ሉቃስ 12፡13-59

  1. ገንዘብን የሕይወት ዋንኛ ዓላማ አድርጎ የመሰብሰብ ሞኝነት (ሉቃስ 12፡13-21)

አብዛኛውን ጊዜ ገንዘብና ቁሳዊ ሀብት ለኢየሱስ ተከታዮች አስቸጋሪ ነገሮች ናቸው። ገንዘብ እንደ ዝሙት በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን፣ በጊዜ ርዝመት እያደገ በመምጣት ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የሚገታ ኃጢአት ነው። አንድ ቀን አንድ ሰውዬ ኢየሱስ ታላቅ ወንድሙ የውርስ ሀብቱን እንዲያካፍለው እንዲያደርግ ጠየቀው። ኢየሱስ ግን በሰዎች ላይ ለመፍረድ ፈቃደኛ አልነበረም። ኢየሱስን ያሳሰበው ጉዳይ፥ ሰው ከእግዚአብሔር በላይ ለገንዘብ ትኩረት መስጠቱ ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በገንዘብ ላይ ከመጠን በላይ እንዳያተኩሩ ለማስተማር ምን ጊዜም ስለማይሰለቸው፥ ስለ አንድ ሀብታም የሚያስረዳ ምሳሌ ነገራቸው። ይህ ሰው ሀብቱን በመጨመር የተደላደለ ሕይወት ከመኖር የበለጠ ዓላማ ስላልነበረው፣ የሞትንና የዘላለምን ነገር ፍጹም ዘንግቶ ነበር። ይህም ሰው በሰዎች ፊት ስኬታማ ሲሆን፣ በእግዚአብሔር ፊት ግን ሞኝ ነበር። በሞተ ጊዜ ሀብቱ ቅንጣት ያህል አልረዳውም!

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ገንዘብ ቀስ በቀስ አንድ ሰው ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ሲቀንስ የተመለከትኸው እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አብያተ ክርስቲያናት በገንዘብ ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርጉት እንዴት ነው?

  1. በኢየሱስ ማመን ማለት በእርሱ አምኖ መኖር እንጂ፥ መጨነቅ ወይም መፍራት አይደለም (ሉቃስ 12፡22-34)

በትክክል በኢየሱስ እንደምትተማመን ራስህን ለመፈተን ትፈልጋለህ? ስለ አንድ ነገር ትጨነቅ ወይም ትፈራ እንደሆነ ራስህን ጠይቅ። ስለ ወደፊት ዕጣ ፈንታችን፣ ስለ ልጆቻችን፣ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን የምንጨነቅ ከሆነ፣ በኢየሱስ አንተማመንም ማለት ነው። እየተጨነቅህና እየፈራህ በኢየሱስ ተማምኛለሁ ልትል አትልችልም። ኢየሱስ የእርሱ ተከታዮች የሆንን ሁሉ እምነታችንን ተግባራዊ እንድናደርግና ክፍርሃትና ጭንቀት ነፃ እንድንሆን ተናግሯል። ሁልጊዜም ወፎችን የሚመግብ አምላክ አይተወንምና ስለ ምግብ መጨነቅ የለብንም። ለአበቦች ውብ ቀለም የሚሰጥ አምላክ ከእኛ ጋር ስለሆነ፥ ስለ ልብስም መጨነቅ የለብንም። ጭንቀታችን የሚለውጠው ነገር ስለሌለ፥ ስለ ወደፊቱም ነገር መጨነቅ የለብንም። እግዚአብሔር ከወፎችና ከአበባዎች አብልጦ ስለሚወደን የሚያስፈልገንን እንክብካቤ ያደርግልናል። አስተማማኝ ሀብት እንዲኖረን በማሰብ ሁሉን ከማግበስበስ ይልቅ ካለን ከፍለን በነፃ ማካፈል አለብን። ዘላለማዊ ዋስትና ባላቸው ነገሮች ላይ ብናተኩር ሕይወታችንን የምንመራበት ሁኔታ እግዚአብሔርን ከማስከበሩም በላይ በሰማይ የሀብት መዝገብ እንዲኖረን ያደርጋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ጊዜ ያስጨነቁህን ሁለት ነገሮች ዘርዝር። ለእነዚህ ነገሮች እንድትጨነቅ ያደረህ ምንድን ነው? ለ) በምትጨነቅበት ጊዜ ስለ እምነትህና እግዚአብሔር ስለ አንተና ስለሚያስጨንቁህ ነገሮች የሚጠነቀቅ ለመሆኑ የምታስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው?

  1. ኢየሱስ ስለ ዳግም ምጽአቱ ለደቀ መዛሙርቱ አስተማረ (ሉቃስ 12፡35-59)

ሉቃስ ካደረጋቸው ለየት ያሉ ነገሮች መካከል አንዱ የኢየሱስ ዳግም ተመልሶ መምጣት ሊዘገይ እንደሚችል ማስጠንቀቁ ነው። ኢየሱስ በቅርቡ እንደሚመለስ ከመናገር ይልቅ ባልተጠበቀ ሰዓት ሊመጣ እንደሚችል አስገንዝቧል። ምንም እንኳ ለዳግም ምጽአቱ አንዳንድ ምልክቶችን የሰጠ ቢሆንም፣ ሁልጊዜ በየትኛውም ሰዓት ሊመጣ እንደሚችል እያሰብን በመጠባበቅ እንድንኖር መክሮናል። ኢየሱስን በታማኝነት የምናገለግል ከሆነ ዛሬ፥ በሚቀጥለው ሳምንት ወይም ከ100 ዓመት በኋላ ቢመጣ ለውጥ የለውም። ኢየሱስ ስለ ዳግም ምጽአቱ ካስተማራቸው እውነቶች መካከል የሚከተሉትን እንመለከታለን።

ሀ. አንድ ሰው ከሰርግ መቼ እንደሚመለስ ወይም ሌባ በስንት ሰዓት ለዝርፊያ እንደሚሰማራ እንደማናውቅ ሁሉ፣ ማንም ኢየሱስ የሚመጣበትን ጊዜ በትክክል አያውቀውም። ስለሆነም ሁልጊዜ ተዘጋጅተን ልንጠብቅ ይገባል።

ለ. የእግዚአብሔር ተከታዮች ሁሉ፥ ጌታቸው ለባሪያዎቹ የሚሠሩትን ሥራ ሰጥቶ ከሄደ ባሪያዎች ጋር ይመሳሰላሉ። ሰውዬው እስኪመጣ ድረስ ለመዝናናት ከማሰብ ይልቅ፥ ጌታው የጠየቀውን ሁሉ በማሟላት ተግቶ መሥራቱ አስፈላጊ ነው። እንደዚያ ከሆነ፣ ኢየሱስ በድንገት ቢመጣ ዋጋችንን እንቀበላለን እንጂ አናፍርም። ነገር ግን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ የታዘዝነውን ሥራ በትጋት እየሠራን ካልቆየን ቅጣትን እንቀበላለን።

ሐ. ኢየሱስ በመስቀል ላይ መከራ (ጥምቀት) ላይቀበል ወዲያውኑ ዘላለማዊውን መንግሥት ቢጀምር ደስ ይለው ነበር። ይህ ግን የእግዚአብሔር ዕቅድ አልነበረም። በኢየሱስ መስቀልና በዳግም ምጽአቱ መካከል ሰዎች ኢየሱስን ለመከተል ስለሚወስኑ ወይም በባህላዊ የአምልኮ መንገዳቸው ስለሚቀጥሉ፣ በቅርብ የቤተሰብ አባላት መካከል ሳይቀር መከፋፈል ይከሰታሉ።

መ. ገበሬዎች ዝናብ መች እንደሚመጣ ያውቃሉ። የነፋስን አቅጣጫና የትኛው ዐይነት ደመና ዝናብን እንደሚያመጣ ይለያሉ። ነገር ግን እይሁዶች ከመንፈሳዊ ዕውርነታቸው የተነሣ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላቸው እንደምትገኝ የሚያሳዩትን ምልክቶች ለመለየት አልቻሉም ነበር። ወደ ፍርድ ቤት ከመቅረብ ይልቅ ከጠላታቸው ጋር ዕርቅን ለመፈጸም መሞከርን ካወቁ፣ የፍርድ ቀን ከመምጣቱ በፊት ከእግዚአብሔር ጋር ዕርቅ ለማድረግ መንፈሳዊ ግንዛቤ አይኖራቸውም? መረታትና ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቅህ እያወቅህ ወደ ፍርድ ቤት መሄዱ ሞኝነት ነው። ከዚህ የሚከፋው ደግሞ ኢየሱስን ባለማመን አሰቃቂውን የዘላለም ሞት መቀበሉ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስ በማንኛውም ቀን የሚመለስ ከሆነ ይህ አኗኗርህን | የሚለውጠው እንዴት ነው? ለ) ኢየሱስ ሰቶሎ እንደሚመለስ የሚያስረዳውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዘንግተን በመንፈሳዊ ሕይወታችንና በአገልግሎታችን ልንቀዘቅዝ የምንችለው እንዴት ነው? ይህንን እንዴት ልታስወግድ ትችላለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: