የጥንት ክርስቲያኖች ሕይወት ጥቅል ማብራሪያ (የሐዋ. 2፡42-47)

የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ምን መምሰል አለበት? ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሕይወቷ ብርቱና አዳጊ ለመሆን የምትችለው እንዴት ነው? ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት በምታድግበት ጊዜ፥ ክርስቶስ እንደሚፈልጋት ብርቱና ሕያው ሆና ለመኖር ምን ማድረግ ይኖርባታል? ዓለም በቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ በማድረስ እምነቷን እንዳታዳክምና እንዳታጠፋ ምን እናድርግ? ሉቃስ ለማደግ ከፈለግን እንደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ እንደ ግለሰብ ክርስቲያኖች ልናደርጋቸው የሚገቡንን ነገሮች ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል።

ሀ. ትምህርት፡- በሚቀጥለው እሑድ 3,000 ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያንህ ቢመጡ፥ በአዲሱ እምነታቸው እንዲያድጉ እንዴት ልትረዳቸው ትችላለህ? የሐዋርያት ሥራ ብዙዎቹ ሰዎች ክርስቶስ ሲያስተምር ሰምተው ስለማያውቁ፥ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት ምን እንደሆነ አለማወቃቸውን ገልጾአል። ስለሆነም፥ ተከታታይና ሥርዓታዊ ትምህርት ማግኘታቸው ወሳኝ ነበር። ሐዋርያት ባለማቋረጥ እነዚህን ክርስቲያኖች ያስተምሩ እንደነበር ሉቃስ በግልጽ ጠቅሷል።

ለ. ኅብረት፡- ይህ ቃል ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም አለው። አንዳንዶች ሉቃስ የሚገልጸው ኅብረት እሑድ ቀን በቤተ ክርስቲያን መሰብሰብ ይመስላቸዋል። ሉቃስ ግን ከዚህ የጠለቀ አሳብ ነበረው። እርሱ የሚናገረው ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው በሚገባ ለመተዋወቅ ስለሚሰባሰቡበት ጊዜ ነው። ችግር በሚኖርበት ጊዜ እርስ በርሳቸው ይረዳዱ ነበር። ለክርስቶስ ጸንተው ለመቆም እርስ በርሳቸው ይጽናኑ ነበር። እንዲህ ዓይነት ኅብረት ለመመሥረት ሰዎች በአነስተኛ ቡድኖች መደራጀት አለባቸው። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን፥ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች ስላልነበሩ ሰዎች በግለሰብ ቤቶች ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር። ብዙውን ጊዜ ሰዎች በታላላቅ ሕንጻዎች ላይ ያተኩራሉ። ምንም እንኳ ታላላቅ ሕንጻዎች ለአምልኮ ቢያመቹም፥ ለኅብረት አያመቹም። ምእመናን ሁሉ እርስ በርሳቸው ሊተዋወቁ፥ ሊበረታቱ፡ ሊጸልዩ፥ ለአገልግሎታቸውና ለሕይወታቸው በኃላፊነት ሊጠያየቁ በሚችሉባቸው አነስተኛ ቡድኖች መደራጀታቸውን ቤተ ክርስቲያን ማረጋገጥ አለባት።

ሐ. አብሮ እንጀራ መቁረስ፡- ዛሬ በብዙ አብያተ ክርስቲያናት የጌታ እራት የሚሰጠው በወር አንድ ጊዜ ሲሆን፥ ብዙ ሰዎች የጌታን እራት አይወስዱም። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ግን እንዲህ አልነበረም። ከ1ኛ ቆሮ. 11፡17-34 እንደምንመለከተው በየእሑዱ የቤት ለቤት ቤተ ክርስቲያን አባላት በሚሰበሰቡበት ጊዜ አብረው ይበሉ ነበር፡፡ ከምግቡም መካከል የጌታ እራት ይገኝበታል። ስለሆነም፥ በየሳምንቱና ምናልባትም ከዚያ ባነሰ ጊዜ የጥንቱ ክርስቲያኖች፥ የጌታን እራት በመካፈል ጌታ ስለ እነርሱ መሞቱን ያስታውሱ ነበር።

መ. ጸሎት፡- ይህ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት የሚያደርጉበት ከመሆኑም በላይ፥ የአገልግሎትና የቤተ ክርስቲያን እድገት ኃይል መሆኑን በማመን፥ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ለጸሎት ከፍተኛ ትኩረት ትሰጥ ነበር።

በመቀጠል፥ ሉቃስ ከእነዚህ ነገሮች የተነሣ ምን እንደ ተከሰተ ይገልጻል።

ሀ. የሚያምኑት ሰዎች በአድናቆት ይመለከቷቸው ነበር። መንፈስ ቅዱስ ተአምራት ከማድረጉም በተጨማሪ የሰዎችን ሕይወት ሲለውጥ ሲያዩ አይሁድ ተደነቁ።

ሊ. በሐዋርያት እጅ ተአምራት ይደረጉ ነበር፡- በአብዛኛው ተአምራትን ያደረጉት ሐዋርያት መሆናቸው አስገራሚ ነው። በዚህም እግዚአብሔር ሐዋርያት ለቤተ ክርስቲያን የሾሟቸው መሪዎች እንደሆኑና የሚናገሩትም ከእርሱ እንደ መጣ ያመለክት ነበር።

ሐ. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነት ነበር፡- ሁሉንም ነገር በአንድነት ከመካፈላቸው በላይ፥ የሚኖሩትም ሆነ የሚበሉት አብረው ነበር።

መ. ራስ ወዳድነት አልነበረም፡- ክርስቶስ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይመለሳል ብለው ይጠባበቁ ስለነበር የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ስለወደፊቱ አይጨነቁም ነበር። ይልቁንም፥ እንደ አንድ ኅብረተሰብ ነበር የሚኖሩት። ሀብታሞቹ ያላቸውን ሸጠው ለሌላቸው ያካፍሉ ነበር። ይህ ከራስ ወዳድነት የጠራ ሕይወት መምራታቸውን ያሳያል።

ለለ ራሳቸውና ስለ ቤተሰባቸው ብቻ ሳይሆን፥ ስለ ጠቅላላው የእግዚአብሔር ቤተሰብ ያስቡ ነበር። ማንም ንብረታቸውን ሸጠው እንዲያካፍሉ ሳያስገድዳቸው፥ በገዛ ፈቃዳቸው ይህንን ያደረጉ ነበር። ይህ ሰዎችን እኩል ለማድረግ ኃይልን ከሚጠቀመው ኮሚኒዝም የተለየ ነው። እንዳንድ ምሑራን ይህ ሥራን ማቆም፥ እንደ አንድ ኅብረተሰብ መኖርና ንብረትን መሸጥ፥ የኢየሩሳሌም ክርስቲያኖችን ለድኅነት በመዳረጉ፥ የአውሮጳ ክርስቲያኖችን እርዳታ እንዲፈልጉ አስገድዷቸዋል ይላሉ (2ኛ ቆሮ. 9)።

ሠ. አምልኮ ያደርጉ ነበር። የጥንት ክርስቲያኖች ከይሁዲነት እምነት አልተላቀቁም ነበር። ስለዚህ የአምልኳቸው ማዕከል ያደረጉት ቤተ መቅደስን ነበር።

ረ. ሕይወታቸውንና ለእግዚአብሔር ያላቸውን ቅንዓት በዙሪያቸው የነበረው ማኅበረሰብ በሰፊው ያውቅላቸው ነበር።

ሰ. የቤተ ክርስቲያን እድገት ነበር። ለማያምኑ ሰዎች የተለወጠ ሕይወት፥ አንድነት፥ ፍቅርና ሕያው የሆነ አምልኮ ከማየት የበለጠ የሚስባቸው ምንም ነገር የለም። ከዚህ በኋላ ሰዎች ለማመን ስለሚፈልጉ ምስክርነቱ ቀላል ይሆናል። በጥንቱ ክርስቲያኖች የተለወጠ ሕይወት ምስክርነት ተስበው ሌሎችም ክርስቶስን ለመከተል ፈልገው ነበር፡

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የምንማራቸውና ዛሬ ለቤተ ክርስቲያናችን ለመጠቀም የምንችላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) አብያተ ክርስቲያናት ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚመሳሰሉት ወይም የሚለያዩት እንዴት ነው? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን እንድትመስል ከተፈለገ፥ ሊለወጡ የሚገባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? የቤተ ክርስቲያንህን ልማዶች ለመለወጥ እንዴት ልትጀምር ትችላለህ? አንዳንድ ዕቅዶችን አውጣ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: