ክርስቶስና በዝሙት የተያዘች ሴት (ዮሐ. 8፡1-11)

ተመስገን የአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ነው። አንድ ቀን አንዲት የኳየር ዘማሪ የሆነች ወጣት ወደ እርሱ መጥታ ማርገዟን ገለጸችለት። ተመስገን በነገሩ በጣም ተናደደ። «የቤተ ክርስቲያናችንን ስም ያጠፋሽ ኃጢአተኛ ሴት ነሽ። እኛ እንዳንቺ ዓይነቷን ሴት አንፈልግም» አላት። ልጅትዋ በኃፍረት ተሸማቅቃ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ወጥታ ሄደች። ክርስቲያን የነበሩት ወላጆቿም በእርግዝናዋ ስላፈሩ ከቤታቸው ለቅቃ እንድትሄድ አስገደዷት። መሄጃ ስፍራ ስላጣች በጎዳና ላይ ትንከራተት ጀመር። ከዚያም ለራሷና ለልጇ የመተዳደሪያ ገንዘብ ለማግኘት ስትል እምነቷን ትታ ወደ ሴተኛ አዳሪነት ገባች።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዮሐ 8፡1-11 አንብብ። ኢየሱስ ለሴቲቱ ያደረገውን፥ ተመስገን ለኳየር ዘማሪዋ ካደረገው ጋር አነጻጽር። የሰዎቹ ተግባር የሚለያዩት ወይም የሚመሳሰሉት እንዴት ነው? ለ) ለኳየር ዘማሪዋ ክርስቶስ ምን ዓይነት ምላሽ የሚሰጣት ይመስልሃል? ሐ) እንደ ተመስገን ዓይነት መጋቢዎች እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሊገጥማቸው ምን እንዲያደርጉ ትመክራቸዋለህ? በኃጢአት ላይ ያለህን ጥብቅ አቋም ሳትለውጥ፥ ምሕረትን፥ ይቅርታንና ፍቅርን የምታሳየው እንዴት ነው?

ብዙ ምሑራን ዮሐንስ 7፡53-8፡11 ያለው ክፍል የዮሐንስ ወንጌል የመጀመሪያ ቅጅ አካል ነው ብለው አያምኑም። በርካታ የዮሐንስ ወንጌል የጥንት ቅጆች ይህን ክፍል አይጨምሩም። ይህን ክፍል ብንዘለው ታሪኩ ከ7፡52 ወደ 8፡12 ምንም ሳይደናቀፍ ይቀጥላል። ይህም በመገናኛው ድንኳን በዓል ጊዜ የተነገረ አሳብ ነው። ይህ የአመንዝራይቱ ሴት ታሪክ ለምን በዚህ ስፍራ እንደገባ ባናውቅም፥ ፈሪሳውያን ክርስቶስን ለማጥመድ በሚፈልጉበት ጊዜ የተከሰተ እውነተኛ ታሪክ ሳይሆን አይቀርም።

አንድ ቀን ክርስቶስ በቤተ መቅደስ እያስተማረ ሳለ፥ የሃይማኖት መሪዎች በምንዝር የተያዘች ሴት አስከትለው ደረሱ። ይህንንም ያደረጉት ክርስቶስን ለማጥመድ አስበው ነበር። በሴቲቱ ላይ ባይፈርድ፥ በዝሙት የተያዙ ሰዎች ተወግረው መሞት እንዳለባቸው የሚያዘውን የብሉይ ኪዳን ሕግ በመተላለፉ (ዘዳግ 22፡22-24፤ ዘሌዋ 20፡10) ሊከሱት ሆነ። ባንጻሩ በሴቲቱ ላይ በመፍረድ እንድትወገር ቢያደርግ፥ የብዙ ሰዎችን ወዳጅነት ያጣ ነበር። በተለይም ይከተሉት የነበሩትን «የኃጢአተኞችና የቀራጮችን» ወዳጅነት ያጣ ነበር። ሮማውያን፥ አይሁዶች የሞት ቅጣት እንዲበይኑ አይፈቅዱላቸውም፡፡ ስለሆነም፥ ሴቲቱ ተወግራ እንድትሞት ቢያደርግ ኖሮ የሮም መንግሥት ይቀጣው ነበር፡፡

እነዚህ ፈሪሳውያን የእግዚአብሔር ሕዝብ ጻድቃን ሆነው እንዲኖሩ ከልባቸው የማይፈልጉ መሆናቸው ግልጽ ነው። የሙሴ ሕግ የተሰጠው ግን ሕዝቡ በጽድቅ እንዲኖር ለመርዳት ነበር። አለዚያ ከሴቲቱ ጋር ዝሙት የፈጸመውንም ሰውዩ በያዙት ነበር። በእግዚአብሔር ፊት፣ ዝሙትን መፈጸም ለወንድም ሆነ ለሴት ኃጢአት ነው። ወንዱ ሰውዬ የት ነበር? አንዳንዶች ወንዱ ሰውዩ ከፈሪሳውያን አንዱና ክርስቶስን ለማጥመድ ሲል ሴቲቱን የተጠቀመ ነው ይላሉ። የሚወገሩት ዝሙት ሲፈጽሙ የተገኙት ብቻ በመሆናቸው፥ ቢያንስ ፈሪሳውያን ሰውየውን ያውቁት ነበር። መሪዎቹ ምንም ዓይነት ርኅራኄ አልነበራቸውም። አለዚያ ክርስቶስን ሰው ወደሌለበት ስፍራ ወስደው ስለ ሴቲቱ ጉዳይ ሊያማክሩት ይችሉ ነበር። ሴቲቱ በትዕቢተኛ ሃይማኖተኞች መካከል የተገኘች መሣሪያ ነበረች።

በመጀመሪያ ክርስቶስ ምንም አልተናገረም። ነገር ግን በመሬት ላይ አንድ ነገር ይጽፍ ጀመር። ምን ይሆን የጻፈው? ከሴቲቱ ጋር ዝሙት የፈጸመውን ሰውዩ ስም ይሆን የጻፈው? ሴቲቱን ለመውገር የቆሙትን ፈሪሳውያን ኃጢአት ይሆን የዘረዘረው? ምንም የምናውቀው ነገር የለም። ከዚያም ኃጢአት ሠርቶ የማያውቅ ሰው፥ በሴቲቱ ላይ የመጀመሪያውን ድንጋይ እንዲወረውር ጠየቃቸው። ይህን በማለቱ ክርስቶስ የብሉይ ኪዳንን ሕግ እየደገፈ ነበር። ነገር ቀን ኃጢአት ሠርቶ የማያውቅ ሰው እንዲወግራት በመጠየቁ ማንም ሰው እንዳይወግራት እየተከላከለላት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዘንድ ትልቅ ስፍራ ያለው ምሕረትና ይቅርታ እንጂ፥ በትምክህት የተሞላ ፍርድ እንዳልሆነ እያስተማራቸው ነበር። ከዚያም ኢየሱስ መሬት ላይ ተመልሶ ይጽፍ ጀመር። የጻፈው ነገር መሪዎቹን ስላሳፈራቸው አካባቢውን ጥለው ሄዱ። ሴቲቱ ብቻ በክርስቶስ አጠገብ እንደ ቆመች ቀረች።

ክርስቶስ የፍቅር አምላክ እንደ መሆኑ፥ ለዚህች ኃፍረት ላሸማቀቃት ሴትት የፍቅር እጁን ዘረጋላት። በተጨማሪም፥ እግዚአብሔር ኃጢአትን ዝም ብሎ የማያልፍ ቅዱስ አምላክ ነው። ይህች ሴት አጥፍታለች። ምን ይባላት? በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ ሊፈርድባት አልፈለገም። ሁለተኛ፥ በኃጢአት እንድትቀጥልም አልፈለገም። ስለሆነም፥ ሕይወቷን እንድትለውጥ ነገራት። እንደ ክርስቶስ እኛም ኃጢአተኞችን መውደድና መቀበል አለብን። ይህ ማለት ግን ከኃጢአት ሕይወታቸው ጋር እንስማማለን ማለት አይደለም። በሕይወታቸውና በእምነታቸው እግዚአብሔርን ያከብሩ ዘንድ የንጽሕናን ሕይወት እንዲኖሩ መርዳት አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ትልቅ ኃጢአት ፈጽመዋል በሚባሉ ሰዎች ላይ ክርስቲያኖች የሚናገሩት የትምክህት ቃል ምንድን ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የኃጢአት ልምምዳቸውን እንዲተዉ ሳንወቅሳቸው፥ በደፈናው የምናልፋቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? ሐ) ክርስቶስ በምድር ላይ ቢሆን ኖሮ ከነዚህ ሰዎች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት የሚያደርግ ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: