ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት መምጣት እንዲሰብኩ 70 ደቀ መዛሙርትን ላከ (ሉቃስ 10፡1-24)

ሌሎቹ ወንጌላት ኢየሱስ ለስብከት አገልግሎት 12 ደቀ መዛሙርት መላኩን ብቻ ሲገልጹ፣ ሉቃስ ግን 70 ደቀ መዛሙርት እንደ ላከ ያስረዳል። (ማስታወሻ፡ የተለያዩ መዛግብት የተለያዩ ቁጥሮችን ስለሚጠቅሱ ኢየሱስ የላከው 70 ደቀ መዛሙርትን ነበር ወይስ 72? የሚል ክርክር እንዳለ አስተውል።) ኢየሱስ በ12 ደቀ መዛሙርቱ አማካይነት አብዛኛውን የገሊላ አካባቢ በወንጌል ለማዳረስ የቻለ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ በይሁዳ ውስጥ በሚገኙ ብዙ ከተሞች አገልግሎቱን ለማስፋፋት ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት ተጠቅሟል።

ሉቃስ የ70ዎቹን ደቀ መዛሙርት መላክ በገለጸበት ታሪክ፤ ስለ መጭው መንግሥት እንዲሰብኩ ለተላኩት ሁሉ የሚጠቅሙ ትምህርቶችን አቅርቧል። ኢየሱስ እነርሱን እንደ ላከ ሁሉ፣ እያንዳንዳችንንም ይልከናል።

ሀ. ለሥራው በቂ የሆኑ ሠራተኞች የሉም። በዚህ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ይልቁንም እግዚአብሔር ተጨማሪ የወንጌል ሠራተኞች እንዲያስነሣ ተግተን መጸለይ ይኖርብናል። ይህ ጸሎት እኛ ሁሉንም ነገር ለመሥራት እንዳንሞክር ወይም ከእኛ በኋላ ተነሥተው የበለጠ ስኬታማ የሆኑትን ወገኖች እንዳንቃወም ያደርገናል።

ሊ ኢየሱስን ማገልገል ቀላል ላይሆን ይችላል። ሰዎች በቀላሉ አይቀበሉን ይሆናል። ይህ በጎችን በተኩላዎች መካከል እንደ መስደድ አደገኛ ነው።

ሐ «የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች» የሚለው የወንጌሉ መልእክት ግልጽ መሆን ነበረበት። ይህም ሰዎቹ ለኢየሱስ የሚሰጡትን ምላሽ ያህል ቅርብ ነው። ኢየሱስ እንደ ንጉሥ ወደ ልባቸው በመምጣት ሕይወታቸውን ለመለወጥ ዝግጁ ነው ። ይህን ካደረጉ ተከታዮቹ ይባረካሉ። ንጉሡን ለመስማት ካልፈለጉ ግን በራሳቸው ላይ ታላቅ ፍርድን ያመጣሉ።

ወንጌሉ በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ነው። የሚያምኑት የዘላለምን ሕይወት እንደሚያገኙና እምቢተኞቹ ግን የዘላለምን ፍርድ እንደሚቀበሉ ያስረዳል። እግዚአብሔር ማንም መንግሥቱን እንዲቀበል አያስገድድም። ስለሆነም መቀበል አለመቀበሉ የእኛ ምርጫ ነው። ይሁንና ፍጻሜያችን ንጉሡን በመቀበላችን ወይም ባለመቀበላችን ይወሰናል። ንጉሡ ኢየሱስን እንደተቀበልን ከሚያሳዩ ዐበይት መረጃዎች አንዱ የኢየሱስን መልእክተኞች የምናስተናግድበት መንገድ ነው።

መ. ደቀ መዛሙርት ሁሉ የኢየሱስ መልእክተኞች ስለሆኑ፣ የእያንዳንዳችን ስብከት እንደ ኢየሱስ ስብከት ነው። ስለሆነም የኢየሱስን ተከታይ አለመቀበል ኢየሱስን አለመቀበል ነው።

ሠ. የሰይጣን መንግሥት በኢየሱስ አገልግሎት እየተጠቃና እየተሸነፈ ነው፡ (ኢየሱስ ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ ሲል ይህንን ማለቱ ነበር። ሰይጣን ሙሉ በሙሉ ባይደመሰስም፣ በኢየሱስ ተከታዮች አገልግሎት አማካይነት መንግሥቱ ተጠቅቷል።) የኢየሱስ ተከታዮች ከኢየሱስ በተቀበሉት ሙሉ ኃይልና ሥልጣን ያገለግላሉ (ማቴዎስ 28፡18-20 አንብብ)፣ ስለዚህ እኛም መንግሥቱ እንዳይስፋፋ ለማድረግ ሥልጣን አለን። እንዲሁም ያለእርሱ ፈቃድ ምንም ወይም ማንም ሊነካን እንደማይችል ስለምናውቅ፣ በኢየሱስ ጥበቃ ሥር ሆነን እናገለግላለን።

ረ. የኢየሱስ ተከታዮች የጠራ አመለካከት እንዳላቸው ማረጋገጥ አለባቸው። ተአምራት ከመሥራት ችሎታ የሚበልጠው የደኅንነት ተአምር ነው። ስማችን በሰማይ በሚገኘው የእግዚአብሔር ልጆች መጽሐፍ በአንድ ከተማ ውስጥ የሚወለዱትን ልጆች ስም የሚመዘግብ መጽሐፍ ዐይነት) ወይም “የክብር መዝገብ” ውስጥ መመዝገቡ ከሥጋዊ ፈውስ ወይም አጋንንትን ከማውጣት የበለጠ ነው። ብዙውን ጊዜ ታላላቅ አገልጋዮች የፈውስ ፕሮግራሞችን ሲያካሂዱ ስናይ፥ የደኅንነትን ተአምር እንዘነጋለን። የአንድ ሰው ደኅንነት ከአንድ መቶ ሰዎች ሥጋዊ ፈውስ የበለጠ ነው! ሥጋዊ ፈውስ ያገኘው ሰው በኢየሱስ ካላመነ የኋላ ኋላ ሞቶ ወደ ሲኦል መሄዱ አይቀርም። የዳነ ሰው ግን ለጊዜው ከበሽታው ባይፈወስ እንኳ፥ በሰማይ የፈውስንና ከእግዚአብሔር ጋር ደስ የመሰኘትን በረከት ያገኛል።

ሰ. እግዚአብሔር ልጆቹ ለእርሱ ሲሠሩ ደስ ይለዋል። ሉቃስ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት እንዳደረገ ይነግረናል። ልጆቹ ለእርሱ ባላቸው ፍቅር ተነሣሥተው ሲያገለግሉት ከማየት የበለጠ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር የለም።

ሸ. በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሥራ የዚህ ዓለም ተቃራኒ ነው። ዓለም የተማሩትንና ሀብታሞችን ታከብራለች። እግዚአብሔር ግን ሀብታሞችና ምሑራን ያልሆኑትን ለመጠቀም ይመርጣል። እግዚአብሔር ምሥጢሩን የሚገልጸው እንደ ሕጻናት በትሕትና ሲታዘዙለት እንጂ በሀብትና በዕውቀት ሲታበዩ አይደለም። ይህ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በትምህርት ላይ አለቅጥ እንዳያተኩሩ የሚያስጠነቅቅ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ እውነቶች እያንዳንዳቸው ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: