- ኢየሱስ ለአይሁዶች የእግዚአብሔርን መንግሥት መርህ አስተማረ (ሉቃስ 14፡1-24)
ምንም እንኳ ፈሪሳውያን ኢየሱስን ቢጠሉትም፣ ብዙ ጊዜ ግን ሊፈትኑት ሲሉ በቤታቸው ምግብ ይጋብዙት ነበር። አንድ የሰንበት ቀን አንድ የታወቀ ፈሪሳዊ ኢየሱስን ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር ወደ ቤቱ ጋበዘው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት የእብጠት በሽታ ያለበትን ሰው በቤቱ ውስጥ አኑረው ነበር። ኢየሱስ ፈተናቸውን አልፈራም። ይልቁንም በዚህ ዕድል በመጠቀም ሦስት ዐበይት እውነቶችን አስተማረ።
ሀ. ከሕግና ሥርዐት ይልቅ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች መርዳቱ፥ እግዚአብሔርን የበለጠ ደስ ያሰኘዋል።
ለ. በእግዚአብሔር ፊት፣ ከሌሎች ክብርን ከመጠበቅ ይልቅ፥ ትሑት መሆኑ የተሻለ ነው። እዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚደረገው የተከበሩ የአይሁድ እንግዶች ከጋባዥ አጠገብ ይቀመጡ ነበር። ኢየሱስ በተጋበዘበት ቤት ውስጥ ብዙ ፈሪሳውያን የክብር ስፍራውን ለመያዝ ሲሽቀዳደሙ በመመልከቱ፥ እግዚአብሔር ትሕትናን እንደሚወድ የገለጸው በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። በትሕትና መንፈስ የበታችነት ወይም የበላይነት ስሜት ላያውከን ዝቅ ያለውን ስፍራ መምረጡ ምንኛ መልካም ነው። ከዚያ በኋላ ጋባዥ ከፈለገ ወደ ክብር ስፍራ ሊጠራን ይችላል። ይህም ሆኖ፣ በግብዣው ቦታ ከምንቀመጥበት ስፍራ የሚልቀው እግዚአብሔር፥ ትዕቢተኞችን እንደሚጠላና ዝቅ ዝቅ እንደሚያደርጋቸው፣ ትሑታንን ግን እንደሚወዳቸውና ከፍ ከፍ እንደሚያደርጋቸው የሚያስተምረው መንፈሳዊ መርህ ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ብዙውን ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በትዕቢት ተይዘው ልዩ ትኩረትና ልዩ መቀመጫ የሚፈልጉባቸው ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው? እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ስላለተማረው ስለዚሁ መርሕ የዘነጉት ነገር ምንድን ነው?
ሐ. ክብርን የሚቀበሉት እግዚአብሔርን እንደሚከተሉና ለደኅንነት ግብዣም እንደተዘጋጁ የሚናገሩ ሰዎች ላይሆኑ፣ በትክክል ለመምጣት የሚፈቅዱ ናቸው። በአይሁድ ባህል መሠረት ሁለት ግብዣዎች ይቀርቡ ነበር። አንደኛው፥ ሰዎች ጊዜውን አውቀው እንዲዘጋጁ የሚቀርብ ጥሪ ነበር። ሁለተኛው ደግሞ ጋብቻው ሊጀመር ሲል የሚቀርብ ግብዣ ነበር። ኢየሱስ ለመምጣት ፈቃደኞች ለሆኑ ሰዎች ስለተላኩት ግብዣዎች የሚገልጽ ታሪክ ነገራቸው። ሁለተኛው ግብዣ በመጣ ጊዜ ግን ተጋባዦቹ ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ ነው በሚሉት ሥራ ተጠምደው ነበር። እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ማመኻኛዎች ብቻ ነበሩ። በመጀመሪያ መልካም መሆኑን አይቶ ሳያጠራ መሬት የሚገዛው ማን ነው? ማረስ መቻሉን ሳይሞከርስ በሬ የሚገዛው ማን ነው? መጀመሪያ የተጋበዙት ሰዎች ለመምጣት አልፈቀዱም። ስለሆነም ግብዣው ለተራ ሰዎችና ለጎዳና ተዳዳሪዎች ተሰጠ። በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔር የደኅንነት ግብዣውን ለሁሉም ሰው ሰጥቷል። ነገር ግን እንደ አይሁድ የሃይማኖት መሪዎችና ሀብታም ሰዎች መጀመሪያ ግብዣውን ተቀብለው ላለመምጣት ወስነዋል። ለእነርሱ የደኅንነትን ጥሪ መቀበሉ ተስማሚ አልሆነም። ነገር ግን ተስፋ የሌላቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለማኞችና ያልተማሩ የገጠር ሰዎች ወይም ማኅበረሰቡ ንቆ ያገለላቸው ሁሉ በትሕትና የደኅንነትን ጥሪ ተቀብለው በታላቁ ግብዣ ላይ በመገኘት ደስ ይሰኛሉ። ኩሩዎቹና ግድ የለሾቹ ግን በተጠሩ ጊዜ ለመምጣት ካልፈለጉ የእግዚአብሔርን የዘላለም ሕይወት ግብዣ ተቀብለው ደስ ሊሰኙ አይችሉም።
የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ብዙውን ጊዜ የሃይማኖት ሰዎች፥ ሀብታሞችና የተማሩ ሰዎች የኢየሱስን የደኅንነት ግብዣ ለመቀበል እስከማይችሉበት ደረጃ ድረስ በሥራ የሚጠመዱት እንዴት ነው? ለ) ከእነዚህ ክፍል ስለ እግዚአብሔር የተለየ አሠራር ምን እንማራለን?
- ኢየሱስን ለመከተል ቁርጥ ውሳኔና ታላቅ ዋጋ መክፈልን ይጠይቃል (ሉቃስ 14፡25-35)
ብዙዎቻችን እጅግ በርካታ ሰዎች ወደ ክርስቶስ በመመለሳቸው እንደሰታለን። በሕዝብ የተጨናነቁ አብያተ ክርስቲያናት የእግዚአብሔር በረከት፣ የመንፈሳዊ ረሀብና የወንጌሉ ኃይል ምልክቶች ናቸው። ኢየሱስ በምድር ላይ ባገለገለበት ዘመን እርሱን ከብበው የሚዞሩ ብዙ ሕዝቦች የኃይሉ ምልክቶች ነበሩ። ይሁንና ኢየሱስ በሚከተሉት ብዙ ሰዎች እምብዛም አይደሰትም ነበር። ስለሆነም ሙሉ በሙሉ ሕይወታቸውን ሳይሰጡ ሥጋዊ ፍላጎታቸውን ብቻ እንዲያሟላላቸው በሚፈልጉት ሰዎች ደስ አይሰኝም ነበር። ስለዚህ ብዙ ሕዝብ ሲከተሉት አይቶ ኢየሱስ ደቀ መዝሙርነት ስለሚያስከፍለው መሥዋዕትነት ጠንካር ያለ ተግሣጽ ሰነዘረ። ኢየሱስ ዛሬ በእኛ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ቢገኝ ኖሮ፥ እጃቸውን እያነሡ እንከተልሃለን እንዲሉት የሚጠይቅ አይመስልም። ተከታዮቹ ሊሆኑ ከፈለጉ ምን ያህል ዋጋ መክፈል እንደሚያስፈልጋቸውና፥ ምን ዐይነት ፈተና እንደሚጠብቃቸው ይገልጽላቸው ነበር። በኢየሱስ እናምናለን እያሉ ሙሉ በሙሉ ባልተለወጡ ሰዎች፥ ኢየሱስ ደስ እንደማይሰኝ በማቴዎስ 28፡19-20 ላይ የተጠቀሰው ታላቁ ተልእኮ ያስገነዝበናል። ይልቁንም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጓቸውና ከእርሱ የተማሩትን ሁሉ እንዲያካፍሏቸው አዝዛቸዋል። ኢየሱስ የእርሱ ተከታይ ስለ መሆን አራት ጠቃሚ ትምህርቶችን አስተምሯል።
ሀ. የኢየሱስ ተከታይ መሆን ማለት በሕይወት ውስጥ ከሌሎች ነገሮች ሁሉ በላይ እርሱን መውደድ ማለት ነው። ብዙውን ጊዜ ከሁሉም በላይ የምንወደው ቤተሰባችንን ነው። ቤተሰቦቻችንን መውደዳችን ብቻ ሳይሆን፣ ዋስትናችንም ያረፈው በእነርሱ ላይ ነው። ስንታመም ወይም ችግር ሲደርስብን፣ ፈጥነው የሚደርሱልንና የሚረዱን እነርሱ ናቸውና። ኢየሱስ ግን እርሱን ከቤተሰቦቻችን በላይ እንድንወድና፥ ከዚህም የተነሣ በአንጻራዊ መልኩ «እንድንጠላቸው» ጠይቆናል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል እርሱ የሰጠንን ቤተሰቦቻችንን በእርግጥ እንድንጠላቸው ማለቱ አይደለም። የቤተሰባችንን አባላት ጨምሮ ሰዎችን ሁሉ መውደድ እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምረናል። በዚህ ስፍራ ኢየሱስ ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት፥ ለእርሱ ያለን ፍቅር በሕይወት ውስጥ ከማንም ሰው ወይም ከምንም ነገር በላይ የጠለቀ መሆን እንዳለበት እንድንገነዘብ ነው።
ሊ. የኢየሱስ ተከታይ መሆን ማለት በመከራ መንገድ መጓዝ ነው። ብዙ ጊዜ መስቀሎችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ምልክት አድርገን እናስቀምጣለን። ለአይሁዶች ግን መስቀል ሥቃይ የታከለበት የሞት ምልክት ነው። ኢየሱስ አይሁዶች ለመሞት መፍቀድ እንዳለባቸው እያስጠነቀቃቸው ነበር። በእርሱ ላይ ላለው እምነታቸው በሥጋ ለመሞት መፍቀድ ነበረባቸው። ከዚህም በላይ የኢየሱስ ተከታዮች ለሥጋ ምኞታቸው ለመሞት መፍቀድ አለባቸው። ለሕይወታችን፣ ለዕቅዶቻችን፣ ወይም ለምቹ ሕይወት ላሉን መብቶች መሞት አለብን። ሉቃስ በዚህ ዐይነት ሕይወትን ለኢየሱስ አሳልፎ መስጠት «ያለውን ሁሉ መተው» ሲል ይጠራዋል።
ሐ ኢየሱስ ሰዎች እጃቸውን አንሥተው ምን እያደረጉ እንደሆነ ሳያውቁ እንከተልሃለን እንዲሉት በማድረግ ፈንታ በሚገባ የታሰበበት ውሳኔ እንዲያደርጉ ጠይቋቸዋል። አንድ ቤተ ሠሪ ቤቱን መሥራት ከመጀመሩ በፊት በቂ ገንዘብ እንዳለው አስልቶ እንደሚያውቅ፥ ወይም አንድ ንጉሥም ወደ ጦርነት ከመሄዱ በፊት የሚገጥመውን ጦር ማሸነፍ አለማሸነፉን አስቀድሞ እንደሚያገናዝብ ሁሉ፣ እኛም ኢየሱስን የመከተል ዕቅዳችንን በጥንቃቄ ልንመረምር ይገባል። የሚገጥሙንን በረከቶችና መሥዋዕትነቶች አውቀን ሁሉንም በጥንቃቄ ልናደርገው ይገባል።
መ. የደቀ መዝሙርነት ሕይወት ለዓለም ብርሃን የመሆን ሕይወት ነው። ከመቆየቱ የተነሣ ጣዕሙን ያጣ ጨው፥ መንገድ ላይ ተጥሎ እንደሚረገጥ ሁሉ፥ ሙሉ በሙሉ የተለወጠ ሕይወት ለመኖር የማይፈልግ የክርስቶስ ተከታይም ዋጋ የሌለው ነው። የኢየሱስ ተከታዮች ለእርሱ ሊጠቅሙ የሚችሉ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት የሚሆኑት ሕይወታቸው ከተለወጠና ለዓለም ጣዕም የሚሰጡ ሲሆን ብቻ ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስ ሊከተሉት የፈለጉትን ሰዎች ያስጠነቀቀበትን ሁኔታ፣ እኛ እማኞች ለመሆን የሚፈልጉትን ወገኖች ከምንመከርበት መንገድ ጋር አነጻጽር። ለ) ሰዎች አማኞች ከመሆናቸው በፊት ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሏቸው ነገሮች በመግለጽ እንደ ኢየሱስ ልናስጠነቅቃቸው ከፈለግን፣ በማብራሪያችን ውስጥ ምን ነገር ሊለወጥ ይገባል ትላለህ?
ኢየሱስ በግማሽ ልባቸው ከሚከተሉት አንድ ሺህ ደቀ መዛሙርት ይልቅ በሙሉ ልባቸው የሚከተሉት ጥቂት ሰዎች ይበልጥ ጠቃሚ እንደሚሆኑ ያውቃል። ኢየሱስ ዓለምን የለወጠው በአሥራ ሁለት ሕይወታቸውን ለእርሱ በሰጡት ደቀ መዛሙርት አማካይነት ነበር። እኛ ግን በግማሽ ልባቸው ኢየሱስን ከሚከተሉት በሺዎች ከሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ጋር ዓለምን ለመለውጥ አልቻልንም። ምናልባትም አማኞችን ብቻ ሳይሆን ለክርስቶስ ራሳቸውን የሰጡትን ደቀ መዛሙርት የምናፈራበትን መንገድ መቀየስ አለብን። ምናልባትም ሙሉ በሙሉ ራሳችንን ለክርስቶስ የሰጠን ደቀ መዛሙርት ነን ወይ? ብለን መጠየቅ አለብን። ወይስ ኢየሱስን የምንከተለው ለምናገኛቸው የግል ጥቅማ ጥቅሞች ይሆን? እንደ ቡታ፣ ሰዎች በሰውነቴ ላይ የፈለጉትን ቢያደርጉ በልቤ ውስጥ የተሰወረውን ኢየሱሴን አያገኙትም የማለት ድፍረት አለህ?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)