በበዓለ ኀምሳ ዕለት ጴጥሮስ ያቀረበው ስብከት (የሐዋ. 2፡14-41)

ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ፥ በተመዘገቡት ልዩ ልዩ ስብከቶች አማካይነት ክርስቲያኖችን ለማስተማር ይፈልጋል። የጴጥሮስ፥ የእስጢፋኖስና የጳውሎስ ስብከቶች የሐዋርያት ሥራን ብዙውን ክፍል ሸፍነዋል። እነዚህ የጥንት ሐዋርያት ስለ ክርስቶስ ምን እንዳስተማሩ፥ እንዴት እንደ መሰከሩና ለተለያዩ ሰዎች እንዴት ወንጌሉን እንዳብራሩ የሚያመለክቱ ምሳሌያዊ (ሞዴል) ስብከቶች ናቸው። እነዚህን ስብከቶች በጥንቃቄ በማነጻጸር የሚከተሉትን አሳቦች ልናገኝ እንችላለች። 1) የምስክርነት ዋናው ነገር ስለ ክርስቶስ ማንነት፥ በመስቀል ላይ ስላከናወነው ተግባርና ሰዎች ለመዳን በእርሱ ማመን እንዳለባቸው ማብራራት ነው። 2) የሚቀርበው መረጃ እንደ አድማጩ ይለያያል። ለምሳሌ፥ ጴጥሮስና ጳውሎስ ለአይሁዶች በሚሰብኩበት ጊዜ፥ ሁል ጊዜም ክርስቶስ የብሉይ ኪዳንን ትንቢቶች በፈጸመበት ሁኔታ ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል። ነገር ግን ብሉይ ኪዳንን ለማያውቁ አሕዛብ ሲሰብኩ የፍጥረት ምሳሌዎችንና የአንዳንድ ታዋቂ ጥንታዊ ፈላስፎችን አሳቦች ላይለውጡ ተጠቅመዋል።

የጴጥሮስ ስብከት የጥንት ክርስቲያኖችን እምነት ያብራራል።

ሀ. አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል። የመንፈስ ቅዱስ መምጣት በኢዩኤል 2፡28-32 ላይ ለተነገረው ትንቢት ፍጻሜ ነበር። በዚህ ስፍራ እግዚአብሔር መንፈሱን የጾታ፥ የዕድሜ ወይም የኢኮኖሚ ደረጃ ገደብ ሳያደርግ ለሰዎች ሁሉ እንደሚሰጥ ተናግሮ ነበር። ይህ መንፈስ ቅዱስ ወደ መሪዎች ብቻ ይመጣ ከነበረበት የብሉይ ኪዳን ዘመን የተለየ ነው።

ለ. የስብከቱ ማዕከል (እምብርት) ሁል ጊዜም የክርስቶስ ሞት፥ ትንሣኤና ዕርገት ነው። ጴጥሮስ ስብከቱን የሚሰሙት አይሁዶች ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደሚያውቁ ተናግሯል።

  1. በእግዚአብሔር እንደ ተላከ የሚያረጋግጡትን፥ የኢየሱስን ተአምራትና የሕይወት ፍሬዎች አይተዋል።
  2. አይሁዶች ስለሞቱ ያውቁ ነበር። ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ ሞት ሲናገር፥ የሰውን ኃላፊነትና የእግዚአብሔርን ሉዓላዊ ዕቅድ ገልጾአል። የክርስቶስ ሞት የእግዚአብሔር ዕቅድ አካል ቢሆንም፥ አይሁዶች በክርስቶስ ላይ ለፈጸሙት የስቅለት ተግባር ተጠያቂ ናቸው።
  3. አይሁዶች ስለ ትንሣኤው ሰምተዋል። ጴጥሮስ ከክርስቶስ ሞት ይልቅ በትንሣኤው ላይ ትኩረት ሰጥቷል። ከብሉይ ኪዳንና እነርሱም በዓይናቸው ካዩት ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ሕያው እንጂ ሙት እንዳልሆነ ለአይሁዶች አረጋግጠውላቸዋል።
  4. ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ ዕርገት በሚያብራራበት ወቅት፥ አሁን ክርስቶስ በሰማይ ተቀምጦ በሚገኝበት የከበረ ስፍራ ላይ አተኩሯል። ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱስ ምንጭ ብቻ ሳይሆን፥ አምላክም ነው። እርሱ ዳዊት በመዝሙር 2፡34 ላይ የጠቀሰው ጌታ ነው።

ሐ. ለአድማጮች የቀረበ የውሳኔ ጥሪ

  1. ይህ ውሳኔ ስለ ክርስቶስ ማንነት ትክክለኛ እውቀትን ማካተት አለበት። ጴጥሮስ ክርስቶስ ጌታና በብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃል የተሰጠው መሢሕ እንደሆነ፥ ለአይሁድ ገልጾአል። ስለ ክርስቶስ ማንነት በትክክል ካላወቁ የሚያድን እምነት ሊያገኙ አይችሉም ነበር። የሚያድነው እምነት ሳይሆን፥ በክርስቶስ ማመን ነው።
  2. ንስሐ መግባት ያስፈልጋቸዋል። ንስሐ መግባት በቅዱስ እግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኛ መሆናችንን አምነን መቀበል ነው። ይህም የቀድሞ ሕይወታችንን ለውጠን የእግዚአብሔርን መንገድ ለመከተል የምንወስንበት ነው። ማንም ሰው የኃጢአቱን ጥልቀትና ክርስቶስም የኃጢአቱን ቅጣት እንደ ከፈለለት እስካልተገነዘበ ድረስ፥ የወንጌሉን ምሥጢር ሊያውቅ አይችልም። ክርስቶስን ማመን ደግሞ እርሱን ለመከተል መወሰንን ይጠይቀናል። ዛሬ የብዙ ሰዎች እምነት ባዶና ጊዜያዊ የሚሆንበት ምክንያት፥ ክርስቶስ የሚሰጠውን ድነት (ደኅንነት) ከመረዳታቸው በፊት የክፋታቸውን ጥልቀት አለመረዳታቸው ነው።

3 ውሳኔአቸው ጥምቀትን ይጨምራል። ክርስቶስ፥ ዮሐንስና እርሱ ተከታዮቹን በማጥመቅ ያደርጉት የነበረውን ሥርዓት ደቀ መዛሙርቱም እንዲቀጥሉ ነግሯቸው ነበር። ይህ ጥምቀት በራሱ ማንንም አያድንም። ነገር ግን ጥምቀት በልባቸው ክርስቶስን ለመከተል መወሰናቸውን የሚገልጹበት ውጫዊ ሥርዓት ነበር። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች እንዳመኑ ወዲያውኑ ይጠመቁ ነበር። ለዚህ ነው የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች እምነትንና ጥምቀትን እንደ አንድ በክርስቶስ የማመን ተግባር የሚገልጹት።

መ. ላመኑት የተሰጠ የተስፋ ቃል። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት፥ ጴጥሮስ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ስለሚያገኙት በረከት ተስፋ ሰጥቷል። ይህም ይቅርታንና መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ያስችላቸዋል። በዚህ ስፍራ መንፈስ ቅዱስ ከሌሎች ይልቅ የተሻለ ቅድስና ባላቸው ሰዎች ላይ እንደሚመጣ አልተናገረም። ወይም ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት የተለየ የጸሎት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው አልጠቀሰም። ይልቁንም፥ ንስሐ ገብተው በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበሉ ተገልጾአል።

ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ ለምስክርነታቸው ኃይልን እንደሚሰጥ ተናግሯል። ይህም በጴጥሮስ ምስክርነት በምሳሌ ተብራርቷል። ከጴጥሮስ ስብከቶች አንዱን ብቻ ከሰሙ በኋላ 3,000 ሰዎች ክርስቶስ መሢሐቸውና አምላካቸው እንደሆነ አምነዋል። ከእነዚህ ሰዎች ብዙዎች ከጥቂት ሳምንታት በፊት ክርስቶስ እንዲሰቀል ሲጠይቁ የነበሩ ናቸው። በብዙ ሰዎች ልብ ውስጥ ይህን መሳይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- በጴጥሮስ ስብከት መሠረት፥ ሰዎች ለድነት (ለደኅንነት) ሊያውቋቸው፥ ሊያምኗቸውና ሊያደርጓቸው የሚገቧቸው አስፈላጊ ነገሮች ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: