የኢየሱስ የዕለት ተዕለት ሕይወት እንዴት ነበር? ሉቃስ ኢየሱስ ሁልጊዜ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ላይ እንደ ነበር በመግለጽ፥ የዕለት ተዕለት ሕይወቱን ጠቅለል አድርጎ ገልጾአል። ስለ እግዚአብሔር መንግሥት መልካሙን የምሥራች እየሰበከ ከመንደር መንደር ይዞር ነበር። ብዙውን ጊዜ ከኢየሱስ ጋር የሚጓዙት 12ቱ ደቀ መዛሙርት ናቸው ብለን እናስባለን። ነገር ግን ሌሎች ደቀ መዛሙርትም ከኢየሱስ ጋር ነበሩ። ቢያንስ ኢየሱስ በኋላ ለስብከት አገልግሎት ያሰማራቸው 70 ደቀ መዛሙርት እንደ ነበሩ እናውቃለን፡፡ የኢየሱስ የቅርብ ተከታዮች በሙሉ ወንዶች አልነበሩም። ሉቃስ ኢየሱስ ሴቶችንም ይቀበል እንደ ነበር ለማሳየት፣ ሴቶችም ከኢየሱስ ጋር ከቦታ ቦታ እየዞሩ ያገለግሉ እንደ ነበር አመልክቷል። እንዲያውም እነዚህ በኢየሱስ ይቅርታ ልባቸው የተነካ ሴቶች በገዛ ገንዘባቸው የኢየሱስንና የደቀ መዛሙርቱን ፍላጎት ያሟሉ ነበር። በታሪክ እንደሚታወቀው ከማንም በላይ ግልጽ በሆነ መንገድ ለኢየሱስ ያላቸውን ፍቅር ሲገልጹና የእግዚአብሔርን ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ሲደግፉ የኖሩት ሴቶች ናቸው። ይሁንና በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ እንኳ ሳይቀር፥ በታሪክም ውስጥ ሴቶች በወንዶች ሲጫኑና ሊናቁ ኖረዋል።
ጳውሎስ በክርስቶስ ዘንድ ወንድና ሴት የሚባል ነገር እንደሌለ ገልጾአል (ገላ. 3፡28)። ይህ ማለት ክርስቲያን መሆን የአንድን ሰው ፆታ ያስወግዳል ማለት አይደለም። ነገር ግን ክርስትና ወንዶችና ሴቶች እኩል እንደሆኑ ያስተምራል። ሁለቱም ፆታዎች ለእግዚአብሔር አስፈላጊና ጠቃሚዎች ናቸው። ሁለቱንም በራሱ አምሳል ፈጥሯቸዋል። ሴቶችን በማናናቅ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስፍራ እንደሌላቸው የሚያስተጋባ የትኛውም አመለካከት፥ ኢየሱስ ስለ ሴቶች ካስተማረው ትምህርት ጋር የሚጋጭ ነው። ኢየሱስ እርሱን ስለ መከተል የተለያዩ ትምህርቶችን አስተምሯል።
ሀ. የአራቱ መሬት ምሳሌ። ፍሬ ሊያፈሩ የሚችሉት የእግዚአብሔርን ቃል የሚያምኑና የሚጸኑ ብቻ ናቸው ሉቃስ 8፡1-15)። ሉቃስ ኢየሱስ እያስተማረ ሳለ ምሳሌ የተጠቀመባቸውን ጊዜያት ገልጾአል። ኢየሱስ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበ ጊዜ አጋጣሚውን በመጠቀም በእርሱ አምነው መንገዳቸውን ለመለወጥ ያልፈለጉ ሰዎችን ለመገዳደር ፈለገ። በተጨማሪም፥ ደቀ መዛሙርቱ በሕዝቡ ግፊት እንዳይናወጡም ለማስተማር ፈልጓል። ወንጌሉን ከሚሰሙት ሕዝብ መካከል አንድ አራተኛው ብቻ እግዚአብሔርን የሚያከብር ምላሽ ሰጥተዋል። ሌሎች ሦስት ምላሾች ደግሞ ወዲያውኑ ኢየሱስን ለመቀበል አለመፈለግ፣ በስደት ጊዜ የማይጸና ጊዜያዊ እምነትና የዓለምን ነገሮች በመውደድ የሚሰናከል ጊዜያዊ እምነት ናቸው። እነዚህ ሁሉ ለእግዚአብሔር መንግሥት ዘለቄታ ያለው ጥቅም የማያስገኙ ናቸው። ለእግዚአብሔር መንግሥት ዘላቂ ፍሬ ሊሰጡ የሚችሉት ኢየሱስን የሚከተሉና የእግዚአብሔር ቃል በልባቸው ውስጥ ሰርጾ እንዲለውጣቸው የሚያደርጉ ብቻ ናቸው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ እነዚህ አራት ምላሾች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት እንደሚከሰቱ ግለጽ። ለ) ይህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአባላት ብዛት እንዳንደነቅ ምን ሊያስተምረን ይችላል? ሐ) የእግዚአብሔር ቃል በምእመናን ልብ ውስጥ ሥር እየሰደደ መሆኑን የሚያሳየን መረጃ ምንድን ነው?
ለ. የብርሃን ምሳሌ። ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉት ስለ ኢየሱስ የሚመሰክሩና የተለወጠ ሕይወታቸውን የሚያሳዩ ብቻ ናቸው (ሉቃስ 8፡16-18)፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በሕይወታቸው ውስጥ እንዲኖር የሚያደርጉ የኢየሱስ ተከታዮች ብቻ ፍሬያማ ክርስቲያኖች ሊሆኑ እንደሚችሉ ከፍ ብለን ተመልክተናል። ኢየሱስን በትክክል የሚከተሉ ሰዎች በቃላቸውና በተግባራቸው ለዓለም እንደ ከዋክብት የሚያበሩ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። የኢየሱስ ተከታዮች ቃሉን ከመደበቅ ይልቅ ለሁሉም በገሃድ ሊመሰክሩ ይገባል። ይህንን ካላደረግን፣ ለቃሉ ያለን መንፈሳዊ መነቃቃት ይወሰድብናል።
ሐ. የእውነተኛ መንፈሳዊ ቤተሰብ ምሳሌ። እውነተኛ የቤተሰብ አባላት ኢየሱስን የሚከተሉት ብቻ ናቸው (ሉቃስ 8፡19-21)። ኢየሱስ የሥጋ ቤተሰቡን ይወድ የነበረ ቢሆንም፣ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ከዚህ እንደሚበልጥ ያውቅ ነበር፡፡ በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናቸው (ዮሐ 1፡12)፣ በአንድነት የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት መሆናችንን እንዴት እናውቃለን? የመጨረሻው ፈተና በአንደበታችን የምንናገረው ቃል ወይም በቤተ ክርስቲያን የምንዘምረው መዝሙር ሳይሆን፣ ለእግዚአብሔር ቃል መታዘዝ አለመታዘዛችን ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ኢየሱስ እነዚህን ሦስት ማብራሪያዎች ለደቀ መዛሙርቱ ማስተማር አስፈላጊ እንደሆነ ያሰበው ለምንድን ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)