፩. ክርስቶስ አምስት ሺህ ሰዎችን መገበ (ዮሐ 6፡1-15)
ዮሐንስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለማረጋገጥ የጠቀሰው አራተኛው ምልክት፥ ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን መመገቡን ነው። ይህ በአራቱም ወንጌላት ውስጥ ከተጠቀሱት ጥቂት ተአምራት መካከል አንዱ ነው። ይህም ተአምሩ ደቀ መዛሙርቱን በጣም እንዳስደነቃቸው የሚያመለክት ነው። ይህ «ምልክት» ስለ ክርስቶስ ምን ያስተምራል? እራት መልእክቶች ያሉት ይመስላል፡-
- አንደኛው፥ ክርስቶስ የሥነ ፍጥረት ጌታና መሪ፥ ነገሮችንም ቢሆን ለማብዛት ይችላል።
- ሁለተኛው፥ ክርስቶስ ዳግማዊው ሙሴ ነው። እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ከሰማይ መና እንዳዘነበ ሁሉ፥ በክርስቶስም አማካይነት ለሰዎች ምግብ ሰጥቷል። (ማስታወሻ፡- አይሁዶች ሙሴን የሚመለከቱት መና እንዳወረደላቸው አገልጋይ ነበር።) ምንም እንኳ ሙሴ መና ለማውረድ በመሣሪያነት ያገለገለ ቢሆንም፥ ክርስቶስ ግን በቀጥታ ለሕዝቡ ምግብ ሰጥቷል። አይሁዶች መሢሑ ለሕዝቡ ውኃ እንደሚሰጥ የሚናገር ታሪክ እንደነበራቸው ሁሉ፥ መሢሑ ሕዝቡን ለመመገብ መና ያወርዳል የሚልም አባባል ነበር። ዮሐንስ ምናልባትም ክርስቶስ ሕዝቡን በመመገብ እንዴት የተለየ መና እንደሰጣቸው እያመለከተ ይሆናል። ሕዝቡ ከዚህ ተአምር በኋላ ክርስቶስን ለማንገሥ የፈለጉት በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።)
- ሦስተኛው፥ የዘላለም ሕይወትን ምግብ የሚሰጠው ኢየሱስ ነው። በዮሐንስ 4፣ ውኃ የዘላለም ሕይወት ተምሳሌት ሆኖ እንደ ቀረበ ሁሉ፥ በዚህ ክፍል ምግብ ክርስቶስ በእርሱ ለሚያምኑት የሚያሰጠውን የዘላለም ሕይወት ያመለክታል።
- አራተኛው፥ ዮሐንስ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ለምንም ነገር መጨነቅ እንደሌለባቸው አስተምሯል። ክርስቶስ ደግሞ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች በቀላሉ ምግብ እንደ ሰጣቸው ሁሉ፥ ለእኛም በየዕለቱ የሚያስፈልገንን ይሰጠናል።
ይህ ተአምር ደቀ መዛሙርቱን ብቻ ሳይሆን አይሁዶችንም አስደንቋል። ከፈውስ ወይም አጋንንትን ከማውጣት በላይ፥ ይህ ተአምር አይሁዶች ክርስቶስን ለማንገሥ እንዲነሣሡ አድርጓቸዋል። ነገር ግን በኢየሱስ ላይ የነበራቸው እምነት በራስ ወዳድነት የተሸነፈ ነበር። ሥጋዊ ፍላጎታቸውን እስካሟላላቸው ድረስ በንጉሥነቱ ጥላ ሥር ለመኖር ፈቃደኞች ነበሩ። ነገር ግን ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲሆኑ በሚጠይቃቸው ጊዜ፥ እምነታቸው አብሯቸው ይኖራል? ኢየሱስ አንዳንድ ለመረዳት የሚያስቸግሩ አሳቦችን መናገር በሚጀምርበት ጊዜ፥ ኢየሱስን ለማንገሥ የነበራቸውን አሳብ ለውጠው እንደ ተቃወሙት በዚህ ክፍል ውስጥ እንመለከታለን (ዮሐ 6፡66)። ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን የተመለከተው የክርስቶስ ዝና ከመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ አድርጎ ነው። ትክክለኛ እምነት በእርሱ ላይ ባይኖራቸውም ብዙ ሕዝብ ይከተለው ነበር። ይህ የራስ ወዳድነት እምነታቸው በጥቂት ወራት ውስጥ ይጠፋል። ክርስቶስ የመጣው የሰዎችን የራስ ወዳድነት ፍላጎት እንደሚያሟላ ንጉሥ ሆኖ አይደለም። እርሱ የመጣው የመንፈሳዊና የሥጋዊ ሕይወታቸው ንጉሥ ለመሆን ነው። ስለዚህም ኢየሱስ ሕዝቡን ትቶ ሄደ።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት የራስ ወዳድነት እምነት ይዘው ክርስቶስን የምንከተለው ሥጋዊ ፍላጎቶቻችንን እስካሟላ ድረስ ብቻ ነው የሚሉበትን ሁኔታ፥ ምሳሌ በመስጠት አብራራ። ለ) ብዙውን ጊዜ የዚህ ዓይነቱ እምነት ከጥቂት ጊዜ በኋላ ምን ይሆናል? ሰዎች በእምነታቸው ይገፋሉ? መልስህን አብራራ።
፪. ክርስቶስ በውኃ ላይ ተራመደ (ዮሐ 6፡16-24)።
ይህ አምስተኛው የክርስቶስ ምልክት በሁሉም ወንጌላት ውስጥ ተጽፎአል። ዮሐንስ ይህን ተአምር በተመለከተ የተናገረው ብዙ ነገር የለም። በዚህ ክፍል የጠቀሰው ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን በመመገቡ ምክንያት በኢየሱስና በአይሁድ መካከል የተከሰተውን ውይይት ከመጥቀሱ በፊት ነው። ይሁንና፥ ይህ ተአምር ክርስቶስ ተፈጥሮን ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠር ያሳያል። ክርስቶስ የስበትን ሕግ ሽሮ ልክ በደረቅ መሬት ላይ እንደሚራመድ ሰው በውኃ ላይ መራመዱ ብቻ ሳይሆን ነፋሳትን፥ ማዕበሎችንና ሞገዶችን ሁሉ ጸጥ ማሰኘት ይችላል። ይህም ኢየሱስ በየትኛውም የሕይወታችን ማዕበል ውስጥ እንደሚገኝ ያሳያል። በክርስቶስ እስካመንንና ማዕበላችንን ጸጥ እንዲያደርግልን እስከለመንነው ድረስ ሰላም ይኖረናል። ይህ ውጫዊ ስደቶቻችንን፥ ሕመማችንንና ሞታችንን ጸጥ ላያደርገው ይችላል፤ ይሁንና ከእምሮ በላይ የሆነ ውስጣዊ ሰላም ይኖረናል። ምክንያቱም የክርስቶስ ተከታይ የሆነ አማኝ፥ ክርስቶስ ማዕበልን እንደሚቆጣጠርና ውጤቱንም እንደሚወስን ያውቃል።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)