የመጀመሪያው የክርስቲያኖች ስደት እና የፊሊጶስ ምስክርነት (የሐዋ. 8፡1-40)

  1. የመጀመሪያው የክርስቲያኖች ስደት (የሐዋ. 8፡1-3)

ክርስቶስ ስደት በደቀ መዛሙርቱ ላይ እንደሚመጣ በተደጋጋሚ አሳስቦአቸው ነበር። ለብዙ ዓመት፥ ክርስቲያኖች በአይሁዶች ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው በሰላም ይኖሩ ነበር። ምንም እንኳ አልፎ አልፎ ሐዋርያት ቢታሰሩና ቢሰደቡም፥ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ፥ ክርስቲያኖች በሰላም ይኖሩ ነበር። ከእስጢፋኖስ መገደል በኋላ ግን የአይሁድ መሪዎች ስደትን አስነሡ። በሳውል አስተባባሪነት ክርስቲያኖች እየተያዙ እስር ቤት ይጣሉ ጀመር። ምንም እንኳ ሉቃስ ስለዚህ ጉዳይ ባይገልጽም፥ ጳውሎስ ለብዙ ክርስቲያኖች ሞት ምክንያት መሆኑን አልሸሸገም። ይህም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሲጸጽተው ኖሯል (የሐዋ. 22፡4)። ስደት ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው። የሚገርመው ታዲያ፥ ስደት እግዚአብሔርም ዓላማውን ለመፈጸም የሚጠቀምበት ታላቅ መሣሪያ መሆኑ ነው። አንደኛው፥ ስደት እምነትን ያጠራል፥ እውነተኛነትን ያመጣል። እምነቱ ሞት እንደሚያመጣበት የሚያውቅ ሰው፥ ኢየሱስን ያለ እውነተኛ ምክንያት አይከተልም። ሁለተኛው፥ ስደት ክርስቲያኖች የወንጌሉን ብርሃን ይዘው በተለያዩ አገሮች እንዲሰራጩ ያደርጋል። በአንድ አውላላ ሜዳ መሀል ላይ ትልቅ እሳት ተቀምጧል፤ አንድ ሰው መጥቶ እሳቱን ቢበትነው፥ እሳቱ በሜዳው ሁሉ ላይ ይሰራጫል። አሁን እሳቱ አንድ መሆኑ ቀርቶ ብዙ ይሆናል። ልክ እንደ ብዙዎቻችን ሐዋርያቱም በኢየሩሳሌም ተደላድለው ተቀምጠው ነበር። ክርስቲያኖች ወንጌልን ከኢየሩሳሌም ውጭ ለማድረስ አልቻሉም። ሐዋርያቱ ወንጌልን ወደ ይሁዳ፥ ሰማርያና አሕዛብ አድርሱ ያላቸውን ጌታ አልታዘዙም፡፡ ስለሆነም፥ እግዚአብሔር በስደት አማካይነት ደቀ መዛሙርቱን በመበተን በየሄዱበት ሁሉ የወንጌል እሳት እንዲቀጣጠል አድርጓል።

የውይይት ጥያቄ፡- ስደት እነዚህን ሁለት ነገሮች ሲያከናውን የተመለከትኸው እንዴት ነው?

  1. ፊልጶስ በሰማርያ መሰከረ (የሐዋ. 8፡4-25)

ምንም እንኳ 12ቱ ሐዋርያት በእናት ቤተ ክርስቲያናቸው በኢየሩሳሌም ቢቀመጡም፥ ሌሎች ብዙ ክርስቲያኖች ግን በየስፍራው ተበትነው ነበር። ሉቃስ የሌሎች ክርስቲያኖችን ተግባር እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ሲል፥ ፊልጶስ ወንጌልን በሰማርያ መስበኩን ገልጾአል። ፊልጶስ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ ነበር። እንደ ሐዋርያትና እስጢፋኖስ ሁሉ፥ የፊልጶስም መልእክት በተአምራት የታጀበ ነበር። ርኩሳን መናፍስት ከሰዎች ይወጡ ነበር። በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በፊልጶስ አማካይነት የክርስቶስ አገልግሎት ከኢየሩሳሌም ውጭ ተስፋፋ።

ሉቃስ ስለ ፊልጶስ አገልግሎትና ስሰማርያ ወንጌል እንዴት እንደ ተስፋፋ ሁለት ለየት ያሉ ነገሮችን ይነግረናል። አንደኛው፥ ስለ «አስማተኛው ሲሞን» የገለጸውን አሳብ ነው። ሉቃስ ሲሞንን የጠቀሰው ለሐሰተኞች ክርስቲያኖች ምሳሌ አድርጎ ሳይሆን አይቀርም። ሲሞን ያመነው ለግል ጥቅም ሲል ነው፤ ከጊዜ በኋላ የቤተ ክርስቲያን ጠላት ሆኗል። ሲሞን በሰማርያ አካባቢ በአስማተኛነቱ የታወቀ ሰው ሲሆን፥ በፊልጶስ በኩል የሚሠራውን የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲመለከት ተደነቀ። እንደ ሌሎች ሳምራውያን በክርስቶስ አምኖ ተጠመቀ። ነገር ግን እምነቱ እውነተኛ ነበር ወይስ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ? እምነቱ እውነተኛ አይመስልም ነበር። ጴጥሮስ የሰማርያ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ እጁን ጭኖ በጸለየላቸው ጊዜ፥ ሲሞን አሁንም ስግብግብነት ልቡን ሞልቶት ነበር። ሲሞን መንፈስ ቅዱስን ለሌሎች ለማደል እርሱም ሥልጣን እንዲኖረው በማሰብ፥ ለጴጥሮስ ገንዘብ ሊሰጠው ሞከረ። በአስማቱ ገንዘብ ይሰበስብ እንደነበር ሁሉ፥ ይህንንም ጥሩ የንግድ አጋጣሚ አድርጎ ተመለከተ። ጴጥሮስ የሲሞንን ክፉ ምኞች ተመልክቶ፥ ከእግዚአብሔር ፍርድ አስጠነቀቀው። ሲሞን እግዚአብሔር እንዳይፈርድበት ፈርቶ ጴጥሮስ እንዲጸልይለት ከመጠየቁ ውጭ ያደረገው ነገር ስለሌለ፥ ከልቡ ንስሐ የገባ አይመስልም። ሲሞን በኋላ የሐሰት ትምህርት መሪ ሆኖ በክርስትና ላይ እንደተነሣና ብዙ ሳምራውያንን ከወንጌሉ መስመር እንደ መለሰ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንደ ሲሞን ለግል ጥቅም ሲሉ ያመኑ ሰዎች እንዴት እንዳጋጠሙህ ግለጽ። ለ) እንደዚህ ዓይነት ሰዎች እንዴት ከእምነት ወደ ኋላ እንደሚመለሱና አንዳንድ ጊዜም የክርስቶስ ጠላቶች እንደሚሆኑ አብራራ። ሐ) ይህ ሁኔታ ወንጌልን ስንሰብክ የሰዎች እምነት በሚታዩ ነገሮች ማለትም በጤንነት፥ በተአምራት፥ በሀብትና በመሳሰሉት ላይ እንዳይመሠረት ጥንቃቄ እንድናደርግ ምን ያስተምረናል?

ሁለተኛው፥ ሉቃስ መንፈስ ቅዱስ በሰማርያ ክርስቲያኖች ላይ በተለየ ሁኔታ መውረዱን ገልጾአል። ሉቃስ ይህን ታሪክ የጠቀሰበት ምክንያት፥ መንፈስ ቅዱስ በሁለት ደረጃዎች መምጣቱ ያልተለመደ በመሆኑ፥ ክርስቲያኖች ልክ በዚሁ ዓይነት መንገድ ይመጣል ብለው እንዳይጠባበቁ ለማሳሰብ ሊሆን ይችላል። ይህ ባይሆን ኖሮ ሉቃስ ስለ ኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ሕይወት ሲናገር ከጠቀሳቸው አሳቦች ጋር ሊያዳብለው ይችል ነበር (የሐዋ. 2፡42-47፣ 4፡32-35)።

ሳምራውያን ድነትን (ደኅንነትን) መቀበላቸውንና በእግዚአብሔርም ቤተሰብ ውስጥ እኩል መብት መጎናጸፋቸውን የአይሁድ ክርስቲያኖች ተረድተው የነበረባቸውን የእምነት ማጣት ዐቢይ መሰናክል ማሸነፍ ነበረባቸው። አይሁዶች ሳምራውያንን ይጠሏቸው ነበር። ቀደም ሲል እንደ ተመለከትነው፥ ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለማለፍ ከሁሉም የሚቀርበው አቋራጭ መንገድ በሰማርያ በኩል አድርጎ ማለፍ ቢሆንም፥ በዚህ መንገድ ግን አይጠቀሙም ነበር። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ፥ ክርስቶስ የሚጠብቁት መሢሕ እንደሆነ እንዲያሳውቃቸው ፊልጶስን ላከ። የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰማርያ ክርስቲያኖች የሚነገረውን ዜና ስትሰማ ለማመን ተቸገረች። ስለሆነም፥ ስለ ሁኔታው እንዲያጣሩ ሁለት ታላላቅ ሐዋርያትን (ዮሐንስንና ጴጥሮስን) ላኩ። ጴጥሮስና ዮሐንስ የሳምራውያኑ ክርስቲያኖች እምነት ትክክል መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ፥ እጃቸውን በላያቸው ጭነው በመጸለይ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ አደረጉ። በዚህ ክፍል መንፈስ ቅዱስ በሳምራውያኑ ላይ ሲወርድ የተገለጠበት ምልክት አልተጠቀሰም። መንፈስ ቅዱስ በተቀበሉ ጊዜ ግልጽ ምልክት እንደ ተከሰተ የሚያጠራጥር ባይሆንም፥ በልሳን መናገራቸው አልተጠቀሰም። ሳምራውያኑ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉበት ሁኔታ በመነሣት ከዚህ የሚከተሉትን ነጥቦች ልንገዘብ እንችላለን።

ሀ. ሁሉም ሳምራውያን መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት በአንድ ጊዜ ነበር። አንዳንዶች ሲቀበሉ፥ ሌሎች ግን ያልተቀበሉበት ሁኔታ አልተገለጸም።

ለ. ይህ የመንፈስ ቅዱስ መገኘት እንጂ፥ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት አይደለም።

ሐ. የሰማርያ ክርስቲያኖች ካመኑ በኋላ፥ መንፈስ ቅዱስን ሳይቀበሉ እንደ ቆዩ የሚያመለክት አሳብ በሐዋርያት ሥራ ታሪክ ውስጥ አናገኝም። በአይሁድ ክርስቲያኖች ላይ ከተፈጸመው ጋር ተመሳሳይ ነው። ከሐዋርያት ሥራ 2 በኋላ የአይሁድ ክርስቲያኖች አምነው ሲድኑ፥ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ሲጠባበቁ ግን አንመለከትም።

መ. እግዚአብሔር ቀደም ሲል ለአይሁድ ክርስቲያኖች አሁን በክርስቶስ አማካይነት የእርሱ ሕዝብ እንዲሆኑ በይፋ ለማሳወቅ ጴጥሮስን እንደ ላከ ሁሉ፥ የሰማርያ ክርስቲያኖችም እንደ አይሁዳውያኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን በይፋ ለማወጅ ጴጥሮስን ተጠቅሞበታል። ይህም ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማይ መክፈቻ ቁልፍ ከመያዙ ልዩ ኃላፊነት ጋር የተያያዘ ነበር (ማቴ. 16፡19)። እያንዳንዱ አዲስ ቡድን ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብ ተቀላቅሎ እንዲያገለግል እግዚአብሔር የመረጠው እርሱን ነበር።

ሠ. እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በሳምራውያን ክርስቲያኖች ላይ ሳያወርድ ከቆየባቸው ምክንያቶች አንዱ፥ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ የጎሣ ልዩነት እንደሌለ ለአይሁዶች ለማስተማር ነው። ከእንግዲህ በኋላ አይሁድ፥ ሳምራዊ፥ አሕዛብ ብሎ ነገር አይኖርም። ይልቁንም ሁሉም አንድ ቤተሰብ ይሆናሉ። በእግዚአብሔር ቤተሰብ መካከል መበላለጥ እንደሌለ ለማሳየት፥ መንፈስ ቅዱስ በሳምራውያኑ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲወርድ በልዩ ሁኔታና ኃይል ወረደ።

ረ. መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል የተደረገ ጸሎትም ሆነ አዲስ አማኞች በልሳን እንዴት እንደሚናገሩ የተሰጠ ትምህርት አልነበረም፡፡ (መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ እንደ ወረደ ምልክቱ በልሳን መናገር ነው የምንል ከሆነ)። ጴጥሮስ እጁን ጭኖ እስኪጸልይላችው ድረስ መንፈስ ቅዱስ በሰማርያ ሰዎች ላይ ሳይወርድ ቆይቶ፥ ከዚያ በኋላ ግን በሁሉም ላይ ወረደ።

ይህ ክፍል፥ መንፈስ ቅዱስ በተለመደው ሁኔታ ማለትም ሰዎች ድነትን (ደኅንነትን) ካገኙ በኋላ ወደ እነርሱ ይመጣል የሚለውን አሳብ የሚያንጸባርቅ አይመስልም። ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ የሌለው ሰው ክርስቲያን ሊሆን እንደማይችል ገልጾአል (ሮሜ 8፡9)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ይህን ክፍል የሚረዳበትን መንገድ ሌሎች ካሪዝማቲክ ክርስቲያኖች ከሚረዱበት መንገድ ጋር አነጻጽር፡፡ ልዩነቱና ተመሳሳይነቱ ምንድን ነው? ለ) አንተ የትኛውን አመለካከት ትደግፋለህ? ለምን? ስለ መንፈስ ቅዱስ መገኘትና ሙላት ያለህን አመለካከት ለመግለጽ፥ ከመልእክቶች ውስጥ በጥቅሶች ተጠቀም።

በማቴዎስ 28፡19-20 ላይ ክርስቶስ በአብ፥ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንድናጠምቅ አዝዞን ሳለ፥ ሉቃስ ስለ ጥምቀት ሲናገር «በኢየሱስ ስም» የሚለውን ብቻ የጠቀሰው ለምንድን ነው? የ «ኢየሱስ ብቻ» ተከታዮች፥ ይህ ሥላሴ የሚባል ትምህርት ትክክል እንዳልሆነና ክርስቶስ እግዚአብሔር አብ እንደሆነ የሚናገር ነው ይላሉ። የዚህን ምክንያት ሙሉ በሙሉ ባናውቅም፥ የአይሁዶችን አስተሳሰብ መመልከቱ ጠቃሚ ነው። አይሁዶችና የሰማርያ ሰዎች እግዚአብሔር አብን ያውቁታል። መንፈስ ቅዱስ የሚለውም እሳቤ ለእነርሱ እንግዳ አይደለም። ነገር ግን በዓይናቸው ያዩትን፥ ሲናገር የሰሙትን፥ የዳሰሱትን፥ አብረው ምግብ የበሉትንና በመስቀል ላይ የሰቀሉትን ሰው አምላክ ነው ብለው ለመቀበል ለእነርሱ ከባድ ነገር ነበር። ዛሬ ሙስሊሞች የክርስቶስን አምላክነት ለመቀበል እንደሚቸገሩ ሁሉ፥ አይሁዶችና የሰማርያ ሰዎች ተመሳሳይ ችግር ነበረባቸው። ሉቃስ የክርስቲያኖች ጥምቀት ዮሐንስ ያጠምቅ ከነበረው ጥምቀት የተለየ መሆኑንና፥ ሰዎች በግልጽ በክርስቶስ ፍጹም አምላክነት ማመናቸውን ለማሳየት፥ የክርስቶስን ስም መጥቀሳቸው አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቶ ለመግለጽ ፈልጓል። አይሁዶችና የሰማርያ ሰዎች ከሚያውቁትና ከሚያምኑት በተቃራኒ፥ እነዚህ የተጠመቁት ክርስቲያኖች ክርስቶስ መሢሕና ወደ እግዚአብሔር አብ የሚወስደው ብቸኛ መንገድ እንደሆነ ያምኑ ነበር። ዛሬም በአብ፥ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም በመጠመቅ በሥላሴ ላይ ያለንን ጥብቅ እምነት እንገልጻለን።

  1. ፊልጶስ ወንጌልን በታዛዥነት ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አደረሰ (የሐዋ. 8፡26-40)።

አብዛኛውን ጊዜ ብዙ ሕዝብ ካልተሰበሰበ ወንጌልን መስበክ ጊዜን እንደማባከን አድርገን እንቆጥራለን። ደግሞም ለብዙ ሕዝብ መስበኩ የተሻለ ነው ብለን እናስባለን። ለእግዚአብሔር ግን ለአንድ ሰው ነፍስ መስበክና ለብዙ ሕዝብ መስበክ እኩል ነው። ለአንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ነፍስ ሲል እግዚአብሔር መልእክተኛውን በመላክ ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ እንዲጓዝ አድርጓል።

ፊልጶስ ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን በምትገኘው ሰማርያ የወንጌላዊነት አገልግሎቱን በትጋት ይወጣ ነበር። በዚያም ፍሬያማ አገልግሎት ነበረው። ነገር ግን እግዚአብሔር ለእርሱ የተለየ ዕቅድ ነበረው። ወዲያው አንድ መልአክ መጥቶ በኢየሩሳሌምና በጋዛ መካከል ያለውን 80 ኪሎ ሜትር የሚያህል መንገድ እንዲጓዝ አዘዘው። ፊልጶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሰ በኋላ ወደ ጋዛ መውረድ ጀመረ። ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ለማግኘት ምን ያህል ኪሎ ሜትር እንደ ተጓዘ አናውቅም።

ይህ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ማን ነው? ካመነ በኋላስ ወዴት ሄደ? አጋጣሚ ሆኖ የሐዋርያት ሥራ ያሉንን ጥያቄዎች በሙሉ አይመልስልንም፤ የቤተ ክርስቲያንም ታሪክ ቢሆን ምንም የገለጸው ነገር የለም። በጥንት ዘመን የምትታወቀው ኢትዮጵያ ዛሬ ከምናውቃት ኢትዮጵያ ጋር ፍጹም ተመሳሳይ አልነበረችም። ድንበሮቿ የተካለሉት በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው። ጥንት በአማርኛ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል የኩሽ ሕዝብ ማለት ነበር። ኩሽ የሚለው ቃል ከግብጽ በስተ ደቡብ የሚገኙትን ደቡባዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አካባቢዎችን ያመለክታል። በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ «ኢትዮጵያ» ተብሎ የተተረጎመው ቃል በአሁኑ ጊዜ ከግብጽ በስተ ደቡብ፥ ከሱዳን በስተ ሰሜን አንዳንድ ጊዜም ከኢትዮጵያ በስተ ሰሜን ያለውን ግዛት ያመለክታል። የአፍሪካን ክፍል በተመለከተ የሚናገሩት ጥንታዊ ጽሑፎች እጅግ ጥቂት በመሆናቸው፥ የአገሮቹን ትክክለኛ አቀማመጥ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።

ከሉቃስ ዘገባ ለመረዳት እንደሚቻለው። ጃንደረባው በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ትልቅ ሹመት የነበረው የንግሥት አገልጋይ ሲሆን፥ ስለ እግዚአብሔር ከሰማ በኋላ እርሱን ማምለክ ጀመረ። ይህ ሰው የአይሁድን እምነት ተቀብሎ ስለ መገረዙ፥ የብሉይ ኪዳንን ሕግ ስለ መቀበሉ ወይም እግዚአብሔርን ብቻ የሚፈራ ሰው ስለ መሆኑ፥ ምንም ግልጽ አይደለም፤ «እግዚአብሔርን የሚፈራ» የሚለው ሐረግ ጣዖትን ሳይሆን፥ በብሉይ ኪዳን የተገለጠውን እግዚአብሔርን ለሚያመልኩ አሕዛብ የተሰጠ ስያሜ ነበር።

ጃንደረባው ወደ አገሩ በመመለስ ላይ ነበር። በሰረገላው ተቀምጦ እየሄደ ሳለ፥ መንፈስ ቅዱስ ፊልጶስ ወደ ጃንደረባው እንዲሄድ አዘዘው። በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዕቅድ፥ ጃንደረባው ከኢሳይያስ 53 ላይ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሁሉ መከራ ስለሚቀበለው መሢሕ እያነበበ ነበር። እንደ አይሁዶች ሁሉ እርሱም የሚነግሥ መሢሕ እንጂ የሚሠቃይ መሢሕ ይኖራል ብሎ አላሰበም። ስለዚህ እግዚአብሔር በፊልጶስ አማካይነት ክርስቶስ እንዴት ትንቢቱን እንደ ፈጸመና ለዓለም ኃጢአት የታረደ በግ እንደ ሆነ ለጸለት።

ጃንደረባው የቅዱሳት መጻሕፍቱን ገለጻ ከሰማ በኋላ አምኖ ተጠመቀ ታሪክ ስለ ጃንደረባው ሕይወት ምንም የሚነግረን ነገር የለም። ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ በክርስቶስ ማመኑን ቀጥሎበት ይሆን? ስለ ክርስቶስ በመመስከር ቤተ ክርስቲያን መሥርቶ ይሆን? ከጊዜ በኋላ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው፥ በሰሜን ሱዳንና በሰሜን ኢትዮጵያ ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን ተመሥርቶ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከዚህ ታሪክ እግዚአብሔር ድነትን (ደኅንነትን) ለሰዎች ለማድረስ ስለሚያደርገው ጥረት ምን እንማራለን? ለ) ይህ እኛ መመስከር እንዳለብን የሚያሳስበን የሚሆንበትን ምክንያት ግለጽ።

