ሉቃስ 10፡25-42

  1. ክርስቶስን መከተል ሌሎችን በምናስተናግድበት ሁኔታ ሊገለጽ ይገባል (ሉቃስ 10፡25-37)

ኢየሱስን መከተል የእምነትን ብቻ ሳይሆን የሕይወትም ለውጥ ይጠይቃል። አንድ ቀን አንድ የአይሁድ አስተማሪ ኢየሱስ የዘላለምን መንገድ እንዲነግረው ጠየቀው። ኢየሱስ ብሉይ ኪዳንን በመከለስ ምላሽ ሰጠው። ይህ ሰው እግዚአብሔር የሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ በሁለት ትእዛዛት እንደ ተጠቃለሉ ያውቅ ነበር። እነዚህም እግዚአብሔርንና ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ናቸው። ዋናው ጉዳይ ግን ማመናችን ብቻ ሳይሆን እምነታችንን በሥራ ማሳየታችን ነው። ሰውዬው ኢየሱስ ባልንጀራው ማን እንደሆነ እንደሚነግረው ተስፋ በማድረግ ይህንኑ ጥያቄ አቀረበለት። የኢየሱስ መልስ ሰውየውንና አይሁዶችን በብዙ መንገዶች ሳያስደነግጥ አልቀረም።

በኢየሱስ ታሪክ ውስጥ ሌሎችን ሰዎች ለመርዳት ያልፈለጉት መንፈሳውያን ናቸው ተብለው እጅግ የሚከበሩ ሰዎች ነበሩ። እነዚህም የሕዝቡ ሃይማኖታዊ መሪዎች የነበሩት ካህናትና ሌዋውያን ናቸው። ስለ እግዚአብሔር ትክክለኛ ነገሮችን ቢያምኑም፣ ምሕረትን ግን አያውቁም ነበር። ምሕረትን ያሳየው አይሁዶች የሚጠሉት ሳምራዊው ሰው ነበር። ይህ ሰው ትክክለኛ እምነት አልነበረውም። ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ አይሰግድም ነበር። ነገር ግን የተቸገረውን ሰው ረድቷል። ባልንጀርነት በዘር፣ በትውውቅ ወይም በዝምድና ላይ በመመሥረት አይደለም። ማንኛውም ሰው እንግዳም እንኳ ቢሆን፥ የሰው ልጅ በመሆኑ ባልንጀራችን ነው። ስለሆነም ባልንጀራቸውን በመውደድ እግዚአብሔርን የሚታዘዙ ሰዎች ምንም ወሮታ ሳይጠብቁ የምሕረት እጃቸውን የሚዘረጉ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለሌሎች፣ በተለይም ከቤተ ክርስቲያናቸው ውጭ ለሚገኙ የተናቁ ሰዎች የእርዳታ እጃቸውን የማይዘረጉት ለምንድን ነው? ለ) ብዙውን ጊዜ በትክክል ከመኖር ይልቅ ትክክለኛ ነገሮችን ማመን የሚቀልለው ለምንድን ነው? ሐ) በማኅበረሰብህ ጉዳት የሚደርስባቸው ወገኖች እነማን እንደሆኑ ዘርዝር። ኢየሱስ አንተና ቤተ ክርስቲያንህ ለዚህ ችግር ምን እንድታደርጉ የሚፈልግ ይመስልሃል?

  1. የኢየሱስ ተከታይ የሆነ ሰው ከእርሱ ጋር የማሳለፉን ጠቀሜታ ያውቃል (ሉቃስ 10፡38-42)

የአልዓዛር እኅቶች የሆኑት ማርያምና ማርታ የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች ነበሩ። ኢየሱስ የመጨረሻ ሳምንት ጊዜውን ያሳለፈው ቢታኒያ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ነበር። ኢየሱስ ወደ ቤታቸው በሚመጣበት ጊዜ ማርታና ማርያም በተለያየ መንገድ አክብሮታቸውንና ፍቅራቸውን ይገልጹለት ነበር። ማርታ እንግዳ የመንከባከቡን ባህል ተከትላ ለኢየሱስ ምግብ ልታዘጋጅ ወደ ማዕድ ቤት ገባች። ማርያም ግን ከሌሎች ደቀ መዛሙርት ጋር ሆና የኢየሱስን ትምህርት ትከታተል ጀመር። ማርታ በማዕድ ቤት ውስጥ የሚረዳት ሰው ትፈልግ ስለነበር በሁኔታው አዘነች። ኢየሱስ ግን ለእርሱ በማዕድ ቤት ምግብ በመዘጋጀት ከመቆየት ይልቅ ቃሉን መስማቱ እንደሚበልጥ ነገራት።

ብዙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንደ ማርታ ናቸው። ለኢየሱስ እየተጣደፍን ብዙ ጊዜ እናጠፋለን። ከጠዋት እስከ ማታ በተለያዩ ስብሰባዎች ወይም በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ሥራዎች ተጠምደን እንውላለን። ይህ ሁሉ መልካም ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በሚኖረን ግንኙነት ላይ የሚያተኩር ከሆነና ጥድፊያችን ከኢየሱስ ጋር ጊዜ እንዳናሳልፍ ከከለከለን፣ እውነትም ተጣዳፊዎች ነን ማለት ነው። ኃላፊነታችንን ቀለል አድርገን እንደ ማርያም ከኢየሱስ ጋር ኅብረት ልናደርግ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እኛ የምናደርጋቸውና የማርታ ዓይነት ዝንባሌ እንዳለን የሚያመለክቱ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) የማርያምን ዓይነት አመለካከት ለመቀዳጀት ምን ልናደርግ ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: