የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ (ዮሐ. 1-18)

አንድ ጊዜ፣ «ኢየሱስ ክርስቶስ መኖር የጀመረው ከመቼ ጀምሮ ነው? የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው መቼ ነው?» የሚል ጥያቄ ለቤተ ክርስቲያናችን መሪ አቀረብሁለት። ይህ የቤተ ክርስቲያን መሪ ወዲያው በማቴዎስና ሉቃስ ወንጌል ውስጥ ስለተጠቀሰው የኢየሱስ ታሪክ አስታወሰ። «መኖር የጀመረው ከማርያም ከተወለደበት ጊዜ አንሥቶ ነው። እግዚአብሔር በማርያም ማኅፀን ውስጥ ሳለ ሕይወትን ስለ ሰጠው እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው» ሲል መለሰልኝ።

ብዙ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ የገና በዓል በመጣ ቁጥር ኢየሱስ በተአምር ከማርያም መወለዱን የሚያመለክት ታሪክ እንናገራለን። ምንም እንኳ ስለ ወደፊቱ ማሰብ ቢቀልለንም፣ ያለፈውን ጊዜ እንደዚያ ማሰቡ ቀላል አይሆንም፡፡ ስለሆነም እግዚአብሔር በተለይም ኢየሱስ ክርስቶስ ሁልጊዜ የመኖሩን አሳብ መረዳቱ አስቸጋሪ ይሆንብናል። ነገር ግን አእምሮአችን ስለ ወደፊቱ ረጅምና ከእግዚአብሔር ጋር አብረን ስለምንኖርበት ጊዜ እንደሚያስብ ሁሉ፣ ወደ ኋላም በመመልከት እግዚአብሔር ፍጻሜ የሌለው አጀማመር እንደነበረው መረዳት ይኖርብናል።

ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ሕይወት የጻፈውን ይህንን መግቢያ የጀመረው በዚሁ ፍጻሜ በሌለው አጀማመር ሁኔታ ነው። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ትክክለኛ ግንዛቤ ለማግኘት ዮሐንስ ስለ ኢየሱስና እንዴት ከእርሱ ጋር ኅብረት ልናደርግ እንደምንችል የሚናገረውን መረዳት ይኖርብናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐ 1፡1-18 አንብብ። ሀ) ዮሐንስ የኢየሱስን መለኮታዊ ባሕርይ እንዴት እንደሚገልጽ ዘርዝር። ለ) የኢየሱስን ሰብአዊ ባሕርይ የሚገልጹትን ነገሮች ዘርዝር ሐ) ዮሐንስ ስለ ድነት (ደኅንነት) ምን እንደሚያስተምር ዘርዝር።

በዚህ ክፍል ዮሐንስ ከኢየሱስና ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር ያስተዋውቀናል። በተጨማሪም የኢየሱስን ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ ውጤቶች ይገልጽልናል። ዋና ዋና ትምህርቶቹ ሁሉ በዚህ ክፍል ተጠቅሰዋል። ዮሐንስ በኢየሱስ ሕይወት አማካይነት የሚያስተምረውን አሳብ ለመረዳት፣ ይህንን መግቢያ ማወቅ ይኖርብናል።

ሀ. ኢየሱስ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቃል ነው (ዮሐ 1፡1-2)፡፡ ዮሐንስ የኢየሱስን ታሪክ የጀመረው ከመጀመሪያው ነው። የምን መጀመሪያ? ይህ ኢየሱስ በማርያም ማሕፀን ውስጥ ከመፀነሱ በፊት ያለው ጊዜ አይደለም። እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ የፈጠረበት መጀመሪያም አይደለም። ዮሐንስ የሚናገረው ከዘላለም ዘመናት በፊት ስለነበረው ጊዜ ነው። ሰዎች ማሰብ እስከሚችሉበት ድረስ እንኳን ወደ ኋላ ቢመለሱ ኢየሱስ እንደ ነበር ዮሐንስ ያስረዳል። ዮሐንስ መጀመሪያ ብሎ የሚጠራው ይህንን ጊዜ ነው። ነገር ግን ኢየሱስ መጀመሪያ የለውም።

ዮሐንስ ኢየሱስን ቃል (ወይም በግሪክ ሎጎስ) በማለት የጠራው ለምንድን ነው? ለዚህ ሁለት አማራጮች አሉ? አንደኛው፥ አይሁዶች በብሉይ ኪዳን ላይ ተመሥርተው ይህንን አሳብ ሊረዱ ይችሉ ነበር። በብሉይ ኪዳን “የእግዚአብሔር ቃል” በተለያዩ መንገዶች አገልግሏል።

  1. አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በሥራ ላይ መሆኑን ያመለክታል። በፍጥረት ጊዜ ሁሉም ነገር የተፈጠረው ከእግዚአብሔር አፍ በወጣው ቃል ነበር (ዘፍ. 1፡3፣6)። ስለሆነም እግዚአብሔር አንድን ነገር ለማድረግ በሚፈልግበት ጊዜ፥ በአብዛኛው ነገሮች የሚከውነው ከአፉ በሚወጣው ቃል ነው [መዝ. (119)፡25፣ (105)፣ (169)]።
  2. አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ራሱንና ፈቃዱን መግለጹን ያመላክታል (1ኛ ሳሙ. 3፡21)።

ስለሆነም ዮሐንስ ይህንን የተለየ ስም ለኢየሱስ ሲሰጥ፥ ኢየሱስ የፍጥረት እንደራሴ እንደሆነ መግለጹ ነው። (ማስታወሻ፡ በአዲስ ኪዳን ለኢየሱስ ይህንን ስም የተጠቀመው ዮሐንስ ብቻ ነው።) በተጨማሪም ኢየሱስ እግዚአብሔር ነገሮችን ለመግለጽ የመረጠበት መንገድ ነው። ለዚህ ነው ዮሐንስ እኔን ያየ አብን አይቷል የሚለው (ዮሐ 14፡9)። የዕብራውያን ጸሐፊ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ፍጹም ነጸብራቅ፣ የመጨረሻና ከሁሉም የላቀ መገለጥ እንደሆነ አመልክቷል (ዕብ 1፡3)።

ቃል ለሚለው አገላለጽ ሁለተኛው አማራጭ ከግሪኮች የተገኘ ነው። ይህ ግሪኮች ለዓለም ምክንያትና ዓላማ በመስጠት ወደ ልዩ ፍጻሜ ስለሚመራው አመክኒዮአዊ መርሕ የሚሰጡት ስያሜ ነበር። ዓለም በዕድል ሳይሆን በእግዚአብሔር ትመራለች። እግዚአብሔር ዓለምን በጥበቡ አማካይነት ንድፍ በመንደፍ፣ በመፍጠር፣ በመደገፍና አስቀድሞ ወደ ወጠናቸው ዕቅዶች በመምራት ያስተዳድራታል። ስለሆነም ዮሐንስ ለግሪክ አንባብያኑ ኢየሱስ ዓለምን ለመፍጠር የእግዚአብሔር እንደራሴ ብቻ ሳይሆን፥ ታሪክና ፍጥረት ሁሉ ፈቃዱን እንዲፈጽሙ የሚመራቸው መሆኑን አመልክቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ ሁለት ስለ «ቃል» የተነገሩን ነገሮች ኢየሱስን በተሻለ ሁኔታ እንድናውቀው የሚረዱን እንዴት ነው?

ለ. ኢየሱስ አምላክም ከአብም የተለየ ነው። ዮሐንስ ኢየሱስ ቃል በመሆኑ በመጀመሪያው ይኖር እንደነበርና አምላክ በመሆኑ ደግሞ፥ ከእግዚአብሔር አብ የተለየ መሆኑን ገልጾአል። «የኢየሱስ ብቻ» (Only Jesus) እምነት ተከታዮች ኢየሱስና እግዚአብሔር አብ አንድ መሆናቸውን ቢናገሩም፣ ኢየሱስ አምላክ ቢሆንም፥ ከእግዚአብሔር አብ እንደሚለይ በዚህ ክፍል በግልጽ መገንዘብ ይቻላል። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አባቶች የሥላሴን ጽንሰ አሳብ እንዲመሠርቱ ካደረጉት ጥቅሶች አንዱ ይኼ ነበር። ሥላሴ አንዱ አምላክ በሦስት አካላት (አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ) እንደሚገለጽ የሚያስረዳ ትምህርት ነው።

ሐ. ኢየሱስ የፍጥረት ሁሉ እንደራሴ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሦስቱም የሥላሴ አካላት አባላት በፍጥረት ሥራ ላይ እንደ ተካፈሉ ያሳያል። እዚህ ላይ ትኩረት የተሰጠው በኢየሱስ ድርሻ ላይ ነው። ዮሐንስ ኢየሱስ በዘፍጥረት ምዕራፍ አንድና ከዚያም በኋላ በተፈጠሩት ሰዎችና ነገሮች አፈጣጠር ላይ ተሳታፊ እንደ ነበር ገልጾአል።

መ. ኢየሱስ የሕይወት ምንጭ ነው። ሕይወት ላላቸው ነገሮች ሁሉ የሚያስፈልገውን አካላዊ ሕይወትና በተለይም በእርሱ ለሚያምኑ መንፈሳዊ ሕይወትን የሚሰጠው እርሱ ነው። ዮሐንስ ከሚወዳቸው ቃላት አንዱን በመጠቀም የኢየሱስን የሥራ ውጤቶች ይገልጻል። ይህም የዘላለም ሕይወት መስጠቱ ነው። ዮሐንስ ይህንን ቃል ከ40 ጊዜ በላይ የጠቀሰው ሲሆን፣ ይህም በተለይም ኢየሱስ በእርሱ ለሚያምኑት ሰዎች ስለሚሰጠው ሕይወት የሚያመለክት ነው። በኋላም ኢየሱስ እርሱ ሕይወት እንደሆነ ይገልጻል ( ዮሐ 14፡6)። በተጨማሪም ኢየሱስ ሰዎችን ከሞት ስለሚያስነሣ የትንሣኤ ሕይወት ምንጭ ነው (ዮሐ 11፡25-26)።

ሠ. ኢየሱስ የብርሃን ምንጭ ነው። ዮሐንስ በቀዳሚነቱ የሚናገረው ስለ መንፈሳዊ ብርሃን ነው። ይህም በዮሐንስ 24 ጊዜ የጠቀሰው ሌላው ተወዳጅ ቃል ነው። ዮሐንስ ወደ በኋላ ኢየሱስ የዓለም ብርሃን እንደሆነ የተናገረውን አሳብ ያቀርባል (ዮሐ 8፡12)። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ብርሃን ሁለት ፍችዎች አሉት። በዚህ ስፍራ ብርሃን የሚለው ቃል ኢየሱስ የመንፈሳዊ ብርሃን ወይም የመንፈሳዊ መረዳት ምንጭ መሆኑን የሚያመለክት ይመስላል። ኢየሱስ እግዚአብሔርንና ፈቃዱን ለሰዎች ይገልጣል። ይህ ዳዊት የእግዚአብሔር ቃል የእግሬ መብራት ነው ካለው እሳብ ጋር ይመሳሰላል [መዝ. 119፡105]። ዮሐንስ ኢየሱስ የዘላለምን ሕይወት መንገድ እንደሚያበራና ሰዎች ግን እርሱንም ሆነ የሚሰጣቸውን ብርሃን እንዳልተገነዘቡ አመልክቷል።

ብዙውን ጊዜ ይህ ብርሃን የሚለው ቃል ከጨለማ ጋር እየተነጻጸረ ቀርቧል። ጨለማ ክፉውን ዓለም፣ በእግዚአብሔር ላይ የሚሰነዘረውን ተቃውሞና ሰይጣን የሚቆጣጠረውን ሕይወት አቅጣጫ ያመለክታል። ብርሃን ከዚህ በተቃራኒው ለእግዚአብሔርና ለቃሉ መታዘዝን ያመለክታል።

ረ. መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ ብርሃን እንደሆነ መሰከረ። አንዳንድ ምሑራን ከመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት መካከል የመጥምቁ ድርሻ ምን እንደሆነና ከኢየሱስ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ያላወቁ ሰዎች ስለነበሩ፥ ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን ችግር ለማስወገድ እንደፈለገ ያስባሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ መጥምቁ ዮሐንስ ሰዎችን ብርሃን ወደነበረው ኢየሱስ ያመለከተ ምስክር መሆኑን ገልጾአል። (ማስታወሻ፡ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የተለያዩ ሰዎች እንደመሰከሩ የሚያስረዳው ሌላው የዮሐንስ ተወዳጅ ቃል «ምስክር» የሚለው ነው።) እውነተኛው የድነት (የደኅንነት) ብርሃን ኢየሱስ ብቻ ነው። ደማቅ ብርሃን በጨለማ ውስጥ መንገድን እንደሚመራ ሁሉ፣ መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ብርሃን ወደ ኢየሱስ ያመለክት ነበር።

ሰ. ብዙሃኑ ሕዝብ ቃል የሆነውን ኢየሱስን አልተቀበሉትም። ዮሐንስ ሰዎች ለኢየሱስ የሰጧቸውን የተለያዩ ምላሾች አመልክቷል። ሕዝቡ ኢየሱስን እንደ አዳኝ ባይቀበለውም፣ ኢየሱስ ለመስጠት የመጣውን የዘላለም ሕይወት አምነው የሚቀበሉ ጥቂቶች ነበሩ። ኢየሱስ ዓለምን የፈጠረ ቢሆንም፣ አሁን ወደ ዓለም የመጣው እንደ ሰብአዊ ሰው ነበር። የፈጠራቸው ሰዎች ግን ኢየሱስ ፈጣሪያቸው ወይም አዳኛቸው እንደሆነ አላወቁም ነበር።

ሸ. በኢየሱስ ያመኑ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ። ኢየሱስ ልዩ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። የኢየሱስን ያህል መለኮታዊ ማንነት ያለው ማንም የለም፡፡ (ይህ ሁላችንም አማልክት ነን ከሚለው የአዲሱ ዘመን ትምህርት ይለያል።) ነገር ግን ዮሐንስ በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት እንደሆኑ ገልጾአል። ይህም የእግዚአብሔር ልጆች ያደርጋቸዋል። (ማስታወሻ፡ በኢየሱስ ስም ማመን ማለት በኢየሱስ ማመንን የሚያመለክት የአይሁዶች አገላለጽ ነው። ስም የስሙን ባለቤት ያመለክታል) መንፈስ ቅዱስ አዲስ ልደት ስለሰጣቸው ከእግዚአብሔር ተወልደዋል። በዮሐንስ ምዕራፍ 3 ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ስለ መንፈሳዊ ልደት ከሰጠው ማብራሪያ ወደፊት ስለዚሁ ጉዳይ ሰፋ አድርገን እንመለከታለን።

ቀ. ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ክብር የሚያሳይ ሰው ሆነ፡፡ በኢየሱስ መለኮታዊ ባሕርይ ላይ ብቻ ከሚገባው በላይ እንዳናተኩር በማሰብ፣ ዮሐንስ ስለ ፍጹም ሰብአዊነቱም እንድናስብ ያደፋፍረናል። የዘላለም ቃል የሆነው ኢየሱስ በሆነ ምሥጢራዊ መንገድ ሰው ሆነ። ይህንን ምሥጢር ዮሐንስ ሊያብራራ አልሞከረም። «በመካከላችን አደረ» የሚለው የግሪኩ ቋንቋ አገላለጽ፣ በሰዎች መካከል ድንኳን ከመትከል ጋር ተመሳሳይ ነው። በብሉይ ኪዳን የመገናኛው ድንኳን ለአይሁድ ማኅበረሰብ የእግዚአብሔርን ህልውና ያመጣ እንደ ነበረ ሁሉ፣ ኢየሱስ በሥጋ ተገልጦ በሰዎች መካከል የእግዚአብሔርን ህልውና አምጥቷል። ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሆነው ዮሐንስ የኢየሱስን መለኮታዊ ክብር እንዳየ ገልጾአል። በተራራው ላይ የእግዚአብሔር ክብር በኢየሱስ ላይ ሲንጸባረቅ ተመልክቷል። በተጨማሪም ተአምራትን ሲፈጽምና በመስቀል ላይ ሞቶ ሲነሣ በመመልከቱ። የእግዚአብሔር ክብር እንደ ተገለጸበት ተረድቷል (ዮሐ 2፡11)። የኢየሱስን ልዩ መሆን ለማሳየት፣ ዮሐንስ ሦስት አሳቦችን ተጠቅሟል፡፡

  1. ኢየሱስ “አንድያ” ወይም ልዩ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር። ዮሐንስ ኢየሱስ መለኮታዊ፣ ልዩና ከሌሎች የተፈጠሩ የእዚአብሔር ልጆች ሁሉ የተለየ መሆኑን ገልጾአል።
  2. ኢየሱስ በጸጋ ተሞልቶ ነበር። የወንጌሉ መሠረት ሊቀበሉት ለማይገባቸው ሰዎች የሚሰጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ወይም ሞገስ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ጸጋ በመልካም ሥራችን ልንቀበል አንችልም። ምክንያቱም ጸጋው የሚጠይቀውን መመዘኛ ልናሟላ አንችልም። ነገር ግን እግዚአብሔር ሊቀበሉት ለማይገባቸው ሰዎች ጸጋውንና ሞገሱን በነፃ ይሰጣል። ከሁሉም የሚበልጠው ጸጋ የተገለጠው እንደ መሥዋዕት ወደ ምድር ተልኮ በመጣው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ማስታወሻ፡ ዮሐንስ ጸጋን የተጠቀመው እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባውን የቃል ኪዳን ፍቅር የሚያንጸባርቀውንና «ሄሰድ» የተባለውን የብሉይ ኪዳን ጽንሰ አሳብ ለመግለጽ ሳይሆን አይቀርም [መዝ. (26)፡3]፡፡
  3. ኢየሱስ በእውነት ተሞልቶ ነበር። እውነት ዮሐንስ 25 ጊዜ ያህል የጠቀሰው ሌላው ልዩ ቃል ነው። ኢየሱስ «እኔ እውነት ነኝ» ብሏል (ዮሐ 14፡6)። እውነት ሁሉ በእርሱ ስለሚገኝ፣ ኢየሱስ የእውነት መሠረት ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ በኑባሬ እውነት በመሆኑ ግማሽ እውነት ወይም የመጥፎና ጥሩ ቅይጥ አይገኝበትም።

በ. ጸጋንና እውነትን ወደ ሰዎች ያመጣው ኢየሱስ ሕግን ከሰጠው ከሙሴ በላይ ነው። አይሁዶች ያከብሩት የነበረው ሕግ ማንም ሙሉ በሙሉ ሊጠብቀው ስላልቻለ ሞትን አፍርቷል። ኢየሱስ ግን የእግዚአብሔርን ይቅርታ (ጸጋ) እና የእግዚአብሔርን የደኅንነት መንገድ (እውነት) አምጥቷል። ስለሆነም ኢየሱስ ሕግን በማምጣቱ አይሁዶች ካከበሩት ሙሴ ይልቃል።

ተ. ኢየሱስ እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ማየትና ማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ በበለጠ የተሟላ መንገድ ይገልጻዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔርን ያዩት ሰዎች ታሪክ ተጽፎ እናገኛለን። ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘት ክብሩን አይቷል (ዘጸ 33፡18-23)። ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤልና ዮሐንስም እግዚአብሔርን በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ አይተውታል (ኢሳ. 6፡1፤ ሕዝ. 1፡25-28፤ ራእይ 4፡2-3)። እንግዲህ ዮሐንስ ማንም እግዚአብሔርን አላየም ሲል ምን ማለቱ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው፣ ከውስንነታችን የተነሣ እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ልንረዳው ስለማንችል ስለ ራሱ የሚሰጠን ከፊል መገለጥ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ለሙሴ ጀርባውን ብቻ እንደሚያሳይ በመግለጽ ይህንን እውነት በተምሳሌታዊ መልኩ ገልጾታል። ለዚህም ነው ራእዮችን ያዩ ሰዎች ፊቱን ላለመግለጽ የሚጠነቀቁት። ትኩረት የሚሰጡት በእግዚአብሔር ዙሪያ በሚገኙት ነገሮች ላይ ሲሆን፣ እግዚአብሔር አንድን ነገር እንደሚመስል ይገልጻሉ። እነዚህም እንኳ ሰዎች ይረዷቸው ዘንድ ቀለል ተደርገው የሚቀርቡ ናቸው። እግዚአብሔር እኛ ልናስብ ወይም ልንገምት ከምንችለው ከማንኛውም ነገር በላይ ታላቅ ነው። ይሁንና የእግዚአብሔር መለኮታዊ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን በሙሉ ክብሩ አይቶታል። ኢየሱስ ወደ ምድር ሲመጣ ዓለም የእግዚአብሔርን ሙሉ መገለጥ ለማየት ችላለች። በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ኢየሱስ አብዛኛውን ጊዜ መለኮታዊ ባሕርዩን ሸፍኖታል።

የውይይት ጥያቄ፡- ከዚህ ክፍል ስለ ኢየሱስ መለኮታዊና ሰብአዊ ባሕርያት ልንማር የምንችላቸውን ነገሮችን ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

3 thoughts on “የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ (ዮሐ. 1-18)”

Leave a Reply

%d bloggers like this: