የዮሐንስ ወንጌል ልዩ ገጽታዎች

፩. ዮሐንስ ከመጽሐፉ አብዛኛውን ክፍል ያዋቀረው፥ ሰባት ሰባት ነገሮችን ባካተቱ ሁለት ምድቦች ከፋፍሎ ነው።

ሀ. ሰባት ምልክቶች፡- ማርቆስ ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተአምራት (ለምሳሌ፣ ፈውስ) የኃይል መግለጫዎች ወይም ተአምራት ብሎ ሲጠራ፣ ዮሐንስ ግን «ምልክቶች» ማለትን መርጧል። ምልክት ወደ ሌላ ነገር የሚያመላክት ክስተት ነው። ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ሁሉ መለኮታዊነቱንና መሢሕነቱን የሚያሳዩ ነበሩ። ብዙዎቹ ምልክቶች ደግሞ የማስተማሪያ አጋጣሚዎች ነበሩ። ኢየሱስ የታመመውን ሰውዬ ከፈወሰ በኋላ፥ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል በመሆኑ በሰንበት ላይ ሥልጣን እንዳለው ገልጾአል። አምስት ሺህ ሰዎችን እንጀራ ከመገበ በኋላም እርሱ መንፈሳዊ እንጀራ እንደሆነ አስተምሯል። ዮሐንስ ሰባት ምልክቶችን ዘርዝሯል:-

 1. ውኃን ወደ ወይን መለወጥ (ዮሐ 2፡1-11)።
 2. የሹሙን ልጅ መፈወስ (ዮሐ 4፡46-54)፡፡
 3. በቤተ ሳይዳ መጠመቂያ፥ ለሠላሳ ስምንት ዓመት ታሞ የኖረ ሰው መፈወስ (ዮሐ 5፡1-15)፡፡
 4. አምስት ሺህ ሰዎችን መመገብ (ዮሐ 6፡1-15)፡፡
 5. በውኃ ላይ መራመድ (ዮሐ 6፡16-21)፡፡
 6. ዐይነ ስውሩን መፈወስ (ዮሐ 9፡1-7)፡፡
 7. አልዓዛርን ከሞት ማስነሣት (ዮሐ 11፡17-44)፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- ዘጸአት 3፡14-15 አንብብ። እግዚአብሔር ስሙ ምንድን ነው? አለ። ምን ማለት ይመስልሃል?

ለ. ሰባቱ የ«እኔ ነኝ» ዐረፍተ ነገሮች፡- አይሁዶች እጅግ ከሚያከብሯቸው የእግዚአብሔር ስሞች አንዱ፥ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ለሙሴ የሰጠው ነው። ለአይሁዶች ይህ እጅግ የተቀደሰ ስም በመሆኑ ለመጥራት አይደፍሩም ነበር። ዛሬም እንዴት እንደሚጠራ በትክክል አይታወቅም። አንዳንዶች ያህዌ ሊሉ (ይሄኛው በይበልጥ ትክክል ይመስላል)፣ ሌሎች ደግሞ ጄሆቫ ብለው ይጠሩታል። «እኔ እኔ ነኝ» የሚለው ስም እግዚአብሔር በራሱ ሕያው እንደሆነ ያመለክታል። ለህልውና ወይም ለመኖር በማንም ወይም በምንም ላይ አይደገፍም። ከቶውንም ሳይለውጥ ሁልጊዜ በእርሱነቱ ይኖራል። እርሱ የተስፋ ቃሎቹን ለመፈጸም በሕዝቡ ፈንታ የሚሠራ አምላክ ነው። ስለሆነም ዛሬ ከእኛ ጋር የሚሠራው ከአብርሃም ጋር የሠራው እግዚአብሔር ነው። በዮሐ 8፡58 ላይ ኢየሱስ ከአብርሃም በፊት «እኔ ነኝ» ብሏል። ይህንን ሲናገር አይሁዶች ኢየሱስ የብሉይ ኪዳኑ የቃል ኪዳን አምላክ ነኝ እያለ መሆኑን ስለተገነዘቡ ሊገድሉት ፈለጉ። ኢየሱስ ስለ ባሕርዩ ቁልፍ እውነቶችን ለማሳየት ሲል ስሙን ታላቁ «እኔ ነኝ» ወደሚል አሳድጓል። ከእነዚህም መካከል ዮሐንስ ሰባቶቹን ዘርዝሯል:-

 1. እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ – የመንፈሳዊ ምግብ ምንጭ (ዮሐ 6፡35)።
 2. እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ – የመንፈሳዊ ብርሃን ምንጭ (ዮሐ. 8፡12)።
 3. እኔ በር ነኝ – ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ግንኙነት መንገድ (ዮሐ 10፡7)።
 4. እኔ መልካም እረኛ ነኝ – ለእግዚአብሔር ሕዝብ ፍላጎቶች የቆመ (ዮሐ 10፡11)።
 5. እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ – በመጀመሪያም ሆነ ከሞት በኋላ ሕይወትን የሚሰጥ (ዮሐ 11፡25)።
 6. እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ – የእውነት ሁሉና የዘላለም ሕይወት ምንጭ ወደሆነው እግዚአብሔር አብ ለመቅረብ ብቸኛ መንገድ (ዮሐ 14፡6)።
 7. እኔ እውነተኛው የወይን ግንድ ነኝ – የበረከትና ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ግንኙነት ምንጭ (ዮሐ 15፡1)።

፪. ዮሐንስ፣ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር ያደረጓቸውን የተለያዩ ቃለ ምልልሶች አቅርቧል። አንድ ሰው እንደ ገለጸው፣ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር ያካሄዱቸው 27 ቃለ ምልልሶች አሉ። ለአብነት ያህል፣ የኒቆዲሞስ፤ የሳምራዊቷ ሴት፣ የተፈወሰው ሰውዬና የሌሎችም ግለሰቦች ቃለ ምልልሶች ቀርበዋል።

፫. ምንም እንኳ ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ ከ20 ዓመታት በፊት ተጽፈው ለቤተ ክርስቲያንና ለዮሐንስ አገልግሎት ይሰጡ እንደ ነበር ባይጠረጠርም፣ ከዮሐንስ ወንጌል ውስጥ 90 በመቶው በሌሎች ወንጌሎች ውስጥ አይገኝም። ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ብዙ ተጨማሪ ነገሮችን ሊጽፍ ይችል እንደ ነበርና ኢየሱስ ያደረጋቸውን ነገሮች በሙሉ የሚይዙ መጻሕፍት እንደማይኖሩ ገልጾአል ዮሐ 21፡25)።

፬. ተመሳሳይ ወንጌላት፥ ኢየሱስ ብዙ ምሳሌዎችን ተጠቅሞ እንዳስተማረ ቢናገሩም፣ በዮሐንስ ውስጥ አንድም ምሳሌ አልተጠቀሰም። ይህም ሆኖ ዮሐንስ ኢየሱስ አሌግሪ የሚባል ሌላ ዐይነት ዘዴ እንደተጠቀመ አመልክቷል። ምሳሌ ከሕይወት ገጠመኝ የሚመነጭ ታሪክ ሲሆን፣ አሌጎሪ ግን በኢየሱስና በሌላ ነገር መካከል አነጻጻሪ ሆኖ የሚቀርብ ምሳሌ ነው። ለምሳሌ፡- ኢየሱስ ራሱን በር፣ የወይን ግንድ፣ መልካም እረኛ በማለት ጠርቷል።

፭. ዮሐንስ በሌሎች ወንጌላት ውስጥ ያልተጠቀሱትን ብዙ ነገሮች ገልጾአል። ከእነዚህም መካከል የዳግም ልደት ትምህርት፣ ኢየሱስ የሕይወት ውኃ መሆኑ፣ ኢየሱስ የሕይወት እንጀራ መሆኑ ተጠቅሰዋል።

፮. የዮሐንስ ወንጌል ከማንኛውም የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ በላይ ስለ መንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ዓላማ ያብራራል። በዮሐ 14-16 ላይ የሚገኘው ትምህርት መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ክርስቶስና በእግዚአብሔር አብ እንዴት እንደሚላክ ይናገራል። የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ትኩረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ በማምጣት፣ በኢየሱስ የሚያምኑትን ሰዎች በማስተማርና በኢየሱስ ማመን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለደቀ መዛሙርቱ በማስገንዘብ ያገለግላል።

፯. ዮሐንስ መንፈሳዊ እውነቶችን ለመግለጽ ተቃራኒ ቃላትን ይጠቀማል። ብዙውን ጊዜ፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ከላይና ከታች፣ እውነትና ሐሰት፣ ሕይወትና ሞት፣ ፍቅርና ጥላቻ፣ ሕግና ጸጋ፣ መንፈሳዊ ልደትና ሥጋዊ ልደት፣ እንዲሁም ማመንና አለማመንን ጠቅሷል። ዮሐንስ ከሚወዳቸው ሌሎች ቃላት መካከል ሥራ፣ ዓለም፣ ሥጋ፣ ሰዓትና መቀበል፣ ፍቅር፣ እውነት፣ ማወቅ፣ ክብርና ምስክርነት ይገኙባቸዋል።

፰. ማቴዎስና ሉቃስ ጽሑፎቻቸውን የጀመሩት የኢየሱስን መፀነስና መወለድ በሚገልጹ ትረካዎች ሲሆን፣ ዮሐንስ መጽሐፉን የጀመረው ከዘላለም ዘመን ሲሆን ቃል ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር ከነበረበት ጊዜ ይጀምራል። ዮሐንስ የኢየሱስን ዘላለማዊ ህልውና በመግለጽ ለሰብአዊ ሕይወቱ መድረክ ይከፍታል። ይህም ዮሐንስ ካቀረበው የፍጹም ሰብአዊነቱ ገለጻ ባሻገር፥ ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል።

፱. ሦስቱ ተመሳሳይ ወንጌላት ያተኮሩት በገሊላ ውስጥ በተፈጸሙት ጉዳዮች ላይ ሲሆን፣ ዮሐንስ በሰማርያና በይሁዳ ኢየሱስ ያከናወናቸውን አገልግሎቶች ገልጾአል።

፲. ዮሐንስ በመጽሐፉ የሰዎችን ማመንና አለማመን አመልክቷል። አንደኛው፥ ሰዎች በኢየሱስ ያምኑ ነበር። ይህ ግን ሰዎች ኢየሱስ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች እስካሟላ ድረስ መሢሕ መሆኑን ለመቀበል የሚፈቅዱበት ጥልቀት የሌለው እምነት ነበር። ሁለተኛው፣ በኢየሱስና በሃይማኖት መሪዎች መካከል የማያቋርጥ ግጭት/አለማመን ይካሄድ ነበር። ይህ አለማመን ወደ ሌሎችም አይሁዶች ይተላለፍ ጀመር። እነዚህ ሁለት ጉዳዮች እስከ ምዕራፍ ስድስት ከቀጠሉ በኋላ፥ ድንገተኛ የአቅጣም ለውጥ ይከሰታል። ግጭቱና አለማመኑ እስከ መስቀል ሞት ድረስ እያደገ የሚሄድ ሲሆን ኢየሱስ ከሰዎች የሚጠብቃቸው ነገሮች እየከበዱ ሲሄዱና ከመሢሑ የሚጠብቋቸውን የራስ ወዳድነት ፍላጎቶች ሳያሟላ ሊቀር፥ በኢየሱስ ላይ የነበራቸው እምነት እየቀነሰ ሊሄድ ችሏል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: