በዕብ 4፡14-16፤ 7፡25 ላይ ክርስቶስ ሊቀ ካህናችን እንደሆነና እንደሚማልድልን ተገልጾአል። እርሱ የሚጸልየው ስለ ምንድን ነው? ለእርሱ አስፈላጊ ነገር ምንድን ነው? እርሱ የሚጸልየው ስለ ሥጋዊ ጤንነታችን፥ ከአደጋ ስለ መትረፋችን፥ ስለ ቁሳዊ በረከት ነው? በዮሐንስ 17 ላይ ክርስቶስ እንደ ሊቀ ካህናችን ስለምን እንደሚጸልይ የሚያሳይ ምሳሌ አለ። ሐዋርያው ዮሐንስ ክርስቶስ ልቡን ከፍቶ የጸለየበትን አጋጣሚ ተገንዝቦአል። የጸለየውም ለራሱ፥ አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት፥ ለእናንተና ለእኔ ነው። ከከርስቶስ ጸሎት ምን እንማራለን?
ሀ. በጸሎታችን ሁሉ ቀዳሚው ጥያቄአችን መሆን ያለበት የእግዚአብሔር ክብር ነው። ሊያሳስበን የሚገባው የፍላጎታችን መሟላት መሆን የለበትም። ለእግዚአብሔር ክብርን ስለሚያመጣው ነገር ሳይሆን እኛ ለምንፈልጋቸው ነገሮች የምንጸልይ ከሆነ፥ እንደ ክርስቶስ ፈቃድ እየጸለይን አይደለም። ክርስቶስ እግዚአብሔርን በሚያከብርበት ጊዜ እግዚአብሔርም እርሱን እንደሚያከብረው በመገንዘብ፥ እግዚአብሔርን ለማክበር ፈለገ። ይህ ለእኛም እውነት ነው። በእግዚአብሔርና እርሱን በሚያስከብሩ ነገሮች ላይ ስናተኩር፥ እግዚአብሔርም እኛን ያከብረናል። ለመሆኑ ክርስቶስ እግዚአብሔርን ያከበረው እንዴት ነው? ክርስቶስ እግዚአብሔርን ያከበረው እንዲያደርግ የነገረውን ነገር ሁሉ በማድረግ ነው። ክርስቶስ ሲያስተምር፥ ተአምራትን ሲሠራና ሞትን ሲቀበል፥ እግዚአብሔርን እያከበረ ነበር። እኛም እግዚአብሔርን የምናከብረው ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ብቻ ሳይሆን፥ በዕለት ተዕለት እርምጃችን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ነገር ስናደርግ ብቻ ነው። ብዙውን ጊዜ ሰዎች እግዚአብሔርን እያከበሩ እንደሆነ ላያውቁ ይችላሉ። እግዚአብሔር ግን ያውቃል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔርን ሊያከብሩ ይችላሉ ብለህ ያቀረብሃቸው ጸሎቶች የትኞቹ ናቸው? ለ) እግዚአብሔር ለእርሱ መገዛትህንና እርሱን ማክበርህን ታሳይ ዘንድ እንድታከናውናቸው የጠየቀህ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
የክርስቶስ ጸሎት ስለ ራሱ የነበረውን ቁልፍ ግንዛቤ ያንጸባርቃል። አንደኛው፥ ስለ ማንነቱ የነበረው ግንዛቤ ነው። እርሱ እግዚአብሔር ወልድ ነው፤ ለአብ የሚገዛ ነው፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር አብ ጋር አንድ ነው።
ሁለተኛው፥ እርሱ በሰዎች ዘላለማዊ ሕይወት ላይ ሥልጣን አለው። ክርስቶስ ከአብ የተቀበላቸውና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ያመኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወትን ያገኛሉ። ሦስተኛው፥ በዚህ ክፍል የዘላለም ሕይወት ተብሎ የተጠራው ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው ክርስቶስን ወደ ምድር በላከው በእግዚአብሔር አብና ለሰው ልጆች ኃጢአት በሞተው በክርስቶስ ነው።
ለ. ጸሎት ስለ ማንነታችን ባለን ግንዛቤ ላይ ይመሠርታል። ክርስቶስ ለአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጸልዮአል። እነዚህ እውነቶች ዛሬም ለእኛ ይጠቅማሉ። አንደኛው፥ ደቀ መዛሙርት የሚባሉት እግዚአብሔርን «ያዩ» ናቸው። ክርስቶስ እግዚአብሔርን ለአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መገለጡን እንደ ተናገረ ሁሉ፥ መንፈስ ቅዱስ እኛን ወደ ክርስቶስ በሚያመጣን ጊዜ እግዚአብሔር አብ ማን እንደሆነ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነና እኛም እንዴት ከእነርሱ ጋር ልንዛመድ እንደምንችል በመግለጥ ይጀምራል። ሁለተኛው፥ ደቀ መዛሙርት ከዓለም «ተጠርተው የወጡ» ወይም የተለዩ ናቸው። ዓለም ከምትከተለው ሕይወት ስለ ተለየን፥ በዓለም የሚኖሩ ሰዎች ከሚከተሉት የሕይወት ዘይቤ ተለይተን እንኖራለን። በቀዳሚነት ግን እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንንና ሌሎቹ ግን ስላልሆኑ፥ በዚህ ተለይተናል።
ሐ. ጸሎት የታዛዥነት ሕይወት ምልክት ነው። ጸሎት በቤተ ክርስቲያን ወይም በቤታችን ብቻ የምንጸልየው ሳይሆን፥ ለዘለቄታው ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገው ግንኙነት ነው። ያ ግንኙነት ደግሞ የታዛዥነትን ሕይወት ይጠይቃል። አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከክርስቶስ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ለመጠበቅ መታዘዛቸው አስፈላጊ እንደ ነበረ ሁሉ፥ እኛም በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ልንመጣ የምንችለው በመገዛትና በመታዘዝ የተመላለስን እንደሆነ ነው።
መ. ክርስቶስ በጸሎቱ ጊዜ በቀዳሚነት የጠየቀው በደቀ መዛሙርቱ መካከል አንድነትና ስምምነት እንዲኖር ነበር። ክርስቶስ እግዚአብሔር በስሙ ኃይል እንዲጠብቃቸው ጠይቋል። ነገር ግን ክርስቶስ የጠየቀው ለአካላዊ ጥበቃ ወይም ከሰይጣን ስለሚደርስባቸው ጥቃት አልነበረም። እግዚአብሔር ደቀ መዛሙርቱን ከስደት ነፃ እንዲያደርጋቸው ወይም ቁሳዊ ሀብት እንዲሰጣቸው አልጠየቃቸውም። ክርስቶስ የጠየቀው ደቀ መዛሙርቱ እግዚአብሔር አብና ወልድ ያላቸውን ዓይነት አንድነትና ስምምነት እንዲኖራቸው ነው። ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው በፍቅርና በአንድነት መመላለሳቸው ክርስቶስ ከሰማይ በእግዚአብሔር የተላከ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆኑ ማረጋገጫ እንደሆነ ገልጾአል። አንድነታችን የእግዚአብሔር አብን፥ የእግዚአብሔር ወልድንና የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን አንድነት ማንጸባረቅ አለበት።
ክርስቶስ እግዚአብሔርን የጠየቀው ሁለተኛው የጸሎት ጥያቄ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት በቅድስና እንዲጠብቃቸው ነበር። ከዓለም በመለየት፥ ወደ ገዳም በመግባት ወይም ክርስቲያኖች ብቻ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ በመኖርና ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ባለማድረግ፥ የቅድስናን ሕይወት መኖር አይቻልም። ቅድስና የሚመጣው ለክርስቶስ በመታዘዝ ነው። የመታዘዝ ሕይወት የሚገኘው ደግሞ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት በማወቅ ነው። ከዓለም የምንለየው ክርስቲያን ካልሆኑት ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ባለማድረግ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት በመጠበቅ ብቻ ነው።
ሦስተኛው የጸሎት ጥያቄ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ፥ ሙሉ ክብሩን ወደምናይበት ሰማይ መሄድ እንድንችል ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከእግዚአብሔር ጋር በታዛዥነት ሕይወት ለመኖር ልናውቃቸው የሚገቡን የቃሉ እውነቶች ምንድን ናቸው? ለ) ኢየሱስ ካቀረባቸው ሦስት ጸሎቶች መካከል እኛ ልናደርገው የሚከብደን የትኛው ነው? ለምን? ሐ) ክርስቶስ ስለ ብዙ ነገሮች ሊጸልይልን ሲችል፥ በእነዚህ ሦስቱ ብቻ የተወሰነው ለምን ይመስልሃል? መ) የክርስቶስን ጸሎት እኛ ዘወትር ከምንጸልይባቸው ርእሶች ጋር በማነጻጸር ተመሳሳይነታቸውንና ልዩነታቸውን አውጣ። ጸሎትህ የኢየሱስን ጸሎት እንዲመስል ምን ለውጥ ማድረግ አለብህ?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)