መከፋፈል በአይሁዶች መካከል (የሐዋ 6፡1-7)

በኢትዮጵያ በአንዲት ትልቅ ከተማ ውስጥ ከአንድ ትልቅ ነገድ የተገኙ ሰዎች ይኖሩ ነበር። ለሥራ ወደ አካባቢው የሄዱ የደቡብ ኢትዮጵያ ተወላጆች በአባልነት የሚሳተፉበት ቤተ ክርስቲያን በአካባቢው ነበረች። ሁሉም እንዲሰማው ሲባል አምልኮው በአማርኛ ቋንቋ ተደረገ ምንም እንኳ ትልቅ ጎሣ ከሚባለው ወገን ጥቂት ሰዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ አምልኮ ፕሮግራም ላይ ቢገኙም፥ አገልግሎቱ በራሳቸው ቋንቋ ስለማይሰጥ ብዙዎች ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ ውጭ ተቋም አድርገው ይመለከቷት ነበር። ፕሮግራሙ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ለመጡ ሰዎች የተዘጋጀ መሰላቸው። የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች በሙሉ የሌላ አካባቢ ሰዎች በመሆናቸው ጥቂት የአካባቢው ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ለአካባቢው ነዋሪዎች ተስማሚ እንድትሆን ለማድረግ የሚቻልበት መንገድ እንደሌለ ተገነዘቡ። በመጨረሻም፥ የአካባቢው ምእመናን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተገንጥለው የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን መሠረቱ። የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ከሌላ አካባቢ የመጡትን ሰዎች ብቻ ይዛ ቀጠለች።

በሌላ የኢትዮጵያ ከተማ፥ አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን አባላት የአካባቢው ነዋሪዎች ነበሩ። ለአምልኮ የሚያገለግለው የአካባቢው ቋንቋ ሲሆን፥ ሽማግሌዎቹም በሙሉ የአካባቢው ሰዎች ነበሩ። በዚያች ከተማና ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ሰዎችም ነበሩ። የአካባቢው ሰዎች ሁሉንም ነገር ስለ ያዙ፥ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡት ሰዎች የእንግድነት ስሜት ይሰማቸው ነበር። «አመለካከታችንን የምንገልጽበት መድረክ እንኳ የለንም። የሥራ መስኮች፥ የአመራር ቦታዎችና የመዝሙር አገልገሎቶች በሙሉ የተያዙት በአካባቢው ሕዝብ ብቻ ነው። እኛ ምንም ድርሻ የለንም። ይህ ፍትሐዊ አይደለም።» ሲሉ ያማርራሉ።

የውይይት ጥያቄ:- ሀ) በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን እንዴት እንደ ተመለከትህ አብራራ። ለ) ሰይጣን በእነዚህ ሁኔታዎች ተጠቅሞ፣ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ መከፋፈልን ሊያስከትል የሚችለው እንዴት ነው? ሐ) የመጀመሪይቱ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ብትሆን ኖሮ፥ የአካባቢው ሰዎች የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል መሆናቸው እንዲሰማቸው ለማድረግ ምን የተለየ ነገር ታደርግ ነበር? መ) የሁለተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ብትሆን፥ የአናሳው ጎሣ አባላት የቤተ ክርስቲያን አካል መሆናቸው እንዲሰማቸው ምን የተለየ ነገር ታደርግ ነበር? ሠ) የሐዋ 6፡4-7 አንብብ። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ባሕላዊ ችግሮችዋን የፈታችው እንዴት ነበር? ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት የአብያተ ክርስቲያናት ችግሮች ለመፍታት ከሐዋርያት ሥራ 6፡1-7 ልንጠቀምባቸው የምንችላችው መርሖዎች ምንድን ናቸው?

መከፋፈል በአይሁዶች መካከል (የሐዋ 6፡1-7)

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ውጥረቶች መከሰታቸው የማይቀር ነው። በእኩል አልታየንም የሚሉ ቤተሰቦች፥ ጎሣዎችና ነገዶች ሁልጊዜ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እዚህን ውጥረች እንዴት መፍታት እንዳለብን ማወቅ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ሰይጣን መከፋፈልን ለመፍጠር ይጠቀምባቸዋል። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ አስቀድሞ የጸለየው አንድነት እንዲኖራቸው ነበር (ዮሐ 17፡21)። ግን ሰይጣን የክርስቶስን ተከታዮች ለማሸነፍ ከሚጠቀምባቸው ታላላቅ መሣሪያዎቹ አንዱ መከፋፈል ነው።

በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁለት ዓይነት የአይሁድ ሰዎች ነበሩ፡፡ በመጀመሪያ በፍልስጥኤም አገር የተወለዱ የአካባቢው አይሁዶች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የግሪክ ቋንቋ ቢናገሩም፣ በየዕለቱ የሚጠቀሙት ግን በአረማይስጥ ቋንቋ ነው፡፡ ራሳቸውን እንደ ንጹሕ አይሁድም ይቆጥሩ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያቀደውን ሕይወት ያረክሳል ብለው ስለሚያስቡ፥ ከግሪኩ ባሕላ ጋር መቀላቀል አይፈልጉም ነበር፡፡ ሁለተኛው፥ የግሪክ አይሁዶች ነበሩ እነዚህ ከፍልስጥኤም ውጭ የተወለዱ አይሁዶች ነበሩ። አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ግሪክኛ ሊሆን፥ ፍልስጥኤም አገር ከተወለዱ አይሁዶች የተለየ የአለባበስና የአኗኗር ሁኔታ ይታይባቸው ነበር፡፡ እነዚህ እሁዶች ብሉይ ኪዳንን እስካልተቃረነባቸው ድረስ፥ ከአሕዛብ ዓለምና ባሕል ጋር ተስማምተው ለመኖር ፈቃደኞች ነበሩ፡፡

ቀደም ሲል ከዓለም ሁሉ አይሁዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጡ እንደነበር ተመልክተናል፡፡ ለምሳሌ፥ ከቆጵሮስ የመጣው በርናባስ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጠቃሚ ሰው ለመሆን በቅቷል። ከየትም ይምጡ ከየት፥ አይሁዶች ሁሉ ንብረቶቻቸውን እየሸጡ ለሐዋርያት ይሰጡ ነበር፡፡ ገንዘቡን እንደ አስፈላጊነቱ ማካፋፈል የሐዋርያቱ ተግባር ነበር። ነገር ግን ከውጭ የመጡት የግሪክ አይሁዶች ምንም መተዳደሪያ የሌላቸውን መበለቶች በማስተናበሩ ረገድ አድልዖ እንደ ተፈጸመ በማሰብ ቅሪታዎችን ያሰሙ ጀመር፡፡ የፍልስጥኤም አይሁዳውያን መበለቶች፣ ከሌላ ባሕልና ቋንቋ ከመጡት አይሁዳውያን የበለጠ እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው አሰቡ። ይህም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ውጥረትን አስከተለ፡፡ ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈልና ለማፍረስ ተግቶ እየሠራ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ውጥረቶች በጸሎት ወይም ስለ አንድነት በመስበክ ብቻ የሚወገዱ አይደሉም፡፡ የውጥረቶቹ ምንጭ ተፈልጎ መፍትሔ መሰጠት አለበት፡፡ የተገለጸውን ሁኔታ በተመለከት በትክክል እድልዎ ይፈጸም ወይም ይህ የአንድ ቡድን ችግር ይሁን የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ነገሩ እውነትም ይሁን ውሸት ሰዎች የሚያምኑት ነገር ለእነርሱ እውነት ከሆነ፣ መፍትሔ መስጠቱ አስፈላጊ ነበር፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚታየው መከፋፈል በጎሣዎች መካከል የሚቀሰቀሱ ቅራኔዎች በመሆናቸው በዚህ ክፍል ውስጥ የተወሰኑትን መርሖች መከተሉ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ከዚህ ክፍል የሚከተሉትን እውነቶች መመልከት እንችላለን።

ሀ. ምንም እንኳ ጸሎትና ትምህርት የመፍትሔው አካላት ቢሆኑም፣ በችግሩ ላይ ግልጽ ውይይት እስካልተካሄደበት ድረስ ወደ ጥላቻና ቂም የሚመራ የአድልዎ ድርጊት ሊወገድ አይችልም። ሐዋርያት የግሪክ አይሁዶችን ለመገሠጽም ሆነ ራሳቸውን ለመከላከል አልሞከሩም፡፡ ሐዋርያት የግሪክ አይሁዶች ችግራቸውን በጸሎት ለጌታ እንዲያቀርቡ ወይም ነገሮች በራሳቸው ጊዜ እንዲፈቱ አልጣሩም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን በሕዝቡ ሁሉ ፊት አንሥተው ግልጽ ውይይት እንዲካሄድ አደረጉ።

ለ. ሐዋርያት ችግሩ በራሱ መንገድ እንዲቃለል ከመጠበቅ ይልቅ ወዲያው ሐሜቱን እንደ ሰሙ መፍትሔ መፈለግ ጀመሩ። እንዲህ ዓይነት ችግሮች እንዲሁ ስለማይወግዱ በፍጥነት ትኩረት ካልተሰጠባቸው እየተስፋፉ ይሄዳሉ። መከፋፈል ከሆነ በኋላ ደግሞ፣ ክፍተቱን ለማጥበብ ቀላል አይሆንም።

ሐ. ችግሩ በምእመናን ሁሉ ፊት ለግልጽ ውይይት ቀረበ። ሉቃስ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ሁኔታውን ለማጥናት እንደ ተሰበሰቡ ገልጿል። ሐዋርያቱ የራሳቸውን መፍትሔ መስጠታቸው መልስ አይሆንም ነበር። እነርሱም ከፍልስጥኤም አካባቢ ስለሆኑ፥ ሁልጊዜ ለአንድ ወገን ያደላሉ የሚል ግምት ነበራቸው። ጉዳዩ ከምእመናን ተሰውሮ በሐዋርያት (ሽማግሌዎች) ብቻ ቢቃለል ኖሮ አንደኛው ወይም ሌላኛው ወገን ሽማግሌዎቹ አድልዎአዊ ብያኔ እንዲሰጡ ገፋፍቷል የሚል ሐሜት ይሰራጭ ነበር፡

መ. ሐዋርያቱ (ሽማግሌዎቹ) ለችግሩ መፍትሔ ለመፈለግ ሳይሹ መመሪያዎችን ብቻ ሰጡ። (መንፈስ ቅዱስ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች መረጡ።) ከዚያም ምእመናኑ መበለቶቹን የሚረዱ ሰባት ሰዎች እንዲመረጡ አደረጉ። ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ከሚዋጋባቸው መንገዶች አንዱ መሪዎች ለችግሮች መፍትሔ በመስጠትና ትናንሽ ጉዳዮችን በማከናወኑ ተግባር ላይ እንዲጠመዱና እንደ ጸሎት፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፥ ምስክርነት፥ የቤተ ክርስቲያን ዕቅድ የመሳሰሉትን ዐቢይ ጉዳዮች ቸል እንዲሉ በማድረግ ነው።

ሠ. መፍትሔው በጎሣዊ ስሜት ወይም በዓለማዊ ሁኔታ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ወመርሖዎች ላይ የተመሠረተ ነው። አራት የፍልስጥኤም አይሁዶችንና ሦስት የግሪክ አይሁዶችን ምረጡ አላሏቸውም። ይህ መከፋፈልን እንጂ የእግዚአብሔርን ቤተሰብ አንድነት አያመጣም ነበር። ወሳኙ ነገር ትምህርት፥ የገንዘብ ብዛት ወይም የአስተዳደር ችሎታ ሳይሆን፥ የመንፈስ ቅዱስ ሙላትና መንፈሳዊ ጥበብ ነበር። ተወካዮቹ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ምሪት የሚሠሩ ከሆነ፥ ለሁሉም ሰው ፍትሐዊ የሆነ መፍትሄ መስጠት ይችላሉ።

ረ. አብዛኞቹ የፍልስጥኤማውያን አይሁዶች የአናሳውን ባሕል ለማክበር ከተለመደው መስመር መጡ። በፍልስጥኤማውያን አይሁዶች የተሞላችው ቤተ ክርስቲያን ምእመናን፥ ሰባቱንም ሰዎች ከግሪክ አይሁዶች መካከል መምረጣቸው አስደናቂ ነገር ነበር። ሰባቱ ዲያቆናት የግሪክ ስሞች የነበሯቸው ሲሆኑ፥ አንደኛው በትውልዱ አሕዛብ ሆኖ ሳለ ወደ ይሁዲነት የተለወጠ ሰው ነበር። ወቀሳው የተሰነዘረው ከዚሁ ክፍል አባላት በመሆኑ፥ ብዙ ቁጥር ያላቸው ክርስቲያኖች ከአናሳው ጎሣ ወገን በሆኑት ላይ መቅናት ጀመሩ፡፡

የአናሳ ወገን አካል መሆን ሁልጊዜ አስቸጋሪ ነው። ቋንቋና ባሕል አስፈላጊ ነገሮች ቢሆኑም ብዙ ጎሣ ላለበት ባሕል፣ ቋንቋና ፍላጎት መገዛት ፍትሐዊ አይደለም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዲሞክራሲ አለ ማለት ሁልጊዜ የብዙኃኑ ፍላጎት ያሸንፋል ማለት ነው። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በዲሞክራሲ ላይ ሳይሆን በፍቅር ላይ ነው። ፍቅር ደግሞ፥ እየተጎዳ ያለው ማን ነው? እንዴት ልርዳ?” ይላል። ፍቅር ሁልጊዜ የግል ወይም የባሕል መብቶችን በመናቅ፥ የሌሎችን ጥቅም ለማስቀደም ይፈልጋል፡፡ ጳውሎስ ስለ «ብርቱ» ክርስቲያኖችና «ደካማ» ክርስቲያኖች ከተናገረ በኋላ «ብርቱዎቹ ክርስቲያኖች «ደካማዎቹ» የሚጎዱበትን ነገር ማድረግ እንደሌለባቸው አስረድቷል (1ኛ ቆሮ. 10፡23-32)። በተመሳሳይ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ከተፈለገ፥ የብዙ ምእመናን ባሕል ከሆነው ከዲሞክራሲው አስተሳሰብ በማለፍ የአናሳውን ባሕል ለማክበር መሻት አለበት። ይህ በሚሆንበት ጊዜ፥ ክርስቲያኖች ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈል የሚሸርበውን ሴራ በቀላሉ ሊያፈርሱ ይችላሉ፡፡ የጥርጣሬው መርዝ ከተወገደ በኋላ የአናሳው ባሕል በተራው የአናሣውን ባሕል ያከብረዋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላምና አንድነት የሚሰፍነው ሰዎች ቤተኛነት ሲሰማቸውና አንዱ ሌላውን ሲያደምጥና ሲያከብር ነው፡፡

የውይይት ጥያቄ:- ሀ) በአብዛኛውና በአናሳው ጎሣ መካከል በቤተ ክርስቲያን ውጥረት የተነሣበትን ሁኔታ ግለጽ፡፡ ለ) እነዚህ መርሖዎች አንድነትና ሰላም ለማምጣት የሚረዱት እንዴት ነው?

ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፈልና ለማዳከም ይችል የነበረው ችግር፣ የአማኞችን ፍቅርና አንድነት የበለጠ ለመግለጽ ቻለ። ከዚህም የተነሣ፥ ቤተ ክርስቲያን የበለጠ በፍጥነት ማደግ ጀመረች። ብርቱ የቤተ ክርስቲያን ጠላት የነበሩት ካህናት ሳይቀሩ በክርስቶስ አምነው ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት ጀመሩ፡፡

ሉቃስ፣ ሁለተኛው ዐቢይ የመሪዎች ቡድን እንዴት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ ተጀመረ ገልጾአል። የመጀመሪያው ቡድን የሐዋርያት ሲሆን፥ ይህም በኋላ በእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በጳጳሳት ወይም ሽማግሌዎች ተተክታል። የእነዚህ አገልጋዮች ተቀዳሚ ኃላፊነት መንፈሳዊ ሲሆን በስብከት፣ በማስተማርና በምስክርነት ላይ ያተኩራል። ሁለተኛው ቡድን ዲያቆናትን የሚያካትት ነበር። ዲያቆናት አንዳንድ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታየው ወጣቶች አይደሉም። ይሁንና ዲያቆናት እጅግ አስፈላጊ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ናቸው። «ዲያቆን» የሚለው ቃል «ማዕድ እገልጋይ» ወይም በአጭሩ «አገልጋይ» ማለት ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያንን በሚያስፈልጋት የሚያገለግል ማለት ነው። ዲያቆናት የድሆች ችግር መቃለሉን መመልከት ነበረባቸው። በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3 ላይ ጳውሎስ ለሁለቱም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መመዘኛዎችን አስፍሯል። ለሽማግሌዎችና ለዲያቆናት የቀረበው መዘኛ ብዙም ልዩነት የለውም።

የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ራስ የሆኑት ሐዋርያት አሁን ደግሞ ኃላፊነቱን ለሌሎች ሲያስተላልፉ ይታያሉ፤ ሐዋርያቱም በዲያቆናቱ ላይ እጆቻቸውን ጭነው ጸለዩላቸው። ይህም አይሁዶች በረከትን፥ ሥልጣንን፥ ብሎም ኃላፊነትን ለማስተላለፍ የሚጠቀሙበት መንገድ ነበር። እነዚህ ሰባቱ ከተቀሩት አባላት ተለይተው ለድሆች እንክብካቤ እንዲያደርጉ ኃላፊነት ተሰጣቸው። ሐዋርያት ይህንን ኃላፊነት ከሰጧቸው በኋላ በሥራቸው ውስጥ ጣልቃ አልገቡም። በዲያቆናቱ ላይ እምነት የነበራቸው ሲሆን፥ መንፈስ ቅዱስም እንደሚመራቸው ያምኑ ነበር። ዛሬ ሽማግሌዎች ከሚፈጽሟቸው ስሕተቶች መካከል አንዱ፥ ኃላፊነት በሰጧቸው ሰዎች ሥራ ውስጥ ጣልቃ መግባት ነው። ትክክለኛ ሰዎች ተመርጠው ከሠለጠኑና የሥራ ኃላፊነታቸውም ተብራርቶ ከተነገራቸው በኋላ፥ በመንፈስ ቅዱስና ለሰዎቹም በሚሰጣቸው ጥበብ ላይ መደገፍ ይኖርባቸዋል። የሽማግሌዎቹ ኃላፊነት ከእነርሱ በታች ላሉት ሰዎች ኃላፊነታቸው ምን እንደ ሆነ ግልጽ ማድረግና እያንዳንዱ ሰው የኃላፊነቱ ዓላማ ምን እንደ ሆነ ማሳወቅ ነው። ከዚህ በኋላ ሽማግሌዎቹ ገለል ብለው የተመረጡት ወይም የተወከሉት ሰዎች ሥራውን እንዴት ለማከናወን እንደሚችሉ ዝርዝር ነጥቦችን እንዲያወጡ ዕድል መስጠት ነው። ሽማግሌዎች መንፈስ ቅዱስ የእነርሱን ሥራ እንደሚመራ ሁሉ፥ እነርሱም የወከሏቸውን ሰዎች ሥራ መምራት እንዳለባቸው ማጤን ይኖርባቸዋል። ከዚያም የተፈለገው ዓላማ ከግቡ መድረስ አለመድረሱን በየጊዜው መከታተል አለባቸው። ሥራው እንዴት እንደሚካሄድ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ መግባት የለባቸውም። የሰዎችን ሞራል፣ የፈጠራ ችሎታ እና ጥበብ የሚያደናቅፈው የመሪዎች ጣልቃ ገብነት ነው። ከመጠን በላይ ጣልቃ ገብ መሆን መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ውጭ በሌሎች ሰዎች አማካይነት አይሠራም ማለታችን ነው።

የውይይት ጥያቄ:- ሀ) ሽማግሌዎች ለሰዎች የሥራ ኃላፊነት ከሰጡ በኋላ ጣልቃ ሲገቡ የተመለከትህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ኃላፊነቱ የተሰጣቸው ሰዎች ምን ተሰማቸው? ሐ) ሽማግሌዎች ለሥራው የመጨረሻ ውጤት ሠራተኞቹን በኃላፊነት እየጠየቁ፥ ሠራተኞቹ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት በችሎታቸው እንዲጠቀሙ ለማድረግ የሚችሉበት የተሻለ መንገድ ምን ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: