ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት (ሐዋ. 1፡1-10)

ከበደና ሲሳይ የአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ናቸው። ቤተ ክርስቲያናቸው የምትገኘው ሙስሊሞችና የክርስትና ሃይማኖትን በልማድ የሚከተሉ ሰዎች በብዛት በሚገኙባት አነስተኛ ከተማ ውስጥ ነበር። ወንጌል ወደዚያች ከተማ የመጣው ከ40 ዓመታት በፊት ሲሆን፥ የምእመናን ቁጥር ቀስ በቀስ ወደ 400 ደርሷል። አንድ ቀን የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች ዓመታዊ የዕቅድ ስብሰባ አካሄዱ። በዚህ ጊዜ ከበደ ብድግ ብሎ፥ «ምእመኖቻችን በቂ የእግዚአብሔር ቃል እውቀት የላቸውም። ስለሆነም፥ ልናደርግ የሚገባን እጅግ አስፈላጊው ነገር የሕዝባችንን እውቀት ማሻሻል ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ይበልጥ ከተረዱ ከዚህ የተሻለ ሕይወት ይኖራሉ። የሐሰት አስተማሪዎችም በቀላሉ አያሸንፉዋቸውም። ስለሆነም፥ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል የሚያጠኑበትን ቤተ መጻሕፍት መክፈት ይኖርብናል፥ በተጨማሪም፥ የማታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድኖችን ማደራጀት አለብን” አለ። ሲሳይ ግን፥ «እስቲ አካባቢያችሁን ዘወር ብላችሁ ተመልከቱ። ከዚህ ቤተ ክርስቲያን በ50 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ ሌላ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ አማኝ የለም። ወንጌልን ከሰማን አሁን 20 ዓመታት ሞልተዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሲኦል እየገቡ፥ እኛም በክርስቶስ ማዳን ደስ በመሰኘት ላይ ነን። የወንጌል ስርጭት ማካሄድ አለብን። እስቲ እያንዳንዱ ምእመን በወር አንድ ቅዳሜ እየወጣ ለማኅበረሰቡ እንዲመሰክር እናሠልጥነው በዚህ አካባቢ ወደሚገኙ ስፍራዎች እየሄዱ ወንጌልን የሚሰብኩ ሁለት ወንጌላውያንን እንቅጠር።

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋርያት ሥራ 1፡8 እና ኤፌ 4፡11–18 አንብብ። ሀ) ለቤተ ክርስቲያን የተሰጡት ሁለት ዐበይት ትእዛዛት ወይም ኃላፊነቶች ምንድን ናቸው? ለ) ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በአንድ ኃላፊነት ላይ ብቻ የሚያተኩሩባቸውን መንገዶች በምሳሌ አብራራ። ሐ) እነዚህን ሁለት ኃላፊነቶች ሚዛናዊ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ይህንን እንዴት ልናደር እንችላለን?

እንደ ሰዎች ሁሉ፥ አብያተ ክርስቲያናትም ራስ ወዳድ ሊሆኑ ይችላሉ። አብያተ ክርስቲያናት በራሳቸው ላይ በማተኮር አምልኮን፥ ሕንፃ ግንባታን፡ የመዘምራን ቡድን ማደራጀትን ብሎም አባሎቻቸውን ማስተማርን ያስቀድማሉ። ጸሎታቸው ብዙውን ጊዜ፥ «ጌታ ሆይ፥ ባርከን» ከሚለው አያልፍም፡፡ ምንም እንኳ ለአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በሚገባ የታሰበበት የትምህርት ፕሮግራም እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም፥ እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ራስ ወዳድ እንዳትሆን መጠንቀቅ አለባት። አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ወደ ጠፉት የመድረስ ራእይ መያዝ አለበት። ብዙ ምእመናን ከጓደኞቻቸው ጋር በራሳቸው ቤተ ክርስቲያን በማምለክ ‹ሰላም› ደስ ስለሚሰኙ፥ ወደ ወንጌል ስርጭት መንፈሳዊ ግንባር ለመሄድ አይፈልጉም። ሰዎች ወንጌልን ካልሰሙ ወደ ሲኦል እንደሚላኩ ይዘነጋሉ።

ነር ግን የሰዎችን ወይም የአባሎችን ቁጥር ለማብዛት፣ በአብዛኛው ስብከቶቻቸው ከትምህርት ይልቅ በወንጌል ስርጭት ላይ የሚያተኩሩ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አሉ። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ብዙ አባላት ቢኖራቸውም፥ አባሎቻቸው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያልበሰሉ «ሕጻናት» ክርስቲያኖች ናቸው።

ጤናማ ቤተ ክርስቲያን እንድትኖረን ከተፈለገ፥ የቤተ ክርስቲያን ሽማግለዎች ለማስተማርና ለወንጌል ስርጭት ራሳቸውን መስጠት አለባቸው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሚሰበሰበው ገንዘብ አብዛኛው ለእነዚህ ሁለት አገልሎቶች መዋሉን ለማረጋገጥ በጀታቸውን በጥንቃቄ መገምገም አለባቸው፡፡ በተጨማሪም፣ እነዚህን ሁለት አገልግሎቶች በሚገባ ማቀድና መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ ልክ አንድ ቤት ሁለት ምሰሶዎች እንዳሉት ሁሉ፥ የቤተ ክርስቲያን ሁለት ምሰሶዎች ትምህርትና ወንጌል ስርጭት ናቸው።

የውይይት ጥያቄ:- የሐዋ. 1ን አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል ስለ ቤተ ክርስቲያን አገልሎት ምን ልንማር እንችላለን? ለ) ስለ ቤተ ክርስቲያን አመሠራረት ምን ልንማር እንችላለን?

ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት (ሐዋ. 1፡1-11)

የሉቃስ ወንጌልና የሐዋርያት ሥራ ታሪኮች የተያያዙ ናቸው። በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ሉቃስ የክርስትና እምነት መሥራች ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይነግረናል። አሁን በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ደግሞ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንዳደገችና እንደ ተስፋፋች ይተርክልናል። ሉቃስ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፉን የጀመረው ከሞት ወደ ተነሣው ክርስቶስ ታሪክ በመመለስና ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸውን የመጨረሻ ትምህርቶችና ትእዛዛት በማቅረብ ነው። ከዚህ ክፍል የሚከተሉትን ነጥቦች ለማስተዋል ሞክር፡-

ሀ. ሉቃስ «የመጀመሪያ መጽሐፉን» ይጠቅላል። ይህም የሉቃስ ወንጌል ነው፡፡

ለ. ሉቃስ መጽሐፉን የጻፈው ለቴዎፍሎስ ነው። ይህም ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈለት ግለሰብ ነው። ምናልባት ቴዎፍሎስ የሉቃስን መጽሐፍ በሰዎች አስገልብጦ በዓለም ሁሉ ለማሰራት የሚያስፈልገውን ወጪ ለመክፈል ተስማምቶ ሊሆን ይችላል።

ሐ. የሉቃስ ወንጌል ክርስቶስ ማድረግና ማስተማር ስለጀመረው ሥራ ይናገራል። ሉቃስ ክርስቶስ «ማድረግ ስለጀመረው ሥራ» ሲል፥ ክርስቶስ አሁንም ሥራውን ይቀጥላል ማለቱ ነበር። መሥራቱን የሚቀጥለው እንዴት ነው? የሐዋርያት ሥራ ኢየሱስ በተከታዮቹ አማካይነት እንዴት እየሠራ፥ እንዴት እየፈጸመና ሰዎችንም ለድነት (ለደኅንነት) እንዴት እያዘጋጀ እንደሆነ ይገልጽልናል። ኢየሱስ ሥራውን ዛሪም ቀጥሎበታል። ወንጌሉን በምናሰራጭበት ጊዜ አንደበቱ ነን ከዚህ በፊት ወንጌል ወዳልተሰበከበት ስፍራ ስንሄድ ደሞ እግሮች እንሆናለን። እንዲሁም የተጎዱትን ሰዎች በምንረዳበት ጊዜ እጆች ነን። አንድ ሰው እንዳለው፥ «በዚህ ሕይወት ሰዎች በዓይን የሚያዩት ኢየሱስ ክርስቶስ፥ እኛ ብቻ ነን።» የክርስቶስን ባሕርያትና ተግባራት እየመሰልን ስንሄድ፥ ክርስቶስ በእኛ አማካይነት በዚህች ምድር ላይ ማገልገሉን ይቀጥላል።

መ. ሉቃስ በክርስቶስ አገልግሎት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ስለሚፈጽመው ተግባር ትኩረት ሰጥቷል። ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እንዳስተማረና እንደ ሠራ ሁሉ፥ የክርስቶስ ተከታዮችም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እንደሚሠሩ ሉቃስ አሳይቷል። መንፈስ ቅዱስ እጅግ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ፥ ደቀ መዛሙርቱ እርሱን ከመቀበላቸው በፊት አገልግሎታቸውን ለመጀመር እንዳይሞክሩ ክርስቶስ ጥብቅ መመሪያ ሰጥቷቸዋል።

ሠ. ደቀ መዛሙርቱ አሁንም የእግዚአብሔርን ዓላማዎች አልተረዱም ነበር። አሁንም ምድራዊ ንጉሣዊ አገዛዝ ይመሠረታል ብለው ያስቡ ነበር። ይህ ለእኛ ማስጠንቀቂያ ሊሆነን ይገባል። ከክርስቶስ ጋር ከሦስት ዓመታት በላይ የኖሩት ደቀ መዛሙርት፥ የእግዚአብሔርን ዓላማዎች ካልተረዱ፥ እኛም የእግዚአብሔርን የወደፊት ዓላማ ለመረዳት እንደምንቸገር መገንዘብ አለብን፡፡ የራሳችን ግላዊ አሳቦች ሊኖሩን ቢችሉም፣ እግዚአብሔር ለመጨረሻው ዘመን ምን ዕቅዶችና ዘዴዎች እንዳሉት ላንረዳ እንችላለን፡፡

ረ. ክርስቶስ፥ ደቀ መዛሙርቱ ምድራዊ መንግሥት መቼ እንደሚጀመር ከማሰብ ይልቅ፥ መንግሥቱን በሚጠባበቁበት ጊዜ ሊያደርጓቸው ስለሚገባቸው ተግባራት ማተኮር እንዳለባቸው ገልጾአል። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻ ትእዛዙን ሰጥቷል። ይህ «ታላቁ ተልእኮ» የተሰጠው ክርስቶስ እስኪመለስ ድረስ የደቀ መዛሙርቱ ድርሻ ምን እንደሆነ ለማመልከት ነው። ከዚህ ትእዛዝ የሚከተሉትን እውነቶች ልብ በል፡-

  1. ምስክርነት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መደረግ አለበት። ለዚህ ነው ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይልን እንደሚቀበሉ የገለጸው። እኛ ብዙውን ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በልሳን ለመናገር፥ ተአምራትን ለማድረግና ለፈውስ አገልግሎት እንደሚያስፈልግ እናስባለን። ክርስቶስ ግን መንፈስ ቅዱስ ከመጣባቸው ቀዳሚ ምክንያቶች አንዱ፥ ለምስክርነት ኃይልንና ፍሬያማነትን ለመስጠት እንደሆነ ገልጾአል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ለምስክርነት ኃይልን ሊሰጥ፥ በሚያሳድዷቸው መሪዎች ፊት ድፍረትን ሲሞላባቸው (የሐዋ. 4፡8-10)፥ በስብከት ጊዜ ድፍረትንና ኃይልን ሊሰጣቸው (የሐዋ. 2፡14-41)። እንዲሁም ወንጌሉን ይዘው የሚሄዱበትን መንገድ ሲመራቸው (የሐዋ 16፡6-10)፣ መዘተ… እንመለከታለን።
  2. የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚውና ውጫዊው አገልግሎት ስለ ክርስቶስ መመስከር ነው። ቀደም ሲል፥ ይህን ትእዛዝ የክርስቶስን በጎች መመገብ እንዳለብን ከሚናገሩ ሌሎች ትእዛዛት ጋር ሚዛናዊ ማድረግ እንዳለብን ተመልክተናል። በማቴ 28፡19-20 ይህ ትእዛዝ የበለጠ በግልጽ ተብራርቷል። ይህም ግቡ አማኞችን ሳይሆን ደቀ መዛሙርትን ማፍራት እንደሆነ የሚያመለክት ነው። ነገር ግን በጠፉት ላይ ሳይሆን ባሉን በጎች ላይ ስለምናተኩር፥ ምስክርነትን የግላችንም ሆነ የቤተ ክርስቲያናችን ተቀዳሚ ጉዳይ ላይሆን ይችላል።
  3. መመስከር የአማኞች ሁሉ ኃላፊነት ነው። ክርስቶስ ይህን ትእዛዝ የሰጠው ለጴጥሮስ ወይም ለጥቂት ደቀ መዛሙርት ብቻ ሳይሆን፥ ለተከታዮቹ ሁሉ ነው። ዛሬ ብዙ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን፥ ለምስክርነት ገንዘብ የሚከፍሏቸው ወንጌላውያን ኃላፊነት ብቻ እንደሆነ ያስባሉ። አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ሕያው ምስክርነት በመስጠት ለዚህ ትእዛዝ አይገዙም። አንዳንድ ክርስቲያኖች ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበሉት «ወንጌልን የመስበክ» ስጦታ ስላላቸው፥ እግዚአብሔር በሚመሰክሩበት ጊዜ በተለየ መንገድ ይጠቀምባቸዋል። ምንም እንኳ ወንጌልን የሚሰብኩ ወንጌላውያንን፥ በተለይም ምእመናን ሊደርሱ ለማይችሉባቸው አካባቢዎች ማሰማራት ተገቢ ቢሆንም፥ የምስክርነት ኃላፊነት የሁሉም ምእመናን ነው። እንደ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል ስለ ክርስቶስ እንዴት በግልጽ ሊመሰክርና ይህንን ትእዛዝ በሕይወቱ ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚችል ማስተማር አለብን።
  4. ይህ የምስክርነት አገልግሎት አራት ዐበይት ክፍሎች አሉት። ሉቃስ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ትእዛዝ ተግባራዊ እንዳደረገች ለማሳየት እነዚህን አራት ክፍሎች የመጽሐፉ መሠረታዊ አስተዋጽኦዎች አድርጎ ተጠቅሞበታል። ዛሬም እነዚህን ክፍፍሎች ማስታወስ አስፈላጊ ነው። ዛሬ የእኛ ኢየሩሳሌም የምንኖርበት ከተማ ወይም ማኅበረሰባችን ነው። ለእኛ የአይሁድ ምድራችን ደግሞ አጎራባች አካባቢያችን፥ ቀበሌዎቻችን፥ ወይም አውራጃችን ነው። ሰማርያ፥ ከእኛ ጋር በባሕል ተመሳሳይ ሆነው ሳለ ነገር ግን የተለየ ቋንቋ የሚናገሩትን አጎራባች ጎሳዎች ያመለክታል። የምድር ዳርቻ ከእኛ ርቀው የሚገኙትን ሕዝቦች ያሳያል። እነዚህ ወገኖች በመልክዓ ምድርም ሆነ በባሕል ርቀው የሚገኙ ናቸው። ይህም የአርሶ አደሩ ባሕል በደጋማው የኢትዮጵያ ክፍሎች ከሚኖሩ ሕዝቦች እንደሚለይ፥ ወይም የሱዳን ባሕል ከኢትዮጵያ እንደሚለየው ማለት ነው። የእያንዳንዷ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቤተ ክርስቲያናቸው እንዴት ባለ ስልታዊ ዕቅድ ወደ እነዚህ አራት አካባቢዎች ወንጌልን እንደምታደርስ ማሰብ ይኖርባቸዋል።
  5. ወንጌሉን ወደ ኢየሩሳሌም፥ ይሁዳ፥ ሰማርያና የምድር ዳርቻ የመድረስ ተግባር በጊዜ ቅደም ተከተል የሚካሄድ ተልዕኮ አልነበረም። ክርስቶስ መጀመሪያ ኢየሩሳሌምን፥ ከዚያ ይሁዳን፥ በኋላ ደግሞ ሰማርያን በወንጌል እንድንደርስ አይደለም የጠየቀው። ይልቁንም በአንድ ጊዜ በአራቱም አካባቢዎች መሥራት አለብን። እንደዚሁም ለጎረቤቶቻችን በአንድ ጀማ ስብከተ ወንጌል ላይ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት መናገሩ ብቻ በቂ አይደለም። እያንዳንዱ አዲስ ትውልድ ወንጌሉን መስማት አለበት። ልጆቻችንም በክርስቶስ ለማመን የራሳቸውን ውሳኔ እንዲሰጡ ያለማቋረጥ የወንጌሉን ቃል ልንሰብክላቸው ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያንህ ሽማግሌዎች ትኩረት ሊሰጡ የሚገባቸውና ከዚህ ትእዛዝ የሚመነጭ ዐበይት ትምህርቶች ምንድን ናቸው? ለ) የቤተ ክርስቲያንህን የምስክርነት አገልግሎት ግምገማ መሠረት፥ ከአራቱ አካባቢዎች በየትኞቹ ላይ ሥራዎች እንደሚካሄዱና የትኞቹ ቸል እንደ ተባሉ ግለጽ። ሐ) በዚህ ሳምንት በግልህ እንድትመሰክርላቸው እግዚአብሔር በልብህ ውስጥ ያስቀመጣቸውን የሦስት ሰዎች ስም ዝርዝር።

ሰ. ስለ ክርስቶስ ዕርገት የገለጸው ሉቃስ ብቻ ሲሆን፥ በወንጌሉም ሆነ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ይህንኑ አድርጓል። ክርስቶስ የመጨረሻ ትእዛዙን ከሰጠ በኋላ ወደ ሰማይ ተመልሷል። በዚያም ዘወትር ስለ እኛ ይማልዳል (ዕብ 7፡25)። ደቀ መዛሙርቱን ሊያበረታቱ የመጡት መላእክት ክርስቶስ በሄደበት መንገድ እንደሚመለስ ገልጸዋል። ብዙ ክርስቲያኖች ይህ የክርስቶስን መመለስ እንደሚያመላክት ያስባሉ። አንደኛው፥ የሚመጣው በደመና ይሆናል (ማቴ. 24፡30)። ሁለተኛው፥ ብዙ ሰዎች ያዩታል። ሦስተኛው፥ የሚመጣው ወዳረገበት ስፍራ ማለትም ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ነው (ዘካ. 14፡4)። ይህንና ሌሎችንም ጥቅሶች በማቅረብ የክርስቶስ የዘላለም መንግሥት ሰማያዊ ብቻ ሳይሆን፥ በምድርም ላይ እንደሚመሠረት ይናገራሉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d