖት መሪዎች ደግሞ ባለማመንና በቅንዓት ሳቢያ ኢየሱስን ለመከተል እምቢ አሉ።
ኢየሱስ ሁለቱም ቡድኖች ከእርሱ ጋር ባላቸው ግንኙነት እንዲያድጉ ይፈልግ ነበር። ስለሆነም ኢየሱስ ሽባውን በሚፈውስበት ጊዜ ሰውዬውን በቀጥታ ከመፈወስ ይልቅ፥ በመጀመሪያ «ኀጢአቱን ይቅር አለው»፥ ከዚያም ፈወሰው። ኃጢአቱን ይቅር ማለት ከፈውሱ የበለጠ አስፈላጊ ነበር። ኃጢአቱ ይቅር መባሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጠዋል፤ ከደዌው መፈወሱ ጊዜያዊ ዕረፍት ይሰጠዋል። ሉቃስ ኢየሱስ መለኮታዊ ፈዋሽ ከመሆኑም ባሻገር፣ የሰዎችን ታላቁን በሽታ እንደሚያድን ገልጾአል። ይኸውም የኃጢአት ስርየት ነው። የሚያሳዝነው ሁሉም ነገር ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ሰዎች ያተኮሩት ኃጢአትን ይቅር በማለቱ ላይ ሳይሆን በተአምሩ ላይ መሆኑ ነው።
የውይይት ጥያቄ፡– ተአምራትና ፈውሶች ዛሬም አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን እንዴት ለሰው ልጅ ከሚያስፈልገው መሠረታዊ ጉዳይ እንደሚያርቁት ግለጽ።
- ኢየሱስ፥ ማቴዎስ(ሌዊ) እንዲከተለው ጠራው (ሉቃ. 5፡27-32)
ሉቃስ ኢየሱስ የመጣው የሰዎችን ነፍስ ለመፈወስ ነው የሚለውን እውነት አጉልቶ ለማሳየት ሲል አይሁዶች እጅግ ኃጢአተኛ እንደሆነ የሚቆጥሩትን ሰው፥ ኢየሱስ በጠራው ጊዜ የሆነውን ነገር ገልጾአል። ማቴዎስ እጅግ የተጠላ ቀረጥ ሰብሳቢ ሰው ነበር። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች እግዚአብሔርን በተሳሳተ መንገድ በመረዳታቸው፣ እግዚአብሔር ምግባረ መልካም ሰዎችን ብቻ እንደሚፈልጎ አድርገው ያስቡ ነበር። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን እንደሚጠላና የቅጣት ጊዜውን እንደሚጠባበቅ ያስቡ ነበር። ኢየሱስ ግን እግዚአብሔር (እንደ ሉቃስ) ሐኪም እንደሆነ ነገራቸው። የሐኪሙ ዓላማ የታመሙትን ሰዎች መፈወስ እንደሆነ ሁሉ፥ ኢየሱስም በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የታመሙትን ለማከም ነበር የመጣው። ነገር ግን አንድ ሐኪም በሽተኛ አይደለሁም ብሎ የሚያስበውን ሰው ለመርዳት እንደማይችል ሁሉ፣ ኢየሱስም መንፈሳዊ በሽታ እንዳለባቸው የማያስተውሉትን ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ለመርዳት አልቻለም።
- ኢየሱስ ስለ ጾም ተጠየቀ (ሉቃስ 5፡33-39)
የኢየሱስ ተከታዮች ሊማሯቸው ከሚገባ ነገሮች አንዱ፥ እንደ ጾም ካሉት መንፈሳዊ ሥርዐቶች በስተ ጀርባ ያሉትን ምክንያቶች ነው። መንፈሳዊ ሥርዐቶች መልካም ቢሆኑም፣ እንኳ ለተሳሳተ ምክንያት ሊውሉ ይችላሉ። አይሁዶች በጾም መንፈሳዊነታቸውን ለሌሎች ያሳዩ ነበር።
ኢየሱስ ግን ስለ መንፈሳዊነት ያለው አመለካከት ከፈሪሳውያኑ ሙሉ በሙሉ የተለየ መሆኑን ገለጸላቸው። አንደኛው ቁም ነገር፥ ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረገው ግንኙነት ነው። መሢሕና አዳኝ የሆነው ኢየሱስ በመካከላቸው ስለነበር፣ በጊዜው ጾም የሚጾሙበት ምክንያት አልነበረም። ጾም ከኢየሱስ ጋር እንዳይሆኑ ያግዳቸው ነበር። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ፣ ጾም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ምክንያቱም ደቀ መዛሙርቱ በጸሎት ከኢየሱስ ጋር እንዲገናኙ ረድቷቸዋል። ሁለተኛው፣ መንፈሳዊነት የተወሰኑ ደንቦችን (በብሉይ ኪዳን እንደተጠቀሰው በተወሰኑ ቀናት መጾም)፣ ወይም ፈሪሳያውያን እንደሚያደርጉት መንፈሳዊነትን ለሌሎች በማሳየት ሊሆን አይገባውም። ነገር ግን ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር የልብ ግንኙነት ስለ ማድረግ አዲስ መርሕ ሰጥቷል። ይህ አዲስ ግንኙነት በልምምድ ላይ ሳይሆን በልብ ዝንባሌ ላይ የሚያተኩር አዲስ የወይን አቁማዳ ሆኗል። ይህ አሮጌውን ማለትም በደንቦች ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት አስወግደው በልባቸው የኢየሱስን ትምህርት የሚቀበሉበትና የሚታዘዙበት ጊዜ ነበር። የአይሁዶች ልማዳዊ አኗኗር ኢየሱስን ከመከተል ጋር አብሮ ሊሄድ አይችልም።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንደ ኢየሱስ ሳይሆን እንደ ፈሪሳውያን በመመላለስ ኢየሱስን ስለ መከተል የተሳሳተ ግንዛቤ ልንይዝ የምንችለው እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔር በአዲስ የወይን አቁማዳ ውስጥ አዲስ ወይን በመጨመር ልብህን የለወጠባቸውን መንገዶች ዘርዝር።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)