ጴጥሮስ አንድ ሽባ ለማኝ በፈወሰ ጊዜ የተነገሩ ተከታታይ ታሪኮች (የሐዋ. ሥራ 3፡1-5፡42)

«ይምጡና በዓለም የታወቀውን ሰባኪና የፈውስ አገልጋይ ይስሙ። የታመማችሁ ሁሉ ብትመጡ ትፈወሳላችሁ። የታመሙና ዓይነ ስውር ጎረቤቶቻችሁን ሁሉ አምጧቸው። ክርስቶስ በስብሰባው ላይ እንደሚፈውሳቸው ንገሯቸው።» ከተማዪቱን ለመጎብኘት ለሚመጣው ዝነኛ የፈውስ አገልጋይ የሚደረገው ማስታወቂያ እንዲህ እያለ ይቀጥላል። እንደዚህ ዓይነት አሳቦችን በክርስቶስና በሐዋርያት የአገልግሎት ዘመን ከተፈጸሙት ሁኔታዎች ጋር ስናነጻጽር አያሌ ልዩነቶች እንመለከታለን። በመጀመሪያው ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያት ተአምራትን በመሥራት ሰዎችን ወደ ራሳቸው ለመሳብ አልጣሩም። ሁል ጊዜም እግዚአብሔርን ለማክበር ይፈልጉ ነበር። ሁለተኛው፥ የክርስቶስና የሐዋርያቱ ትኩረት ሰዎች ንስሐ ገብተው እንዲመሰክሩ ማድረግ እንጂ፥ መፈወስ አይደለም። ሰዎችን መጥታችሁ ተፈወሱ እያሉ ሲጋብዙ አንመለከትም። ሦስተኛው፥ ሁል ጊዜ ማለት ይቻላል፥ ክርስቶስና ሐዋርያቱ ከተፈወሰው ግለሰብ ጋር ይገኛሉ እንጂ የጅምላ ፈውስ አያካሂዱም።

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በሐዋርያት ሕይወት ውስጥ በሚሠራው መንፈስ ቅዱስ አማካይነት ክርስቶስ አገልግሎቱን እንደ ቀጠለ ያሳያል። ከክርስቶስ አገልግሎት ውስጥ ተአምራትና ፈውስም ይገኙ ነበር። የሐዋርያት ሥራ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምሳሌ መሆን ካለበት፥ ተአምራት እንዴት መፈጸም እንዳለባቸውና ለቤተ ክርስቲያን የተአምራት አስተዋጽኦ ምን መሆን እንዳለበት በምሳሌ ማሳየት ይኖርበታል።

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋ. 3ን አንብብ። ሀ) የጴጥሮስንና የዮሐንስን ተአምር ከዛሬዎቹ ዝነኛ አገልጋዮች ተአምራት ጋር አነጻጽር፡፡ ልዩነቱና ተመሳሳይነቱ ምንድን ነው? ለ) እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያንን እድገት ለማገዝ ተአምሩን የተጠቀመው እንዴት ነው? ሐ) በጴጥሮስ ስብከትና በምዕራፍ ሁለት ስብከት መካከል ያለው ተመሳሳይነት ምንድን ነው?

የሐዋርያት ሥራ 3-5 ጴጥሮስ አንድ ሽባ ለማኝ በፈወሰ ጊዜ የተነገሩ ተከታታይ ታሪኮች ናቸው። እነዚህ ታሪኮች የመጽሐፉ አንድ ክፍል ናቸው።

  1. የሽባው ለማኝ መፈወስ (የሐዋ. 3፡1-10)

ሐዋርያት ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ እርሱን ወክለው ሥራውን ቀጥለዋል። ከክርስቶስ አገልግሎቶች አንዱ ሰዎችን መፈወስ ነበር። ሉቃስ ቀደም ሲል ሐዋርያት ሁሉ ተአምራት መፈጸማቸውን ገልጾአል፤ በዚህ ክፍል ደግሞ በጴጥሮስ ላይ ትኩረት አድርጓል። ሉቃስ ጴጥሮስና ዮሐንስ ሽባውን ለማኝ ስለ ፈወሱበት ሁኔታ በመግለጽ ተአምራቶቹን ያብራራል።

ዮሐንስና ጴጥሮስ ለአምልኮ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚሄዱበት ጊዜ፥ በቤተ መቅደሱ ደጃፍ ላይ ሽባ ሰው ምጽዋት ሲለምን አገኙት። በብዙ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አካባቢ እንደሚታየው፥ ከምእመናን ምጽዋት የሚለምኑ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ለማኙ ገንዘብ ከመለመኑ በስተቀር እፈወሳለሁ የሚል እምነት አልነበረውም። ሌሎች ለማኞችም በአካባቢው እንደሚኖሩ አያጠራጥርም። ጴጥሮስ እርሱን ለምን እንደ መረጠው አናውቅም። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ የጴጥሮስን ልብ ስለነካው ጴጥሮስ ለማኙ ተነሥቶ እንዲራመድ አዘዘው። ወዲያውም ቅጽበታዊ ፈውስ ተፈጸመ። ጴጥሮስ፥ «በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም» በማለት የተናገረውን ማጤኑ አስፈላጊ ነው። ከዚህ አያሌ እውነቶችን መገንዘብ እንችላለን።

ሀ. በደቀ መዛሙርቱ አእምሮ ውስጥ የናዝሬቱ ኢየሱስ የሚለው ስም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደሚል ተቀይሮ ነበር። ከዚህ በኋላ፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ «ኢየሱስ» የሚለው ስም ለብቻው አላገለገለም። ይልቁንም ኢየሱስ የሚለው ስሙ ከክርስቶስና መሢሑ ጋር አብሮ ይጠቀስ የነበረ ሲሆን፥ ይህ ካልሆነ ለብቻው ክርስቶስ እየተባለ ተጠርቷል።

ለ. ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ኢየሱስ ወይም ኢያሱ የሚለው የተለመደ ስም ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስን ከሌሎች ኢየሱሶች ለመለየት ሰዎች «የናዝሬቱ» የሚል ሐረግ ይጠቀሙ ነበር። ይህም መሢሑና ኃይልን የሰጣቸው ክርስቶስ በናዝሬት እንዳደገ የሚያመለክት ነበር።

ሐ. «በ. . . ስም» የሚለው ስሙን የያዘውን አካል የሚያመለክት የአይሁዶች አገላለፅ ነበር። ይህም ስሙ በራሱ ምትሐታዊ እንደሆነ በማሰብ የሚደረግ አጠራር ሳይሆን፥ ራሱ ክርስቶስን የሚያመለክት ነው።

መ. ጴጥሮስ ተአምሩ በኢየሱስ ስም እንደ ተፈጸመ ሲናገር፥ ተአምሩ የተሠራበት ኃይልና ሥልጣን ከክርስቶስ መገኘቱን መግለጹ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ብዙ ክርስቲያኖች በጸሎታቸው ውስጥ «በኢየሱስ ስም» ሲሉ ምን ማለታቸው ይመስልሃል? ይህ ከአይሁዶች አጠቃቀም ጋር ይመሳሰላል ወይስ ይለያያል?

  1. ክርስቶስ በተአምሩ ለተደነቁት ሰዎች ሰበከ (የሐዋ. 3፡11-26)።

እግዚአብሔር ተአምራትን ከሚያደርግባቸው ምክንያቶ አንዱ፥ የወንጌልን ስብከት ለማጽናት ነው። (የሐዋ. 2፡22፤ ዕብ. 2፡4፤ 2ኛ ቆሮ. 12፡12 አንብብ።) ሌላው ምክንያት ደግሞ ሰዎች በደንብ እንዲያደምጡ ለመቀስቀስ ነው። ተአምራት በማይኖርበት ጊዜ ችግሮቻችንን ራሳችን እንደምንፈታ በማሰብ ተደላድለን እንቀመጣለን። እግዚአብሔር ተአምራትን በሚያመጣበት ጊዜ ግን እንደ ተአምራት አምላክ ችግሮቻችንን ይፈታልን ዘንድ፥ ወደ እርሱ እንድንቀርብ መጋበዙ ነው።

ጴጥሮስ ያደረገውን ተአምር ሰዎች በተመለከቱ ጊዜ ይህን የመሰለ ሁኔታ ተፈጽሟል። የጴጥሮስ ስብከት ከበዓለ ኀምሳ በኋላ ካቀረበው ስብከቱ ጋር ተመሳሳይ ነው። ከዚህ ስብከት ውስጥ የሚከተሉትን ነገሮች መመልከት ይቻላል።

ሀ. ጴጥሮስ፥ ተአምሩ የተፈጸመው በክርስቶስ እንጂ በራሱ እንዳልሆነ በአጽንኦት ገልጾአል። የሰቀሉት ክርስቶስ ልክ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ እንደሚያደርገው አሁንም በደቀ መዛሙርቱ አማካይነት ተአምራትን በመሥራት ላይ ነበር።

ለ. ጴጥሮስ፥ ስለ ክርስቶስ ማንነት የነበረው ግንዛቤ ጨምሯል። ከክርስቶስ ትንሣኤ ጥቂት ሳምንታት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ «ቅዱስና ጻድቅ» መሆኑን አጥብቀው ሊያምኑ ችለዋል። ይህ ለእግዚአብሔርም ለመሢሑም የሚያገለግል ስያሜ ነው፡፡ እንዲሁም ጴጥሮስ ክርስቶስን «የሕይወት ራስ» (ምንጭ) ሲል ጠርቶታል። ይህ አስደናቂ ዓረፍተ ነገር አይሁዶች ለነገሮች ሁሉ ሕይወት የሚሰጠውን ክርስቶስን እንደ ገደሉት ያመለክታል።

ሐ. ክርስቶስ ነቢያት የመሰከሩለት ነቢይ ነው። (ዘዳግም 18፡18 አንብብ።) ይሁን እንጂ በወንጌላት ውስጥ አይሁዶች ክርስቶስ በሙሴ ትንቢት የተነገረለት መሢሕ መሆኑን አምነው እምብዛም አይናገሩም ነበር። ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በኋላ ግን ደቀ መዛሙርቱ፥ ክርስቶስ ሙሴ ትንቢት የተናገረለት ታላቅ መሢሕ መሆኑን ተገንዝበዋል።

መ. ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ፍጻሜ ነው።

ሠ. እግዚአብሔር ለአይሁዶችና ለጠቅላላው ዓለም ተስፋ የገባላቸውን በረከቶች ለመቀበል እንዲችሉ፥ የግድ ክርስቶስን እንደ መሢሐቸው መቀበል ነበረባቸው። ከዚያ በኋላ ክርስቶስ እንደ መሢሐዊ ንጉሥ ወደ እስራኤል በመመለስ አይሁዶች ሲጠባበቁ የነበረውን የበረከት ጊዜ ያመጣል።

  1. ጴጥሮስና ዮሐንስ በአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ተከሰሱ ( የሐዋ. 4፡1-31)።

ስደት የተከታዮቹ ሕይወት አካል እንደሚሆን ክርስቶስ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። እስከዚህ ጊዜ ድረስ ደቀ መዛሙርቱ በሕዝቡ ዘንድ ታዋቂ ነበሩ፥ የሚጠላቸውም ሰው አልነበረም። ብዙም ሳይቆይ የሃይማኖት መሪዎች በደቀ መዛሙርቱ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ይሰነዝሩ ጀመር። የአይሁድ መሪዎች ክርስቶስን በመግደል፥ የእርሱን ጉዳይ ከፍጻሜ ያደረሱ መስሏቸው ነበር። ወዲያውኑ ግን ክርስቶስ የፈጸመውን ተአምራት የሚሰብኩ ብዙ ደቀ መዛሙርት ይታዩ ጀመር። ይህም ክርስቶስን ለማስቆም ያደረጉትን ጥረት ከንቱ አደረገው።

የሃይማኖት መሪዎቹ ጴጥሮስንና ዮሐንስን አሰሯቸውና በቀጣዩ ጠዋት የአይሁድ ከፍተኛ ችሎት በነበረው ሸንጎ ፊት አቀረቧቸው። ክርስቶስ ቀደም ሲል ደቀ መዛሙርቱ በሃይማኖት መሪዎች ፊት በሚቀርቡበት ጊዜ መጨነቅ እንደሌለባቸው ገልጾ ነበር (ማቴ 10፡19)። በዚህ ዓይነት ስፍራ ሲቀርቡ መፍራታቸው ተፈጥሮአዊ ጉዳይ ነው። ደቀ መዛሙርቱ በሸንጎው ፊት በሚጠይቋቸው መሪዎች ደረጃ ሲታዩ ያልተማሩ ተራ የገጠር ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን ጴጥሮስ ለመሪዎቹ የሰጠው ምላሽ ድፍረት የተሞላበትና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ከምናገኘው ትረካ ሁሉ በጣም በግልጽ የቀረበ ነው።

ሀ. እንዲፈውሱ ኃይልና ሥልጣን የሰጣቸው አይሁዶቹ የገደሉትና ከሞት የተነሣው ክርስቶስ ነበር።

ለ. ክርስቶስ የሃይማኖት መሪዎች የጣሉትና እግዚአብሔር የመረጠው የእግዚአብሔር ሕዝብ የማእዘን ራስ ነው።

ሐ. ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው። አይሁዶች የብሉይ ኪዳን ተከታዮች በመሆናቸው፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ሊያገኙ አይችሉም። ክርስትና ግን እጅግ የተለየ እምነት ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ ከክርስቶስ በቀር ሌሎች መንገዶች ሁሉ እንደማያዋጡ ያስተምራል። መሐመድም ሆነ ቡድሃ ወደ እግዚአብሔር ሊያደርሱን አይችሉም። ወደ ቅዱሱ አምላካችን መቅረብ የምንችለው በክርስቶስ ስናምን ብቻ ነው። የትኛውም ሃይማኖት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የለውም።

የደቀ መዛሙርቱ ስብከት በጣም ብርቱ በመሆኑ፥ የሃይማኖት መሪዎቹ ተደነቁ። እንዳልተማሩ የገጠር ሰዎች ሳይሆን ክርስቶስ በነበረው ዓይነት ሥልጣን ይናገሩ ነበር። እኛንም ሰዎች የክርስቶስ መሆናችንን የሚያውቁት፥ በንግግራችንና በኑሮአችን ነው።

ጴጥሮስ ካሁን በኋላ በክርስቶስ ስም እንዳይናገሩ ለተሰጠው ትእዛዝ ያቀረበው ምላሽ፥ በክርስቲያኖችና በመንግሥት መካከል ላለው ግንኙነት መልካም ማብራሪያ ነው። መንግሥትን እንድናከብርና ቀረጥ እንድንከፍል ታዝዘናል (ሮማ 8፡1-7፤ ማር. 12፡13-17)። ነገር ግን መንግሥት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚተላለፍ ነገር እንድናደርግ ሲያዘን (ክርስቶስ እንዲመሰክሩ አዝዟቸዋል፡፡ የመንግሥትን ትእዛዝ መቀበል አንችልም። መንግሥትን አለመታዘዝ ቅጣትን እንደሚያስከትል ወደ በኋላ እንመለከታለን። ነገር ግን ጊዜያዊ ከሆኑ ጌቶች በላይ ዘላለማዊ የሆነውን ንጉሥ ማክበር እጅግ የተሻለ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- አንተ ወይም ሌላ ሰው ከመንግሥት ወይም ከሥራህ ኃላፊ በላይ፣ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ የተገደዳችሁትን ሁኔታ አብራራ። ምንድን ነው የሆነው? እግዚአብሔር ያንን ሰው እንዴት ነው ያከበረው?

በዚህ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ድፍረትን የሰጣቸው ምን ነበር? ክርስቶስ ከስደትና ከመከራ ይጠብቀናል ብለው በማመናቸው ነበር? አልነበረም። ድፍረት ያገኙት እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ በመምራት ላይ እንደሆነ በማመናቸው ነበር። እግዚአብሔር በአሕዛብና በሕዝብ መሪዎች ላይ ልዑል እንደሆነ በጸሎታቸው አመልክተዋል። እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ውጊያ ቢገጥሙ ሊያሸንፉት አይችሉም። ደቀ መዛሙርቱ እግዚአብሔር የሰዎችን ክፉ ተግባር (ክርስቶስን መግደላቸውን) በመጠቀም አሳቡንና ፈቃዱን መፈጸም እንደ ቻለ ተገንዝበዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔር ሳያውቀው በሕዝቡ ላይ የሚደርስ ምንም ነገር የለም። ክፋት በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ስለሆነ፥ አብዛኛውን ጊዜ እግዚአብሔር መንግሥቱን ለማስፋፋት ይጠቀምበታል፡፡

የእነዚህን ጥንት ክርስቲያኖች ጸሎት ማንበብ አስገራሚ ነው። እግዚአብሔር ከስደት እንዲታደጋቸው አልጠየቁትም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያንና ለመንግሥቱ የሚጠቅመውን ነገር እንዲወስን ፈቅደውለታል። በሥራቸው ድፍረት በአገልግሎታቸው ደግሞ ፍሪያማነትን እንዲሰጣቸው ተማጠኑት። ጸሎታቸው «እግዚአብሔር ሆይ፥ ሥራህ እንዲስፋፋ እንጸልያለን። ቤተ ክርስቲያን እንድታድግና ክብርህ እንዲገን እንለምንሃለን። የምንፈልገው አንተ በእኛ እንድትከብር ብቻ ነው። በእኛ ላይ የሚደርሰው መከራ አያሳስበንም» የሚል ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የደቀ መዛሙርቱ ጸሎት እኛ በስደት ወይም ችግር ወቅት ከምንጸልየው እንዴት ይለያል? ለ) «እድነን» ከሚለው ጸሎታችን በተቃራኒ የደቀ መዛሙርቱ ጸሎት ከፍተኛ መንፈሳዊ ብስለትን የሚያሳየው እንዴት ነው?

እግዚአብሔር ጸሉታቸውን መለሰ። ኃይሉ እንደ ቀጠለና እርሱ ሁሉን ነገር እንደሚቆጣጠር ለማሳየት ሲል ቤቱን አናወጠው። እንዲሁም፥ ለጸሎታቸው መልስ በመስጠት ቃሉን የሚሰብኩበትን ድፍረት አጎናጻፋቸው።

  1. ሉቃስ የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ራስ ወዳድ አለመሆን ገለጸ (የሐዋ. 4፡32-37)

የሐዋርያት ሥራ ምዕ. 5 እንድ ባልና ሚስት መሬት ሸጠው ግማሹን ገንዘብ ለሐዋርያት ሰጥተው ግማሹን ለራሳቸው ካስቀሩ በኋላ፥ ሁሉንም እንደ ሰጠ ሰው በመምሰል እግዚአብሔርን ስላታለሉ ሰዎች የሚያወሳ ታሪክ ነው። ሉቃስ የእነዚህን ባልና ሚስት ድርጊት ከሌሎች ሰዎች ጋር ያነጻጽራል። በዚያን ዘመን የቤተ ክርስቲያን አንድነት የጠበቀ ሲሆን፥ ብዙ ሰዎች ከራስ ወዳድነት በፀዳ መንፈስ ንብረታቸውን እየሰጡ ገንዘቡን ለሐዋርያት ይሰጡ ነበር፡፡ ገንዘቡም ለጋራ ጥቅም ይውል ነበረ፡፡ በመሆኑም፥ ሐዋርያት ሥራ ፍለጋ ሳይሄዱ የስብከት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ይችሉ ነበር። በተጨማሪም፥ ክርስቲያኖች በየቀኑ እየተሰበሰቡ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲማሩ፥ እንዲጸልዩና እንዲያመልኩ አስችሏቸዋል። ሉቃስ በርናባስ የተባለው ሰው ንብረታቸውን ሸጠው ገንዘብ ካመጡት ግለሰቦች አንዱ እንደሆነ ገልጾአል። ደቀ መዛሙርቱ በርናባስ ሰዎችን የማበረታታት ልዩ ተሰጥኦ እንዳለው በመረዳታቸው፥ «የመጽናናት ልጅ» ብለው ሰየሙት። እግዚአብሔር የበርናባስን ስጦታ በሚገባ ተጠቅሞበታል። ብዙም ሳይቆይ፥ በርናባለ ሁሉ ሰው የፈራውን ሳውልን አጽናንቶታል። ሳውልም ጳውሎስ ተብሎ ታላቅ የአሕዛብ ሐዋርያ ለመሆን በቃ፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- ብዙ ክርስቲያኖች ሌሎችን ከማጽናናት ይልቅ የምንተቻቸው ለምን – ይመስልሃል? አጽናኝ መሆን የሚጠቅመው ለምንድን ነው? የማጽናናት ስጦታ ያላቸውን ሦስት ሰዎች ዘርዝር። በዚህ ሳምንት ውስጥ እግዚአብሔርን፥ በዚህ መንገድ ስለማገልገላቸው አመስግናቸው።

  1. ሐናንያና ሰጲራ በመዋሸታቸው እግዚአብሔር ቀሠፋቸው (የሐዋ. 5፡1-11)፡፡

ለቤተ ክርስቲያን እጅግ አደገኛ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ፥ ያልሆንነውን እንደሆንን አስመስለን የምንቀርብበት የግብዝነት ኃጢአት ነው። ሉቃስ እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ ያለውን ጥላቻ ለማሳየት ሲል፥ የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ለማጥራት የወሰደውን እርምጃ በምሳሌ አብራርቷል። የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ለመምሰል ስንፈልግ እንዲህ ዓይነቱንስ ብርቱ ፍርድ እንመኛለን? በአንድ ወቅት አንድ ግለሰብ እንደ ተናገረው፥ እግዚአብሔር ዛሬ በሐናንያና በሰጲራ ላይ የወሰደውን ብርቱ የፍርድ እርምጃ ተግባራዊ ቢያደርግ፥ ቤተ ክርስቲያኖቻችን በሙሉ ባዶአቸውን ይቀሩ ነበር በማለት ተናግሯል።

የሐናንያና ሰጲራ ኃጢአት፥ በሕዝቡ ፊት መንፈሳዊ መስለው ለመታየት መሞከራቸው ነበር። ይህንንም ያደረጉት እውነተኛውን ነገር በመደበቅ ነበር። ንብረታቸውን እንዲሸጡ ያስገደዳቸው ሰው አልነበረም፡፡ ከሸጡትም በኋላ እንኳ በገንዘቡ የፈለጉትን ለማድረግ ይችሉ ነበር። ለሐዋርያቱ 50 በመቶ ወይም 70 በመቶ ለመስጠት መፈለጋቸውን ሊናገሩ ይችሉ ነበር። ነገር ግን እንደ በርናባስና ሌሎችም ሰዎች ከልባቸው መንፈሳውያን መስለው ለመታየት ስለ ፈለጉ፣ መቶ በመቶ ሰጥተናል አሉ። እግዚአብሔርም ሐናንያንና ሰጲራ በመቅስፍ በግብዝነታቸው የተነሳ ፈጣን እርምጃ ወሰደባቸው።

ይህም ሁኔታ ሰዎች በእግዚአብሔር ኃይል እንዲደነቁና በቅድስና እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቅድስና እምብዛም ስፍራ ሲሰጠው አናይም። እንደ ውሸት፣ ብዝነት፣ ማጭበርበር፣ ሐሜት፣ መከፋፈልና ዝሙትን የመሳሰሉ የብዙ ክርስቲያኖች ዕለታዊ ሕይወት ሆነዋል። እግዚአብሔር ሕይወታቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ለማስማት አሻፈረኝ የሚሉ ሰዎችን እንድትቀጣ፥ ለቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ሰጥቷታል። ስለዚህ እኛ አንዳንዶችን በመጽሐፍ ቅዱሱ መርሕ መሠረት ብንቀጣቸው (ማቴ 18፡15-17 እንብብ)፥ በቤተ ክርስቲያናችንና በሕይወታችን ውስጥ እግዚአብሔርን መፍራትና ቅድስና ሊሰፍን ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ራሳቸውን በቅድስና ለመጠበቅ ብርቱ የቅጣት እርምጃ የማይወስዱት ለምንድን ነው? ለ) የቅድስና ጉድለት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አቋም አደገኛ የሚሆነው እንዴት ነው? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ የማቴ 18፡15-17ን መርሕ በመከተል፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ንጹሕ እንዲሆን ብትጥር ምን ለውጥ ይመጣል ብለህ ታስባለህ?

  1. ሐዋርያቱ ስለ ክርስቶስ በመናገራቸው እንደገና ስደት ደረሰባቸው (የሐዋ. 5፡12-42)።

እግዚአብሔር፥ ሐዋርያቱን ብዙ ተአምራት እንዲያደርጉ ስላስቻላቸው፥ የሃይማኖት መሪዎች ጠላት ሆነው ተነሡባቸው፥ ሐዋርያትም በማስተማሩና በክርስቶስ ስም ተአምራት በማድረጉ ተግባር ሲቀጥሉ፥ የሃይማኖት መሪዎቹ ደሞ ሊያስሯቸው ወሰኑ፡፡ ከዚያም ክርስቶስን እንደ ገደሉ ሁሉ ሐዋርያቱንም ለመግደል አሰቡ። እግዚአብሔር ግን የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ምን ያህል ደካሞች እንደሆኑ አሳያቸው። ይህንንም ያደረገው መልአኩን ልኮ ደቀ መዛሙርቱን በማስፈታት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በአይሁድ ታሪክ በሃይማኖተኛነቱ ዝነኛ የሆነውንና ገማልያል የተባለውን ሰው ምክር በመጠቀም፥ ሐርያቱን ከሞት አዳነ፡፡ (ገማልያል ሳውል ድነትን (ደኅንነትን) ከማግኘቱ በፊት መምህሩ ነበር፡፡ ገማልያል የአይሁድ መሪዎች እነጴጥሮስ ከእግዚአብሔር ወይም ለጊዜው ብቅ ያሉ ቡድኖች መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ ጊዜ እንዲወስዱ መከራቸው።

ምንም እንኳ ገማልያል የሃይማኖት መሪዎች ሐዋርያቱን እንዳይገድሏቸው ቢያሳምናቸውም። ይህ ሐዋርያቱ ለክርስቶስ ብለው መከራ ከመቀበል አላስጣላቸውም። ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ በኋላ ስለ ክርስቶስ እንዳይናገሩ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ ተገርፈው ተለቀቁ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ለዚህ ስደት የሰጡት መልስ ምን ነበር? አንደኛው፣ ደስ ተሰኝ፡፡ ሥጋዊ ጉዳት ቢደርስባቸውም እንደ ክርስቶስ መከራ ለመቀበል በመቻላቸው መንፈሳዊ ደስታ ተሰምቷቸዋል። ሁለተኛው፥ እምነታቸውን ሳይደብቁ በግልጽ ይሰበሰቡና ያስተምሩ፥ ደግሞም ስለክርስቶስ ይመሰክሩ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ከዚህ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ማለትም ስለደረሰባት ስደትና ለስደቱም ስለሰጠችው መልስ ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d