የክርስቶስ ስቅለት፣ ቀብር እና ትንሣኤ (ዮሐ. 19፡17-20:31)

  1. የክርስቶስ ስቅለት (ዮሐ 19፡17-37)

ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ሞት አያሌ አስገራሚ ዝርዝሮችን አቅርቧል።

ሀ. የሃይማኖት መሪዎች በክርስቶስ ላይ ያቀረቡትን ክስ ለመቀየር ፈለጉ። አንድ ሰው በወንጀል ተከስሶ ስቅላት በሚፈረድበት ጊዜ፥ ሮማውያን በአንገቱ ዙሪያ ወንጀሉን የሚገልጽ ጽሑፍ ያንጠለጥሉ ነበር። የክርስቶስ ክስ «የአይሁድ ንጉሥ» የሚል ነበር። የሃይማኖት መሪዎች ክሱ እንዲቀየር ቢጠይቁም፥ ጲላጦስ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

ለ. የክርስቶስን ልብስ መከፋፈላቸው፡- ዮሐንስ ክርስቶስ የብሉይ ኪዳንን ትንቢት እንደ ፈጸመ ካመለከትባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች ይሄ አንደኛው ነው። ዮሐንስ የክርስቶስ ልብስ ላይ ዕጣ እንደ ተጣጣሉና ከወታደሮቹ አንዱ ዕጣውን አሸንፎ እንደ ወሰደ ገልጾአል። (ማስታወሻ፡- እያንዳንዱ ወታደር ከተሰቀለው ግለሰብ ልብስ መውሰዱ በሮም የተለመደ ድርጊት ነበር።)

ሐ. ክርስቶስ ለሚወደው ደቀ መዝሙር እናቱን በአደራ ሰጠ። ሉቃስ ብዙ ሴቶች በኀዘን ተሰብረው በክርስቶስ መስቀል አጠገብ መቆማቸውን ቢገልጽም፥ ዮሐንስ ግን ክርስቶስ እናቱን ለሌሎች ልጆቿ ሳይሆን፤ ለእርሱ ለራሱ አደራ ማለቱን ጠቅሷል።

መ. የሌቦቹ እግሮች መሰበርና የክርስቶስ ጎን መወጋት፡- ሰውን በስቅላት መግደል ረዥም ጊዜ ይወስዳል። አንዳንድ ጠንካራ ሰው ለመሞት እስከ ሁለት ቀን ሊፈጅበት ይችላል። ይህን ረዥም ጊዜ የሚወስድ አሟሟት ለማፋጠን ከሚደረጉት ነገሮች አንዱ በመስቀል ላይ የተሰቀሉትን ሰዎች እግሮች መስበር ነበር። ዮሐንስ አሁንም ክርስቶስ በሁለት መንገዶች የብሉይ ኪዳን ትንቢትን እንደ ፈጸመና የሁለቱ ሌቦች እግሮች እንደ ተሰበሩ አመልክቷል። እንደኛው፥ ቶሎ ስለ ሞተ እግሩን መስበር አላስፈለገም። ሁለተኛው፥ በጦር ተወግቷል። በጦር ሲወጋ ውኃና ደም መውጣቱ፥ ጦሩ የክርስቶስን ልብ እንደ ወጋ የሚያሳይ መሆኑን የሕክምና ሳይንስ ያስረዳል። ይህም የክርስቶስን መሞት ያሳያል። ይህን ታላቅ እውነት ዮሐንስ በዓይኑ እንደ ተመለከተ ገልጾአል። ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ሞት የሰጠው ምስክርነት እውነት ነበር። አንዳንድ ሙስሊሞች፥ ክርስቶስ ራሱን ስቶ የነቃው በመቃብር ውስጥ ነው፤ ነቅቶ ድኗል ማለታቸው የሚታመን አባባል አይደለም።

  1. የኢየሱስ መቀበር (ዮሐ 19፡38-42)። ሁሉም ወንጌላውያን በክርስቶስ ቀብር ወቅት የአርማትያሱ ዮሴፍ ስላደረገው መልካም ተግባር የገለጡ ሲሆኑ፥ ዮሐንስ ግን ኒቆዲሞስን ጠቅሷል። ኒቆዲሞስ የዘላለም ሕይወትን መንገድ ለማወቅ መጀመሪያ ወደ ክርስቶስ የመጣ የሃይማኖት መሪ ነበር (ዮሐ 3)። ከዚያ በኋላ ሕቡዕ ወይም አይሁዶች ያላወቁት አማኝ በመሆን በሃይማኖት መሪዎች ፊት ስለ ክርስቶስ ለመከራከር ሞክሯል (ዮሐ 7፡50-51)። እነዚህ ሁለት ሕቡዕ አማኞች ከኢየሱስ ሞት በኋላ በግልጽ ተከታዮቹ ሆኑ። የክርስቶስን አስከሬን ለመውሰድ ፈቃድ ካገኙ በኋላ ወስደው በመቃብር ውስጥ አኖሩት። ቀደም ሲል ኒቆዲሞስ 25 ኪሎ ግራም የሚመዝን የከርቤና የእሬት ቅልቅል እንዳመጣ ዮሐንስ ገልጾአል። ይህም ኒቆዲሞስ ለክርስቶስ የነበረውን ፍቅርና አክብሮት ያሳያል። ነገሥታት በሚቀበሩበት ጊዜ ብዙ ዓይነት ቅመም ጥቅም ላይ ይውል ነበር። (2ኛ ዜና 16፡14)። ዮሐንስ የክርስቶስን ሥጋ በጥንቃቄ በተልባ እግር ልብስ መሸፈናቸውን መግለጹ፥ ሂደቱን ሲከታተል እንደ ነበረ ያስረዳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐ 20- አንብብ። ሀ) እነዚህ ምዕራፎች ስለ ክርስቶስ ምን ይነግሩናል? ለ) ክርስቶስን ስለ መከተል ምን እንማራለን?

  1. የኢየሱስ ትንሣኤ (ዮሐ. 20)።

ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ የሰጠውን ገለጻ ማንበብ፥ ፎቶግራፋዊ መረጃን እንደ መመልከት ይቆጠራል። ታሪኩ ያተኮረው የተለያዩ ሰዎች ስለ ትንሣኤው በሰጡት ምላሽ ላይ ነው።

ሀ. መግደላዊት ማርያም፡- ጌታችን ከሞት ሲነሣ በመጀመሪያ የተመለከተችው ይህቺው መግደላዊት ማርያም ነበረች። ይህም ለኢየሱስ ለነበራት ፍቅርና እርሱን ለማግኘት ስላሳየችው ቆራጥነት የተደረገላት አክብሮት ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስ መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ ሄዳ የክርስቶስን ሥጋ እንዳጣችው ገልጾአል። ከዚያም ወደ ዮሐንስና ጴጥሮስ ፈጥና በመሄድ ነገረቻቸው። ወደ መቃብሩ በተመለሰች ጊዜ ግን ክርስቶስን አገኘችው። ክርስቶስ ገና ወደ አብ ስላላረገ ማርያም እንዳትነካው አስጠነቀቃት። (የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያተኩረው ክርስቶስን በመንካት ሳይሆን፥ ይዞ እንዳይሄድ በመከልከል ላይ ነው።) ክርስቶስ ይህን ያለው ለምንድን ነው? አንዳንዶች ክርስቶስ በቀጥታ ወደ ሰማይ ሄዶ ራሱን ለአብ ለማቅረብና ከዚያ በኋላ ወደ ምድር ለመመለስ ዐቅዶ ሳለ፥ ማርያም ይዛ ልታቆየው እንደ ፈለገች ያስረዳሉ። ትክክለኛው ትርጓሜ ግን፥ ክርስቶስ ከማረጉ በፊት የተወሰነ ጊዜ እንዳለውና ማርያም ሌላ ጊዜ ስለምታገኘው ይዛው ለመቆየት ማሰብዋ አስፈላጊ እንዳልሆነ የሚገልጸው ነው። ይልቁንም ማርያም ሄዳ ትንሣኤውን ለአሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት እንድትናገር አሳሰባት። ክርስቶስ በዚህ ጊዜ ከእግዚአብሔር አምላካቸውና አባታቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አሳይቷል። እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር የተለየ ግንኙነት እንዳለውም ገልጾአል። ምክንያቱም እርሱ የክርስቶስ ልዩ አባትና አምላክ ሲሆን፥ ይህም ከደቀ መዛሙርቱ ግንኙነት ፍጹም የተለየ ነበር።

ለ. ጴጥሮስ፡- ማርያም መቃብሩ ባዶ እንደሆነ ስትናገር ሰምቶ ወደ መቃብሩ ሮጠ። ወደ መቃብሩ ዘልቆ ሲገባም፥ ከከፈኑ ጨርቅ በስተቀር የኢየሱስን ሥጋ አላገኘም። መቃብሩ ባዶ መሆኑን ከተመለከተ በኋላ የሆነውን ነገር በቅጡ ሳይረዳ ተመለሰ።

ሐ. ዮሐንስ፥ «ሌላው ደቀ መዝሙር፡- ከጴጥሮስ ቀድሞ ቢሮጥም፥ ከመቃብሩ ውጭ ቆሞ ወደ ውስጥ ተመለከተ እንጂ፥ ወደ መቃብሩ ውስጥ አልገባም ነበር። ከዚያ በኋላ እርሱም ጴጥሮስን ተከትሎ ወደ መቃብሩ ውስጥ ገባ። ዮሐንስ የከፈኑን ጨርቅ ሲመለከት፥ በክርስቶስ ትንሣኤ አመነ።

መ. ቶማስ በሌለበት አሥሩ ደቀ መዛሙርት፡- በራቸውን ዘግተው ቁጭ ብለው ሳሉ ክርስቶስ በአምላካዊ ባሕሪው በደቀ መዛሙርቱ መካከል ተገኘ። በዚህ ጊዜ ክርስቶስ ሦስት ነገሮችን አድርጓል፡-

  1. ክርስቶስ ሐዋርያቱ (የተላኩ ማለት ነው) አድርጎ ሾማቸው። እግዚአብሔር እርሱን በላከበት ሁኔታና ሥልጣን፥ ክርስቶስ ለዓለም ወኪሎቹ አድርጎ ላካቸው።
  2. ከዚያም ክርስቶስ በእስትንፋስ መንፈስ ቅዱስን ሰጣቸው። ከዚያ በኋላ የምስክርነት ኃይላቸው ይመጣ የነበረው ከመንፈስ ቅዱስ ነበር። ይህ ክስተት ምን ትርጉም ይሰጣል? የመንፈስ ቅዱስ ሙሉ ህልውና በዚህ ጊዜ አለመኖሩን ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 እንመለከታለን። በመሆኑም፥ ሁለት አማራጮች ነበሩ። አንደኛው፥ ክርስቶስ ከ50 ቀናት በኋላ በበዓለ ኀምሳ ቀን ስለሚሆነው ነገር እየተነበየ ነበር። የእርሱ እስትንፋስ ተስፋ በሰጠው መሠረት፥ መንፈስ ቅዱስ በቅርቡ እንደሚመጣላቸው የሚያሳይ ውጫዊ ተምሳሌት ነበር። ሁለተኛው፥ ክርስቶስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ላይ ሙሉውና ዘላቂው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል እስኪመጣላቸው ድረስ በእምነትና በታማኝነት እንዲቆዩ ለማድረግ ጊዚያዊ የመንፈስ ቅዱስ ህልውና ሰጥቷቸዋል።
  3. ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን ይኖራቸዋል። ይህ ጥቅስ በግሪኩ፥ «ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ይቅርታን አግኝተዋል። ይቅር ያላላችኋቸው ይቅርታን አላገኙም» ይላል። ክርስቶስ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ለማለት ወይም ላለማለት ፍጹም ሥልጣን አልሰጣቸውም። ነገር ግን ይህ ምንባብ እንደሚያሳየው፥ በመንግሥተ ሰማይ የሚሆነውን ነገር እንዲያውጁ ብቻ ሥልጣን ሰጣቸው። እግዚአብሔር በክርስቶስ ያመኑትን ይቅር ስላለ፥ ይቅርታ መስጠቱን ለማወጅ ሥልጣን ነበራቸው። ነገር ግን ሰዎች በክርስቶስ ካላመኑ፥ ይቅርታን እንዳላገኙ ለማወጅ ሥልጣን አላቸው ማለት እንጂ፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ሐዋርያ ንስሐ ያልገባ ሰው እንደሚድን ወይም ንስሐ የገባ ሰው እንደማይድን ያወጀበትን ሁኔታ አንመለከትም። ይቅርታን ለመስጠት ሥልጣኑ የእግዚአብሔር እንጂ የሰዎች አይደለም። ነገር ግን በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላይ ተመሥርተን፥ በክርስቶስ ያመኑ ወገኖች ኃጢአት ይቅር እንደሚባል ለማሳወቅ፥ ያላመኑ ሰዎች ደግሞ ይቅርታን እንደማያገኙ ለማስጠንቀቅ እንችላለን።

ሠ. ኢየሱስ ቶማስ ባለበት ከአሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ጋር ተገናኘ። ቶማስ ኢየሱስ ለአሥሩ ደቀ መዛሙርት በታየ ጊዜ አብሯቸው ስላልነበረ፥ በክርስቶስ ትንሣኤ ለማመን ተቸገረ። በክርስቶስ ጎንና በእግሮቹ ላይ የነበረውን ቁስል ዳስሶ ከተመለከተ በኋላ አመነ። ቶማስ ኢየሱስ በምድር ከነበረበት ጊዜ አንሥቶ በአማኞች ሁሉ ላይ ለሚታየው ነገር ተምሳሌት ሆኗል። አንደኛው፥ ክርስቶስን «ጌታዬና አምላኬ» ማለቱ ክርስቲያኖች ሁሉ ሊኖራቸው የሚገባው እምነት ነው። ክርስቶስ ተራ ሰው ሳይሆን፥ እንደ እግዚአብሔር አብ ያለ ፍጹም አምላክ ነው። ሁለተኛው፥ ቶማስ መሆን ለሌለብን ነገር ምሳሌ ነው። ቶማስ ክርስቶስን በዓይኖቹ እስከሚያይ ድረስ ለማመን ፈቃደኛ አልሆነም ነበር። ነገር ግን በዓይናቸው ሳያዩ ትንሣኤውን የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው። ማንኛችንም ብንሆን ድነትን (ደኅንነትን) አግኝተን ወደ መንግሥተ ሰማይ ከመሄዳችን በፊት፥ ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን በአካል ልናየው አንችልም። ወደ መንግሥተ ሰማያት ስንሄድ ግን እናየዋለን። እስከዚያው ግን በዚህች ምድር ላይ እንደ ኖረ፥ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ በእምነት ዓይናችን እናየዋለን። የዕብራውያን ጸሐፊ እንዳለው፥ «እምነት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው» (ዕብ 11፡1)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የክርስቶስ ስቅለት፣ ቀብር እና ትንሣኤ (ዮሐ. 19፡17-20:31)”

Leave a Reply

%d