መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን ለመግለጥ ያደረገው አገልግሎት (ዮሐ 1፡19-51)

የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐ 1፡19-2፡25 አንብብ ሀ) ይህ ክፍል ስለ ኢየሱስ ምን ይነግረናል? ለ) በኢየሱስ ስለ ማመንና እርሱን ስለ መከተል ምን እንማራለን?

ሌሎች ወንጌላት ቀደም ብለው ይህንኑ እንዳደረጉ ስለሚያውቅ ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ መጠመቅ አልጻፈም። ከዚህ ይልቅ መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ በሰጠው ምስክርነት ላይ አትኩሯል። ዮሐንስ ስለ ራሱና ስለ ኢየሱስ ማንነት ግልጽ ግንዛቤ ነበረው።

ሀ. መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ራሱ ለሃይማኖት መሪዎች የሰጠው መግለጫ ( ዮሐ 1፡19-28)

  1. መጥምቁ ዮሐንስ አይሁዶች «የምትመጣው መሢሕ አንተ ነህ ወይ?» በማለት በጠየቁት ጊዜ መልሱ «እኔ አይደለሁም» የሚል ነበር።
  2. መጥምቁ ዮሐንስ ኤልያስ አልነበረም። በሌሎች ወንጌላት ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስን ኤልያስ እያለ ሲጠራ እንመለከታለን (ማቴ. 11፡13-14)። እንግዲህ ልዩነቱ ምንድን ነው? ምናልባትም የሚናገሩት ስለ ሁለት የተለያዩ ሰዎች ሊሆን ይችላል። በመጀመሪያ፣ ሞትን ሳይቀምስ ወደ ሰማይ የተወሰደ ኤልያስ የሚባል ነቢይ ነበር። አይሁዶች መሢሑ ሊመጣ ሲል ይህ ወደ ሰማይ ተወስዶ የነበረው ኤልያስ ተመልሶ ይመጣል ብለው ያምኑ ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ እርሱ ወደ ሰማይ ተወስዶ የነበረው ኤልያስ እንዳልሆነ ገልጾላቸዋል። በኋላ ኢየሱስ ወደ ሚልክያስ 4፡5 በማመልከት ስለ ኢየሱስ ምጽአት የሚያውጅ ተምሳሌታዊ ኤልያስ እንደሚመጣ ገልጾላቸዋል። መጥምቁ ዮሐንስ ይሄኛው ኤልያስ ነው።
  3. መጥምቁ ዮሐንስ ነቢዩ አይደለም (ዘዳግ 18፡15፣ 18 አንብብ)። አይሁዶች ሙሴ አንድ ልዩ ነቢይ እንደሚመጣ እንደተነበየ ያውቁ ነበር። አይሁዶች ይህ ነቢይ ከመሢሑ የተለየ ነው ብለው ያስቡ ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስ  በመጽሐፉ ከሚያሳያቸው ነገሮች መካከል አንዱ፥ ኢየሱስ መሢሕም ነቢይም እንደሆነ ነው። ስለሆነም ዮሐንስ ራሱን አይሁዶች ሲጠብቁ የኖሩት ነቢይ አድርጎ አላቀረበም።
  4. መጥምቁ ዮሐንስ ለመሢሑ መንገድ ለማዘጋጀት የተላከ መልእክተኛ ነበር። ከመሢሑ ጋር ሲነጻጸር፣ መጥምቁ ዮሐንስ የመሢሑን የጫማ ክሮች ለመፍታት እንደማይገባው ባሪያ ነበር።

ለ. መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር በግ እንደሆነ መስክሯል (ዮሐ 1፡29-34)። እግዚአብሔር በመሢሑ ላይ መንፈስ ቅዱስን በርግብ አምሳል እንደሚያወርድ ለመጥምቁ ዮሐንስ ገልጾለታል። ምንም እንኳ ጥምቀቱ ተለይቶ ባይገለጽም፣ መጥምቁ ዮሐንስ ርግብ በኢየሱስ ላይ ሲወርድ አይቷል። ነገር ግን ዮሐንስ ኢየሱስ ከፖለቲካዊ መሢሕ በላይ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ስለዚህም ኢየሱስን «የእግዚአብሔር በግ» ሲል ጠርቶታል። ምሑራን ይህ ሐረግ ከብሉይ ኪዳን እንደ መጣ ቢያውቁም፣ ከየትኛው የብሉይ ኪዳን ክፍል እንደሆነ ይጠይቃሉ። ዮሐንስ አብርሃም ልጁን ለመሠዋት በሄደ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ስለሰጠው በግ (ዘፍጥ. 22፡1-14) መናገሩ ይሆን? ወይስ ይህ ለመሥዋዕትነት የሚቀርበውን የፋሲካ በግ (ዘጸ 12፡1-11፣ 21) የሚያመለክት ይሆን? ምናልባት በኢሳ 53፡7 የተጠቀሰውን በግ ያመለክት ይሆን? ዮሐንስ የትኛውን ለማመልከት እንደፈለገ በግልጽ ባናውቅም፣ የመሥዋዕቱ አሳብ ግን በሚገባ የሚታወቅ ነው። በብሉይ ኪዳን ለኃጢአት ስርየት በግ ዋነኛው መሥዋዕት እንደ ነበረ ሁሉ፣ ኢየሱስም ለሰው ልጆች ኃጢአት የሚሞት መሥዋዕት ነበር። የእግዚአብሔር ፍጹም መሥዋዕት እንደ ሆኑ፤ ኢየሱስ ለአይሁዶች ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ሁሉ ኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ይቀርባል።

ሐ. ከመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ሁለቱ ኢየሱስን ተከተሉ (ዮሐ 1፡35-51)። የኢየሱስ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት የመጡት ከየት ነበር? በገሊላ እርሱን ያገኙት ሰዎች ነበሩ? አልነበሩም። የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የመጡት ከመጥምቁ ዮሐንስ ነበር። ኢየሱስ ከተጠመቀ ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ ሲያልፍ ተመለከተ። ከዚያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ መለስ ብሎ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ኢየሱስ የእግዚአብሔር በግ እንደሆነ ነገራቸው። ቀደም ሲል ኢየሱስ ከእርሱ እንደሚልቅ ገልጾላቸው ነበር። በዚህም ጊዜ ከመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ሁለቱ ተከተሉት። የዮሐንስ ወንጌል ከእነዚህ የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መካከል የአንዱን ስም ብቻ ይነግረናል። እርሱም እንድርያስ ነው። ሁለተኛውስ ደቀ መዝሙር ማን ነበር? ምናልባትም ራሱ ሐዋርያው ዮሐንስ ላይሆን አይቀርም። በዚያኑ ዕለት እንድርያስ ወንድሙን ስምዖን ጴጥሮስን ወደ ኢየሱስ አመጣው። ጴጥሮስም የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ነበር። በመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት ምክንያት እንድርያስ ኢየሱስ ተራ ሰው ሳይሆን መሢሕ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር ሲገናኝ፣ ኢየሱስ ስሙን ኬፋ በማለት ለወጠው። የጴጥሮስ የመጀመሪያ ስሙ ስምዖን ነበር። ኢየሱስ ይህንን ስም ወደ ኬፋ (በአረማይስጥ) ወይም ጴጥሮስ (በግሪክ) ለወጠው። እነዚህ ሁለቱም ስሞች «ዓለት» የሚል ፍች አላቸው። ይህም ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ ጴጥሮስ ከዋንኞቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አንዱ እንደሚሆን ያመለክታል።

እንድርያስ ለሌሎች ለመመስከር ምሳሌ ሆነ። ምስክርነቱ የተወሳሰበ አልነበረም። ያደረገው ነገር ቢኖር ለወንድሙ ስለ ኢየሱስ በመናገር ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር እንዲገናኝ ማድረግ ነበር።

በቀጣዩ ዕለት ተጨማሪ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ መምጣት ጀመሩ። በመቀጠል ኢየሱስ ወደ ራሱ የጠራው ደቀ መዝሙር ፊልጶስ ነበር። ፊልጶስ ኢየሱስን በመከተል ላይ እንደ ነበሩት ሌሎች ደቀ መዛሙርት ሁሉ የገሊላ ሰው ስለነበር፣ እርሱም የመጥምቁ ዮሐንስ ተከታይ ሳይሆን አይቀርም። ፊልጶስ ናትናኤል የሚባል ሰው አገኘ። ፊልጶስ ኢየሱስ ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ፍጻሜ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ናትናኤል ኢየሱስ ከናዝሬት ገሊላ እንደመጣ ሲሰማ ጥርጣሬ አደረበት። ገሊላ ብዙም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ የማይታይባት ኋላቀር የእስራኤል ክፍል ነበረች። በእርሱ አስተሳሰብ መሢሑ ንጹሕና አጥባቂ አይሁዶች ከሚገኙበት የይሁዳ ክፍል መምጣት ነበረበት።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንድርያስና ፊልጶስ በዚህ ታሪክ ውስጥ የምስክርነት ምሳሌዎች ሆነው የቀረቡት እንዴት ነው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ምስክርነት የወንጌላውያን ኃላፊነት እንደሆነ አድርገው የሚያስቡት እንዴት ነው? ሐ) ይህ ክፍል ምስክርነት ከሁላችንም እንደሚጠበቅ የሚያሳየው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ከናትናኤል ጋር በተገናኘ ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ተራ ሰው ሳይሆን መለኮታዊ አምላክ እንደሆነ አሳይቷል። ይህንንም ያደረገው ከሰዎች ጋር በአካል ላይገናኝ ልባቸውን እንደሚያውቅ በመግለጹ ነው። ኢየሱስ ከዚህ በፊት ከናትናኤል ጋር ተገናኝቶ ባያውቅም፣ አምላክ ስለሆነ “እውነተኛ እስራኤላዊ” መሆኑን ተረድቶ ነበር። ይህም ናትናኤል በሥጋ ብቻ ሳይሆን በመንፈስም እስራኤላዊ ሰመሆን እግዚአብሔርን ይወድ እንደ ነበር ያመለክታል። ይህ ናትናኤልን አስደንቆታል። ከዚያ በኋላ ግን ኢየሱስ በአካል ባይኖሩም ሰዎች የሚያደርጓቸውን ነገሮች ለማወቅ እንደሚችል አሳይቶታል። ኢየሱስ ናትናኤል ከበለስ በታች ሲቀመጥ በሥጋዊ ዐይኑ ባይመለከትም፣ ሁሉን አዋቂ አምላክ በመሆኑ ይህ ችሎታ ነበረው። ይህ ችሎታ ናትናኤልን ስላስደነቀው በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት ሊመሰክር በቅቷል። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ከዚህ የሚበልጥ ታያለህ ሲል፤ ወደፊት ተጨማሪ ተአምራትን እንደሚያይ ገልጾአል።

ነገር ግን ኢየሱስ ለናትናኤል «ሰማይ ተከፍቶ መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያለህ» ሲል ምን ማለቱ ነበር? ይህ ለመረዳት የሚያስቸግር አገላለጽ ነው። አንዳንድ ምሑራን ምናልባት ናትናኤል ከዛፍ ሥር ተቀምጦ መላእክት ከሰማይ በመሰላል ሲወጡና ሲወርዱ የሚያሳየውን የአብርሃምን ሕልም ታሪክ እያነበበ ሳይሆን እንደማይቀር ይገምታሉ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እርሱ በሰማይና ምድር መካከል እንደ መሰላል የሚያገለግል መሆኑን እየተናገረ ነበር። ከእርሱ ጋር ባላቸው ግንኙነት፣ ተአምራቱን መመልከታቸው፣ ትምህርቱን መስማታቸውና ሞቱንና ትንሣኤውን መመልከታቸው የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢራት ሁሉ እንደ መረዳት ነበር። እንደ መንፈሳዊ መሰላል፣ ኢየሱስ እግዚአብሔርን ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸዋል። የደቀ መዛሙርቱንም ፍላጎቶች ለእግዚአብሔር ያስተላልፋል። ዮሐንስ በተጨማሪም ከእግዚአብሔር ርቃ ከተቅበዘበዘችው የቀድሞዋ እስራኤል (ያዕቆብ) በተቃራኒ ፍጹም እስራኤል እንደሆነ እያመለከተ ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: