የሐዋርያት ሥራ መግቢያ

«እንደ መጀመሪያው ምእተ ዓመት ቤተ ክርስቲያን ብንሆን ኑሮ ደስ ይለኝ ነበር። በዚያን ጊዜ የነበሩት ተአምራት፥ በምእመናን መካከል የነበረው ፍቅርና ኅብረት የተለየ ነበር። ከሁሉም በላይ፥ እንደ ቀድሞዎቹ ሐዋርያት በልሳን ብናገር ትልቅ ነገር ነበር። አሁን የሚያስፈልገን እንደዚያች የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን እንድንሆን የሚያደርገን መነቃቃት (ሪቫይቫል) ነው።»

የውይይት ጥያቄ:- እንደዚህ ዓይነት አባባሎችን የሰማህበትን ሁኔታ ግለጽ። እነዚህ አገላለጾች ትክክል ይመስሉሃል ወይስ ስሕተት? መልስህን አብራራ።

ሁላችንም ከላይ የተጠቀሱትን ዓይነት አሳቦች ሰምተናል። የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ በምናነብበት ጊዜ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ከዛሬይቱ እንደምትለይ እንረዳለን። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከተጻፈባቸው ምክንያቶች አንዱ ቤተ ክርስቲያን ምን መምሰል እንዳለባት ፍጹማዊ ምሳሌ ለመስጠት ነው። ቤተ ክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ ኃይልና አገልግሉት የሚገለጥባት መሆን አለባት፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚታይባትና ፍቅር የሚሰበክባት፥ በድፍረት የተሞላ ምስክርነት የሚሰጥባት፥ እንዲሁም ወንጌል ወዳልተሰበክበት አካባቢ የሚኬድባት፥ የቃሉ ትምህርትና ጸሎት የሚደረግባት ስፍራ ልትሆን ይገባል። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ከዛሬይቱ ያን ያህል የተለየች ነበረች? የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በምናጠናበት ጊዜ መከፋፈል የተለመደ ተግባር መሆኑን እንረዳለን። ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን የሚገኙ የሐሰት ትምህርቶች፥ ቅንዓት፥ ትዕቢት፥ ውሸት ያኔም ነበሩ። ስለ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ፍጹማዊ ምሳሌ እግዚአብሔርን ማመስገን ሲኖርብንም፥ ባለፉት ነገሮች ተወጥረን ስለ ዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ስብከት፥ ጸሎት፥ ምስክርነት፥ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት፥ የመንፈስ ቅዱስ መገኘትና፥ የእግዚአብሔር ኃይል መታየት እግዚአብሔር በጥንቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለመመልከት የፈለጋቸው ነገሮች ዛሬም የማይሞከሩ አይደሉም። ያጣነው ነገር ቢኖር እግዚአብሔርን የሚያስከብር ዓይነት ሕይወት ለመኖር አለመቻላችን ነው።

የሐዋርያት ሥራ እንደ ወንጌላት ሁሉ ታሪካዊ መጽሐፍ ነው። ክርስቶስ ካረገበት አንሥቶ ጳውሎስ በሮም እስከ ታሰረበት ጊዜ ድረስ ያለውን የቀድሞይቱን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያወጋል። ይህም ከ30 ዓ.ም. እስከ 64 ዓ.ም ድረስ ያለውን ዘመን ይሸፍናል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከወንጌላቱ ተከትሎ እንዲገባ የተደረገው የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስለሚቀጥል ነው። ነገር ግን የሐዋርያት ሥራ ለተለያዩ መልእክቶች እንደ ዳራ (background) ያገለግላል። የሐዋርያት ሥራ ብዙዎቹ የአዲስ ኪዳን መልእክቶች የተጻፉበትን ታሪካዊ ዘመን ይሸፍናል። መጽሐፉ ለመልእክቶቹ ታሪካዊ ዳራ በመሆን ያገለግላል። መልእክቶቹም ቀጣዩ የአዲስ ኪዳን ሥነ ጽሑፍ ዐቢይ ክፍል ሆነው ተመድበዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ሐዋርያት ሥራ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ ጸሐፊው፥ መጽሐፉ ስለ ተጻፈበት ዘመን፥ መጽሐፉ ስለ ተጻፈበት ምክንያት ያገኘኸውን መረጃ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋ. 1፡1-2 እና ሉቃስ 1፡1-4 እንብብ። ሀ) እነዚህ ሁለት መጻሕፍት የተጻፉት ለማን ነበር? ለ) በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ጸሐፊው ቀደም ሲል መጽሐፍ ለመጻፉ ምን መረጃ ይሰጣል? ያ መጽሐፍ ስለ ምን የሚናገር ነበር? ሐ) ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ግንዛቤህ፥ በሉቃስና በሐዋርያት ሥራ ታሪኮች መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?

ከጥንት ጀምሮ የሐዋርያት ሥራ ከጳውሎስ ጋር አብሮ ያገለግል በነበረው ሉቃስ እንደ ተጻፈ ይታመናል። ዛሬም አብዛኞቹ ምሑራን የሉቃስ ወንጌልና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጸሐፊ አንድ ሰው እንደሆነ ይስማማሉ። ስለሆነም፥ የሉቃስ ወንጌልን የጻፈው ሉቃስ ከሆነ፣ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍንም የጻፈው እርሱ ራሱ ነው ማለት ነው። አማኞቹ ምሑራን ሉቃስና የሐዋርያት ሥራ የአንድ ትልቅ መጽሐፍ ሁለት ክፍሎች እንደሆኑ ያስባሉ። ክፍል አንድ የሆነው ሉቃስ ስለ ክርስቶስ ሕይወት ይተርካል። ክፍል ሁለት የሆነው የሐዋርያት ሥራ ክርስቶስ የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን እድገት ያብራራል። በ170 ዓ.ም. የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሉቃስ ወንጌልና የሐዋርያት ሥራ በሉቃስ መጻፋቸውን ገልጸዋል።

ከሐዋርያት ሥራ እንደምንመለከተው፥ ጸሐፊው የታሪኩ አካል ነው። ጸሐፊው፥ የድርጊቱ ተካፋይ መሆኑን ለማመልከት፥ «እኛ» እያለ ጽፎአል (የሐዋ. 16፡10-16፤ 20፡5-21፣18፤ 27፡1-28፡16)። በሌሎች ስፍራዎች ጸሐፊው «እነርሱ» እያለ ጽፎአል። «እኛ» ከሚሉ ምንባቦች አንዱ በታሪኩ መጨረሻ አካባቢ በሮም የተከሰተውን ሁኔታ ይገልጻል። በዚህ ጊዜ ከጳውሎስ (ምናልባትም ከሮም) የተጻፉት አያሌ መልእክቶች የሉቃስን ሰላምታ ይጨምራሉ (ፊልሞን 23-24 እና ቆላ. 4፡10-14 አንብብ።) ይህም ሉቃስ የሐዋርያት ሥራን ከሮም ጽፎታል የሚለውን አመለካከት ይበልጥ ያጸናል።

ስለ ሉቃስ መጽሐፍ ባጠናንበት ወቅት፥ ሉቃስ ታሪኮቹን በጥንቃቄ መርምሮ እንደ ጻፈ ተመልክተናል። ሁኔታው አመቺ በሚሆንበት ጊዜ፥ ክስተቶቹ ሲፈጸሙ የተመለከቱትን የዓይን ምስክሮች አነጋግሯል። ይህ ሳይቻል ሲቀር ደግሞ ተአማኒነት ካላቸው ሰዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። በዚህ ዓይነት የክርስቶስን ታሪክ ከልደቱ እስከ ዕርገቱ ድረስ ዘግቧል። ሉቃስ፥ ክርስትና እንዲያድግና ጠንካራ ሆኖ እንዲኖር ከተፈለገ፥ ስለ መሥራቹ ግልጽ ግንዛቤ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ተረድቶ ነበር።

ሉቃስ የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ የጻፈው በዚሁ ተመሳሳይ መንገድ ነው። ቴዎፍሎስና ሌሎችም አሕዛብ ይህ «መንገድ» ወይም ክርስትና የተባለ አዲስ እንቅስቃሴ ከየት እንደ መጣ ለማወቅ ይፈልጉ ነበር። ስለሆነም፥ ሉቃስ የክርስትናን ታሪካዊ ዘገባ ሁለተኛ ክፍል ጻፈ። በዚህ ጽሑፍ ከ30 እስከ 64 ዓ.ም. አካባቢ የተፈጸሙትን ዐበይት ክስተቶች አስፍሯል። በእነዚህ ሁለት መጻሕፍት አማካይነት፥ ክርስትና እንዴት እንደተ ጀመረና በሮም መንግሥት ውስጥ እንዴት እንደ ተስፋፋ እንረዳለን።

ሉቃስ የጻፈው ለማን ነው?

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የተጻፈው እንደ ሉቃስ ወንጌል ሁሉ ቴዎፍሎስ ለተባለ ሰው ነው። ምሑራን ቴዎፍሎስ ማን እንደሆነ አለማወቃቸውን ቀደም ብለን ተመልክተናል። አንዳንድ ምሑራን ይህ ስም በተምሳሌታዊ መልኩ ክርስቲያኖችን እንደሚያመለክት ቢናገሩም፥ ቴዎፍሎስ አንድ ሀብታምና የተማረ ግሪካዊ ሳይሆን አይቀርም። ሉቃስ ቴዎፍሎስን ያውቀው ነበር፡፡ አንዳንዶች ሉቃስ ወደ ክርስቶስ ከመራው በኋላ፥ በመንፈሳዊ ሕይወቱ እንዲያድግ እየረዳው ሳይሆን አይቀርም ይላሉ። ከዚህ የበለጠ ትክክለኛ የሚመስለው አሳብ ቴዎፍሎስ ሉቃስን በገንዘብ የሚረዳው ሰው ነው፡፤ የጥንቷም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዲጻፍና በሮም ግዛት ሁሉ እንላለፋፋ የሚፈልግ ሰው ነው የሚለው ነው።

የሉቃስ ዋነኛ ዓላማ ግን ይህ «መንገድ» የተባለው አዲስ ሃይማኖት እንዴት ከገጠሪቱ ፍልስጥኤም ወደ ሮም እንዳደገ ለክርስቲያኖችና ስለ ጉዳዩ ለማወቅ ፍላጎት ላላቸው አሕዛብ ማብራራት ነበር። ምናልባት ሉቃስ ለንጉሡም፥ ክርስትና የሮምን መንግሥት እንደማይፈታተን ለመግለጽ የፈለገ ይመስላል። ክርስትና በይሁዲነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑና እንደ ሄሮድስና ጲላጦስ ያሉ የሮም ባለሥልጣናት ከክርስትና ምንም ክፋት ስላላዩ፥ የሮም መንግሥት ክርስቶስ አደገኛ ነው ብሎ በማሰብ ክርስቲያኖችን እንዳያሳድድ ነበር። እንደ ጳውሎስ ያሉትን ሰዎች ማበረታታት እንጂ ማሳደድ አይገባም ነበር።

ሉቃስ መጽሐፉን የጻፈበት ዘመንና ቦታ

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋርያት ሥራ 28፡30 አንብብ። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በተደመደመበት ወቅት ጳውሎስ የት ነበር?

የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ መጀመሪያ የጠቀሰው ጀስቲን ማርቲር የተባለ የቤተ ክርስቲያን መሪ ነው። ጊዜውም በ140 ዓ.ም. አካባቢ ነበር። ይህም መጽሐፍ ከዚህ ጊዜ ቀደም ብሎ እንደ ተጻፈ ያመለክታል። መጽሐፉ ከ80-130 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት እንደ ተጻፈ የሚናገሩ ምሑራን አሳብ ተቀባይነት ያለው አይመስልም። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ታሪክ የሚያበቃው በ64 ዓ.ም. አካባቢ ነው። ያኔ ጳውሎስ ገና ከሮም እስር ቤት አልተለቀቀም ነበር። ለመለቀቅ ግን እየተጠባበቀ ነበር። መጽሐፉ የተጻፈው ከዚህ ጊዜ በኋላ ቢሆን ኖሮ፥ ጸሐፊው ስለ ሮም መቃጠል፥ በዚያ ስለነበረው የክርስቲያኖች ስደት፥ በ67 ዓ.ም. የተፈጸመውን የጴጥሮስና የጳውሎስ መገደል፥ በ70 ዓ.ም. የተካሄደውን የኢየሩሳሌምን መውደቅ ይጠቅስ ነበር። ስለሆነም፥ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጳውሎስ ከሮም እስር ቤት ለመለቀቅ በሚጠባበቅበት ከ62-64 ባለው ጊዜ ተጽፎ ተጠናቅቋል ማለት ይቻላል።

የመጽሐፉ ጸሐፊ ሉቃስ እንደሆነና፥ መጽሐፉንም የጻፈው ጳውሎስ እስር ቤት በነበረባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ነው የሚለው አሳባችን ትክክል ከሆነ፥ መጽሐፉ ሊጻፍ የቻለው በሮም ነው። ጸሐፊው በዚህ ጉዞ ከቂሣሪያ ወደ ሮም ከጳውሎስ ጋር አብሮ እንደ ነበረ፥ በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ ራሱንም ጨምሮ «እኛ» እያለ ካቀረበው ጽሑፍ ለመረዳት ይቻላል።

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ርእስ

መጀመሪያ ሉቃስ ይህን መጽሐፍ ሲጽፍ «የሐዋርያት ሥራ» የሚል ርእስ የሰጠው አይመስልም። ርእሱ የተሰጠው ከጊዜ በኋላ ከሌሎች መጻሕፍት እንዲለይ ለማድረግ ታስቦ ነው። የሐዋርያት ሥራ በዋነኛነት የሚያተኩረው በጳውሎስና በጴጥሮስ ላይ ነው። ሌሎች ሐዋርያት ብዙም ስላልተጠቀሱ፥ በዚህ ጊዜ ምን እንዳደረጉ አይታወቅም። ስለሆነም፥ አንዳንድ ምሑራን «የሐዋርያት ሥራ» ለመጽሐፉ ተስማሚ ርእስ አይደለም ይላሉ። ምናልባትም ሉቃስ ሌሎች ሐዋርያት ለሠሩት ሥራ ጴጥሮስንና ጳውሎስን ምሳሌ አድርጎ እየተጠቀመ ይሆናል። ስለሆነም፥ መጽሐፉ እግዚአብሔር ወንጌሉን ለማስፋፋት ሌሎች ሐዋርያትን ሁሉ እንዴት እንደ ተጠቀመ ያሳያል። ሐዋርያት ሁሉ እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዳልኖሩ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል። እንዳንዶች እስከ ምሥራቅ እስያ ድረስ ሲሄዱ፥ ሌሎች ከግብጽ በስተ ደቡብና ከዚያም አልፈው ተጉዘዋል። ወደ ሰሜን ሩሲያ የሄዱም ነበሩ። አንዳንዶች የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት አማካይነት ባከናወናቸው ተግባራት ላይ ስለሚያተኩር፥ «የመንፈስ ቅዱስ» ሥራ ሊባል ይገባዋል ይላሉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2 thoughts on “የሐዋርያት ሥራ መግቢያ”

Leave a Reply

%d bloggers like this: