መጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ኢየሱስ አመለከታቸው (ዮሐ. 3፡22-36)

ራስ ወዳድነት የምእመናን ብቻ ሳይሆን የመሪዎችም ሁሉ ትልቁ ችግር ነው። ሕይወታችንን የገዛው ራስ ወዳድነት ካልተወገደ በቀር ኢየሱስ የሚፈልገውን ዓይነት አመራር ተግባራዊ ልናደርግ አንችልም። ይህ ራስ ወዳድነት የተለያዩ ገጽታዎች አሉት። አንደኛው፥ አንድ መሪ የግል ጥቅሙን (ገንዘብ፥ ክብር) በሚፈልግበት ጊዜ፥ ራስ ወዳድነት ግላዊ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው፥ አንድ መሪ ከጠቅላላው የእግዚአብሔር ቤተሰብ ይልቅ የራሱን ቤተሰብ ወይም ጎሳ ለመጥቀም በሚፈልግበት ጊዜ፥ ራስ ወዳድነት ቤተሰባዊ ገጽታ ይይዛል። ሦስተኛው፥ እግዚአብሔር አንድን ሰው በሚባርክበት ጊዜ መሪው ኃይልን፥ ሥልጣንንና ክብርን በመሻት የቅንዓት ስሜት ሊያድርበት ይችላል። እነዚህ ሦስቱም ለቤተ ክርስቲያን መሪ አደገኛ መርዞች ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሦስት የራስ ወዳድነት ምሳሌዎች ቤተ ክርስቲያንን ሲያቆስሉ ያየህባቸውን እጋጣሚዎች ግለጽ። ለ) ለትክክለኛ መንፈሳዊ አመራር የሚበጀው አመለካከት የትኛው ነው?

በቅንዓትና በራስ ወዳድነት መንፈስ ሳይያዙ እንዴት ትክክለኛ አመራር መስጠት እንደሚቻል ለመገንዘብም ሆነ ለመማር መጥምቁ ዮሐንስ ጥሩ ምሳሌ ነው። መጥምቁ ዮሐንስ የኢየሱስ ዘመድ ነበር። ከኢየሱስ በዕድሜ የሚበልጥ ከመሆኑም በላይ አገልግሎቱንም የጀመረው ከእርሱ ቀድሞ ነው። ስለሆነም እንደ አይሁዶች ልማድና እንደ እኛም ግምት፥ ዮሐንስ ከኢየሱስ የበለጠ ክብር ይገባው ነበር። የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት፥ ኢየሱስ ከእርሱ የበለጡ ተከታዮችን እያፈራና አብዛኞቹም ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን እየተከተሉ መሆኑን ሲነግሩት፥ በቅንዓት ተይዞ የኢየሱስን አገልግሎት ለማደናቀፍ መሞከር ይችል ነበር። ዮሐንስ ግን ነገሮችን የሚመራው እርሱ ሳይሆን እግዚአብሔር እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ስለሆነም እግዚአብሔር እስከ ከበረ ድረስ በቅንዓትና በራስ ወዳድነት መንፈስ ከመነሣት ይልቅ ሌሎችን በአገልግሎታቸው ለማበረታታት ችሏል። መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ራሱና ስለ ኢየሱስ የተገነዘባቸውን ነገሮች አስተውል።

ሀ. እግዚአብሔር የነገሮች ሁሉ ምንጭ ነው። አንድ ሰው በቤተ ክርስቲያን ላለው ሥልጣን መንፈሳዊ ስጦታ፥ ተወዳጅነት፥ ስኬት ሁሉ ምንጩ እግዚአብሔር ነው። ሁሉም የሚመጣው «ከሰማይ» ነው።

ለ. መጥምቁ ዮሐንስ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ያለውን ስፍራ ያውቅ ነበር። ዮሐንስ “የሙሽራው ወዳጅ” እንደመሆኑ መጠን፣ የሙሽራው ማለትም የኢየሱስ ስኬት ተካፋይ መሆን እንዳለበት ያምን ነበር። ደስታው ኢየሱስ ሲከብርና እግዚአብሔርም የሰጠውን ተግባር ሲፈጽም ማየት ነበር። ምንም እንኳ የዮሐንስ አገልግሎት እያበቃና ተከታዮቹም እየቀነሱ ቢመጡም፥ ይህ ግን ለእርሱ ምኑም አልነበረም። ራሱ ዮሐንስ እንደተናገረው «እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባኛልና» ብሏል። መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ የመሢህነቱን ተግባር ሲያከናውን በመመልከቱ በደስታ ተሞልቷል። አንድ መሪ ሌላው ከእርሱ የበለጠ ሲወደድና ፍሬያማ ሲሆን ሲያይ ደስ ሊሰኝ የሚችለው ብስለት ሲኖረው ነው። አንድ መሪ ይህን ለማድረግ የሚችለው ለእርሱም ሆነ ለሌላው መሪ አገልግሎትንና ፍሬን የሚሰጥ እግዚአብሔር እንደሆነ ሲያስብ ብቻ ነው። ሁለቱም የሙሽራው , ወዳጆች በመሆናቸው በራሳቸው ሳይሆን በክርስቶስ ክብር ደስ ሊሰኙ ይገባል። የመንፈሳዊ መሪ ትልቁ ምኞት እርሱ ሳይሆን እግዚአብሔር ከብሮ ማየት ነው። እግዚአብሔር በወጣትና ይበልጥ ተወዳጅ በሆነ መሪ ሊተካው ሲፈልግ እንኳ፥ ይህንን መቀበል አለበት። ከሁሉም የሚልቀው የቤተ ክርስቲያን ዕድገትና የክርስቶስ መክበር ነውና።

ሐ. ኢየሱስ ክርስቶስ «ከላይ» ማለትም ከሰማይ ነው። እርሱ አምላክ ነው፤ ዮሐንስ ግን «ከምድር» ነው። በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ፥ ክርስቶስ ከሌላው ሰው መላቅና መከበር አለበት። አንድ መሪ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በመፈወሱ ምክንያት ሰዎች ከኢየሱስ ይልቅ እርሱን የሚመለከቱ ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው። አንድ መሪ ፍሬያማ ነው የሚባለው፥ ሰዎች ክርስቶስን እንዲመለከቱ ሲያደርግ ነው። የጀማ ስብከት የሚያካሂዱ ታዋቂ መሪዎችንና የፈውስ አገልጋዮችን ከምንመረምርበት መንገድ ውስጥ አንዱ፥ «እየከበረ ያለው ማን ነው? አገልጋዩ ነው ወይስ ክርስቶስ? ይበልጥ ታዋቂነትን እያገኘ ያለው ማን ነው?» ብለን በመጠየቅ ነው።

መ. እውነትን በትክክል መናገር የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው፤ ምከንያቱም እግዚአብሔርን ያየም ሆነ የመንግሥተ ሰማይን እውነቶች ሁሉ የሚያውቅ እርሱ ክርስቶስ ነው። የኢየሱስ ቃል የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ልንታዘዘው ይገባል። እግዚአብሔር ለማንም የሰው ልጅ ያልሰጠውን መንፈስ ቅዱስን በምልአት ለክርስቶስ ሰጥቶታል። እግዚአብሔር ክርስቶስን ስለሚወደው በምድር ላይ ሥልጣንን ሰጥቶታል።

ሠ. የሰው ልጆች ምርጫ ቀርቦላቸዋል። መጥምቁ ዮሐንስን ተቀበሉም አልተቀበሉም ይሄን ያህል ወሳኝ አይደለም፤ ነገር ግን ክርስቶስን ይቀበሉት ይሆን? ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ፥ ኢየሱስ ስለ ራሱ የሰጠውን ምስክርነት የተቀበሉ ጥቂቶች ናቸው። ይሁን እንጂ በታሪክ ሁሉ ውስጥ ከኢየሱስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ኢየሱስን በተመለከተ ትልቅ ልዩነት (መከፋፈል) ሆኖአል። ኢየሱስን የድነታቸው (የደኅንነታቸው) ምንጭ አድርገው ያልተቀበሉ ሰዎች፥ የእግዚአብሔርን ቁጣና ዘላለማዊ ቅጣት ይቀበላሉ። ነገር ግን ኢየሱስን የድነታቸው (የደኅንነታቸው) ምንጭ አድርገው የተቀበሉ ሰዎች፥ እግዚአብሔር ለዘላለም ለልጆቹ የሚሰጠውን ልዩ ሕይወት ያገኛሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዮሐንስ ስለ ራሱ አገልግሎት የነበረውን ግንዛቤና የድነትን (የደኅንነትን) ግልጽ መልእክት አብራራ። ለ) እንደ መሪዎች ይህን አሳብ መረዳታችንና እግዚአብሔር ለሌሎች እንድናካፍል የሚፈልገውን መልእክት በትክክል መረዳታችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? ሐ) ከመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት ለሕይወትህና በቤተ ክርስቲያንህ ላለህ አገልግሎት ልትጠቀምባቸው የምትችላቸውን ነገሮች ዝርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “መጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ኢየሱስ አመለከታቸው (ዮሐ. 3፡22-36)”

  1. I really enjoyed the reading and the questions. I came across this reference as I was searching google engine to know the names of disciples of John the Baptist.

Leave a Reply

%d bloggers like this: