ሉቃስ ስለ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሚናገርበት ጊዜ፥ ትኩረቱን ከጴጥሮስ ወደ ጳውሎስ ላይ ያደርጋል። ነገር ግን ሉቃስ መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን እስከ ምድር ዳርቻ ለማድረስ ጳውሎስን እንዴት እንደ ተጠቀመበት ከመግለጹ በፊት፥ ቤተ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም ተወስና ከተቀመጠችበት ሁኔታ በመነሣት በሮም ማዕከል ስለሆነችበት ሁኔታ ያብራራል። እግዚአብሔር ወንጌልን መጀመሪያ ወደ ሰማርያ፥ ቀጥሎም ብዙ አሕዛብ በክርስቶስ ወዳመኑባት እንጾኪያ ለማድረስ የተጠቀመባቸው ግለሰቦች፥ አሁን ወንጌሉን እስከ ምድር ዳርቻ ለማድረስ ተልእኮ የተሰጣቸው የመጀመሪያዎቹ አለመሆናቸው የሚያስደንቅ ነው። እግዚአብሔር በሌሎች ሰዎች ነበር የተጠቀመው። ሉቃስ ስለ እነዚህ የለውጥ ጊዜያት በሚያብራራበት ወቅት፥ እስጢፋኖስና ፊልጶስ በተባሉ ሁለት ዲያቆናት ላይ አጽንኦት ሰጥቷል።
እስጢፋኖስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መበለቶችን እንዲያገለግል የተመረጠ የግሪክ አይሁዳዊ ነበር። ይህ ማለት ግን መንፈስ ቅዱስ የሰጠውን አስደናቂ ስጦታ በሌሎች መንገዶች ከጥቅም ላይ ሊያውል አይችልም ማለት አይደለም። ሐዋርያትም፥ «መስበክ፥ ማስተማርና መፈወስ» የእኛ አገልግሎት ነው። ብለው በቅናት መንፈስ ተይዘው የእስጢፋኖስን አገልግሎት አላገዱም። ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ በወደደው ሰው ሁሉ አማካይነት ሊሠራ እንደሚችል ተገንዝበው ነበር። ስለሆነም መንፈስ ቅዱስ ለአንድ ሰው ስጦታዎችን በሚያድልበት ጊዜ፥ ሐዋርያት የአገልግሎት በር አይዘጉበትም ነበር። ዛሬም ብዙ ሽማግሌዎች ይህን ምሥጢር ማወቅ ይኖርባቸዋል። አንዳንድ አገልግሎቶችን መፈጸም ያለባቸውና ክብርንም መውሰድ ያለባቸው እነርሱ ብቻ እንደሆኑ በማሰብ ሰዎችን አጥብቀው የሚቆጣጠሩ ከሆነ፥ ደስ ያሰኘውን ሰው የመምረጥና የመገልገል መብት ያለውን መንፈስ ቅዱስን መቃወማቸው ነው። አንድ ሽማግሌ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የአንድን ሰው አገልግሎት በሚወስንበት ጊዜ፥ መንፈስ ቅዱስን መቃወሙ ነው፡፡ ይህ ችግር ዘወትር ስለሚከሰት፥ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ያላቸው ሰዎች ለብዙ ዓመታት ያገለገሉበትን ቤተ ክርስቲያን ጥለው በመሄድ፥ በነጻነት ለማገልገል ወደሚችሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት ይፈልሳሉ።
እስከዚህ ጊዜ ድረስ፥ የማስተማርና የመፈወስ አገልግሎት ሲያከናውኑ የነበሩት ሐዋርያቱ ብቻ ነበሩ። አሁን ግን እስጢፋኖስ እንደ እነርሱ ከፍልስጥኤም ውጭ የኖሩ አይሁዶችን ለማስተማር ነጻነት አገኘ። በኢየሩሳሌም ብዙ ምኩራቦች ነበሩ። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ የፍልስጥኤም አይሁድ ያልሆኑ ሰዎች የሚሰበሰቡበት ነበር። ከምኩራቦቹ አንዱ «ነፃ የወጡ ሰዎች ምኩራብ» ይባል ነበር። በዚህ ምኩራብ ውስጥ ሲሰበሰቡ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ከቀሬና፥ ከእስክንድሪያ፥ ኪልቂያና እስያ የመጡ አይሁዶች ነበሩ። እነዚህ አይሁዶች ባርያ ሆነው የኖሩና በኋላ ነጻነታቸውን ያገኙ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል ባሪያዎች የነበሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ፥ ከፍልስጥኤም ውጭ የመጡ በመሆናቸው፥ አንድ ላይ ተሰባስበው የራሳቸውን ምኩራብ አቋቋሙ። 12ቱ ሐዋርያት በሙሉ ከፍልስጥኤም አካባቢ የመጡ በመሆናቸው ተቀባይነትን ለማግኘት ወደማይችሉባቸው ምኩራቦች እስጢፋኖስ ሄደ። ስለ ክርስቶስ ወንጌል በሚናገርበት ጊዜ እነዚህ አይሁዶች እጅግ ተቆጡ። ስለ እስጢፋኖስ የሐሰት ወሬ ካሰራጩ በኋላ፥ ለምርመራ ወደ አይሁድ ሸንጎ አቀረቡት።
ሉቃስ የእስጢፋኖስን ረዥም ስብከት የዘገበበት በርካታ ምክንያቶች አሉት። አንደኛው፥ የእስጢፋኖስ ስብከት ሐዋርያትና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ክርስቶስ የአይሁድ መሢሕ መሆኑን በመግለጽ ላቀረቡት ስብከት ምሳሌ ነበር። ሁለተኛው፥ ስብከቱ ቢያንስ እስጢፋኖስ ከኢየሩሳሌምና ከአይሁዶች በተጨማሪ በርከት ላሉ አካባቢዎች መመስከር መጀመሩን ያሳያል። እስጢፋኖስ እግዚአብሔር ታላላቅ ሥራዎችን ከፍልስጥኤም ውጭ ላሉ አይሁዶች ማድረጉን ገልጾአል። እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና ይሁዳ የተወሰነ ሳይሆን፥ ለዓለም ሁሉ ዕቅድ ያለው አምላክ ነው። ሦስተኛው፥ ስብከቱ በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያንና በይሁዲነት መካከል ትልቅ ልዩነት መፈጠሩን የሚያሳይ ይመስላል። እስጢፋኖስ የእግዚአብሔር ሕዝብ የአምልኮ ማዕከል ከእንግዲህ በኋላ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሱ እንዳልሆኑ አሳይቷል፤ ደግሞም ከእንግዲህ በኋላ የሙሴን የብሉይ ኪዳን ሕጎች መከተል አስፈላጊ አለመሆኑን ገልጾአል። አይሁድ እስጢፋኖስ የቤተ መቅደስና የሙሴ ሕግጋት ተቃዋሚ እንደሆነ አድርገው የከሰሱት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። ከእስጢፋኖስ ስብከት ከዚህ የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች ማስተዋል እንችላለን።
ሀ. የአይሁዶች ታሪክ የተጀመረው በፍልስጥኤም ላይሆን፥ በአሕዛብ መካከል ነበር። እግዚአብሔር አብርሃምን የጠራው የባቢሎናውያን ምድር ከሆነችው ዑር ነበር። ከነዓንን እንደሚወርስ የተስፋ ቃል ቢሰጠውም፥ አብርሃም ምንም መሬት አልነበረውም ማለት ይቻላል።
ለ. ቀጣዩ የአይሁድ ዐቢይ ታሪክም የተፈጸመው በከነዓን ላይሆን በግብጽ ነበር። በእስጢፋኖስ ዘመን የነበሩት አይሁዶች በክርስቶስና በሐዋርያት ላይ ቅናት እንዳደረባቸው ሁሉ፥ የአይሁድ ቅድመ አያት የሆኑት አሥሩ የያዕቆብ ታላላቅ ልጆችም በዮሴፍ ላይ ቀንተው በባርነት ወደ ግብጽ ሸጡት። እግዚአብሔር ግን የግብጽ አሕዛብ አይሁዶችን እንዲያድኑ አደረገ። አሁንም እግዚአብሔር ፈቃዱን የፈጸመው ከኢየሩሳሌም ውጭ ነበር።
ሐ. በአይሁድ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው ሙሴ፥ በእግዚአብሔር የተመረጠው ግብጽ አገር እያለ ነበር። 120 ዓመት የሚሆነውን የሕይወት ዘመኑን ያሳለፈው ከከነዓን ውጭ በመጀመሪያ በግብፅ ቀጥሎም በምድያም፥ በመጨረሻም በምድረ በዳ ነበር። እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘው ከፍልስጥኤም ውጭ በሲና ተራራ ላይ ነበር። እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሠራቸው ታላላቅ ተአምራት፥ ከፍልስጥኤም ውጭ በምድረ በዳ የተከናወኑ ነበር። ሙሴ ከእርሱ የሚልቅ ነቢይ እንደሚመጣ የተነበየው በዚያ ነበር። እግዚአብሔር ቅዱስ ሕጉን የሰጠው ከፓ
ለስቲና ውጭ በሲና ተራራ ላይ ነበር።
መ. በሙሴ ዘመን እንደ ነበሩት እንደ ያዕቆብ ልጆች ሁሉ አይሁዶች እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ በዐመፀኛነት ኖሩ። እግዚአብሔር በታላቅ ኃይሉ ነፃ ካወጣቸውም በኋላ እንኳ ልባቸው ግብፅ ስለነበር ወደዚያው ለመመለስ ይፈልጉ ነበር። ጣዖት ሠርተው ለማምለክ ሞክረዋል። በክርስቶስ ዘመን የታየው የአይሁዶች ዐመፀኛነት በምድረ በዳም በነበሩት አይሁዶች ላይ የታየ ነበር።
ሠ. እግዚአብሔር የመረጠው የመገናኛው ድንኳን ንድፉ የተሠራው በአሕዛብ አገር ሳሉ ነበር። ንጉሥ ዳዊት እግዚአብሔር የሚኖርበትን ዘላቂ ቤተ መቅደስ ለመገንባት ፈለገ። አሳቡን ያመነጨው እግዚአብሔር አልነበረም። በእስጢፋኖስ ዘመን የነበሩት አይሁዶች የእግዚአብሔር ትኩረት፥ ፍቅርና ዓላማ በቤተ መቅደሱ እንደ ተጠቃለለ ያስቡ ነበር። ከ60 ዓመት ቀደም ብሎ የተገነባው ታላቁ የሄሮድስ ቤተ መቅደስ እጅግ ውብ በመሆኑ፥ እግዚአብሔር ምንም ነገር እንዲደርስበት አይፈልግም የሚል አሳብ ነበራቸው። ይህን ሲያስቡ ግን ማንኛውም ሰው ሠራሽ ሕንጻ እግዚአብሔርን ለማስተናገድ ብቃት እንደሌለው ዘንግተው ነበር። ፍጥረት በሙሉ እንኳ እግዚአብሔርን ሊይዝ አይችልም። ከቤተ መቅደስ እጅግ የምትበልጠው ምድር ራሷ በምሳሌያዊ አገላለጽ የእግሩ መረገጫ ብቻ ናት።
የውይይት ጥያቄ፡- ዛሬ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሚደረግ ግንኙነትና አምልኮ በላይ በተለየ ሁኔታ እዚያ እንደሚገኝ በማሰብ፥ በቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ላይ ከፍተኛ ትኩረት የምናደርገው እንዴት ነው?
ዛሬ አንዳንድ ክርስቲያኖችም እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያናቸው ላይ ምንም ክፉ ነገር እንደማያደርስ አድርገው ያስባሉ። ቀደም ሲል የኮሚኒስት መንግሥት አብያተ ክርስቲያናትን በመዝጋት አምልኮ እንዲቆም ያደርጋል ብለው አላሰቡም ነበር። እግዚአብሔር ግን በቤተ ክርስቲያን ሕንጻ የተወሰነ አምላክ አይደለም። እግዚአብሔር ውብ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሠርተን እርሱ እንደሚኖርበት ልዩ ስፍራ እንድንመለከት አላዘዘንም። ከአንድ መቶ ዓመት በላይ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በግለሰብ ቤቶች እንጂ፥ በቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች ውስጥ አያመልኩም ነበር። በኮሚኒስት ዘመን አምልኮ ይደረግ የነበረው በአማኞች ቤት ውስጥ ነበር። በዚህ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን አድጋለች። በዚህ ረገድ በእስጢፋኖስ ዘመን እንደ ነበሩት አይሁዶች የተሳሳተ አሳብ ይዘናል ማለት ነው።
ረ. እስጢፋኖስ አይሁዶች እግዚአብሔር ስለ ፍልስጥኤም ምድርና ስለ አይሁድ ሕዝብ ብቻ እንደሚጨነቅ በማሰባቸውና በቤተ መቅደስ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረጋቸው፥ አድማጮቹ እንደ ብሉይ ኪዳን አይሁዶች ሆነው መገኘታቸውን ገልጾአል። አለማመን አሁንም በሕዝቡ ላይ ይታይ ነበር። በብሉይ ኪዳን አባቶቻቸው የእግዚአብሔርን መንገድና እርሱም የሰጣቸውን መሪዎች ተቃውመው ነበር። ሙሴ፥ ዳዊት፥ ኢሳይያስና ኤርምያስ ሁሉም አይሁዶች እግዚአብሔር የላካቸውን መሪዎች እንደ ተቃወሙ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ናቸው። በእስጢፋኖስ ዘመን ደግሞ አይሁዶች መሢሑን ኢየሱስን ተቃውመዋል። የእስጢፋኖስ አድማጮችም እግዚአብሔር የላካቸውን ሐዋርያትና ክርስቲያኖችን በመቃወም ላይ ነበሩ። እንደ ብሉይ ኪዳኖቹ ሁሉ፥ በእስጢፋኖስም ዘመን የነበሩት አይሁዶች በእጃቸው የእግዚአብሔርን ሕግ ይዘው ነበር። የሚያስፈልገው ግን የእግዚአብሔርን ሕግ መታዘዝ እንጂ መያዝ አይደለም። አይሁዶች ክርስቶስን ባለመቀበላቸው የእግዚአብሔርን ሕግ ተላልፈዋል። በሥጋ የተገረዙ አይሁዶች ያልተገረዘ ልብ ነበራቸው። ይህም እነርሱ እንደሚንቋቸው አሕዛብ ያልተገረዙ አድርጓቸዋል።
እስጢፋኖስ ለቤተ መቅደሱ ከፍተኛ ትኩረት አልሰጠም፤ እንዲያውም አድማጮቹን የመደባቸው ከዐመፀኞች ጎራ ነው፤ በዚህም ይሰሙት የነበሩት ሁሉ እጅግ ተቆጡ። ነገር ግን እግዚአብሔር የሰማይ በሩን ከፍቶ እስጢፋኖስ ዙፋኑንና በአብ ቀኝ በሥልጣን የተቀመጠውን ክርስቶስን እንዲመለከት ሲያደርግ፥ የአይሁዳውያኑ ቁጣ ቅጥ አጣ፡፡ ከቤት በማውጣት በድንጋይ ወግረው ገደሉት። እስጢፋኖስ የጌታውን ምሳሌ በመከተል ነፍሱን በክርስቶስ እጅ አኖረ። እንደ ክርስቶስ ሁሉ፥ እስጢፋኖስም አይሁዶችን ይቅር በማለት እግዚአብሔር በሥራቸው እንዳይፈርድባቸው ጸለየ።
ሉቃስ እስጢፋኖስን የክርስቲያን ሰማዕት ምሳሌ አድርጎ ጠቅሶታል። እስጢፋኖስ እምነቱን ደብቆ በዝምታ መኖር ሲችል ይህን ግን አላደረገም። ይልቁንም ወንጌልን በድፍረትና በግልጽ ሰበከ። በሕይወት ለመኖርም ሆነ ለመሞት ሙሉ ሥልጣኑን ለእግዚአብሔር ሰጠ። ሞት ሲመጣበት ደግሞ በእርጋታና በእግዚአብሔር ላይ በመታመን ሕይወቱን ሰጠ። እስጢፋኖስ ለዚህ ሥቃይ በዳረጉት ሰዎች ላይ ጥላቻና መራርነት አላደረበትም። እግዚአብሔር ግን ይቅር እንዲላቸው ለመነ። ይህ የፍጹም መሥዋዕትነት ፍቅር ምልክት ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ከእስጢፋኖስ ሕይወትና አሟሟት ለክርስቶስ ስለ መመስከር ምን እንማራለን?
ሉቃስ በዚህ አጋጣሚ ሳውል የተባለ ሰው ያስተዋውቀናል። በአይሁድ ባሕል፥ አንድ ሰው በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት ምስክርነት የሰጠ ሰው የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወረውር ነበር። ሉቃስ ምስክሮቹና ምናልባትም ሌሎችም ሰዎች ልብሶቻቸውን ሳውል እንዲጠብቅላቸው እንዳደረጉ ገልጾአል። አንዳንድ ምሑራን ሳውል፥ እስጢፋኖስ በድንጋይ እንዲወገር መስማማቱን ብቻ ሳይሆን፥ በድንጋይ ሲወገርም ሁኔታውን ይቆጣጠር እንደነበር ያመለክታል ይላሉ። የምኩራብ መሪዎች ግድያውን ሳውል እንዲያስፈጽም ኃላፊነት ሰጥተውት ነበር።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)