አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ማትያስን ደቀ መዝሙር አድርገው መረጡት (የሐዋ. 1፡12-26)

ለአይሁዶች 12 ቁጥር ትልቅ ትርጉም አለው። በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ በ12 ነገዶች የተከፈለ ሲሆን፥ ክርስቶስም ወደ ምድር ሲመጣ የአዲሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ (ቤተ ክርስቲያን) መሪዎች እንዲሆኑ 12 ሰዎችን መርጧል። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ በእግዚአብሔር መንግሥት በ12 ዙፋናት ላይ ተቀምጠው እንደሚገዙ ተናግሯል (ማቴ. 19፡28)። ይሁዳ ክርስቶስን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ የራሱን ሕይወት በማጥፋቱ የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር ወደ 11 ዝቅ ብሎ ነበር። ሉቃስ በይሁዳ ላይ ስለደረሰው ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥቷል። ቀደም ሲል ራሱን ሰቅሎ እንደ ሞተ ተገልጾአል (ማቴ 27፡5)። አሁን ደግሞ ሉቃስ የይሁዳ ሥጋ ለረዥም ጊዜ እዚያው ተሰቅሎ በመቆየቱ በወደቀ ጊዜ እንደ ፈራረሰ ገልጾአል። ይሁዳ ለካህናቱ በመለሰው ገንዘብ የተገዛው መሬት በተዘዋዋሪ መንገድ የደም መሬት ተብሎ ተጠራ። ሉቃስ፥ ይሁዳ ክርስቶስን አሳልፎ ከሰጠበትና ራሱን ሰቅሎ ከገደለበት አንሥቶ እስከ ክርስቶስ ሞት፥ ትንሣኤ፥ ዕርገትና ክብረት ድረስ ሁሉም ነገር በቅዱሳኑ መጻሕፍት አስቀድሞ የተተነበየ መሆኑን ገልጾአል። እንዲሁም ሉቃስ አሥራ አንዱም ደቀ መዛሙርት አብረው እንደነበሩ አስረድቷል። አሁን ግን የክርስቶስ እናት የሆነችው ማርያምና “ወንድሞቹም” አብረው ነበሩ። ወንድሞቹ የተባሉትም የዮሴፍና የማርያም ልጆች ናቸው። በፊት በክርስቶስ ያላመኑ ሲሆኑ፥ አሁን አምነውበታል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው ያዕቆብ በኋላ በኢየሩሳሌም ታላቅ የቤተ ክርስቲያን መሪ ለመሆን በቅቷል።

እግዚአብሔር ለአዲሱ ሕዝቡ አሥራ ሁለት መሪዎችን እንደ መረጠ በማመን አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ከጸሎት በኋላ አንድ ተጣማሪ ደቀ መዝሙር ሐዋርያ መረጡ። ይህንን ሰው ለመምረጥ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት ነበረባቸው። እንደኛው ክርስቶስ በዮሐንስ ተጠምቆ ይፋዊ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንሥተ ወደ ሰማይ እስካረገበት ጊዜ ድረስ ደቀ መዝሙሩ ሆኖ የተከተለው መሆን አለበት። ክርስቶስ ምን እንዳደረገ፥ ማን እንደሆነና ሌላውንም ተግባራቱን በትክክል ማወቅ ነበረበት። ለዚህ የአገልግሎት ደረጃ አዲስ አማኝ ወይም በቂ እውቀት የሌለው ሰው ብቁ ሊሆን አይችልም። ሁለተኛው፥ ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን ማየት ነበረበት። ክርስቶስ ከሞት መነሣቱን በአካል አይተ መመስከሩ አስፈላጊ ነበር።

የውይይት ጥያቄ:- ሀ) አሥራ አንዱ ሐዋርያት እነዚህን ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ያስቀመጡት ለምን ይመስልሃል? ለ) አሥራ ሁለተኛውን ሐዋርያ የመረጡበት መንገድ፣ የአንድ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ለመምረጥ ስለምንጠቀምበት መመዘኛ ምን ያስተምረናል?

አንዳንድ ክርስቲያኖች ደቀ መዛሙርቱ ማትያስን በመምረጣቸው ስሕተት ፈጽመዋል ይላሉ። እግዚአብሔር አሥራ ሁለተኛው ሐዋርያ ጳውሎስ እንዲሆን ይፈልግ ነበር ብለው ያስባሉ። ነገር ግን ሉቃስ ሐዋርያቱ ስሕተት መፈጸማቸውን አልጠቀሰም።

እንደ እኛ እግዚአብሔር የሚመርጠውን ሰው ለመወሰን መጽሐፍ ቅዱስን፣ ጸሎትንና የእግዚአብሔርን ምርጫ አሳብ ተጠቅመዋል። ዛሬም መሪዎችን ለመምረጥ እነዚህን ሦስት ነገሮች መጠቀም አለብን። መሪዎችን ለቤተ ክርስቲያን መምረጥ የተቀደሰና ዐቢይ ተግባር ነው። ብዙ ጊዜ መሪዎች እግዚአብሔር ባዘጋጀው ሳይሆን፥ ዓለም ባዘጋጀው የተሳሳተ መመዘኛ ላይ ተመሥርተው ይመረጣሉ። እንደ ሳሙኤል፥ እግዚአብሔር የሰውን ልብ እንደሚያይና ሰዎች ግን የውጭውን ገጽታ እንደሚያዩ መገንዘብ አለብን (1ኛ ሳሙ. 16፡7)። ማን መሪ ሊሆን እንደሚችልና እንደማይችል መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ መመሪያ ይሰጠናል። እግዚአብሔር እረኞቹ ምን ዓይነት ባሕርያት ሊኖሯቸው እንደሚገባ፥ ምንም ያህል የተማሩ ወይም ብርቱ ቢሆኑም እንኳ አዳዲስ ክርስቲያኖች መሆን እንደሌለባቸው ገልጿል፡፡ እግዚአብሔር ፍላጎታችንን ከፈቃዱ ጋር ለማስማማትና የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን ለማስወገድ ጸሎታችንን ይጠቀማል። በራስ ወዳድነት መንፈስ ተይዘን ለመመረጥ የምንሻ ከሆነ፥ ወይም የገዛ ዘመዳችን እንዲመረጥ የምንጥር ከሆነ ወይም ሌሎች የተሳሳቱ ምክንያቶችን ይዘን መሪዎችን የምንመርጥ ከሆነ ትክክለኛ መሪዎችን ልንመርጥ አንችልም፡፡ እግዚአብሔር ግለሰቡን እንደ መረጠ የሚያመለክት መረጃም መኖር አለበት። ከእነዚህ መካክል አንደኛው መንፈሳዊ ስጦታ ሲሆን፥ ሌሎቹ ጥበብ፥ አርቆ አስተዋይነትና የአመራር ችሎታ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ:- በቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች የተመረጡበትን ሁኔታ አስታውስ፡፡ ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጸሎትና የእግዚአብሔር ህልውና በሕይወታቸው ውስጥ መታየት፣ በውሳኔው ላይ የተጫወተው ሚና ምን ነበር? ለ) ለሚቀጥለው የመሪዎች ምርጫ ቤተ ክርስቲያንህ እነዚህን ሦስት ነገሮች እንዴት በተሻለ ሁኔታ ልትጠቀምበት የምትችል ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: