ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የፋሲካ ምግብ በላ (ዮሐ. 13:1-38)

ከዮሐንስ 13-17 በኋላ የወንጌሉ ትኩረት ይለወጣል። እስካሁን አጽንኦት የተሰጠው ለኢየሱስ ክርስቶስ ይፋዊ አገልግሎት፥ ላደረጋቸው ምልክቶችና ለሕዝብ ላቀረባቸው ትምህርቶች ነበር። ዮሐንስ በዚህ ይፋዊ አገልግሎት ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለሰጠው ቀጥተኛ ትምህርት ብዙም የገለጸው ነገር የለም። አሁን ግን ዮሐንስ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሳለ በመጨረሻው ምሽት ላይ ለደቀ መዛሙርቱ በሰጣቸው እጅግ ጠቃሚ ትምህርቶች ላይ አተኩሯል። የመሞቻው ቀን የተቃረበ መሆኑን የተገነዘበ አባት ለልጆቹ የመጨረሻ ምክሩን እንደሚሰጥ ሁሉ፥ በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ አንዳንድ ወሳኝ የአዲስ ኪዳን ትምህርቶችን አካፍሏቸዋል። የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወንጌላት ክርስቶስ አዲስ ኪዳንና የጌታ እራት ሥርዓትን መመሥረቱን አጉልተው ሲያሳዩ፥ ዮሐንስ ደግሞ ክርስቶስ ከሞቱ፥ ከትንሣኤውና ከዕርገቱ በኋላ ተከታዮቹ ሊኖሩት ስለሚገባ ሕይወት ገልጾአል።

ሀ. ክርስቶስ የትሕትና አገልግሎት የመንግሥቱ ምሳሌ እንደሆነ ገልጿል (ዮሐ 13፡1–17)። በአይሁድ ባሕል የአንድን ሰው እግር ማጠብ እጅግ ዝቅተኛ ሥራ ነው። ይህ አንድ የቤት አገልጋይ የሚያከናውነው ተግባር ነው። ቤተሰቡ አገልጋይ ከሌለው ሚስት ወይም ልጆች እንጂ አባወራው የእንግዳውን እግር አያጥብም። የሚደንቀው ነገር ታዲያ የዓለም ፈጣሪ የደቀ መዛሙርቱን እግሮች አጠበ። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ትሕትና ነው። ክርስቶስ ይህንን ያህል ራሱን ዝቅ ካደረገ፥ እኛም አርአያውን ተከትለን ራሳችንን በሌሎች ፊት ዝቅ ማድረግና ሌሎችን ማገልገል ይኖርብናል።

ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበው ለምንድን ነው? አንደኛው፥ ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚገልጽበት መንገድ በመሆኑ ነው። በተጨማሪም በሞት ከመለየቱ በፊት እነርሱን የሚያገለግልበት የመጨረሻ ዕድል በመሆኑም ነው። ዮሐንስ ይህንን ተግባር «የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው» በማለት ገልጾአል። ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የነበረውን ፍቅር በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ቆይቶ ነበር። አሁን ግን ከቶ በማይረሱት መንገድ ነበር ፍቅሩን ያሳያቸው። ክርስቶስ እንደ ባሪያ እግራቸውን አጠበ። ፍቅር ሁልጊዜ ያገለግላል፥ ይሰጣልም። ፍቅር ከስሜት በላይ ነው። ፍቅር ሌሎችን ማገልገልና ሲያድጉ ማየት ነው። ፍቅር ሌሎችን ማገልገልን እንደ ዝቅተኛነት አይመለከትም።

ሁለተኛው፥ ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ማየት የሚፈልገውን ባሕርይ በምሳሌነት ለመግለጽ ነው። ዮሐንስ ክርስቶስ ሊደርስበት ያለውን ነገር ሁሉ ያውቅ እንደ ነበር ገልጾአል። የመጣበትን ስፍራ ያውቅ ነበር – ከሰማይ። የመጣበትንም ምክንያት ያውቅ ነበር። ለመሞት ተመልሶ የሚሄድበትንም ስፍራ ያውቅ ነበር – ወደ ሰማይ። እንዲሁም እግዚአብሔር አብ የሰጠውን ኃይልና ሥልጣን ሁሉ ያውቅ ነበር። ይህ ግን እንዲኩራራ ወይም ሌሎች እንዲያገለግሉት አላደረገውም። ክርስቶስ ተከታዮቹ ይህንኑ ባሕርይ እንዲይዙ ይፈልጋል። ሥልጣንና ኃይልን ከመፈለግና ሌሎች እንዲያገለግሉን ከመሻት ይልቅ ራሳችንን ዝቅ አድርገን አንዳችን ሌላውን ልናገለግል ይገባል።

አንዳንድ ክርስቲያኖች ምሳሌውን እንድንከተል ያሳየንን ነገር በመውሰድ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግር መታጠብ አለብን ይላሉ። የክርስቶስ ምኞት ግን ከዚህ የላቀ ነው። እግርን ማጠብ ራስን ዝቅ አድርጎ ሌሎችን ማገልገል አንድ ምሳሌ ብቻ ነው። ደቀ መዛሙርት ክርስቶስ ጌታቸውና መምህራቸው እንደ ሆነ ያምኑ ነበር። ጌታቸው ራሱን ዝቅ አድርጎ ካገለገላቸው፥ እነርሱም እንዲሁ ከማድረግ መቆጠብ የለባቸውም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እርስ በርሳቸው አገልግሎት ሊሰጣጡ የሚችሉባቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች ጥቀስ። ለ) እነዚህ የጠቀስሃቸው ነገሮች ተግባራዊ እየሆኑ ናቸው? ከሆኑ ለምን? ካልሆኑስ ክርስቲያኖች ሁሉ ሌሎችን ዝቅ ብለው ቢያገለግሉ በቤተ ክርስቲያናችን ምን ዓይነት ለውጥ ይመጣል?

ለ. ክርስቶስ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጠው ተነበየ (ዮሐ 13፡18-38)። ዮሐንስ ክርስቶስ በሕይወቱ ላይ የሚደርሰውን ማንኛውም ነገር ለመቆጣጠር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው በተደጋጋሚ ገልጾአል። ጊዜው ከመድረሱ በፊት ክርስቶስን ማንም ለማሰር አይችልም። ነገር ግን የተወሰነው የእግዚአብሔር ጊዜ ሲደርስ ክርስቶስ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ሰጠ። ክርስቶስ ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠር ለማሳየት ዮሐንስ ክርስቶስ ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ አሳልፎ እንደሚሰጠው ብቻ ሳይሆን፥ ይህም ሰው ይሁዳ እንደ ሆነ መተንበዩን ጠቅሷል። በዮሐ 13፡23 ላይ ኢየሱስ «ይወደው ከነበረው ደቀ መዝሙር» ጋር እንተዋወቃለን። ከዚህ ምዕራፍ ጀምሮ እስከ መጽሐፉ መጨረሻ ድረስ ዮሐንስ ራሱን ለመጥቀስ ይህንን የተለየ ስም ይጠቀማል።

ይሁዳ ከክፍሉ ከወጣ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ይበልጥ ነፃ ሆኖ ማስተማርና ወደፊት ሊኖሩት ስለሚገባቸው ሕይወት ያዘጋጃቸው ጀመር። ከእነርሱ ጋር የሚቆየው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር። ከ40 ቀናት በኋላ በአካል ከእነርሱ ጋር መኖሩ ያበቃል። እርሱ ወደ ሰማይ ስለሚሄድ እርሱ ወደሚሄድበት ሊከተሉት አይችሉም። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሦስት እውነቶችን ገልጾላቸዋል፦

ሀ. ወንጀለኞች የሚሰቀሉበት ታላቁ የኀፍረት ስፍራ ወደ ክብር ስፍራ ይቀየራል። ክርስቶስ በታዛዥነት በመስቀል ላይ በመሞት እግዚአብሔርን ያከብር ነበር። እግዚአብሔርም የኀፍረቱን መስቀል ለውጦ ኢየሱስን ያከብረዋል፤ ለተከታዮቹም ሁሉ የመመኪያ ስፍራ ያደርግላቸው (1ኛ ቆሮ. 1፡18፤ ገላ. 6፡14)። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱና ከሞትም በመነሣቱ፥ ስሙ በታሪክ ሁሉ ከስሞች ሁሉ በላይ የላቀ ስም ለመሆን በቅቷል።

ይህ ለሰው ልጆች ፍጹም እንግዳ ነው፤ እግዚአብሔር ለሰዎች ኀፍረት የሆነውን ነገር ለውጦ ለራሱ ክብር እንደሚጠቀምበት በኢየሱስ ሕይወት በግልጽ ታይቷል። እግዚአብሔር የተጣለውን ድንጋይ (ኢየሱስን) የማዕዘን ራስ አድርጎታል (ማቴ. 21፡42-44)። ሽባዋን ሴት ተጠቅሞ ስለ ጸጋው እንድትመሰክር አድርጓል። የጳውሎስን የሥጋ መውጊያ ወስዶ የእግዚአብሔር ጸጋ በሰው ድካም እንደሚፈጸም አሳይቷል (2ኛ ቆሮ. 12፡7-10)። በሕይወታችን የሚገጥመንን በሽታ፥ ሥቃይና ችግር በመጠቀም ክብሩን ይገልጻል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ኀፍረት የሚመስለውን ነገር በመጠቀም በሕይወትህ ክብሩን ሲገልጽ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ይህ በሕይወታችን የሚከሰተውን ችግር ስለምንመለከትበት መንገድና በዚህም ጊዜ ስለምናደርገው ጸሎት ምን ዓይነት የአመለካከት ለውጥ እንዲኖረን ያደርጋል?

ለ. አዲሱና እጅግ ታላቁ የክርስቶስ ትእዛዝ “እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” የሚል ነው። በአንድ በኩል ይህ አዲስ ትእዛዝ አይደለም። ይህ አሳብ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተሰወረ ሲሆን (ዘሌዋ. 19፡18 አንብብ)፥ ክርስቶስም ሁለቱ ታላላቅ ጠቃሚ ትእዛዛት እግዚአብሔርንና ባልንጀሮቻችንን መውደድ እንደሆነ ገልጾአል (ማቴ. 22፡37-40)። እንግዲህ ይህ ትእዛዝ «አዲስ» የሚሆነው እንዴት ነው? አዲስ ትእዛዝ የሚሆነው፡-

  1. አዲስ አጽንኦት አለው። ምንም እንኳ ብሉይ ኪዳን እርስ በርስ ስለመዋደድ በግልጽ ባይናገርም፥ በሌሎች ብዙ ትእዛዛት ላይ ግን ነገሩ ተወስቷል። አሁን ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ በሌሎች ብዙ ሕግጋትና ደንቦች ሳይሆን በፍቅር ሕግ እንዲመሩ ገልጾአል።
  2. ሰዎች እርስ በርሳቸው በሚኖራቸው ግንኙነት ውስጥ እግዚአብሔር ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚፈልጋቸው ወሳኝ ነገሮች ናቸው። ፍቅር የትእዛዛት ሁሉ ፍጻሜ ሆኖ ተገልጾአል። ከውጫዊ ተግባራት ጋር የሚያያዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕግጋትን ከሚደነግጉ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በተቃራኒ፥ ኢየሱስ ከተከታዮቹ የሚፈልገው አዲስ ውስጣዊ አመለካከትን ነው፤ ይህም አንዱ ለሌላው የሚያሳየው ፍቅር ነው። እግዚአብሔርንና ሰዎችን ከወደድን ክርስቶስ የሚፈልጋቸውን ትእዛዛት መጠበቅ ተፈጥሯዊ ጉዳይ ይሆናል።
  3. የአንድ ክርስቲያን ምልክቱ ወይም መታወቂያው ነው። በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ለመሆን ምልክቱ መገረዝና ውጫዊ ሕግጋትን መጠበቅ ነበር። አሁን ግን የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችን ምልክቱ እርስ በርስ ያለን ፍቅር እንደ ሆነ ተመልክቷል።
  4. በዓይነቱና በጥልቀቱ። ፍቅርን የሚገልጹ ሦስት የግሪክ ቃላት አሉ። ኤሮስ (Eros) ባል ለሚስቱ ያለውን ፍቅር ያመለክታል። ፊሊዮ (Phileo) በጓደኛሞች መካከል የሚታየውን ፍቅር ያሳያል። አጋፔ (Agape) መለኮታዊ ማለትም ራሱን የሚገልጥ ፍቅር ነው። ክርስቶስ ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት እርሱ እግራቸውን እንዳጠበና ስለ እነርሱም ሲል በመስቀል ላይ እንደ ሞተ ሁሉ የእርሱ የሆኑ ሁሉ ይህንኑ እንዲያደርጉ ነው። ለሌሎች መኖር እዲስ ትእዛዝ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የማያምኑ ሰዎች እንደ አንድ አማኝ ከእኛ የሚጠብቁብንን ነገሮች ዘርዝር። ፍቅር ከእነዚህ ነገሮች አንዱ ነው? ለምን? ለ) ፍቅር የክርስቲያን መለያ መሆን አለበት፥ ዛሬ በክርስቲያኖች መካከል ፍቅር ጠፍቶ መከፋፈል የሰፈነው ለምን ይመስልሃል?

ሐ. ጴጥሮስ ለክርስቶስ ሲል ለመሞት እንዳሰበ ቢናገርም፥ ሦስት ጊዜ እንደሚክደው ኢየሱስ ተንብዮአል። ለክርስቶስ ለመኖር ወይም ለመሞት ቃል መግባት ቀላል ቢሆንም፥ ተግባራዊ ማድረጉ ግን ከባድ ነው። እጅግ ደፋር ደቀ መዝሙር የነበረው ጴጥሮስ ክርስቶስን ክዶታል። እኛም ከእርሱ ላንሻል እንችላለን። ነገር ግን ክርስቶስን በመታዘዝ እንድናድግ የሚያበረታቱን ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው፥ ክርስቶስ ጴጥሮስን ይቅር ብሎ እንደገና እንደ ተጠቀመበት ሁሉ እኛንም ይቅር እንደሚለን እናውቃለን። ሁለተኛው፥ ጸንተን እንድንቆም የሚረዳን መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን አለ። ስለ አንተ እሞታለሁ ብሎ ቃል የገባው ጴጥሮስ ሳይሳካለት ቀርቷል። በቃላችን እንድንጻጸና የሚረዳን መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d