ኢየሱስ በዳስ በዓል ላይ ያስተማረው ትምህርት (ዮሐ. 8፡12-59)

በዮሐንስ 7 እና 8 በክርስቶስና በአይሁድ መካከል የተፈጠረው ትግል ተጠናክሮ ቀጥሏል። እነዚህ ሁለቱ ምዕራፎች ያካተቷቸው አሳቦች የተፈጸሙት ክርስቶስ የዳስ በዓልን ለማክበር በኢየሩሳሌም በነበረበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።

ሀ. ክርስቶስ የዓለም ብርሃን ነው (ዮሐ 8፡12)። የዳስ በዓሉ አከባበር በተምሳሌታዊ ተግባራት የተሞላ መሆኑን ቀደም ብለን ተመልክተናል። ክርስቶስ ሕያው ወንዝ መሆኑን የገለጸው በመሠዊያው ላይ ውኃ ሲፈስ በመመልከቱ ላይሆን አይቀርም። በዚህ በዓል ጊዜ የተፈጸሙ ሌሎች ሁለት ዐበይት ነገሮች ነበሩ። አንደኛው፥ የዓለም ሕዝቦችን የሚወክሉ 10 ልዩ ኮርማዎች የሚታረዱበት ጊዜ ነበር። ይህም መሢሑ በአሕዛብ ላይ በረከቱን እንደሚያፈስ ያሳያል። ሁለተኛው፥ የሁለት ታላላቅ መቅረዞች መብራት ነበር። የአይሁድ አፈታሪክ እንደሚናገረው፥ ሁለቱ ታላላቅ ሻማዎች ቁመታቸው ከ20 ሜትር በላይ ሲሆን፥ ከቤተ መቅደሱ ግራና ቀኝ የሚበሩ ነበሩ። ከእነዚህ ሻማዎች የሚወጣው ብርሃን ደማቅ በመሆኑ፥ የኢየሩሳሌም ከተማ ነዋሪዎች ብርሃኑን ከሩቅ ያዩት ነበሩ። ይህ ብርሃን ከቤተ መቅደሱ (ከእግዚአብሔርን የሚወጣውን የእውነት ብርሃን በተምሳሌነት ያመለክታል። ምናልባት ክርስቶስ፥ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» ሲል የተናገረው እነዚህን ታላላቅ ሻማዎች እየተመለከተ ሳይሆን አይቀርም። ይህም ክርስቶስ «እኔ ነኝ» የሚለውን ቃል ሲናገር ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ሙሴ፥ መሐመድ፥ ቡድሃ ወይም ሌላ ማንኛውም መሪ እንዲህ የመሰለውን ቃል መናገር አይችልም። የመንፈሳዊ ሕይወት ብርሃን ክርስቶስ ብቻ ነው። ደግሞም ድነት (ደኅንነት) ሊገኝ የሚችለው ወደ ክርስቶስ በመምጣት ብቻ ነው።

ለ. ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ እግዚአብሔር አብ በቂ ምስክር ነው (ዮሐ 8፡13-18)። ፈሪሳውያን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚያረጋግጡ ምስክሮችን እንዲያቀርብ ጠየቁት። ታዲያ ክርስቶስ ምስክሮችን ሊያቀርብ የሚችለው ከየት ነው? ቀደም ሲል መጥምቁ ዮሐንስ ለዚህ ምስክር እንደ ሆነ ገልጾአል። ነገር ግን መጥምቁ ዮሐንስ ውስን ነው፤ የሚያውቀው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር የነገረውን ብቻ ነበር። ክርስቶስን በሰማይ በሙሉ ክብሩ አላየውም። ስለሆነም፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በብቃት መመስከር የሚችሉት እግዚአብሔርና ራሱ መሆናቸውን ገለጸ። ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የነበረውን መለኮታዊ ክብር የሚያውቁት አብና እርሱ ብቻ ናቸው።

ሐ. ሰዎች በክርስቶስ ካላመኑ በኃጢአታቸው ይሞታሉ (ዮሐ 8፡19-26)። ክርስቶስ አይሁድ እርሱን በተመለከተ ስለሚናገሩት ነገር ሁሉ አስጠንቅቋቸዋል። አይሁዶች በእግዚአብሔር እንደ ተላከና የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ካላመኑ፥ የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ከሆነው እግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው አይችልም። እግዚአብሔር አብንና ወልድን ማመንና ማምለክ የግድ አስፈላጊ ነው። ከሁለት አንዱን ብቻ ማመን በጣም በቂ አይደለም። ኢየሱስን የማይቀበሉ ከሆኑ የእንስሳት መሥዋዕት ቢያቀርቡም እንኳ፥ የኃጢአትን ይቅርታ ማግኘት አይችሉም። ከኃጢአታቸው ሊያነጻቸው የሚችለው የክርስቶስ መሥዋዕት ብቻ ነውና።

መ. ክርስቶስ በመስቀል ላይ ይሰቀላል (ዮሐ 8፡27-30)። በዚያን ጊዜ መንፈሳዊ ዓይን ያሏቸው ሰዎች ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ይገነዘባሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ እውን ለማድረግ ማለትም ለኃጢአታችን ለመሞት ወደ ምድር የተላከ መሆኑን ይረዳሉ።

ሠ. ክርስቶስ ሰዎችን ነፃና እውነተኛ የአብርሃም ልጆች ያደርጋቸዋል (ዮሐ 8፡31-41)። ዮሐንስ፥ ክርስቶስ ይህንን የተናገረው በእርሱ ለሚያምኑት እንደሆነ ገልጿል። እርሱን ለመግደል ጊዜ ይጠብቁ ስለ ነበር፥ ኢየሱስ ይህንን የተናገረው እውነተኛ አማኞች ላልሆኑት ሳይሆን አይቀርም። ክርስቶስ ለእነዚህ ሰዎች እምነታቸው ምን እንደሚያስከትል ተናግሯል። ክርስቶስን መከተል ማለት ትምህርቱን መስማትና መታዘዝ መሆኑን ገልጾአል። በዚህ ጊዜ ተከታዮቹ ከሕይወታቸው ኃጢአትን በማስወገድ እግዚአብሔርን እርሱ እንደሚፈልገው ለማምለክ ዝግጁዎች ይሆናሉ። (ማስታወሻ፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ነጻነት ማለት የምንፈልገውን ልናደርግ እንችላለን ማለት አይደለም።) ነፃ መውጣት ማለት ከሰይጣን አዛዝ መፈታትና እግዚአብሔር አስቀድሞ ወዳቀደልን መንገድ መመለስ ነው። ይህም እግዚአብሔርን መታዘዝ፥ ማምለክና መውደድ ነው።)

ረ. ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ያላቸው ግንኙነት መንፈሳዊ አባታቸው ማን እንደ ሆነ ያሳያል (ዮሐ 8፡42-47)። ክርስቶስ የአንድ ሰው መንፈሳዊ አባት ማን መሆኑን የሚለይ ድንበር እንደ ሆነ አስተምሯል። ሁለት መንፈሳዊ አባቶች አሉ። እነዚህም፥ የማያምኑ ሰዎች አባት የሆነው ሰይጣንና የአማኞች አባት የሆነው እግዚአብሔር ናቸው። አይሁዶች ክርስቶስን ለመቀበል ባለመፈለጋቸው አባታቸው ሰይጣን እንደ ሆነ እያመለከቱ ነበር። (ማስታወሻ፥ «እኛ ዲቃላዎች አይደለንም» የሚለው የአይሁዶች ንግግር ክርስቶስ የዮሴፍና ማርያም ዲቃላ ነው የሚል አንድምታ ሊያስተላልፍላቸው ይችላል።) ክርስቶስ የአይሁድ መሪዎች ሊገድሉት እንደቆረጡ ያውቅ ነበር። ነገር ግን አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ወደ ምድር በተላከው ክርስቶስ ካመነ፥ ያ ግለሰብ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል። ምክንያቱም እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ያዘጋጀውን የሕይወት ስጦታ ስለተቀበለ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ይኖረዋል።

ሰ. አይሁዶች ክርስቶስ አጋንንት እንዳለበት ተናገሩ (ዮሐ. 8፡48-59)። ኢየሱስ ስብከቱን በቀጠለ ቁጥር የአይሁዶች ቁጣ እየከረረ ሄደ። በመሆኑም፥ በሚጠሏቸው ሰዎች ስም «የሰማርያ ሰው» እያሉ ይሳለቁበት ጀመር። ከዚህም በላይ አጋንንት አለብህ አሉት። ክርስቶስ ግን ከእነርሱ እንዴት እንደሚለይ ገለጸላቸው። ከእነርሱ ለሚመጣው ምስጋናም ሆነ ክብር ግድ አልነበረውም። አለዚያ ባሕርዩንና ተግባሩን በመለወጥ አይሁዶች እንዲከተሉት ሊያደርግ ይችል ነበር። ነገር ግን የእርሱ ፍላጎት እግዚአብሔርን ማስከበር በመሆኑ፥ ዓላማው በሚያደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ነው። እርሱ እግዚአብሔርን እያስደሰተ ስለሆነ፥ ሕይወታቸውን ከክርስቶስ ጋር ያስተካከሉ ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ይችላሉ። ደግሞም የዘላለም ሕይወት ይኖራቸዋል። ክርስቶስን ያልተቀበሉ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት የላቸውም።

እንደ ዳዊት፥ ሙሴና አብርሃም የመሳሰሉ ታላላቅ የብሉይ ኪዳን ሰዎች ሞተዋል። ታዲያ ክርስቶስ ሕይወት ለመስጠት እችላለሁ በማለት የሚናገረው ከምን የተነሣ ነው? አይሁዶች ክርስቶስ ከአብርሃም እበልጣለሁ እያለ እንደሆነ ጠየቁት። ምናልባትም ይህንን ጥያቄ ያቀረቡለት አሉታዊ ምላሽ በመጠበቅ ነበር። ክርስቶስ ግን አባታቸው አብርሃም የእርሱን ቀን በማየት ደስ እንደተሰኘ ገለጸላቸው። ከዚያም አሳቡን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ፥ አብርሃም ከመወለዱ በፊት ኢየሱስ «እኔ ነኝ» በማለት ይኖር እንደነበረ ተናገረ። እንዲህ በማለት ለመናገር የሚችለው የብሉይ ኪዳኑ ዘላለማዊ አምላክ ብቻ ነው አይሁድ በዚህ ንግግሩ እጅግ በመቆጣታቸው ወዲያውኑ ሊገድሉት ተነሡ። ነገር ግን ክርስቶስ ጊዜው ስላልደረሰ አመለጣቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- በዚህ ክፍል ከቀረበው የክርስቶስ ትምህርት ስለ ድነት (ደኅንነት) ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: