ሉቃስ ታሪኩን የተናገረው፥ ኢየሱስ አንድን ሰው በሚነካበት ጊዜ በሕይወቱ ውስጥ ምን እንደሚከሰት ለማብራራት መሆኑ ግልጽ ነው። ወጣቱ ገዥ ሕይወቱን የተቆጣጠረውን ገንዘብ ትቶ፥ ኢየሱስን ለመከተል አልፈለገም ኃጢአተኛውና የተናቀው ቀራጭ ግን ገንዘቡን ትቶ ከኢየሱስ ኋላ ለመሮጥ ፈቅዷል። የእግዚአብሔር መንገድ ከእኛ የተለየ ነው። በጥሩ ሕይወታቸው፤ ችሎታቸውና ገንዘባቸው በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው ሰዎች ሳይገቡ ይቀራሉ፡፡ ነገር ግን እኛ ዘወር ብለን የማናያቸውን ሰዎች እግዚአብሔር ዳስሶ ወደ ቤቱ ያመጣቸዋል።
ዘኬዎስ አጭር ሰውና ቀራጭ ነበር። ይህ ሰው ብዙ ገንዘብ ነበረው። ነገር ግን መንፈሳዊ ረሃብ በልቡ ውስጥ ስለ ነበረ፣ ኢየሱስን ያይ ዘንድ በጉጉት ከዛፍ ላይ ወጣ። ኢየሱስ የዘኬዎስን ልብ ያውቅ ነበርና ወንጌሉን ይበልጥ ያብራራለት ዘንድ ወደ ቤቱ ገብቶ በእንግድነት ተቀመጠ። ኢየሱስ ወደ ቤትህ ለመግባት እፈልጋለሁ በማለት ፈንታ ወደ ቤትህ መግባት አለብኝ ማለቱ አስገራሚ ነው። ይህ እግዚአብሔር የወሰነው ስብሰባ ነበር። ኢየሱስ ይህን ሲያደርግ ከዘኬዎስ ጋር አብሮ በመብላት ዝናን ለማግኘት የወሰደው እርምጃ አልነበረም። ተራ አይሁዶች እንኳ ከእንዲህ ዐይነት ሰው ጋር መቀራረብ አይፈልጉም ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ የነፍስ ሐኪም በመሆኑ፣ የደኅንነትን መድኃኒት የሚፈልግ ሰው ወዳለበት ስፍራ ሁሉ ይገባል። ምንም እንኳ ዘኬዎስ በሥጋ ከአይሁድ ወገን የተወለደና የአብርሃም ልጅ ቢሆንም፣ እውነተኛው የአብርሃም ልጅ የሆነው ገና ከኢየሱስ ጋር ከተገናኘ በኋላ ነበር። በመንፈሳዊ ሕይወቱም የአብርሃምን እምነት አግኝቷል።
የዘኬዎስን ሕይወት መለወጡን ወይም አለመለወጡን እንዴት እናውቃለን? ኢየሱስ ባይነግረውም፣ ዘኬዎስ ሕይወቱ መለወጥ እንዳለበት ያውቅ ነበር። ገንዘቡን ለመተው ካልፈቀደው ወጣት ጎዥ በተቃራኒ፣ ዘኬዎስ ከገንዘቡ ግማሹን እርዳታ ለሚፈልጉት ለመስጠትና ቀራጭ ሆኖ በሚሠራበት ጊዜ ላታለላቸው ሰዎች ሁሉ የወሰደውን ገንዘብ እንደሚመልስላቸው ተናግሯል። ዘኬዎስ ይህንን ያደረገው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታን ለማግኘት ሳይሆን፣ ይቅርታን ስላገኘ ነው። እውነተኛ ንስሐ ማለት ሁሉንም ነገር እንደ አዲስ መጀመር ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ኋላ በመመልከት ያበላሹትን ማስተካከል ጭምር ነው።
በብሉይ ኪዳን እንደምናነበው፥ እግዚአብሔር የአንድን ሰው ልብ በሚነካበት ጊዜ ሰውየው የሰረቃቸውን ነገሮች ሁሉ ለመመለስ ጥረት ሲያደርግ እንመለከታለን። ሰዎችን የጎዳባቸውንና ከእነርሱ ጋር የነበረውን ግንኙነት ያቋረጠባቸውን መንገዶች መለስ ብሎ በማጤን፣ እንደገና ግንኙነቱ የሚታደስበትን መንገድ ያፈላልጋል። በዘመናችን ግን ይቅርታ ማለት ሕይወትን እንደ አዲስ መጀመር ብቻ ነው ብለን እንሳሳታለን። ይቅርታ ሲባል ቀደም ሲል የተደረጉትን ነገሮች እንረሳለን ብለን እናስባለን። ይህ ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይቅርታ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይቅርታን በምንከተልበት ጊዜ፥ የተበላሹትን ግንኙነቶች ማስተካከል፣ ከሌሎች የሰረቅነውን ገንዘብ ወይም ሌላ ነገር መመለስ ይጠበቅብናል። ምናልባትም ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኃጢአት ተቆልሎ የሚታየው፥ እግዚአብሔር ክርስቲያኖች የቀድሞ ሕይወታቸውን እንዲያስተካክሉና ከተቻለም በሌሎች ወገኖች ላይ ላደረሷቸው ጉዳቶች ካሳ እንዲከፍሉ እንደሚፈልግ ባለማስተማራችን ይሆናል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ሰዎች ወደ ክርስትና ሊመጡ ወይም በኃጢአት ሲወድቁ፣ ቀደም ሲል የሰረቋቸውን ነገሮች ወይም የወሰዱትን ገንዘብ መመለስ እንደሌለባቸው የሚያስቡት ለምን ይመስልሃል? ለ) ዘሌዋ. 6፡1-7 አንብብ። እግዚአብሔር ለሚሰርቁ ሰዎች የሰጠው መመሪያ ምንድን ነው? ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ይህንን እውነት እንዴት ተግባራዊ እንድናደርግ የሚፈልግ ይመስልሃል?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)