ሰዎች በተለያየ ምክንያት በክርስቶስ ያምናሉ። ነገር ግን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ አንድ ሰው የወንጌሉን መልእክት እንዲረዳና እንዲያምን ዓይኖቹን በመክፈት ረገድ አስተዋጽኦ የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ለማምጣት የሚጠቀምበት ዋነኛው መሣሪያ ሰው ነው። እግዚአብሔር ለጃንደረባው መላእክት እንዲመሰክሩ ማድረግ ቢችልም፥ ይህንን ግን አላደረገም። ወንጌሉን ሁልጊዜ እንዲሠራጭ የሚፈልገው በልጆቹ ምስክርነት አማካይነት ነው። ልጆቹ ካልመሰከሩ ቤተ ክርስቲያን ልታድግና በዓለም ሁሉ ልትስፋፋ አትችልም።

መንፈስ ቅዱስ በሚያስደንቅ መንገድ ፊልጶስን አንሥቶ በብሉይ ኪዳን አሽዶድ ተብላ ወደ ምትጠራው ከተማ ወደ አዛጦን ወሰደው። ከዚያም ፊልጶስ ከአዛጦን በስተ ሰሜን 90 ኪሎ ሜትር ጀምሮ በሜዲትራንያን ባሕር ዳርቻ በሚገኙ ከተሞች ሁሉ እስከ ቂሣርያ ድረስ ወንጌልን መስበክ ጀመረ። ፊልጶስ ከ20 ዓመት በኋላ ከሴት ልጆቹ ጋር በቂሣርያ ከተማ የቆየ ይመስላል (የሐዋ. 21፡8)።

ምንም እንኳ ወንጌልን የት እንደምናሰራጭና ለማን እንደምንሰብክ ማቀዱ መልካም ቢሆንም፥ በሂደቱ ውስጥ ለመንፈስ ቅዱስ የተከፈተ ልብ እንዲኖረን ይህ ታሪክ ያስጠነቅቀናል። የት መሄድና ማንን ማግኘት እንዳለብን የሚወስነው እርሱ ራሱ ነው። ቁም ነገሩ የት እንደምናገለግል ማወቁ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ባስቀመጠን ስፍራ ታማኝ ሆኖ መገኘቱ ነው። ፊልጶስ በሰማርያ፥ ለኢትዮጵያዊ ጃንደረባ በጋዛ እንዲሁም በሌሎች ከተሞች መንፈስ ቅዱስ በመራው ስፍራ ስለ ክርስቶስ በታማኝነት መስክሯል። እኛም በትምህርት ቤት በአካባቢያችን፥ በሥራ ቦታ፥ በተቀየርንበት አካባቢ፥ በአጠቃላይ ባለንበት ስፍራ ሁሉ በታማኝነት ስለ ክርስቶስ መመስከር አለብን። መንፈስ ቅዱስ ከመጋረጃው በስተ ጀርባ ሆኖ ምስክርነታችንን የሚሰሙ ሰዎችን ለማሳመን በሥራ ላይ መሆኑን መገንዘብ አለብን። ሰዎች በክርስቶስ ያምኑ ዘንድ በምስክርነታችን ታማኝ ሆነን መገኘት አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በማኅበረሰቡ ውስጥ እግዚአብሔር ባስቀመጠህ ስፍራ ያለህን ደረጃ ዝርዝር (ለምሳሌ፥ በቤተሰብ፥ በጎረቤት፥ በሥራ ቦታ)። በእነዚህ ግንኙነቶች ውስጥ ምን የምስክርነት ዕድል አለህ? ለ) መንፈስ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ እንድትመሰክር በልብህ ውስጥ ያስቀመጣቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር። በዚህ ሳምንት ጸልይላቸው። መንፈስ ቅዱስ የጊዜ ሠሌዳህንና በግለሰቡ ሕይወት ውስጥ የሚፈጸሙትን ክስተቶች እንዲያቀናጅ፥ አንተም መመስከር እንድትችል ሰውየውም ማመን እንዲችል ጸልይ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: