ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው ለማን ነው? ወንጌሉን የጻፈበት ቦታና ጊዜስ?

የውይይት ጥያቄ:- ዮሐ 20፡30-31 አንብብ። ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈበት ዓላማ ምንድንው?

እንደ ሌሎቹ የወንጌል ጸሐፊዎች ሁሉ፣ ዮሐንስም ለተወሰኑ አንባቢዎች እንደ ጻፈ ግልጽ ነው። ዮሐንስ የተፈጸመውን ታሪክ ብቻ ስለማይናገር፣ መጽሐፉ የታሪክ ሰነድ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የዮሐንስ ወንጌል የማስተማሪያ ወንጌልም ጭምር ነው። ዮሐንስ ወንጌሉን ሲጽፍ ሦስት ዐይነት ሰዎችን በዐይነ ልቡናው የያዘ ይመስላል።

ሀ. ደኅንነትን ያላገኙ አይሁዶችና አሕዛብ። ዮሐንስ በ20፡30-31 ዓላማውን ሲገልጽ፣ መጽሐፉን የሚያነቡ ሰዎች የኢየሱስን ማንነት አውቀው እንዲያምኑበትና፥ የዘላለምን ሕይወት እንዲያገኙ እንደሚፈልግ አመልክቷል። ኢየሱስ ማን እንደሆነና ከእርሱ ጋር በግል የእምነት ግንኙነት በሚደረግበት ጊዜ ምን እንደሚከሰት ጥርት ያለ ግንዛቤ ማግኘቱ ገና ወደ ደኅንነት ላልመጣው ሰው ጠቃሚ ነው። ዮሐንስ መንፈሳዊ ነገርችን የሚፈልጉ ክርስቲያኖች ያልሆኑ ስዎች፥ ይህንን መጽሐፍ አንብበው በሚያገኙት ዕውቀት ኢየሱስን እንዲያምኑ ይፈልጋል።

ለ. ክርስቲያኖች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸውን የእምነት መሠረት እንዲያውቁ ለመርዳት ጽፎአል። ዮሐንስ 20፡30-31፣ «ማመናችሁን ትቀጥሉ ዘንድ» ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። የእነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች እምነት ከሁለት አቅጣጫ ጥቃት ይደርስበት ነበር። አንደኛው ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተነሱ ስለ ክርስቶስ አንዳንድ የተሳሳቱ አሳቦችን የሚያቀርቡ የሐሰት ትምህርቶች ነበሩ። ዮሐንስ የጥንት አማኞች እምነት ንጹሕና ጠንካራ ሆኖ እንዲቆይ ይፈልጋል። ሁለተኛው፣ ከማያምኑ ሰዎች የሚሰነዘር ጥላቻና ስደት እያደገ በመሄድ ላይ ነበር። ስለሆነም ዮሐንስ እነዚህ ክርስቲያኖች፥ በተለይም ኢየሱስን በአካል ያላዩት የክርስቲያኖች ልጆች ከስደቱ ባሻገር በኢየሱስ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጸኑ ይፈልጋል።

ሐ. ብዙ ምሑራን ዮሐንስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩትን አንዳንድ የሐሰት ትምህርቶች ለማረም እንደሚፈልግ ያስባሉ። አንዳንዶች ለምን ከኢየሱስ ትምህርት በኋላ የመጥምቁ ዮሐንስን ትምህርት መከተል ተገቢ እንዳልሆነ ዮሐንስ ማብራሪያ መስጠቱን ይናገራሉ። ዮሐንስ በሚጽፍበት ወቅት የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት በዓለም ሁሉ ተሰራጭተው የሚገኙ ሲሆን፣ በኢየሱስ ማመን እንደሚያስፈልጋቸው ማስተማሩ አስፈላጊ የነበረ ይመስላል። (የሐዋ. 19፡1-7 አንብብ።) ሌሎች ደግሞ ኢየሱስ ሰውና አምላክ በመሆኑ ጉዳይ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ተነሥተው ነበር ይላሉ። አንዳንድ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ሰው ነው ብለን ካሰብን፣ ይህ እንደ ማንኛውም ሰው ኃጢአተኛ ነው ወደሚል ድምዳሜ ይወስደናል ብለው በመስጋታቸው፥ ሰብአዊ ባሕርዩን ለመቀበል ተቸግረው ነበር። ስለሆነም ዮሐንስ ምንም እንኳ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ቃል ቢሆንም ሰው ሆኖ ወደ ሰዎች በመምጣት እንደ ሰው እንደኖረ ያስረዳል (ዮሐ 1፡14)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ ግልጽ ግንዛቤ ማግኘት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? ለ) ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘቱ እምነታችንን የሚያጠነክረው እንዴት ነው? ሐ) ሰዎች ስለ ኢየሱስ ማንነትና ሥራ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ ጠንካራ እምነትና ሕያው ግንኙነት ምን እንደሆኑ እንዲያውቁ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያንህ ምን እየሠራች ነው?

ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈበት ቦታና ጊዜ?

በዮሐንስ ወንጌል ደራሲ ማንነት ላይ የሚደረገው ክርክር የተጻፈበትን ጊዜና ቦታ ይወስነዋል። ይህ ወንጌል ወደ በኋላ እንደ ተጻፈ የሚያስቡ ሰዎች ጊዜውን ወደ 150 ዓ.ም. አካባቢ ይወስዱታል። ሌሎች ደግሞ የዮሐንስ ወንጌል ከ50-70 ዓም. መጀመሪያ ከተጻፉት መጻሕፍት አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን ደራሲው አዛውንቱ ዮሐንስ ነው የሚሉትን ጨምሮ፥ አብዛኞቹ ምሑራን ከ85-95 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተጻፈ ይስማማሉ። በምሑራን እጅ የሚገኘው የዮሐንስ ወንጌል ጥንታዊ ቅጂ በ125 ዓም. የተገለበጠ ነው።

ይህ ወንጌል የተጻፈው በኤፌሶን ላይሆን አይቀርም ይላሉ። በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ሐዋርያው ዮሐንስ በኤፌሶን አካባቢ ይኖርና ይሠራ ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d