ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የፋሲካ ምግብን በላ (ሉቃስ 22፡1-38)

ሀ. ሰይጣን ኢየሱስን አሳልፎ በሚሰጠው በይሁዳ ልብ ውስጥ ሰርጎ ገባ (ሉቃስ 22፡1-6)። ሉቃስ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዴት መልካሙን ተግባር ለመፈጸም በሰዎች ሕይወት ውስጥ እንደሚሠራ ገልጾአል። ነገር ግን ሌላም ኃይል አለ። ይህም ክፋትን በመሥራት በእግዚአብሔር ላይ በደልን እንድንፈጽም የሚያነሣሣን ሰይጣን ነው። ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ ሕይወቱን እንዲቆጣጠርለት አልፈቀደም ነበር፡፡ ምክንያቱን ባናውቀውም፣ ሕይወቱ ከእውነት ርቆ እንዲቅበዘበዝ አድርጓል። የግብዝነት ሕይወት መምራት ጀመረ፡፡ ታማኝ የኢየሱስ ተከታይ ለመምሰል ቢሞክርም፣ ገንዘብ ይሰርቃ ነበር (ዮሐ 12፡6)። ኃጢአትን በሕይወቱ ውስጥ ካሳደረበት ጊዜ አንሥቱ ሰይጣን ወደ ሕይወቱ ለመግባት ዕድል አገኘ። ከዚያም ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ይቀሰቅሰው ጀመር፡፡ ሰይጣን አንድ ክርስቲያን በር ካልከፈተለት በስተቀር በራሱ ኃይል ወደ ሕይወቱ ገብቶ ያለፈቃዱ አንዳች ሊያደርስ አይችልም። ነገር ግን ኃጢአት በሕይወታችን ውስጥ እንዲራባ ከፈቀድን፣ ሰይጣን በሕይወታችን ውስጥ ጠንካራ ይዞታ ስለሚኖረው የበለጠ ክፋት እንድንሠራ ሊያበረታታን ይችላል። ይሁዳ ወደ ሊቀ ካህናት በመሄድ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ። ሰይጣን ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ በማነሣሣቱ፣ ይሁዳ ተሸንፎ በሰይጣን እግር ሥር ሊወድቅ ችሏል። ኢየሱስ ሰይጣን በሰዎች ላይ የነበረውን ኃይል ኢየሱስ ያሸነፈው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ነው (ቆላስይስ 2፡14-15 አንብብ)።

ለ. ኢየሱስ የመታሰቢያ በዓል ጀመረ (ሉቃስ 22፡7-23)። ፋሲካ፥ አይሁዶች ከግብጽ ባርነት የወጡበትን ጊዜ የሚያስታውሱበት እጅግ ታላቅ በዓል ነበር። በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት ሌላው ፋሲካ፣ ማለትም የኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞት የተከናወነው በዚሁ የፋሲካ መታሰቢያ ዕለት ነበር። ኢየሱስ የአይሁዶችን የፋሲካ ባሕል መሠረት በማድረግ ሌላውን የመታሰቢያ ምግብ፣ ማለትም የጌታን እራት ሥርዐት መሠረተ፡ እንጀራው (ኅብስቱ) በመስቀል ላይ የተቆረሰ ሥጋውን ሲያመለክት፤ ወይኑ ለኃጢአታችን የፈሰሰውን ደሙን ያመለክታል። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የበላው እራት የመጨረሻው ነበር። በወደፊት መንግሥቱ መጀመሪያ ላይ እስከሚደረግው በዓል ድረስ፥ ሌላ የፋሲካ ምግብ አብሯቸው እንደማይበላ ገልጾላቸዋል (ኢሳ. 5፡6-8 አንብብ)። ኢየሱስ ሞቱ ድንገተኛ ሳይሆን የታሰበበት ድርጊት ስለመሆኑ ሲገልጽ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ እንደሚሰጠው ተናግሯል።

ሐ. ደቀ መዛሙርቱ ከመካከላቸው ማን ነው ታላቅ በማለት ተሟገቱ (ሉቃስ 22፡24-38)። ኢየሱስ በእነርሱና በእግዚአብሔር መካከል ስለሚመሠረተው አዲሱ ኪዳን ለማስተማር በሚሞክርበት ልዩ የእራት ሥነ ሥርዐት ላይ፥ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ሥልጣንና ክብር ማሰባቸው አስገራሚ ነበር። ኢየሱስ ምድራዊ መንግሥትን ለማቋቋም የሚጀምር ለለ መሰላቸው የትኛውን ሥልጣን እንደሚይዙ ያውጠነጥኑ ነበር። ፕሬዚዳንቱ ማን ሊሆን ነው? ጠቅላይ ሚኒስትሩስ? የመከላከያ ሚኒስትሩስ? ምንም እንኳ ኢየሱስ አመራር ማለት አገልግሎት መስጠት እንደሆነ ያስረዳቸው ቢሆንም፣ የኢየሱስ መንግሥት በምድር ላይ ከሚታየው የተለየ አሠራር እንዳለው አልተገነዘቡም ነበር።

ኢየሱስ ቀደም ሲል የተሰጣቸውን ትምህርት ባለመቀበላቸው እያዘነ፥ በመንግሥቱ ውስጥ ስለሚኖረው አገልግሎት እንደገና አስተማራቸው። መንግሥቱን ከአሕዛብ መንግሥት ጋር አነጻጸረ። አሕዛብ በሰዎች ላይ ኃይልና ሥልጣን እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ከአመራር የሚገኘውን ክብር ይወዳሉ። ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማዘዝ ያስደስታቸዋል። የሰዎችን ክብርና ታዛዥነት አጥብቀው ይሻሉ። በአንጻሩም፣ በእግዚአብሔር መንግሥት አመራር የሚለካው በትሕትና ነው። በትሕትና ራሱን ዝቅ አድርጎ ሌሎችን የሚያገለግል ሰው እርሱ ከሁሉም የበለጠ ነው። ሁላችንም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ታላላቆቹን እንደሚያከብር ታናሽ ልጅ መሆን ስላለብን፣ አንድ ሰው በዕድሜ መግፋቱ ሌሎችን የሚያዝበት መስፈርት አይሆንም። ባሪያዎቻቸውን ከሚያዙ ጌቶች በተቃራኒ፣ እኛ ለሌሎች ፈቃደኛ ባሪያዎች በመሆን ልናገለግላቸው ይገባል። በመንፈሳዊው መንግሥት ሥልጣንንና ኃይልን ሳይሆን እግዚአብሔርንና ሌሎች ሰዎችን ማገልገልን መሻት አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የዓለምን የአመራር መንገድ የሚከተል መሪና የክርስቶስን መንገድ የሚከተል መሪ ከበታቻቸው ያሉትን ሰዎች እንዴት እንደሚያስተዳድሩ እነጻጽር። በአመራራቸው ውስጥ የሚለየው ነገር ምንድን ነው? ለ) ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኢየሱስ እንደሚፈልጋቸው መሆን የሚያስቸግረው ለምንድን ነው?

ነገር ግን ሌላ የኃይል መንግሥት ይመጣል። በዚያ መንግሥት ውስጥ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ይሾማቸዋል። ይህ ጥቅስ የሚተረጎምባቸው ሁለት መንገዶች አሉ።

አንደኛው፣ ኢየሱስ ወደ ምድር ተመልሶ በመምጣት በኢየሩሳሌም መንግሥቱን እንደሚመሠርት የሚናገሩ ምሑራን የሚከተሉት አቅጣጫ ነው። በዚህ ጊዜ በእስራኤልና በዓለም ሁሉ እንደሚገዛ ያምናሉ። በዚያ መንግሥት ውስጥ ደቀ መዛሙርቱ በእስራኤል ላይ የመግዛት ሥልጣን ይኖራቸዋል። ሁለተኛው፣ ሌሎች «የእስራኤል ነገዶች» የሚለው ሐረግ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚል አሳብ እንዳለው የሚያስቡ ምሑራን አሉ። ከኢየሱስ ሞት በኋላ እግዚአብሔር አይሁዶችንና አሕዛብን አንድ ስላደረጋቸው ለአይሁዶች የሚደረግ የተለየ ሞገስ አይኖርም ብለው ያምናሉ (ኤፌ 2፡11-22)። አማኞች ሁሉ መንፈሳዊ አይሁዶች ናቸው። ስለሆነም ኢየሱስ የብሉይ ኪዳንን የአነጋገር ዘይቤ በመጠቀም ሐዋርያቱ በአዲሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ ማለትም በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚገዙበትን መንፈሳዊ ሥልጣን ማመልከቱ ነው ሲሉ ያስተምራሉ።

ኢየሱስ በአሠራራቸው ውስጥ ልዩነት እንደሚኖር አሳይቷል። ቀደም ሲል ደቀ መዛሙርቱ በሌሎች ሰዎች ላይ የተመሠረተ ሕይወት ይመሩ ስለነበር ቦርሳም ሆነ ሻንጣ አያስፈልጋቸውም ነበር። የኢየሱስ ስም እየገነነ ሲሄድ ለተከታዮቹ ከፍተኛ መስተንግዶ ይደረግላቸው ነበር። አሁን ግን ሰዎች በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ የሚኖራቸው አመለካከት መቀየር ጀምሯል። በሰዎች የሚጠሉበት ጊዜ ስለደረሰም፥ የራሳቸውን ፍላጎቶች ያሟሉ ዘንድ ቦርሳና ሻንጣ መያዝ አስፈለጋቸው፡፡

ነገር ግን ኢየሱስ ሰይፍ እንዲገዙ የነገራቸው ለምንድን ነው? ለመንግሥቱ እንዲዋጉ ይፈልግ ስለነበር ነው? አይደለም። ምክንያቱም ደቀ መዛሙርቱ ሁላት ሰይፍ እንዳላቸው ሲናገሩ፤ ይህ በቂ እንደሆነ ገልጾላቸዋል። ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ እንደ ደረሰና በሰይፍ ተዋግተው ሮማውያንን እንደማያሸንፉ ያውቅ ነበር። ለእንዲህ ዐይነቱ ውጊያ ሁለት ሰይፎች አይበቁም፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሰዎች ሊገድሏቸው እንደሚፈልጉና ከዚህም የተነሣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚገጥሟቸው ለመግለጽ ሲል ጠንካራ አገላለጽ የተጠቀመ ይመስላል። ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛ እንደሚቆጠር ሁሉ ተከታዮቹም ይህንኑ ስም የሚጎናጸፉበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። ምናልባትም ሰይፉ የመዋጊያ ሳይሆን፣ ራስን ከሌቦች የመከላከያ መሣሪያ ሳይሆን አይቀርም።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: