የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በዮሐ 20፡30-31 የመጽሐፉ ዓላማ ሆኖ የተገለጸው ምንድን ነው? ለ) የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ፤ ዮሐ 1፡7፤ 3፡16-18፤ 6፡28-29፤ 8፡24፤ 17፡20-21፡፡ እነዚህ ጥቅሶች ስለ እምነት ምን ያስተምራሉ? ኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚገልጽ አጭር ጽሑፍ ጻፍ። ሐ) የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብብ፦ ዮሐ 3፡15-16፣ 36፤ 5፡24፤ 10፡28፤ 17፡2-3። እነዚህ ጥቅሶች ስለ ዘላለማዊ ሕይወት ምን ያስተምራሉ? የዘላለም ሕይወት ምን እንደሆነ ግለጽ።
- የዮሐንስ ወንጌል የተጻፈበት ቀዳሚው ዓላማ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅና የዘላለም ሕይወት መንገድ እንደሆነ ለማሳየት ነው። በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት አላቸው። የማያምኑ ግን የዘላለም ሕይወት የላቸውም። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ እነዚህ እምነትና የዘላለም ሕይወት የሚሉ ቃላት እጅግ ወሳኝ ናቸው።
ሀ. እምነት፡- በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ይህ ቃል ከ98 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። ዮሐንስ «እምነት» የሚለውን ቃል በተለያዩ መንገዶች ይገልጣል። አንደኛው፣ የሕይወት መለወጥ ሳይኖር አንድ ነገር እውነት እንደሆነ መቀበልን የሚያመላክት አእምሮአዊ ግንዛቤ አለ። ስለሆነም አንድ ሰው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እያመነ ያንኑ እምነት ግላዊ አድርጎ በዚያው መሠረት ላይመላለስ ይችላል። ሁለተኛው፣ ለራስ ወዳድነት ጥቅሞች በሚያመች መልኩ ኢየሱስን የሚከተል እምነትም አለ። ዮሐንስ ምን ያህል ሰዎች ኢየሱስን እንከተላለን እንዳሉና ነገር ግን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ የሚጠብቀው ነገር በሚያይልበት ጊዜ ወደኋላ እንዳፈገፈጉ በመጽሐፉ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ገልጾአል (ዮሐ 6፡64-66 አንብብ።) ሦሰተኛው፣ ኢየሱስ የደኅንነት መንገድ መሆኑን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ሕይወትን ለዚያ እውነት ሙሉ በሙሉ አሳልፎ በመስጠት የእውነቱ መገለጫ የሆነ ሕይወት መምራት የሚቻልበትም እምነት አለ። የዘላለምን ሕይወት የሚሰጠው የዚህ ዐይነቱ እምነት ብቻ ነው።
የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዐይነት እምነቶች የያዙ ብዙ ክርስቲያኖች አሉ። አንዳንዶች በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ በማደጋቸው ክርስቶስ ሞቶ እንደ ተነሣ ያውቃሉ። ነገር ግን እምነቱን የግላቸው ስላላደረጉ በሚያውቁት ነገር ላይ የተመሠረተ ሕይወት ይመራሉ። ሌሎች ደግሞ ኢየሱስን የሚከተሉት ምን ሊያደርግላቸው እንደሚችል በማሰብ ነው። እስከ ፈወሳቸው ወይም ከመከራ እስከ ጠበቃቸው ድረስ ይከተሉታል። ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ግን ወደኋላ ይመለሳሉ። እንደዚህ ዐይነቱ የራስ ወዳድነት ሕይወት የዘላለምን ሕይወት አያስገኝም። ዮሐንስ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ለማሳደግ የሚፈልገው ዐይነት እምነት ሙሉ ሕይወታችንን በኢየሱስ ላይ እንድናሳርፍ የሚጠይቅ ነው። ለደኅንነት ፊታችንን የምንመልሰው ወደ ኢየሱስ ብቻ ነው።
ለ. የዘላለም ሕይወት፡- ዮሐንስ ከ40 ጊዜ በላይ ስለ ሕይወት ያነሣል። ከእነዚህም አብዛኞቹ የዘላለምን ሕይወት የሚያመለከቱ ናቸው። «የዘላለም ሕይወት» የሚለውን ሐረግ በምንሰማበት ጊዜ በአመዛኙ ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት፣ ከኢየሱስ ጋር ሁልጊዜ ደስ የምንሰኝበትን ማብቂያ የሌለው ሕይወት እናስባለን። የምናተኩረው በጊዜ ላይ ነው። ዮሐንስ ግን ይህንን ሐረግ የተጠቀመው ከዚህ በሰፋ መንገድ ነው። እርሱ ያተኮረው በእምነት በሚገኝ የሕይወት ጥራት ላይ ነው። ስለሆነም የዘላለም ሕይወት አንድ ክርስቲያን ኢየሱስን እንደ አዳኙ አድርጎ በሚያምንበት ጊዜ የሚሰጠው ልዩ ሕይወት ነው። ያ ሕይወት ከእግዚአብሔርና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አዲስ ግንኙነት ማድረግን ይጨምራል። ኢየሱስ እንደገለጸው፣ «እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት» (ዮሐ 17፡3)። ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታን ያገኘው ሰው ሕይወት ነው። እንዲህ ዐይነቱ ሰው በልቡ ውስጥ የእግዚአብሔር ሰላም ያለው ሲሆን፣ ባሕርዩም የተለወጠ ነው። ጳውሎስ ይህ አዲስ ሕይወት የተለየ ከመሆኑ የተነሣ ነገሮች ሁሉ እንደሚቀየሩ ገልጾአል (2ኛ ቆሮ. 5፡17)። እግዚአብሔር አሁን እንደ ልጆቹ ቆጥሮ የሰጠን መንፈሳዊ የዘላለም ሕይወት ማብቂያ አይኖረውም።
- ዮሐንስ ክርስቲያኖች እምነታቸውን የጣሉበት ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነ በግልጽ ለማሳየት ፈልጓል። የዮሐንስ ወንጌል፥ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መለኮታዊ መሆኑን የሚያመለክት እጅግ የጠራ መልእክት ያቀርባል። አይሁዶች እግዚአብሔር አንድ መሆኑን ለ 1,400 ዓመታት ያህል ያስተምሩ ነበር። ስለዚህ ክርስቲያኖች ኢየሱስም አምላክ ነው ማለታቸው ስለ እግዚአብሔር የነበራቸው መረዳት በከፍተኛ ደረጃ እንደተለወጠ ያመለክታል። ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር እንዴት አንድና ሦስት እንደሚሆን በግልጽ ባያብራራም፣ ዮሐንስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ እንደሆነና ነገር ግን ከእግዚአብሔር አብ የተለየ መሆኑን ያለ አንዳች ጥርጣሬ ገልጾአል።
የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐ 1፡1፣ 4፣ 14፣ 18፣ 3፡34፤ 5፡21፣ 22፣ 24፤ 8፡57-58፤ 13፡3 አንብብና እነዚህ ጥቅሶች የኢየሱስን መለኮታዊነት እንዴት እንደሚያመለክቱ ግለጽ። ዮሐንስ የኢየሱስን መለኮታዊ ባሕርይ በሦስት መንገዶች አሳይቷል።
ሀ. ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክነት ባሕርያት ሁሉ አሉት። ኢየሱስ ሕይወትና ሕይወት ሰጭም ነው (ዮሐ 1፡4፣ 14፡6)። በተጨማሪም የዓለም ብርሃን (ዮሐ 1፡4-9፤ 8፡12)፣ እውነት (ዮሐ 1፡14፤ 14፡6)፣ ክብር (ዮሐ 1፡14፤ 17፡5፣ 24) እና ጸጋ (ዮሐ 1፡14፣ 17) ነው። እነዚህ ሁሉ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔርን የሚያመለክቱ ጽንሰ አሳቦች ናቸው። ከዚህም በላይ ኢየሱስ እግዚአብሔርን በትክክል የሚገልጽ የእግዚአብሔር ቃል ነው። እርሱ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ልጅ (ዮሐ 3፡16) እና