የዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ

ከአራቱ ወንጌሎች የትኞቹም ስለ ጸሐፊዎቹ የሚናገሩት ነገር እንደሌለ ቀደም ብለን ተመልክተናል። ነገር ግን ይህ መጽሐፍ ከተጻፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ «የዮሐንስ ወንጌል» የሚል ስያሜ ተሰጠው። በዚህ መንገድ አንባብያኑ ደራሲው ማን እንደሆነ ሊያውቁ ይችሉ ነበር።

ከጥንት ጊዜ አንሥቶ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስ አራተኛውን ወንጌል እንደጻፈው ያምኑ ነበር። ይህ አመለካከት በአብዛኛው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ተይዞ ቆይቷል። በ115 ዓ.ም. ኢግናቲየስ የተባለ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከዮሐንስ ወንጌል ጠቅሶ ጽፎአል። ከእርሱ በኋላ መጽሐፍ የጻፉት ሌሎች ሰዎች ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን ወንጌል በኤፌሶን ሆኖ እንደጻፈው ገልጸዋል። በጥንት ጽሑፎች ውስጥ ዮሐንስ ይህንን መጽሐፍ እንደጻፈ የሚያጠራጥር ነገር የለም።

ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን ያልሆኑ ምሑራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ። ምክንያታቸውም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ የቀረበው ትምህርት በጣም የጠነከረ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በ100 ዓ.ም. ላይ ከዚህ ደረጃ መድረስ አትችልም የሚል ነው። በሌሎቹ ተመሳሳይ ወንጌላትና በዮሐንስ ወንጌል መካከል ስለ ኢየሱስ የቀረበው አመለካከት ከፍተኛ ልዩነት ስላለው፣ የዮሐንስ ወንጌል በኢየሱስ ደቀ መዝሙር የተጻፈ ሊሆን አይችልም ብለው ያስባሉ። ብዙ ምሑራን በጥንታ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዮሐንስ የሚባል ሌላ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደ ነበረ ይናገራሉ። ይህ የቤተ ክርስቲያን መሪ ምንም እንኳ ስሙ ዮሐንስ ቢሆንም፣ ሽማግሌው ዮሐንስ በመባል ነበር የሚጠራው (2ኛ ዮሐ 1)። ስለሆነም የዮሐንስ ወንጌል በመጀመሪያው ምእተ ዓመት መጨረሻ አካባቢ እንደ ተጻፈ የሚያስቡ ምሑራን መጽሐፉን የጻፈው ሽማግሌው ዮሐንስ እንጂ ሐዋርያው ዮሐንስ ሊሆን እንደማይችል ያስባሉ። የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስ ይህንን መጽሐፍ እንደጻፈው የሚያስቡ ሰዎች የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስና ሽማግሌው ዮሐንስ አንድ ሰው ነው የሚል አሳብ አላቸው። ይህ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ያስተማረችው አሳብ ሲሆን፣ ለመጠራጠር የሚያበቃ ምክንያት የለንም።

ይህንን መጽሐፍ ሐዋርያው ዮሐንስ እንደጻፈው ለመጠራጠር የሚያስችል በቂ ምክንያት የለንም። የጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶችና የታሪክ ምሑራን ሐዋርያው ዮሐንስ እንደ ጻፈው ተስማምተዋል። ደራሲው የአይሁድን ባህልና አምልኮ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ፥ አይሁዳዊ መሆን እንዳለበት እንረዳለን፡፡ የአገሪቱን ዝርዝር መልክዐ ምድራዊ ገጽታዎች መገንዘቡ ደግሞ የጳለስቲና ነዋሪ እንደ ነበር ያመለክታል። ጸሐፊው በኢየሱስ አገልግሎት ውስጥ የተከሰቱትን ብዙ ነገሮች በዐይኑ እንደ ተመለከተ ገልጾአል። ከእነዚህም መካከል ክብሩን (ዮሐ 1፡14)፣ ስቅለቱን (ዮሐ 19፡33-35)፣ የውኃ ጋኖቹ መጠን (ዮሐ 2፡6)፣ ታንኳይቱ ከመሬቱ ምን ያህል ትርቅ እንደ ነበር (ዮሐ 21፡8)፣ ወዘተ… ተመልክቷል። እነዚህን ዝርዝሮች ለማመቅ በስፍራው መገኘት የግድ አስፈላጊ ይሆናል። ከሌሎች ወንጌላት ጋር ሲነጻጸር፣ የዮሐንስ ስም «ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር» ወይም «ሌላው ደቀ መዝሙር» በሚል የተተካባበት ጊዜ አለ። ይህም ዮሐንስ መጽሐፉን በሚጽፍበት ጊዜ የራሱን ስም ከመጥቀስ ይልቅ አማራጭ መንገዶችን ለመጠቀም እንደ መረጠ ያመለክታል።

ዮሐንስና ወንድሙ ያዕቆብ ከጴጥርስ ጋር ከፍተኛ ታዋቂነት የነበራቸው ደቀ መዛሙርት ነበሩ። ወላጆቻቸው ዘብዴዎስና ሰሎሜ ይባሉ ነበር፡ በኋላ ሰሎሜ ከኢየሱስ ጋር ከቦታ ቦታ የሚጓጓዘው የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ቡድን አባል ሆናለች (ማቴ. 27፡55-56ን ከማር 5፡40-41 ጋር አነጻጽር፡፡) አንዳንዶች ሰሎሜ የኢየሱስ እናት የሆነችው ማርያም እኅት ወይም የአጎት/የአክስት ልጅ ናት ብለው ያስባሉ (ማቴ 27:56፤ ማር. 15፡40፤ ዮሐ. 19፡25)። ያዕቆብና ዮሐንስ ያደጉት በገሊላ ባሕር አጠገብ ነበር። አባታቸው ትልቅ የዓሣ ንግድ የሚያካሂድ ሀብታም ይመስላል። ከሁለት ልጆቹ በተጨማሪም ሥራውን የሚያከናውኑ ሠራተኞች ነበሩት (ማር. 1:19-20)። ዮሐንስ ሊቀ ካህኑን ለማወቅና ወደ ቤቱም ገብቶ የኢየሱስን የችሎት ምርመራ የተመለከተው የሀብታም ቤተሰብ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም (ዮሐ 18፡5)።

ምናልባትም እግዚአብሔር በዮሐንስ ሕይወት መሥራት የጀመረው ገና ለግላጋ ወጣት ሳለ ሳይሆን አይቀርም። በመሆኑም ከወንድሙ ከያዕቆብ ጋር ወደ ይሁዳ በመሄድ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ፡፡ በመጀመሪያ ስለ ኢየሱስ የሰማው ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር ሳለ ነበር፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን «የእግዚአብሔር በግ» ባለው ጊዜ ዮሐንስ ይከተለው ጀመር (ዮሐ 1፡35-39)። ኢየሱስ ውኃን ወደ ወይን ጠጅ በመለወጥ የመጀመሪያ ተአምሩን በሠራበት ጊዜ ዮሐንስ በዚያው ነበር (ዮሐ 2፡1-2)። ኢየሱስ ይፋ አገልግሎቱን በጀመረበት የመጀመሪያው ዓመት ዮሐንስ ለአጭር ጊዜ ሲከተለው ከቆየ በኋላ ወደ ቀድሞው የዓሣ ማጥመድ ሥራው ሳይመለስ አልቀረም። ከዚያ በኋላ ኢየሱስ እንደገና ደቀ መዝሙሩ ይሆን ዘንድ ስለጠራው ከታላቁ ወንድሙ ከያዕቆብ ጋር የአባቱን የዓሣ አጥማጅነት ሥራ ትቶ ወደ ክርስቶስ ተመለሰ። ከዚያ በኋላ ለሚቀጥሉት ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት የኢየሱስን ትምህርት በማዳመጥና ተአምራቱን በመመልከት አብሮት ቆይቷል።

ምንም እንኳ ዮሐንስ ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ የሚፈልግ ትሑት ሰው እንደሆነ ብናስብም፣ እርሱና ወንድሙ ያዕቆብ ቁጡዎች በመሆናቸው «የነጎድጓድ ልጆች» የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸው ነበር (ማር. 3፡17፤ ሉቃስ 9፡51-56)። ለሥልጣንና ኃይል ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው እናታቸው በኢየሱስ መንግሥት ውስጥ ልዩ ሥልጣን እንዲያገኙ ጠይቃላቸዋለች (ማቴ 20፡20-28)። በዮሐንስ ባሕርይ ውስጥ ኢየሱስ ለሥልጠና እንዲመርጠው ያደረገ አንድ ነገር ነበር። ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ዮሐንስ፣ ወንድሙ ያዕቆብና ጴጥሮስ የተወሰኑ ተአምራትንና በተራራ ላይ የኢየሱስ መልክ የተለወጠበትን ሁኔታ እንዲመለከቱ ተመርጠዋል። ከእነዚህ ሦስቱ መካከል ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር እጅግ የቀረበ ግንኙነት የነበረው ይመስላል። ራሱን «ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር” በማለት ይጠራ ነበር፡፡ ጴጥርስ ከኢየሱስ አንድ ልዩ መረጃ ለማግኘት የጠየቀው ዮሐንስን ነበር (ዮሐ 13፡23-24)። ኢየሱስ እናቱን አደራ የሰጣት (ለማያምኑ የራሱ ወንድሞች ላይሆን) ለዮሐንስ ነበር (ዮሐ 19፡26-27)። ከኢየሱስ ትንሣኤና ዕርገት በኋላ፣ ዮሐንስ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ መሪ ነበር። ዋነኛነቱ ግን የሐዋርያቱ ቃል አቀባይ የነበረውን የጴጥርስን ያህል አልነበረም። ጳውሎስ ዮሐንስ ከሦስቱ የቤተ ክርስቲያን አእማዶች አንዱ እንደሆነ ገልጾአል (ገላ. 2፡9)። ሉቃስ በጳውሎስና በጴጥርስ ላይ ስላተኮረ፣ ከጥንቷ የቤተ ክርስቲያን ዘመን በኋላ ስለነበረው የዮሐንስ አገልግሎት ብዙም የምናውቀው ነገር የለም። የቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደሚያስረዳው፣ ዮሐንስ ከ70 ዓ.ም. በኋላ ወደ ኤፈሶን በመሄድ የትንሹ እስያ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳስ በመሆን እገልግሏል። በጣም ካረጀ በኋላ ዮሐንስ ዶሚሺያን በተባለው የሮም ንጉሥ ተሰድዶ ወደ ፍጥሞ ደሴት አመራ። ዶሚሺያን ከሞተ በኋላ ግን ንጉሥ ኔርቫ በ96 ዓም. ወደ ኤፌሶን እንዲመለስ ፈቀደለት። በመጨረሻም ወደ 100 ዓ.ም. አካባቢ አረፈ፡፡ ምናልባትም በእምነቱ ምክንያት ሳይገደል ቆይተ አርጅቶ የሞተው ዮሐንስ ብቻ ሳይሆን አይቀርም። የነጎድጓድ ልጅ የነበረው ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተለውጦ የፍቅር ሐዋርያ ለመሆን በቃ። በጽሑፎቹ ሁሉ ኢየሱስን ለመከተል መሠረቱ ፍቅር እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቶ ገልጾአል። ዮሓንስ ከነጎድጓድ ልጅነት ወደ ፍቅር ሐዋርነት ሊለወጥ ከቻለ፣ እኛም እንዲሁ በክርስቶስ ኃይል ልንለወጥ እንችላለን፡፡

የውይይት ጥያቄ:- ሀ) እርሱን ለመከተል ከወሰንህበት ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ ባሕሪህን የለወጠባቸውን መንገዶች ዘርዝር፡፡ ለ) ኢየሱስ አሁንም እንዲለውጥልህ የምትፈልጋቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? ለቤተ ክርስቲያንህ የፍቅር መሪ ትሆን ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንዲለውጥህ ጸልይ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading