- ክርስቶስ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ ብዙ ዓሣ ሰጠ (ዮሐ 21፡1-14)
ሐዋርያው ዮሐንስ መጽሐፉን የደመደመው በዮሐንስ 20፡30-31 ነው። ነገር ግን ስለ ኢየሱስ ታሪክ የጀመረውን ዘገባ ለመቋጨት ሌሎች ሁለት ታሪኮች ቀርተውት ነበር። የመጀመሪያው ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ዓሣን እንዴት በተአምር እንደ ሰጣቸው ነው። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ አዝዟቸው ነበር (ማቴ. 28፡10)። በገሊላ ሳሉ ድንገት በዚያ የተገኘ ይመስላል። የሚያደርጉትን ነገር በማጣታቸው ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ ዓሣ ለማጥመድ ሄዱ። ክርስቶስ መጀመሪያ ከእነዚህ ደቀ መዛሙርት አብዛኞቹን የጠራው ሌሊቱን በሙሉ ሲጥሩ አድረው ምንም ሊያጠምዱ ባልቻሉበት ወቅት በተአምር ብዙ ዓሣ እንዲይዙ በማድረግ ነበር። (ሉቃስ 5፡1-11 እንብብ።) አሁንም ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር የነበረውን ጊዜ ሌላ ተአምር በማድረግ ይደመድማል። ምንም ሊያጠምዱ ባልቻሉበት ወቅት ክርስቶስ መረባቸውን ከጀልባይቱ በተቃራኒ አቅጣጫ እንዲጥሉ አዘዛቸው። መረባቸው በዓሳዎች በተሞላ ጊዜ መጀመሪያ ዮሐንስ («ክርስቶስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር») በኋላም ሌሎች ደቀ መዛሙርት ክርስቶስን ለይተው አወቁት። በመጀመሪያው የዓሣ ማጥመድ ተግባር ወቅት ጴጥሮስ የክርስቶስን ልዩ ኃይል ተመልከቶ እንደ ሰገደለት ሁሉ፥ አሁንም መጀመሪያ ጴጥሮስ ከጀልባይቱ ወርዶ ወደ ክርስቶስ እየዋኘ መጣ። ጴጥሮስ ይህንን ያደረገው ለምን ነበር? አንደኛው፥ ለክርስቶስ የነበረውን ታላቅ ፍቅር የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው፥ ጴጥሮስ ክርስቶስን በመክዳቱ በጥፋተኝነት ስሜት ይሠቃይ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስን እንደሚወደው ለማሳየት ፈልጎ ነበር።
- ክርስቶስ ጴጥሮስን ይቅር አለው (ዮሐ. 21፡15-25)።
ጴጥሮስ ከዚህ በፊት በፈጸመው ስሕተት እንደሚያሠቃይ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። እርሱም ክርስቶስን እስከ ሞት ድረስ ለመከተል ቃል ቢገባም ከድቶታል። ክርስቶስ ይቅር ይለው ይሆን? ክርስቶስ ሌላ ዕድል ይሰጠው ይሆን? አሁንም በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ አገልግሎት ይኖረው ይሆን? ኢየሱስ በእርግጥ ይቅር እንዳለውና አሁንም በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ለማረጋገጥ ሲል፥ ጴጥሮስን በግል አነጋግሮታል። በኢየሱስና በጴጥሮስ መካከል ከተደረገው ውይይት የምንመለከታቸው ጠቃሚ ነገሮች አሉ።
ሀ. ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ከድቶት ስለነበር፥ አሁን ኢየሱስ ፍቅሩን ሦስት ጊዜ እንዲገልጽለት ጠየቀው።
ለ. ክርስቶስ በጴጥሮስ ፍቅር ላይ ያተኩራል። በዮሐ 21፡15 ላይ «ከእዚህ» የሚለው ምንን እንደሚያመለክት አናውቅም። ጴጥሮስ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ስለሚያውቀው የዓሣ ማጥመድ ሥራ ይሆን? ክርስቶስ ጴጥሮስ ከቀድሞ ሕይወቱ ይበልጥ እርሱን ይወደው እንደሆነ መጠየቁ ይሆን? ወይስ «ከእነዚህ» የሚለው ሌሎቹን ደቀ መዛሙርት የሚያመለክት ይሆን? ኢየሱስ ጴጥሮስን እየጠየቀ ያለው ከእነዚህ ደቀ መዛሙርት ይበልጥ ትወደኛለህ እያለው ይሆን? ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ እየጠየቀው ያለው በሕይወቱ ከምንም ነገር ወይም ከማንም ሰው በላይ የሚወደው እርሱን መሆኑን ነው።
ሐ. ክርስቶስ በጥያቄዎቹ ውስጥ ስለ ፍቅር የሚገልጹትን ቃላት ይለውጣል። ኢየሱስ «ትወደኛለህ» እያለ ለሁለት ጊዜ ሲጠይቀው የተጠቀመበት ቃል «አጋፔ» የሚለውን መለኮታዊ ፍቅርን የሚገልጸውን ቃል ነው። ለመጨረሻ ጊዜ ሲጠይቀው ደግሞ፥ «ፊሊዮ» የሚለውን ለወዳጆቹ ያለውን ፍቅር የሚገልጸውን ቃል ነው። ይህ ዮሐንስ ድግግሞሽን ለማስወገድ ሲል ያደረገው ወይም ክርስቶስ በሁለቱ መካከል እያነጻጸረ ስለመሆኑ ምንም የምናውቀው ነገር የለም። ምናልባት ዮሐንስ ሁለቱንም ቃላት የተጠቀመባቸው ተመሳሳይ አሳብ ለማስተላለፍ ሳይሆን አይቀርም።
መ. ኢየሱስ ጴጥሮስን ትሑት ሊያደርገው ተነሣ። ጳጥሮስ «ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ» በሚል የልበ ሙሉነት ዓረፍተ ነገር ቢጀምርም፥ መጨረሻ ላይ የተናገረው አሳብ ግን የለሰለሰ ነበር። «ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህም አንተ ታውቃለህ።» ጴጥሮስ ፍቅሩን ከሌሎች ጋር ለማነጻጸር አልሞከረም። ቀደም ሲል ሌሎች ደቀ መዛሙርት በሙሉ ቢለዩትም እንኳ፥ እርሱ ግን እስከ መጨረሻው እንደሚወደው በትምክሕት ተናግሮ ነበር (ማቴ. 26፡33)። አሁን ሊያደርግ የሚችለው ነገር ቢኖር ልቡን መርምሮ በሚችለው አቅም ክርስቶስን እንደሚወድ መግለጽ ብቻ ነበር። ይህ ከሌሎች መብለጡን ወይም ማነሱን አያውቅም። ለኢየሱስም ሊነግረው የፈለገው በሕይወቱ ከምንም በላይ እንደሚወደው ነበር።
ሠ. ኢየሱስ ለጴጥሮስ ዐቢይ አገልግሎት ሰጠው። ይኸውም የኢየሱስ በጎች እረኛ እንዲሆን ነበር። በጎቹ የክርስቶስ እንጂ የጴጥሮስ አይደሉም። (መሪዎች ሁሉ ይህንን እጅግ ጠቃሚ እውነት መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የቤተ ክርስቲያን ምእመናን የራሳችን ወይም የቤተ እምነታችን ንብረቶች አይደሉም። የመሪዎችም አይደሉም። ንብረትነታቸው ለክርስቶስ ስለሆነ ለእርሱ ልንከባክባቸው ይገባል) መልካም እረኛ የሆነው ክርስቶስ በጎቹን እንዴት እንደሚመግብ ይገልጻል። ይህንን የሚያደርገው እንደ ጴጥሮስ ከምእመናኑ መካከል በሚያስነሣቸው መሪዎች አማካይነት ነው። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ ኃይላቸውን በወንጌል ስርጭት ላይ ስለሚያውሉ፥ ምእመናንን መመገብ እንዳለባቸው ይዘነጋሉ። የታመመና የኮሰሰ በግ ለምን ይጠቅማል? ስለሆነም፥ ጴጥሮስ የእግዚአብሔርን መንጋ መመገብ እንዳለበት ግልጽ ተደረገለት።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የክርስቶስን በጎች መመገብ ለምን ያስፈልጋል? ለ) የጠፉትን በመፈለግና የኢየሱስን በጎች በመመገብ መካከል ሚዛናዊ ለመሆን አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ በጎችዋን የምትመግብባቸውን መንገዶች በምሳሌነት ጥቀስ። ጥሩ ተግባር እየተከናወነ ይመስልሃል? ለምን? መ) በጎቹን በተሻለ ሁኔታ ለመመገብ ምን ቢደረግ ይሻላል ትላለህ?
ክርስቶስ ለጴጥሮስ የሚነግረው አንድ ተጨማሪ አሳብ ነበረው። ለጴጥሮስ እንዴት እንደሚሞት ነገረው። ባረጀ ጊዜ ጴጥሮስ ሕይወቱን እንደ ልብ ማዘዝ አይችልም። ይልቁንም፥ እስረኛ ሆኖ በሌሎች ሰዎች ቁጥጥር ሥር ይውላል። ከዚያ በኋላ ጴጥሮስን ወደማይፈልገው ስፍራ ይወስዱታል። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚለው፥ ጴጥሮስ በሮም በኔሮ ዘመን ታስሮ ነበር። የሚሞትበት ጊዜ ሲደርስ ወደሚሰቀልበት ስፍራ ተወስዶ ተገድሏል። እንደ ክርስቶስ ራሱን ከፍ አድርጎና እጆቹን ዘርግቶ ለመሰቀል ስላልፈለገ፥ ወደ ታች ዘቅዝቀው እንዲሰቅሉት ለመናቸው። እንደ ጌታው ራሱን ወደ ላይ አድርጎ ለመሰቀል ብቁ ነኝ ብሎ አላሰበም ነበር።
ከክርስቶስና ከጴጥሮስ ኋላ ክርስቶስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር (ዮሐንስ) ነበር። ጴጥሮስ አሰቃቂ ሞት እንደሚጠብቀው ካወቀ በኋላ፥ የዮሐንስ አሟሟት እንዴት እንደሚሆን ክርስቶስን ጠየቀው። ጴጥሮስ ይህን ሲል፥ ኢየሱስ ማድላት የለብህም፤ እኔ እንደዚህ የምሠቃይ ከሆነ ሁሉንም በእኩል ማየት አለብህ። ስለሆነም፥ ዮሐንስም በተመሳሳይ መንገድ መሞት አለበት። አይደል? ማለቱ ነበር። ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ለእግዚአብሔር ማቅረብ የለብንም። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው ያለው ዕቅድ የተለየ ነው። አንዳንዶችን በቀላል ሌሎችን ደግሞ በከባድ ሁኔታ ይወስዳቸዋል። ክርስቶስ ጌታ ስለሆነ፥ እያንዳንዳችንን የሚወሰድበትን ሁኔታ የሚመርጠው እርሱ ነው። ከቶውንም ራሳችንንም ሆነ ሕይወታችንን ከሌሎች ጋር ማነጻጸር የለብንም። ይልቁንም፥ በታዛኝነትና ታማኝነት ክርስቶስን እየተከተልሁ ነኝ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን።
ዮሐንስ ይህንን ታሪክ በመጽሐፉ ውስጥ ያካተተው ሌላም ምክንያት ስለነበረው ነው። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፥ ክርስቶስ ዮሐንስ ከመሞቱ በፊት ይመለሳል እየተባለ ይወራ ነበር። ዮሐንስ ይህን መጽሐፍ በሚጽፍበት ጊዜ ቢያንስ የ70 ዓመት አዛውንት ነበር። ስለሆነም፥ የሚሞትበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። አንዳንድ ክርስቲያኖች በዚህ ጊዜ ክርስቶስ የሚመለስበት ጊዜ ተቃርቧል ብለው ያስቡ ነበር። ዮሐንስ ግን ክርስቶስ ዮሐንስ ከመሞቱ በፊት እመለሳለሁ እንዳላለና ዮሐንስ ከመሞቱ በፊት ቢመለስ ወይም ባይመለስ ይህ ጴጥሮስን ሊያሳስበው እንደማይገባ ገለጻለት።
የውይይት ጥያቁ፡- እግዚአብሔር እነርሱንና ሌሎችን የሚመለከትበትን ሁኔታ ከሌሎች ጋር ማነጻጸሩ ለብዙዎች ምን ያህል ቀላል እንደሆነ አብራራ። እንደዚህ ዓይነት ማነጻጸር የሚያስከትለው ውጤት ምንድን ነው?
ክርስቶስ ሁለት ጊዜ ጴጥሮስ እንዲከተለው ጠይቆታል። ወደ ሌሎች ሰዎች በምንመለከትበት ጊዜ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ቢክዱህ እንኳ እኔ አልክድህም ሲል እንደ ተናገረው ጴጥሮስ፥ ከሌሎች እንሻላለን ብለን እንኩራራ ይሆናል። ወይም ደግሞ ሌላ ሰው ከእኔ በላይ እየተጠቀመ ነው ብለን በማስብ በቅንዓት ልንብሰለሰል እንችላለን። ይህም የዮሐንስ አሟሟት እንደ እኔ መሆን አለበት ሲል ጴጥሮስ እንደ ተከራከረው ዓይነት ነው። ዳሩ ግን ዓይኖቻችን በክርስቶስ ላይ ማረፍ አለባቸው። ልናነሣቸው የሚገቡን ጥያቄዎችም፥ «በእውነት ክርስቶስን እንደ ደቀ መዛሙርት እየተከተልን ነን? ክርስቶስን ከማንም ወይም ከምንም በላይ እንወደዋለንን? በታዛዥነት እየተመላለስን ክርስቶስ የሚጠይቀንን እናደርጋለን ወይ?» የሚሉ መሆን አለባቸው። በፍርድ ቀን በክርስቶስ ፊት በምንቀርብበት ጊዜ፥ በትምህርት ቤቶች እንደሚደረገው በአማካይ ውጤት አይደለም ውጤት የሚሰጠን። እኛን ከሌሎች ጋር በማነጻጸር ፈንታ፥ እርሱ ከሚፈልገው ጋር ያነጻጽረናል።
ዮሐንስ ስለ ክርስቶስ ተጨማሪ አሳቦችን ለመናገር ይችል ነበር። እርሱ እንዳለው፥ አንድ ሰው የክርስቶስን ጠቅላላ ታሪክና የታሪኮቹን ቅደም ተከተል ለመዘርዝር ቢፈልግ፥ ዓለም የማይበቃቸው እጅግ ብዙ መጻሕፍት ሊጻፉ ይችሉ ነበር። ነገር ግን ዮሐንስና መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንድናገኝ የፈለገውን እውቀት ሰጥተውናል። ይህም እውቀት በክርስቶስ ለማመንና ለመከተል በቂ ነው። ምንም እንኳ የበለጠ ለማወቅ ፍላጎቱ ቢኖረንም፥ የብዙዎቻችን ትልቁ ችግር የምናውቀውን ከሥራ ላይ ለማዋል አለመቻል ነው። እምነትህ ጠንካራ ነው? የክርስቶስ ተከታይ ነህ? ከእነዚህ በላይ ክርስቶስን ትወደዋለህ?
የውይይት ጥያቄ፡- ከማንኛውም ሰው ወይም ነገር በላይ ክርስቶስን ትወድ እንደሆነ መንፈስ ቅዱስን በጸሎት ለመጠየቅ ጊዜ ይኑርህ። ሕይወትህን ለክርስቶስ እንደገና አሳልፈህ ስጥ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)