ጌታ (ዮሐ 13፡14፤ 20፡28) ነው። እንዲሁም ኢየሱስ የብሉይ ኪዳኑ ዘላለማዊ “እኔ ነኝ” (ለያህዌ ሌላው ስያሜ) መሆኑን ገልጾአል (ዮሐ 8፡57-58)። እግዚአብሔርን በሙሉ ክብሩ ያየው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው (ዮሐ 1፡18)። ዮሐንስ ቃል የሆነው ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ ያስረዳል (ዮሐ 1፡1)። ኢየሱስ ከአብ ጋር አንድ ነው (ዮሐ 10፡30)። ኢየሱስን ማየት እግዚአብሔር አብን እንደ ማየት ነው ( ዮሐ 14፡9)።
ለ. ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልዩ መለኮታዊ መልእክተኛ ነው። ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ከሰማይ ለአገልግሎት ተሹሞ ነው (ዮሐ 3፡34፤ 6፡38)። እርሱ ከእግዚአብሔር የተላከ መምህር ነው (ዮሐ. 3፡2)። ነገር ግን ኃይልን ሁሉ ስለተላበሰ (ዮሐ 13፡3)፣ መንፈስ ቅዱስን ስለሚልክ (ዮሐ 15፡26)፣ ዓለምን ስለሚያሸንፍ (ዮሐ 16፡33)፤ ሰዎችን ከሞት ስለሚያስነሣና ፍርድን ስለሚሰጥ (ዮሐ 5፡22) ፍጹም አምላክ ነው። እርሱ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣል (ዮሐ 10፡28)።
ሐ. ኢየሱስ ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ተስፋዎችና ቃል ኪዳኖች ሁሉ ፍጻሜ ነው። ኢየሱስ መሢሕ (ዮሐ 4፡25-26)፣ የእስራኤል ንጉሥ (ዮሐ 1፡49)፣ የእግዚአብሔር የመሥዋዕት በግ (ዮሐ 1፡29፣ 35)፣ የሰው ልጅ ( ዮሐ 1፡51፤ 3፡13-14)፣ ታላቁ ነቢይ (ዮሐ 6፡14)፣ የዓለም መድኅን (ዮሐ 4፡42) ነው። የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ሁሉ ወደ እርሱ ያመለክታሉ (ዮሐ 5፡39-40፣ 8፡50)። ኢየሱስ በመዝ 23 የተገለጸው መልካም እረኛ (ዮሐ 10፡14) እና በኢሳ. 5 የተጠቀሰው እውነተኛ የወይን ግንድ ነው (ዮሐ 15፡1 እና 5)። እርሱ እውነተኛ የሕይወት እንጀራ ነው (ዮሐ 6፡35)። ለሙታን ሕይወትን የሚሰጠው ኢየሱስ ነው (ዮሐ 11፡25)።
ነገር ግን ዮሐንስ ኢየሱስ ፍጹም ሰው እንደሆነም ያሳያል። እግዚአብሔር (ቃል) ሥጋ ሆነ። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ነገረ-መለኮታዊ ክርክር፣ ኢየሱስ እውነት ሰው ሆኗል ወይ? በአንድ አካል እንዴት ሰውና አምላክ ሊሆን ይችላል? የሚል ነበር። ይህ ክርክር በዮሐንስ ዘመን የነበረ ይመስላል። በተለይም በ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ውስጥ ስለዚህ ክርክር በሰፊው ተገልጾ እናገኛለን። በኋላ በሁለተኛው ምእተ ዓመት አጋማሽ ላይ የተነሣው ብርቱ ክርክር ዛሬ በኦርቶዶክስ፣ በካቶሊክና በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት መካከል፥ የሚታየውን የእምነት ልዩነት አስከትሏል። ዮሐንስ ኢየሱስ ፍጹም አምላክ መሆኑን ያምናል። ኢየሱስ ሥጋ ሆኖ በሰዎች መካከል እንዳደገ ገልጾአልና (ዮሐ 1፡14)። ዮሐንስ ኢየሱስ ስለኖረባት ከተማ (ናዝሬት)፣ ስለ እናቱና ወንድሞቹ፣ ውኃ ስለ መጠጣቱ፣ ስለ ማልቀሱ፣ የደቀ መዛሙርቱን እግር ስለ ማጠቡና ሞቶ ስለ መቀበሩ በመግለጽ፣ የኢየሱስን ሰው መሆን በግልጽ አመልክቷል። ምንም እንኳ የዮሐንስ መጽሐፍ በኢየሱስ ሰብአዊነትና አምላክነት ላይ የሚነሣውን ክርክር ለመዳኘት ባይረዳንም፣ ኢየሱስ በአንድ አምላክም ሰውም እንደሆነ በግልጽ የሚያስረዱ መረጃዎች አሉ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)