ሉቃስ 7፡1-50

  1. ሌሎች ቦታ ለማይሰጧቸው ነገሮች ኢየሱስ ያሳየው ርኅራኄ (ሉቃስ 7፡1-17)

ሉቃስ ክርስቲያኖች በዘርና በፆታ ሳይወሰኑ ለሌሎች ሰዎች መንፈሳዊ ዝንባሌ ሊያሳዩ እንደሚገባ ለማመልከት ጥሯል። ኢየሱስ እንደ አሕዛብና መበለቶች በዘመኑ ያሉትን የተናቁ ሰዎችን ከወደደ፤ እኛም ይህንኑ ልናደርግ ይገባናል። ኢየሱስ ርኅራኄውን ለእንግዶችና ተስፋ ለሌላቸው ለማሳየት፥ የአይሁድን ልማድ አልፎ በመሄድ ሁለት ምሳሌዎችን አቅርቧል፡–

ሀ. ኢየሱስ አሕዛብ የሆነውን የመቶ አለቃ ልጅ ፈወሰ (ሉቃስ 7፡1-10)። በኢየሱስ በማመን ምሳሌነትን ያተረፈ ሰው የተገኘው ከአይሁዶች ሳይሆን፥ ሮማዊ የመቶ አለቃ ነው። የመቶ አለቃው ኢየሱስ ለመፈወስ እንደሚችል ብቻ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔር አብ ኃይልና ሥልጣን እንደሚሠራም ተገንዝቦ ነበር። ኢየሱስ አንድን ሰው ለመፈወስ የግድ በስፍራው መገኘት አያስፈልገውም ነበር። የአንድ ጄኔራል ትእዛዝ ሠራዊቱ የተፈለገውን ተግባር እንዲያከናውን እንደሚያደርግ ሁሉ፣ የኢየሱስም የትእዛዝ ቃል ነገሮችን ለማከናወን ያስችል ነበር። እግዚአብሔር የሰዎችን እምነት ያከብራል። የዚህን የመቶ አለቃ እምነት እንዳከበረ ሁሉ፣ ወደ እርሱ የሚመለሰውን የየትኛውንም አሕዛብ እምነት እንደሚያከብር እሙን ነው።

ለ. ኢየሱስ የመበለቷን ልጅ ከሞት አስነሣ (ሉቃስ 7፡11-17)። በአይሁድ ማኅበረሰብ ውስጥ የመበለቶችን ያህል ለችግር የተጋለጡ ሰዎች ብዙ አይደሉም። መበለቶች የሚንከባከባቸው ባል ስለሌላቸው በልጆቻቸው ላይ ተደግፈው ይኖሩ ነበር። ስለሆነም ይህች መበለት ብቸኛ ልጇን ስታጣ የቀራት ተስፋ አልነበራትም። ነገር ግን ኢየሱስ ለመበለቲቱ አሰበ። ስለሆነም ሴቲቱ ሳትጠይቅና ምንም ዐይነት የእምነት ምልክት ሳታሳይ ልጇን ከሞት አስነሣላት።

የውይይት ጥያቄ፡– በአካባቢህ ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ሰዎች ምንም ዐይነት አክብሮት ወይም እርዳታ የማያገኙትን ወገኖች ሁኔታ ግለጽ። ለእነዚህ ወገኖች ርኅራኄ ለማሳየት አንተና ቤተ ክርስቲያንህ ምን እያደረጋችሁ ነው? ምንስ ልታደርጉ ትችላላችሁ?

  1. ኢየሱስ የመጥምቁ ዮሐንስን ጥያቄ መለሰ (ሉቃስ 7፡18-35)

እግዚአብሔር ባልተጠበቀ መንገድ በሚሠራበት ጊዜ የእግዚአብሔር ልጆች መጠራጠር ይጀምራሉ። እግዚአብሔር በከፍተኛ ደረጃ የተጠቀመበት አንድ አገልጋይ በድንገት ሲሞት፣ የትዳር ጓደኛችንን በመኪና አደጋ ስናጣ፣ ወይም አንድ ሰው ታሞ ሲሞት በእግዚአብሔር ላይ የነበረን እምነት ፈተና ይገጥመዋል። መጥምቁ ዮሐንስም ጥርጣሬዎች ነበሩት። ምንም እንኳ ዮሐንስ ለነቢይነት አገልግሎት የተጠራ ቢሆንም፣ እስር ቤት ተጥሎ ነበር። መሢሑ በታላቅ ኃይል ተገልጦ ክፉ ሰዎችን «በእሳት ጥምቀት» እንደሚያስወግድ ቢጠብቅም፣ እርሱ ያሰበው ሊሳካ አልቻለም። ዮሐንስ ተሳስቼ ነበር ማለት ነው ሲል አሰበ።

ኢየሱስ የሚያደርጋቸውን ተአምራት በመገንዘብ መጥምቁ ዮሐንስ በእምነቱ እንዲጸና አበረታታው። በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንኳ እግዚአብሔር በሥራ ላይ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። የእግዚአብሔር ዓላማ ይበልጥ ግልጽ እስኪሆንልን ድረስ እነዚህ ነገሮች በእምነታችን ጸንተን እንድንቆም ይረዱናል። ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስ መሢሑ በሚመጣበት ጊዜ መንገድ የጠረገ ታላቅ ነቢይ እንደሆነ በይፋ ከመሰከረለት በኋላ፣ አጋጣሚውን በመጠቀም የሃይማኖት መሪዎችን ይገሥጽ ጀመር። ይህንንም ያደረገው በእርሱ ስላላመኑ ነበር። ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ራሱን እየጨቆነ ሲያገለግል ሳለ፣ ተመጻዳቂ ሰው እንደሆነ አድርገው ወቀሱት። ኢየሱስ ከኃጢአተኞች ጋር ሲተባበርና አብሯቸው ሲበላ ደግሞ የሰካራሞችና የሕገ ወጦች ወዳጅ አድርገው ቆጠሩት።

ሉቃስ የተራ ሰዎችን በተለይም የ “ኃጢአተኞችን” ስሜት ከሃይማኖት መሪዎች ጋር አነጻጽሯል። ተራዎቹ ሰዎች መጥምቁ ዮሐንስና ኢየሱስ በሰበኩ ጊዜ ንስሐ ገብተው ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ፣ የሃይማኖት መሪዎች ግን መጥምቁ ዮሐንስን ለመስማት አልፈለጉም። ዮሐንስንና ከዚያ በኋላም ኢየሱስን ለመስማት ባለመፈለጋቸው ከእግዚአብሔር በረከት በሚያጎድላቸው መንገድ ተጓዙ። በአንጻሩም ዮሐንስንና ኢየሱስን በመከተል ሕይወታቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያጣመሩ ሰዎች መንፈሳዊ ጥበብ ያገኙ (የጥበብ ልጆች) እና እግዚአብሔር የባረካቸው ነበሩ።

  1. አንዲት ኃጢአተኛ ሴት ኢየሱስን ሽቶ ቀባችው (ሉቃስ 7፡36-50)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ የቤተ ክርስቲያንህ ሽማግሌ መጠጥ ቤት ውስጥ ከአንዲት ሴተኛ አዳሪ ጋር እየተጫወተ ሲጠጣ ብትመለከት፥ ምላሽህ ምን ይሆናል? ለ) ብዙውን ጊዜ ከኃጢአተኛ ሰው ጋር መገናኘት እኛንም ያቆሽሸናል ብለን የምናስበው ለምንድን ነው?

አደገኛ ኃጢአተኞች ናቸው ከሚባሉት ሰዎች ጋር ስንገናኝ በውስጣችን የሚታገለን የሆነ ነገር አለ። አንዲት ሴተኛ አዳሪ ብናይ ታበላሸናለች በሚል ፍርሃት ቀና ብለን ሳናያት ሮጠን እናልፋለን። ወይም ደግሞ ዱርዬዎች ብለን ከምንጠራቸው ሰዎች ለመራቅ የምንችለውን ያህል ጥረት እናደርጋለን። በግልጽ ኃጢአተኞች እንደሆኑ ከምናውቃቸው ሰዎች አካባቢ ከተገኘን እንበላሻለን የሚል አሳብ አለን።

ይህም የፈሪሳውያን አስተሳሰብ ነበር። ስለሆነም ኢየሱስ በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንረክሳለን በሚል ፍርሃት ያርቋቸው ከነበሩት ሰዎች ጋር ሲተባበር ሊያዩ፥ በጣም ደነገጡ። በአንድ አጋጣሚ ምናልባትም ሴተኛ አዳሪ የሆነች ግለሰብ በኢየሱስ እግር ላይ ሽቶ በማርከፍከፍ በእንባዋ እግሮቹን ታጥብ ጀመር። ይህንን ያደረገችው ለምንድን ነው? ምናልባትም ከዚህ በፊት ኢየሱስ ሰዎች የማይፈልጓቸውን ወገኖች እንደሚቀበልና የእግዚአብሔርም ይቅርታ እንደ ወረደላቸው ሲናገር ሰምታ፣ እግዚአብሔር እንደ ተቀበላት ተረድታ ይሆናል። ይህች ሴት በኢየሱስ ርኅራኄ ስለ ተደነቀች፣ ውድ ሽቶ በእግሮቹ ላይ በማፍሰስ መንፈሳዊ ፍቅርዋንና አክብሮቷን ገለጸችለት።

አንድ ጊዜ ኢየሱስ ስምዖን በተባለ አንድ ፈሪሳዊ ቤት ለማዕድ ተቀምጦ ነበር። ስምዖን ድምፁን ከፍ አድርጎ አሰምቶ ባይናገርም ኢየሱስ አሳቡን ስለተረዳ፣ ስለ ሁለት ባለ ዕዳ ሰዎች ምሳሌ አቀረበለት። አንደኛው የተበደረው የሦስት ዓመት ሥራን የሚጠይቅ ገንዘብ ሲሆን፣ የሁለተኛው ግን የሁለት ወር ብቻ ነበር። ሁለቱም የሚከፍሉትን ባጡ ጊዜ አበዳሪው ማራቸው፡፡ ይበልጥ የምስጋና ስሜት የሚኖረው የትኛው ነበር? ብዙ የገንዘብ ዕዳ የተሰረዘለት ሰው ነበር። በተመሳሳይ መንገድ ጋለሞታይቱ እግዚአብሔር ይቅር ይለኛል የሚል ግምት አልነበራትም። ስለሆነም ኢየሱስ ብዙ ኃጢአትን ይቅር ባላት ጊዜ እጅግ ወደደችው። ነገር ግን እንደ ስምዖን ጻድቃን ነን የሚሉ ሰዎች ጥልቅ የእግዚአብሔር ፍቅር አልነበራቸውም። ኢየሱስ ለእርሱ ያላትን ፍቅር፣ እምነትና የተለወጠ ልቧን በመመልከት፥ ኃጢአት ይቅር እንደ ተባለላት ነገራት።

ምናልባት ሉቃስ እኛም ለምናስበው ነገር ትኩረት እንድንሰጥ እያስጠነቀቀን ይሆናል። በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ከእግዚአብሔር ብዙም እንዳልራቁ ለምናስባቸው ሰዎች ብቻ ወንጌልን የምንሰብክ ከሆነ፣ አብያተ ክርስቲያናት ለኢየሱስ ጥልቅ ፍቅር በሌላቸው ሰዎች ይሞላሉ። ነገር ግን ኃጢአተኛ መሆናቸውን ለሚገነዘቡ ሰዎች የኢየሱስን ይቅርታ ሰብከንላቸው ካመኑ፥ አብያተ ክርስቲያናት ለክርስቶስ ከፍተኛ ፍቅር ባላቸው ሰዎች ይሞላሉ። ስለሆነም ከኃጢአተኞች ራሳችንን ገለል ከምናደርግ፥ የኢየሱስን የይቅርታ ወንጌል ልንሰብክላቸው ይገባል። በኃጢአት ተግባራቸው ተካፋይ ባንሆንም፥ የእግዚአብሔርን ፍቅር ልናውጅላቸው ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በክርስትና ሕይወታችን እየቆየን እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር በማለት ስላሳየን በጎነት ስንዘነጋ፥ ለእግዚአብሔር የነበረን ፍቅር እየቀዘቀዘ የሚሄደው እንዴት ነው? ለ) የፈሪሳውያን ዐይነት አመለካከት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ የተከበሩትን ሰዎች ብቻ ላይሆን ኃጢአተኞችንም በወንጌል ለመድረስ የምትከተላቸውን መንገዶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: