ክርስቶስ ስለ ሞቱ ትንቢት በተናገረ ጊዜ የተለያዩ ሰዎች የሰጡት ምላሽ (ዮሐ.12፡20-50)

ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ የመጨረሻ ቀናት ሲናገር ስለ ኢየሱስ ይፋዊ አገልግሎት የጀመረውን ገለጻ የደመደመው በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የተለያዩ ሰዎች ለኢየሱስ የሰጡትን ምላሽ ምሳሌ አድርጎ በማቅረብ ነው። የእነዚህን ሰዎች ምላሽ የያዘው ልክ በሰርግ ላይ እንደ ተነሣ ፎቶ በዚያን ጊዜ የነበረውንና አሁንም ሰዎች ለኢየሱስ የሚሰጡትን ምላሽ ለማጤን ይረዳሉ።

ሀ. ግሪኮች፡- ዮሐንስ የፋሲካን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ግሪኮች እንደ ነበሩ ገልጾአል። ምናልባትም እነዚህ ግሪኮች እንደ ቆርኔሌዎስ የራሳቸውን ሃይማኖት ትተው የአይሁዶችን ሃይማኖት የተከተሉ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ሰዎች ስለ ክርስቶስ የተነገረውን ዜና ሰምተው ሊያነጋግሩት ፈለጉ። ነገር ግን ምናልባትም ከሕዝቡ ብዛትና አሕዛብ ከመሆናቸው የተነሣ ከክርስቶስ ጋር ለመነጋገር ዕድል የማያገኙ ስለመሰላቸው ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ወደ ሆነው ወደ ፊልጶስ ቀረቡ። ፊልጶስ የገሊላ ሰው በመሆኑ ምናልባት ከአሕዛብ ጋር ቅርበት ሳይኖረው አይቀርም።

ስሙ ወላጆቹ የአሕዛብን ባሕል እንደ ተቀበሉ ያሳያል። ስለዚህ ግሪኮች ፊልጶስ ከክርስቶስ ጋር ቀጠሮ ለመያዝ ሊረዳን ይችላል ብለው ሳያስቡ አይቀሩም። ፊልጶስ ወደ ጓደኛው ወደ እንድርያስ በመሄድ ተያይዘው ወደ ክርስቶስ መጡ። ኢየሱስ ከግሪኮቹ ሰዎች ጋር ስለ መነጋገሩ በዚህ ክፍል የተጠቀሰ ነገር የለም። ምናልባትም ዮሐንስ ይህንን ታሪክ የጠቀሰው ከክርስቶስ ሞት በፊት ወንጌል ወደ አሕዛብ መድረሱን ለማመልከት ይሆናል። በጥቂት ዓመታት ውስጥ፥ የምሥራቹ ቃል ብዙ አሕዛብን ወደ ክርስቶስ ያመጣ ነበር።

ለ. ኢየሱስ፡- ኢየሱስ ሞቱ ያልጠበቀው ነበር? አልነበረም። ሞቱ እየቀረበ መምጣቱን ያውቅ ነበር። ይህ ማለት ግን ክርስቶስ ከሚጠብቀው ስቅለትና ከሚደርስበትም ነገር ጋር ግብግብ አልገጠመም ማለት አይደለም። እስካሁን ድረስ ዮሐንስ የክርስቶስ ጊዜ እንዳልቀረበ ሲገልጽ ነበር የቆየው። አሁን ግን ለስቅለቱ ጥቂት ሰዓታት ሲቀሩ «ጊዜው እንደ ደረሰ» ገልጾአል። የስንዴ ቅንጣት ለመብዛትና ፍሬ ለመስጠት መሞት እንዳለባት ሁሉ፥ ክርስቶስም መሞት ነበረበት። ይህ መርሕ ታዲያ ክርስቶስን በሚከተሉት ሁሉ ላይ የሚሠራ ነው። ለግል ፍላጎታችን ካልሞትን፥ ለሕልማችን ካልሞትን፥ ለተደላደለ ኑሮ ካልሞትን፥ ለኃጢአት ካልሞትን ሕይወታችን በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ እርባና አይኖረውም። የሮም መንግሥት ባስከተለባቸው ስደት በመቶዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ሲሞቱ የተመለከቱ አንድ የጥንት ጸሐፊ እንደ ገለጹት፥ “የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን ዘር ነው።” ሞትን የመረጡት የዘላለም ሕይወትን አግኝተዋል። ነገር ግን ከሞት ለመሸሽ የሞከሩ ሰዎች ትልቁን ሕይወት ማለትም የዘላለም ሕይወትን አጥተዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስን በመከተልህ «የሞትህባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) «ሞትህ ያስከተለው ፍሬ ምንድን ነው? ሐ) ሰዎች ለመሞትና ክርስቶስን በሙሉ ልባቸው ለመከተል አለመፈለጋቸውን እንዴት እንደተመለከትኸው ግለጽ። የሕይወታቸው ዘላለማዊ ፍሬ ምንድን ነው?

ሐ. እግዚአብሔር አብ፡– ሰው እንደ መሆኑ ኢየሱስ ከመስቀል ሞቱ ለማፈግፈግ ፈልጎአል። ለመሆኑ እስከ መጨረሻ እንዲጸና ያደረገው ምንድን ነው? ሦስት ነገሮች አሉ። አንደኛው፥ ክርስቶስ ዓላማውን በግልጽ ያውቃል። ወደ ዓለም የመጣውም ለመሞት እንደ ሆነ ያውቃል። ስለዚህ ለሌሎች ፍላጎቶች ላይገዛ ለእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ለመታዘዝ ቻለ። ሁለተኛው፥ ምንም ይሁን ምን እግዚአብሔርን ለማክበር ቆርጦ ነበር። ለእግዚአብሔር ክብር ለመስጠት እንጂ ለሕይወቱ ትልቅ ግምት አልሰጠም። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር በሞቱ እንዲከብር ጠየቀ። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሕይወትና በፈጸማቸው ተአምራት ደስ መሰኘቱን በሕዝቡ ሁሉ ፊት በይፋ ገለጸ። እግዚአብሔር በሞቱም ይከብር ነበር። ሦስተኛው፥ ክርስቶስ የሞቱን ውጤቶች ለመመልከት ችሎ ነበር። በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ድነትን (ደኅንነትን) ለማስገኘት በመቻሉ ስሙ ከስሞች ሁሉ እንደሚልቅና አንድ ቀን ሰዎች ሁሉ እንደሚያከብሩት ተገነዘበ (ፊልጵ. 2፡9-11፤ ዕብ. 12፡2)።

በሕይወት ዘመናችን የምንፈጽመው ትልቁ ዓላማ ምንድን ነው? ትልቁ ዓላማችን በሕይወታችን፥ በድርጊታችንና በአሳባችን እግዚአብሔርን ማስከበር ሊሆን ይገባል። ዓላማችን ይህ ከሆነ፥ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንደ ብርቱ ሕመም ድህነት፥ ስደት፥ ሞት የመሳሰሉ ነገሮችን ወደ ሕይወታችን ሊያመጣ ይችላል። መብቱም የእርሱ ነው። እግዚአብሔርን ለማክበር እስከፈለግን ድረስ፥ በሕይወታችን የሚከብርበትን መንገድ መምረጡ የእግዚአብሔር ድርሻ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር በሕይወትህ እንዲከብር የምትፈልግባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) በሕይወትህ የእግዚአብሔርን ሳይሆን የራስህን መንገድ የምትከተልባቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? እነዚህን ነገሮች ተናዝዘህ እግዚአብሔር በሁሉም ነገር የእርሱን ክብር እንድትፈልግ እንዲረዳህ ለምነው። ሐ) ከራስህ በላይ የእግዚአብሔርን ክብር በመፈለግህ ሕይወትህን ዓላማህን፥ ሥራህን ቤተሰብህን፥ ወዘተ… እንዴት እንደ ለወጠ አብራራ።

ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ ሰይጣን ድል ያደረገበት ወቅት ይመስል ነበር። ኢየሱስ ይህንን ጊዜ የጨለማ ጊዜ በማለት ጠርቶታል። ዳሩ ግን መስቀሉ ሦስት ነገሮችን አከናውኗል፡-

አንደኛው፥ በዓለም ላይ ፍርድን አምጥቷል። መስቀሉ የታሪክ መለያ መሥመር ነው። ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ያስገኘውን ድነት (ደኅንነት) የማይቀበሉ ሰዎች የዘላለምን ሞት ፍርድ ይቀበላሉ።

ሁለተኛው፣ የዚህን ዓለም አለቃ አሸንፎአል። ሰይጣን ክርስቶስ ተሰቅሎ እንዲሞት በማድረግ ያሸነፈ መስሎት ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ በሞቱ ሰይጣንን አሸነፈው። (ቆላ. 2፡15 አንብብ።) ሰይጣን በሰዎች ላይ የሚያደርሰው ጫና በመስቀሉ ላይ እንደ ተወገደ አዲስ ኪዳን ያስተምራል። ሰይጣን ሽንፈትን ከመከናነቡም በላይ ፍጻሜውም በደጅ ነው። ነገር ግን ሰይጣን ከእርሱ ጋር ወደ ሲኦል የሚወርዱ ሰዎችን ለማግኘት ትግሉን ቀጥሏል። ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ሰይጣን ለመጨረሻ ጊዜ ድል ይመታል፤ ወደ ሲኦልም ይጣላል (ራእይ 20፡10)።

ሦስተኛው፥ መስቀሉ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ይስባል። ይህም በሁለት መንገድ ይፈጸማል። በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች በሙሉ የዘላለም ሕይወት ይቀበላሉ። ኢየሱስ የኃጢአት ዕዳችንን በከፈለበት ዓይናቸው በመስቀሉ ላይ ነውና። በኢየሱስ የማያምኑ ሰዎች ግን በፍርድ ቀን በፊቱ ሲቀርቡ የግዳቸውን እንዲያከብሩት ይደረጋሉ (ፊልጵ. 2፡9-10)።

መ. ሕዝቡ፡- ዮሐንስ የገለጸው ሦስተኛው ምላሽ ሕዝቡ ክርስቶስ ስለ ሞቱ የተናገራቸውን ነገሮች እንደ ተገነዘቡ ያሳያል። መሢሑ ለዘላለም ይገዛል ብለው ስላሰቡ፥ አይሁዶች ክርስቶስ ይህንን እንዲያብራራላቸው ጠየቁት። ክርስቶስ ጥያቄውን በቀጥታ ባይመልስም፥ እርሱ «ብርሃን» እንደ ሆነ በግልጽ ነገራቸው። በምድር ላይ የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነበር። ከዓለም በሚሄድበት ጊዜ ልዩ ብርሃኑ አብሮት ይሄዳል። ስለሆነም፥ ክርስቶስ በመካከላቸው ሳለ በእርሱ ማመን አለባቸው። ከዚያም አይሁዶች በክርስቶስ መንፈሳዊ ብርሃን ደስ ሊሰኙ ይችላሉ። ይህም «የብርሃን ልጆች» ማለትም «የእግዚአብሔር ልጆች» እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል (ዮሐ 1፡12)። ዮሐንስ ከክርስቶስ ተአምራዊ ምልክቶች ባሻገር በአይሁዶች መካክል የተከሰተውን አለማመን ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል። አይሁዶች መሢሑን እንደማይቀበሉ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያውቅ ነበር።

ሠ. ጥቂት የሃይማኖት መሪዎች፡- ወንጌላት በሃይማኖት መሪዎቹ አለማመን፥ ለኢየሱስ ባላቸው ጥላቻና እርሱንም ለመግደል በሸረቡት ሴራ ላይ ትኩረት አድርገዋል። ነገር ግን እንደ ኒቆዲሞስና የአርማትያው ዮሴፍን የመሳሰሉ አንዳንድ መሪዎች በክርስቶስ ማመናቸውን ዮሐንስ ገልጾአል። ይህም ሆኖ ዮሐንስ እነዚህን ሰዎች የጠቀሰው ክርስቲያኖች እንደ እነርሱ መሆን እንደሌለባቸው ለመግለጽ ነው። ከምኩራብ እንዳይባረሩ ስለ ሠጉ በኢየሱስ ማመናቸውን ይፋ ለማድረግ ፈሩ፤ ምክንያቱም ከምኩራብ ከተባረሩ እንደ አይሁዶች ስለማይታዩ ነበር። ይህ ከሆነ ደግሞ የሰዎችን አክብሮት ከማጣታቸውም በላይ ሕይወታቸው በችግር የተሞላ ይሆናል። ዮሐንስ ግን ይህ እርምጃቸው ከእግዚአብሔር ይልቅ የሰውን ምስጋና መምረጣቸውን እንደሚያሳይ ገልጾአል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ለመደበቅ የምንፈተነው እንዴት ነው? ለ) ይህንን የምናደርገው ለምንድን ነው? ሐ) የዮሐንስ አሳቦች በክርስቶስ ያለንን እምነት በግልጽ ለማሳየት ከመፍራታችን ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው?

በዮሐንስ 12፡44-49 ላይ ኢየሱስ ለሕዝቡ የመጨረሻውን ቃሉን ተናግሯል። ማስጠንቀቂያዎቹ ግልጽና ጠንካራ ነበሩ። አንደኛው፥ እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር ወልድ በፍጹም አንድነት ስለሚሠሩና በባሕርይም አንድ ስለሆኑ፥ ለደኅንነት ሁለቱንም መቀበል የግድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጾአል። አይሁዶች በእግዚአብሔር አብ እናምናለን እያሉ፥ እግዚአብሔር ወልድን አንቀበልም ማለት አይችሉም። ስለሆነም ክርስቶስ አምላክ በመሆኑ ከእግዚአብሔርም ተልኮ በመምጣቱና የተናገራቸውም ነገሮች በሙሉ የእግዚአብሔር ቃል በመሆናቸው እርሱን መስማት ነበረባቸው። የዘላለም ሕይወት ሊገኝ የሚችለው አብ ሰዎች በክርስቶስ እንዲያምኑ የሰጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ በማድረግ ብቻ ነው። ሁለተኛው፥ ክርስቶስ እርሱን ባላመኑ ሰዎች ላይ ፍርድ እንደሚመጣ አስጠንቅቋል። ምንም እንኳ ፈራጁ እርሱ ራሱ ቢሆንም፥ ኢየሱስ ቆሞ መመስከር አያስፈልገውም። (ዮሐ 5፡27 አንብብ)። ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት የድነትን (የደኅንነትን) መንገድ ከማሳየታቸውም በላይ ምስክርነቱ የማያምኑ ሰዎችን ይኮንናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች የማያምኑ ጓደኞቻቸው ወይም ዘመዶቻቸው በክርስቶስ ካላመኑ ምንም ያህል ጥሩ ሰዎች ቢሆኑም፥ የዘላለም ፍርድ እንደሚጠብቃቸው በገርነትና በግልጽ ማስጠንቀቅ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading