ከመወለዱ ጀምሮ ዓይነ ስውር የነበረ ሰው መፈወስ (ዮሐ. 9:1-41)

ጌታሁንና ጽጌ ከተጋቡ ብዙ ዓመታት ቢሆናቸውም ልጆች ግን አልወለዱም። ጽጌ ብዙ ጊዜ ብታረግዝም፥ ልጁ ከመወለዱ በፊት ይሞታል። እንዲህ የመሰለውን ገጠመኝ ስናይ «ኃጢአት» የሠራው ማን ነው? ጌታሁን ወይስ ጽጌ?» በማለት እንጨነቃለን። ወርቅነሽ መንፈሳዊ ሴት ናት። አንድ ቀን ግን በጠና ታመመችና ለ10 ዓመት ያህል የአልጋ ቁራኛ ሆነች። አሁንም ታዲያ «ኃጢአት የሠራው ማን ነው?» ብለን እናስባለን። አንድ ክፉ ነገር በክርስቲያን ላይ በሚደርስበት ጊዜ ብዙዎቻችን የምንሰጠው መልስ ኃጢአት እንደ ተፈጸመ የሚገልጽ ነው። ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች ባለማቋረጥ ኢዮብን ኃጢአት ሠርተሃል እያሉ ይነዘንዙት ነበር። ነገር ግን ኃጢአት አንዱ ምክንያት ብቻ ነው። እግዚአብሔር የኢዮብ ወዳጆችን ስለተሳሳተው አሳባቸው እንደ ገሠጻቸው ሁሉ፥ እኛም በማናውቀው ምክንያት ስለሆነው ነገር ዝም ብለን ብንናገር ይገሥጸናል።

የውይይት ጥያቄ፡- አንተ ወይም አንተ የምታውቀው ሌላ ሰው በፈጸማችሁት ኃጢአት የእግዚአብሔርን ፍርድ እየተቀበላችሁ ነው በሚል ተወቅሳችሁ ታውቃላችሁ? ወቀሳው እውነት ነበር? ካልሆነስ በሐሰት የቀረበው ወቀሳ ምን ችግር አስከተለ?

ሀ. ክርስቶስ ዓይነ ስውሩን ሰው ፈወሰ (ዮሐ. 9፡1-12)። እንደ እኛ ሁሉ፥ አይሁዶችም በሰዎች ላይ በሚደርሰው በጎም ሆነ ክፉ ነገር መካከል ቀጥተኛ መንሥዔና ውጤት እንዳለ ያስቡ ነበር። ደግ ሰው ከሆንህ፥ እግዚአብሔር በቁሳዊ ነገሮች ይባርክሃል። መጥፎ ሰው ከሆንህ፥ እግዚአብሔር ይቀጣሃል። በሌላ አነጋገር መልካም ነገሮች ካጋጠሙህ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት አለህ ማለት ነው። ነገር ግን አንድ መጥፎ ነገር ከደረሰብህ፥ ኃጢአት ሠርተሃል ማለት ነው። ደቀ መዛሙርቱ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ሲመለከቱት አንድም ወላጆቹ ወይም ራሱ ከመወለዱ በፊት ኃጢአት እንደ ሠራ አሰቡ።

ክርስቶስ ግን ነገሮችን የተመለከተው በተለየ መንገድ ነበር። እግዚአብሔር ተግባሩን አከናውኖ እስኪፈጽም ድረስ ሰዎች የማያስተውሉት ስውር ዓላማ አለው። ስለሆነም፥ ዕውር ሆኖ የተወለደው ሰው እግዚአብሔር የሚከብርበት መሣሪያ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ማን ኃጢአት እንደ ሠራ ከመጠየቅ ይልቅ፥ ለእግዚአብሔር ክብር የሚያገለግሉ ገጠመኞች እንዳሉ ሊያስቡ ይገባ ነበር። ክርስቶስ ከስቅለቱ፥ ከትንሣኤውና የምድር አገልግሎቱን ከሚዘጋው ከዕርገቱ በፊት ጥቂት ሳምንታት ብቻ ቀርተውት ነበር። ለደቀ መዛሙርቱ ቀኑ በሕይወት የሚኖሩበት ጊዜ ብቻ ነበር። እያንዳንዱ ቀን ለእግዚአብሔር ክብር የምንቆምበት መልካም ዕድል ነው። ሞት በሚመጣበት ጊዜ የሥራ ዘመናችን ያከትማል።

ምንም እንኳ በመልካም ሰዎች ላይ መጥፎ ነገር ለምን ይደርሳል ብለን ብንጨነቅም፥ መጽሐፍ ቅዱስ (እግዚአብሔር) ምክንያቱን አልገለጸልንም። ዋናው ጉዳይ ለጥያቄአችን መልስ ማግኘቱ አይደለም። ምክንያቱም ይህ በእግዚአብሔር ዓላማ ምሥጢር ውስጥ ተሰውሯል። ስለሆነም፥ ጥያቄአችን መሆን ያለበት በዚህ ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔርን እንዴት ላስከብረው እችላለሁ?» ነው። አንድ ቀን አንዲት ወጣት ልጅ ስትዋኝ ሳለ ከድንጋይ ጋር በመጋጨቷ አንገቷ ተሰበረ። ይህች ልጅ ከአንገቷ በታች ሙሉ በሙሉ፥ ሽባ ሆነች። ወደ እግዚአብሔር ብትጸልይም ተአምራዊ ፈውስ ልትቀበል አልቻለችም። ዛሬም ሽባ እንደሆነች ናት። ነገር ግን የደረሰባትን ነገር ለእግዚአብሔር ክብር እንዲሆን ወሰነች። እግዚአብሔርም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሰስዎች ተስፋ እንድትሆን ፈቀደ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በእንተ ወይም በሌሎች ክርስቲያኖች ላይ የደረሱ ክፉ ነገሮችን ዘርዝር። ለ) ክፉ ነገሮች ለእግዚአብሔር ክብር ይውላሉ ብለህ የምታስባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ሐ) ለክፉ ሁኔታዎች ትክክለኛ አመለካከት ከሌለኝ፥ እግዚአብሔርን ለማክበር የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች ልናጣ የምንችለው እንዴት ነው?

እግዚአብሔር ክርስቶስን ለማስከበር በዓይነ ስውሩ ተጠቅሞአል። የዓይነ ስውሩ መፈወስ ስድስተኛው የክርስቶስ «ምልክት» ነበር። ይህ ተአምር ኢየሱስ ሰዎች ለማየት እንዲችሉ የሚያደርግ የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ ሳይሆን፥ የዓለም ብርሃን መሆኑንም ያስተምራል። እርሱ ሥጋዊ ዕውርነትን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ዕውርነትንም ጭምር የሚያስወግድ አምላክ ነው።

ለ. ፈሪሳውያን የዓይነ ስውሩን ፈውስ መረመሩ (ዮሐ 9፡13-41)። ሁለት ዓይነት ዓይነ ስውርነቶች አሉ፡- ሥጋዊና መንፈሳዊ። ኢየሱስ በሥጋው ዕውር የሆነውን ሰው ፈወሰ። ይሁንና እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የማይቀበሉ በመንፈስ ዕውር የሆኑ ሰዎች ገጠሙት። ለእግዚአብሔር ቀላሉ ነገር በመንፈስ ዕውር የሆኑ ሰዎችን መፈወስ ሳይሆን በሥጋ ዕውር የሆኑ ሰዎችን መፈወስ ነው።

ዮሐንስ የተለያዩ ሰዎች፥ በተለይም ፈሪሳውያን ስላዩት ተአምር የሰጡትን ምላሽ እንድናይ ይጋብዘናል። አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ ደግ ሰው እንደ ሆነ ሲያስቡ፥ ሌሎች ደግሞ ነቢይ እንደ ሆነ ያስቡ ነበር። ዓይነ ስውሩ ሰው ግን ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ተላከ እርግጠኛ ነበር። እንዲያውም፥ ከፈሪሳውያን ጋር በጉዳዩ ላይ ሲነጋገር እምነቱ እየጠነከረ ሄደ። የዓይነ ስውሩ ሰው ወላጆች የሚደርስባቸውን ስደት በመፍራት ለመመስከር አልፈለጉም። ፈሪሳውያን በበኩላቸው ክርስቶስ ኃጢአተኛ እንጂ መሢሕ አይደለም የሚል አሳብ ነበራቸው። በስተመጨረሻ ግን መንፈሳዊ መሪዎች ነን ከሚሉት ይልቅ ከዓይነ ስውርነቱ የተፈወሰው ሰው መንፈሳዊ ነገሮችን ለማየት ቻለ። ክርስቶስ ኃጢአተኛ ወይም ክፉ ቢሆን ኖሮ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሊሆን እንደማይችልና የፈውስ ኃይልም እንደማይሰጠው ተናገረ። ይህ ሰው ሥጋዊ ፈውስ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ፈውስ ተቀበለ። ከዚያም ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ተልኮ እንደ መጣ ያስተውል ዘንድ፥ ዓይኑን ከፈተለት፤ ቀድሞ ዕውር የነበረው ሰው አሁን ሰገደለት።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ የሃይማኖት መሪዎች ለእግዚአብሔር አሠራር ዕውር ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው? ለ) የክርስቶስን ሥራ ባናምን መንፈሳዊ ዕውሮች ስለምንሆን የእግዚአብሔርን እውነት ለመረዳት አስቸጋሪ የሚሆንብን እንዴት እንደሆነ ነው ከዚህ ታሪክ የምንረዳው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: