በበዓለ ኀምሳ ቀን የመንፈስ ቅዱስ መውረድ (የሐዋ. 2፡1-13)

ቤተ ክርስቲያን መደበኛ ሆና የተመሠረተችው መቼ ነበር? የኢየሱስ ወደ ምድር መምጣት፥ የክርስቶስ ንጉሣዊ አገዛዝ በሰዎች ሕይወት ውስጥ መጀመሩን ቢያበስርም፥ የቤተ ክርስቲያን አዲስ ምዕራፍ በመደበኛነት የተከፈተው ግን፥ መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ሁሉ ላይ በወረደበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።

አይሁዶች የበዓለ ኀምሳን (የሳምንታት ወይም የመኸር በዓልም ይባላል) ከፋሲካ በዓል 50 ቀናት በኋላ ያከብሩ ነበር። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት 12ቱን ጨምሮ፥ በሙሉ በአንድ ስፍራ ተሰብስበው የነበሩበት ሳይሆን አይቀርም። ከእነዚህ ምንባቦች ምን እንማራለን?

ሀ. መንፈስ ቅዱስ በነፋስ ታጅቦ መጣ። በዕብራይስጥ፥ በግሪክና በአማርኛ ቋንቋ «ነፋስ» እና «መንፈስ» የሚሉት ቃሎች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን፥ ነፋስ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው። (ሕዝ 37፡9፤ 14፤ ዮሐ 3፡8 አንብብ)። ነፋስ የእግዚአብሔር ኃይልና መገኘት ምሳሌ ነው። ለዚህም ነው መንፈስ ቅዱስ በኃይለኛ የነፋስ ኃይል ታጅቦ የመጣው።

ለ. «እሳትም» ነበረ። በብሉይ ኪዳን እሳት የእግዚአብሔር መገኘት ምሳሌ ነው። ሙሴ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ሲገናኘው የሚቃጠል ቁጥቋጦ ተመለከተ (ዘፍ 18፡2)። በምድረ በዳ የእግዚአብሔር መገኘት በእሳት ዐምድ ተመስሏል (ዘፀ. 3፡21)። ለሕዝቡ በሚሰጠውም ራእይ ውስጥ እሳት ይኖራል (ሕዝ 1፡27 ራእይ 1፡14-15)። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በሕዝቡ መሀል ነበር። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔርን ህልውና በግልጽ ለማሳየት መንፈስ ቅዱስ በእሳት ተገለጠ። ሉቃስ እንደ ጻፈው፥ አንድ ትልቅ የእሳት ኳስ ወደ ክፍሉ ገብቶ በመከፋፈል በእያንዳንዱ ደቀ መዝሙር ላይ ተቀመጠ። ይህም መንፈስ ቅዱስ ለእያንዳንዱ ደቀ መዝሙር መሰጠቱን በግልጽ ያመለክታል።

ሐ. እያንዳንዱ ደቀ መዝሙር በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ በልሳን ይናገር ጀመር። ስልሳን መናገራቸው ሕይወታቸው እንደ ተለወጠ የሚያመለክት ነበር። ነገር ግን ልሳን ለምን አስፈለገ? የመንፈስ ቅዱስን መገኘት ከልሳን ጋር የሚያያይዝ የብሉይ ኪዳን መረጃ የለንም። ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስ መገኘት ትንቢትን ከመናገር ጋር ይዛመዳል (ኢዩ 2፡28-32 አንብብ)። ምናልባትም በልሳን መናገራቸው አገልግሎታቸው የተለያዩ ብዙ ቋንቋዎች ወደሚነገርባቸው ሕዝቦች፥ ወንጌልን እንደሚወስድ የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም፡፡ እግዚአብሔር ለእነርሱ መንፈስ ቅዱስን የሰጠበት ዋነኛው ምክንያት፥ ለብዙ አገር ሕዝቦች ወንጌልን በሚመሰክሩበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ኃይልን እንዲሰጣቸው ነበር።

መ. ደቀ መዛሙርቱ የተናገሯቸው ልሳናት፥ ሰዎች የሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች ነበሩ። ሉቃስ በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ለማክበር ወጥተው ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በቋንቋቸው ሲናገሩ የሰሙትን ብዙ የአሕዛብ ዓለም አካባቢዎች ዘርዝሯል። 

በልሳን በተናገሩበት ጊዜ ስለሆነው ነገር ቢያንስ አራት ነገሮችን ልብ ማለት ያስፈልጋል።

እንደኛው፥ ከሌሎች የመንፈስ ቅዱስ ሙላቶች ሁሉ ይለያል። ለዚህም ምክንያቱ ነፋስ፥ ድምፅና እሳት መኖሩ ነው። ይህ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ መሞላታቸውን በትክክል ተረድተው በጥርጣሬ እንዳይወጡ ያደረገበት መንገድ ይመስላል። ከዚያ በኋላ የተከሰተው የመንፈስ ቅዱስ መምጣት ሁሉ እንደዚህኛው አልሆነም። ስለሆነም፥ ዛሬ መንፈስ ቅዱስ ወደ አማኞች የሚመጣው በበዓለ ኀምሳ ቀን በመጣው መንገድ መሆን አለበት ልንል አንችልም።

ሁለተኛው፥ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው በልሳን ተናግረዋል። በኋላ ጳውሎስ በልሳን መናገር ለሁሉም ሳይሆን ለተወሰኑ አማኞች የሚሰጥ የጸጋ ስጦታ እንደሆነ አስተምሯል (1ኛ ቆሮ. 12፡27-31)። ስለሆነም፥ ሉቃስ የገለጸው የተለየ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ነበር። ሉቃስ መንፈስ ቅዱስ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉም አማኞች በልሳን እንደሚናገሩና ትንግርታዊ ምልክት እንደሚከሰት እየገለጸ አይደለም።

ሦስተኛው፥ አይሁዶች እንደገና መንፈስ ቅዱስን በተለየ አስደናቂ መንገድ ሲቀበሉ አንመለከትም። ስለሆነም፥ ይህ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለነበሩት አይሁዶች የተሰጠ ልዩ ገጠመኝ ይመስላል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር እንደምንመለከተው፥ እያንዳንዱ አዲስ ሕዝብ መንፈስ ቅዱስን በሚቀበልበት ጊዜ አስደናቂ ሁኔታዎች ተከስተዋል። ይህም እያንዳንዱ ሕዝብ በእኩል ደረጃ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ተቀባይነትን እንዳገኘና በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተሞላ ክርስቲያኖች ሁሉ ያውቁ ዘንድ ነው።

ስለ መንፈስ ቅዱስ፥ አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ እንዴት እንደሚሞላ፥ ብሎም የመገኘቱ ምልክት ምን እንደሆነ በትክክል ለመረዳት ከፈለግን፥ በጳውሎስና በሌሎች ሐዋርያት መልእክቶች ውስጥ የተጻፈውን አሳብ በጥንቃቄ መመርመር አለብን። ለምሳሌ፥ ጳውሎስ በልሳን ባይናገሩም እንኳ ክርስቲያኖች ሁሉ መንፈስ ቅዱስን መቀበላቸውን በግልጽ አመልክቷል (ሮሜ 8፡9ን ከ1ኛ ቆር. 12፡27-31 ጋር አመሳክር።) 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: