ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት አስነሣው (ዮሐ. 11:1-57)

ሞት የሰው ልጆች ሁሉ ዋነኛ ጠላት ነው። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩበት ጊዜ አንሥቶ ሥጋዊ ሞት የሰው ልጆች ሁሉ የመጨረሻው ጠላት ሆነ፡፡ ሁላችንም በሞት ተሸንፈናል። ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ችግሮች መልስ ይሆን ዘንድ፥ ለዚህ ዋነኛ ጠላት መፍትሔ ሰጥቷል። ይህ አልዓዛር ከሞት የተነሣበት ሰባተኛው «ምልክት» ክርስቶስ በሞት ላይ ፍጹም ሥልጣን እንዳለው ከማሳየቱም በላይ፥ ለሁላችንም ተስፋ የሚሰጥ ምልክት ነው። አልዓዛርን ከሞት ያስነሣው ይኸው ክርስቶስ እኛንም ከሞት ያስነሣናል። ነገር ግን በአልዓዛርና በእኛ ትንሣኤ መካከል ልዩነት አለ። አልዓዛር ከሞት ቢነሣም እንደገና ሞቷል። እኛ ግን ክርስቶስ ከሞት በሚያስነሣን ጊዜ ዳግም አንሞትም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሞት ከሁሉም የከፋ ጠላታችን የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ክርስቶስ እኛንና የምንወዳቸውን ሰዎች ከሞት እንደሚያስነሣ የሚያመለክተው የተስፋ ቃል ታላቅ መጽናኛ የሚሆንልን ለምንድን ነው?

በዚህ ምድር ለኢየሱስ ቅርብ የሆነው ቤተሰብ የማርያም፥ የማርታና የአልዓዛር ቤተሰብ ሳይሆን አይቀርም። ክርስቶስ ብዙ ምሽቶችን በእነዚህ ወገኖች ቤት ያሳልፍ ነበር። ክርስቶስ የሕይወቱን የመጨረሻ ሳምንት ያሳለፈው በእነርሱ ቤት ነበር። ይህንንም ያደረገው ከኢየሩሳሌም ወደ ቢታንያ በየቀኑ 3 ኪሎ ሜትር ያህል እየተጓዘ ነበር። የሥጋ ወንድሞቹ በክርስቶስ ለማመን ባይፈልጉም፥ የዚህ ቤተሰብ አባላት ግን የክርስቶስ የቅርብ ወዳጆችና ደጋፊዎች ነበሩ።

የዮሐንስ ወንጌል በዚህ ስፍራ ትኩረቱን በመለወጥ ወደ ኢየሱስ ሞት እንድንመለከት አድርጓል። ክርስቶስ ከታላላቅ ተአምራቱ መካከል አንዱን በሚፈጽምበት ጊዜ እንኳ፥ በአይሁድ መሪዎች አስተባባሪነት የተቀሰቀሰው የአይሁዶች ቁጣና ጥላቻ ተጧጡፎ ቀጥሏል። ሕዝቡ እንዳይጠፋ ክርስቶስ መሞት እንዳለበት ለመሪዎቹ ግልጽ ነበር። (ዮሐ 11:50 አንብብ።)። ይህም ጥላቻ ክርስቶስን ለመስቀል ሞት ዳርጎታል። ነገር ግን የክርስቶስን ሞት የሚወስነው የአይሁድ መሪዎች ቁጣ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔር የጊዜ ሠሌዳ ነበር። ክርስቶስ ለዓለም ኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነው ጊዜው ሲደርስ ብቻ ነው።

ኢየሱስ የአልዓዛርን መታመም የሰማው በጲሪያ አካባቢ ሆኖ ነበር። አልዓዛርን ለመርዳት ከመፍጠን ይልቅ በዚያው ባለበት አያሌ ቀናት አሳለፈ። የእግዚአብሔር ዕቅድና የጊዜ ሠሌዳ ደቀ መዛሙርቱና ወዳጆቹ ከሚያስቡት የተለየ ነበር። (ማስታወሻ፡ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ ልናውቃቸው ከሚገቡን ነገሮች አንዱ፥ የእርሱ የጊዜ ሠሌዳ ከእኛ እንደሚለይ ነው። እኛ ፈጣን ምላሽ በምንፈልግበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር በአብዛኛው ይዘገያል። ቅጽበታዊ ፈውስን ስንሻ ለረዥም ጊዜ ከበሽታው ጋር እንድንኖር ወይም በታመምንበት በሽታ እንድንሞት ያደርጋል። በዚህ ጊዜ ከእግዚአብሔር የጊዜ ሠሌዳ ጋር ከመታገል ይልቅ ለእርሱ መታዘዝን ልንማር ይገባል። ከእግዚአብሔር ዕቅድና የጊዜ ሠሌዳ ጋር በምንታገልበት ጊዜ በዋናነት ራሳችንን እንጎዳለን።)

ሁለት ቀናት አለፉ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አልዓዛር እንደ ሞተ ያውቅ ነበር። ቀደም ሲል ከአልዓዛር ፈውስ ይበልጥ ለእግዚአብሔር አብና ወልድ ታላቅ ክብር እንደሚሆን ለደቀ መዛሙርቱ ገልጾ ነበር። ለክርስቶስ የአልዓዛር ሞት ከእንቅልፍ ተቀስቅሶ የመነሣት ያህል ብቻ ነበር። እኛም በምንሞትበት ጊዜ ሰውነታችን ለጊዜው ያንቀላፋል። በመጨረሻው ቀን ግን ክርስቶስ ከሞት ያስነሣናል። ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን ግን ነፍሳችን አታንቀላፋም፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው፥ ምንም እንኳ አካላችን ወይም ሰውነታችን ቢያንቀላፋም ስንሞት የማንነታችን መለያ የሆነችው ነፍሳችን በክርስቶስ ፊት ትሆናለች (2ኛ ቆሮ. 5፡1-10)።

ደቀ መዛሙርቱ አይሁዶች ክርስቶስን ምን ያህሉ እንደሚጠሉትና ሊገድሉትም እንደሚፈልጉ ያውቁ ስለ ነበር፥ ወደ ይሁዳ ለመመለስ ፈሩ። ሞት ቢጠብቃቸውም እንኳ ከእርሱ ጋር ለመሆን መወሰናቸው የእውነተኛ ፍቅርና ደቀ መዝሙርነት ምልክት ነበር።

ክርስቶስ ቢታኒያ ሲደርስ አልዓዛር ከሞተ ሦስት ቀን ሆኖት ነበር። በአይሁድ ባሕል አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ የአካባቢው ኅብረተሰብ በሚገኝበት የሦስት ቀን ኀዘን ይደረጋል፤ በአራተኛው ቀን የቅርብ ዘመዶች ብቻ ያለቅሳሉ። ከዚያ በኋላ ለተጨማሪ ሦስት ሳምንት በጣም የቅርብ ዘመዶች ብቻ ሲያለቅሱ ይቆያሉ። ዮሐንስ ስለ አልዓዛር ትንሣኤ በጻፈው ታሪክ የልዩ ልዩ ሰዎችና የክርስቶስ ምላሾች አጽንኦት ተሰጥቷቸዋል።

ሀ. ማርታ፡- ማርያም ከእግሩ ሥር በጸጥታ ቁጭ ብላ የክርስቶስን ትምህርት በምትከታተልበት ወቅት፥ ማርታ ክርስቶስን ለማስተናገድ ትጥር እንደ ነበር ታስታውሳለህ (ሉቃስ 10፡40-41)። ማርታ የክርስቶስን መምጣት እንደ ሰማች ልትቀበለው ወጣች። ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ተአምር ሲሠራ ስላየች አልዓዛርንም ሊፈውሰው እንደሚችል አመነች። አልዓዛር በመጨረሻው ዘመን ከሞት እንደሚነሣ መናገሯ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንደ ነበራት ያሳያል። ክርስቶስ «ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ» በማለት በሙታን ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለውና የዘላለምን ሕይወት ለመስጠት እንደሚችል ሲናገር አመነችው። (ይህ ኢየሱስ የተናገረው «እኔ ነኝ» የሚለው እምስተኛው ዓረፍተ ነገር ነው።) ማርታ ኢየሱስ 1) መሢሕና 2) የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ሙሉ በሙሉ እምናለች። ለክርስቶስ የነበራት ፍቅርና እምነት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ምንም ነገር ቢነግራት አትጠራጠረውም ነበር። እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ሁሉ፥ ማርታም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መስክራለች።

ለ. ማርያም፡- ከማርታ ይልቅ ማርያም ዝግ ያለች ሴት ትመስላለች። ክርስቶስ እየመጣ መሆኑን ብትሰማም እንደ ማርታ ግን ወጥታ አልተቀበለችውም። በቤት ከለቀስተኞቹ ጋር ተቀምጣ ነበር። ነገር ግን ማርታ ክርስቶስ ሊያገኛት እንደሚፈልግ ስትነግራት ከለቀስተኞቹ ጋር እርሱ ወዳለበት እየሮጠች ሄደች። እንደ ማርታ ሁሉ ማርያምም ክርስቶስ የመፈወስ ችሎታ እንዳለው ማመኗን ገልጻለች።

ሐ. ኢየሱስ፡ ዮሐንስ፥ ኢየሱስ በሁኔታው ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው ገልጾአል። ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞት እንደሚያስነሣው ያውቅ ነበር። ነገር ግን የማርያምንና የአይሁዶችን ኀዘን በተመለከተ ጊዜ በመንፈሱ እንደ ታወከና በነገሩም እንዳዘነ ተገልጾአል። ከዚያም አለቀሰ። ክርስቶስ ሊሆን ያለውን እያወቀ ለምን አለቀሰ? ክርስቶስ ያለቀሰው በሁለት ምክንያት ነው። አንደኛው፥ ያለቀሰው ኃጢአት በዓለም ውስጥ ስላስከተለው ሥቃይ ነው። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩበት ጊዜ አንሥቶ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት የሰው ልጅ ታሪክ የሞት ታሪክ ነበር። እንግዲህ ኢየሱስ ያለቀሰው ኃጢአት ፍጹሙን ፍጥረት በማጥፋቱ ነው። ሁለተኛው፥ ኀዘን ላደቀቃቸው ለአልዓዛር ወዳጆች ነበር ያለቀሰው። አልዓዛርን ከሞት እንደሚያስነሣው ቢያውቅም፥ ሌሎች ግን ይህን ዕድል አላገኙም ነበር፡፡ የሌሎች ጉዳት የክርስቶስን ልብ አወከ፥ ስለ ኀዘናቸውም ከማርያምና ከማርታ ጋር አለቀሰ።

በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ማልቀስ ትክክል አይደለም የሚል አመለካከት በአማኞች መካከል ያለ ይመስላል። ለዚህም ጳውሎስ «አታልቅሱ» የሚል መልእክት ማስተላለፉን ይጠቅሳሉ (1ኛ ተሰ. 4፡13-14)። ይህ ግን ጳውሎስ የተናገረውን በቅጡ አለመረዳት ነው። ጳውሎስ በዚህ ምንባብ ላይ የሚናገረው ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳናዝን ነው። ይህን ሲል እንባችንን አውጥተን እንዳናለቅስ መከልከሉ አልነበረም፤ ተስፋ እንደሌላቸው እንዳንሆን እንጂ። ክርስቶስ እንኳ በሞት ምክንያት ስለመጣው ሥቃይ አልቅሷል። ዛሬም ቢሆን የምንወደውን ሰው በሞት ተነጥቀን በምናዝንበት ጊዜ አብሮን ያዝናል። ክርስቲያኖች ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች ማልቀስ ባይኖርባቸውም፥ በሞት ምክንያት ለተለዩአቸው ሰዎች ኀዘናቸውን በለቅሶ መግለጽ ይችላሉ። የምንወደው ሰው በሞት ሲለየን ማልቀሱ ክፋት የለውም። እንባ እግዚአብሔር ኀዘናችንን ለማጠብና ነፍሳችንን ለመፈወስ የሚጠቀምበት መንገድ ነውና። አንድ ሰው እንደ ልቡ እንዳያለቅስ በምንከለከልበት ጊዜ የነፍሱ ኀዘን በእንባ ታጥቦ ኑሮውን በደስታ እንዳይቀጥል ማድረጋችን ነው። ነገር ግን የምንወደውን ሰው ክርስቶስ እንደሚያስነሣውና ነፍሱ በሰማይ እንደምትሆን በመገንዘብ (ክርስቲያን ከሆነ)፥ በተስፋ ቢስነት ሳይሆን የመለየትን ሥቃይ ለመግለጽ ያህል ማልቀሳችን ተገቢ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የሚወዱት ሲሞት ወይም አንድ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲገጥማቸው ክርስቶስ ሰዎች እንዳያለቅሱ የሚከለክል ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ለ) ማልቀስ ተቀባይነት ሊያገኝ ስለሚገባበትና ስለማይገባበት ሁኔታ ለቤተ ክርስቲያንህ ምእመናን ምን ልታስተምር ትችላለህ?

መ. አልዓዛር፡- ስለ አልዓዛርና በወቅቱ ስለነበረው ምላሽ እምብዛም የተነገረን ነገር የለም። ክርስቶስ በጠራው ጊዜ በከፈኑ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ ከመቃብሩ ወጣ።

ሠ. ጥቂት አይሁዶች፡- በኢየሱስ አመኑ። አእምሯቸው ክፍት ስለነበረ ተአምሩን አይተው ክርስቶስ መሢሕ እንደ ሆነ አመኑ። ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ እውነተኛ እምነት ነበራቸው። የአንዳንዶቹ እምነት ግን ዘላቂ አልነበረም። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ክርስቶስን ይክዱታል።

ረ. ጥቂት አይሁዶች በክርስቶስ አላመኑም። ይልቁንም ወደ ፈሪሳውያን ሄደው ከሰሱት። እነርሱም ክርስቶስን ለማስገደል የበለጠ ቁርጥ ውሳኔ አደረጉ። እውነትን ከመፈለግና የክርስቶስን ማንነት ከመገንዘብ ይልቅ የክብር ቦታቸውን ላለማጣት ሠጉ። ኢየሱስ ዐመፅን ቢያስነሣ፥ ሮም አይሁዶችን ትቀጣለች፥ የአይሁድ መሪዎችም ሥልጣናቸውን ያጣሉ። በ76 ዓ.ም. እንደ ሆነው የአይሁድ ሕዝብ ይመኩባቸው የነበሩ ነገሮች ወደሙ። የአይሁድ መሪዎች ክርስቶስን ለመግደል ወስነው ሊይዙት ፈለጉ።

ሰ. ቀያፋ፡- ቀያፋ ሊቀ ካህን ነበር። ይህ ሰው ሕዝቡ ክርስቶስን ተከትሎ በሮም መንግሥት ላይ ቢያምጽ ሊከሰት ስሚችለው አደጋ ሠጋ። «ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ቢሞት እንደሚሻል ገለጸ።» ይህ ሲል ክርስቶስ ቢሞት ዐመፁ እንደማይስፋፋና ሮምም ይሁዳን እንደማታጠፉ መግለጹ ነበር፡፡ ቀያፋ በዚህ ንግግሩ ሳያውቀው ትንቢት እየተናገረ ነበር። ኢየሱስ ለሰው ልጅ ኃጢአት በመስቀል ላይ ባቀረበው መሥዋዕት ሕዝቡን ከጥፋት አዳነ።

የውይይት ጥያቄ፡- እንደ እነዚህ የመሳሰሉትን ድርጊቶች ዛሬ የምናያቸው እንዴት ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐ 12፡1-1 አንብብ። ሀ) ማርያም ለክርስቶስ ያላትን ታላቅ ፍቅር የገለጸችው እንዴት ነበር? ለ) ክርስቲያኖች እንደዚህ ያለ ጽኑ ፍቅር ሊገልጹ የሚችሉባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ሐ) ባለፈው ዓመት ለክርስቶስ ያለህን ፍቅር በተለየ መንገድ የገለጽኸው እንዴት ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: