የጳውሎስ መለወጥ (የሐዋ. 9፡1-31)

በአንድ ወቅት አንድ ጫማ የሚሸጥ ሰው ነበረ። አንድ ቀን አንድ ሰው ስለ ክርስቶስ መሰከረለት። መንፈስ ቅዱስ ልቡን ለውጦ በክርስቶስ እንዲያምን ረዳው። ወዲያውኑ ሥራውን ትቶ ተነሣና መጀመሪያ ለአነስተኛ ቡድኖች፥ ከዚያም በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች ስለ ክርስቶስ መመስከር ጀመረ። በምዕራቡ ዓለም ይህ ሰው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለውጧል። ለክርስቲያን ሠራተኞች ያቋቋመው ትምህርት ቤት ዛሬም ዓለምን በመለወጥ ላይ ይገኛል። በእኛ ዘመን ብዙ አገልግሎት እንደ ሰጠው እንደ ቢሊ ግርሃም ሁሉ፥ ድዋይት ኤል. ሙዲም በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ አሜሪካንና አውሮፓን በከፍተኛ ደረጃ ለውጧል። በአንድ የማይታወቅ ሰው ምስክርነት ዓለም ተለወጠች። እግዚአብሔር ለሰዎች ምን ዕቅድ እንዳለው አናውቅም። እግዚአብሔር የጎዳና ተዳዳሪዎችን፥ ሴተኛ አዳሪዎችን፥ ድሆችን፥ ወይም በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ አንዱን ትንሽ ልጅ ወስዶ ዓለምን ለመለወጥ ሊጠቀምባቸው ይችላል። እኛ ብዙ ጊዜ የምናተኩረው በጀማ ስብከት ላይ ነው። በእግዚአብሔር ዓይን ግን ለአንድ ሰውም (እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ) ሆነ ለብዙ ሰው መስበክ ለውጥ የለውም። እርሱ አንድን ሰው ተጠቅሞ ዓለምን መለወጥ ይችላል።

በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ከሌሎች ሰዎች ሁሉ ይልቅ ክርስትናን ለዓለም ሕዝብ ለማስተዋወቅ ትልቅ ተግባር ያከናወነ አንድ ሰው አለ። ስሙ መጀመሪያ ሳውል ሲሆን፥ በኋላ ጳውሎስ ተብሏል። አነስተኛ የአይሁድ ስብስብ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን፥ በጳውሎስ አገልግሎት በመላው ዓለም ታላቅ እምነት ለመሆን በቅታለች። ዛሬም የጳውሎስ አገልግሎትና የጻፋቸው መጻሕፍት ዓለምን በመለወጥ ላይ ናቸው። ሉቃስ ስለ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን በጻፈው ታሪክ ውስጥ፥ ለጳውሎስ አገልግሎት ትኩረት ሰጥቷል። ሉቃስ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ከይሁዲነት ወጥታ በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ እንድትሰፋ ለማድረግ ጳውሎስን እንዴት እንደ ተጠቀመበት አብራርቷል። በጳውሎስ አማካይነት ወንጌል ወደ ቱርክና ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ተስፋፍቷል። ከጊዜ በኋላ በፍልስጥኤምና በአፍሪካ ምድር እስልምና እየሰፋ ሲሄድ፥ እግዚአብሔር ወንጌልን በዓለም ሁሉ ለማዳረስ በአውሮፓ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ተጠቅሟል።

ሉቃስ ስለ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሲተርክ፥ ትኩረቱን ከጴጥሮስ ወደ ጳውሎስ ያደርጋል። ጴጥሮስ ወደ አይሁድ የተላከ ሐዋርያና እግዚአብሔርም ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሠረት የተጠቀመበት ሰው ነው። ጳውሎስ ደግሞ ወንጌልን ለአሕዛብ ለመስበክ የተላከ ሐዋርያ ነው። ትላንት ሉቃስ በቀድሞ ስሙ ሳውል (የአይሁድ ስም)፥ በኋላም ጳውሎላ (የሮም ስም) የተባለውን ሰው እንዳስተዋውቀን ታስታውሳላችሁ። ቀድሞ የቤተ የክርስቲያኖች አሳዳጅ የነበረው ሳውል በኋላ ጳውሎስ፥ እንዴት የአሕዛብ ሐዋርያ ሊሆን እንደ ቻለ እንመለከታለን። ሉቃስ በጳውሎስ ምስክርነት ስለ ተደነቀ በመጽሐፉ ውስጥ በተለያዩ ሦስት ስፍራዎች ጠቅሶታል (የሐዋ. 9፡1-31፤ 22፡1-21፤ 26፡1-3)።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) እግዚአብሔር በሰዎች ሕይወት ውስጥ እንደሚሠራ ከዚህ ክፍል ምን እንማራለን? ለ) ስለ ቤተ ክርስቲያን መስፋፋት ምን እንማራለን? ሐ) ሉቃስ ስለ ቤተክርስቲያን እንድናውቅና እንድንከትል የሚፈልጋቸው እውነቶች ምንድን ናቸው?

የጳውሎስ መለወጥ (የሐዋ. 9፡1-3)

ከእስጢፋኖስ መገደል በኋላ፥ አይሁዶች በክርስቲያኖች ላይ የነበራቸው ጥላቻ እየበረታ በመምጣቱ የመጀመሪያው ስደት በቤተ ክርስቲያኖች ላይ ተነሣ። ይህ ስደት የመጣው ከሮም የፖለቲካ መሪዎች ሳይሆን፥ ከአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ዘንድ ነበር። ከታሪክ እንደምንረዳው ክርስቶስን ለመከተል በወሰኑ ሰዎች ላይ ስደትን የሚያስነሡት የፖለቲካ መሪዎች ሳይሆኑ፥ የሃይማኖት መሪዎች ናቸው።

ከክርስቶስ ሞት በኋላ – በኢየሩሳሌም የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ተለውጧል። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎችም ሰዎችን ለማሳደድና ለመግደል ሥልጣን አገኙ። እነርሱም፥ ሳውል የተባለው ዝነኛ ወጣት ክርስቲያኖችን አስሮ ለምርመራ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያመጣ ሥልጣን ሰጡት። ጳውሎስ በኋላ እንደ ገለጸው፥ እርሱ አስሮ ካመጣቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ተገድለዋል (የሐዋ. 22፡4፤ 26፡10)። በዚህ ስደት ምክንያት ክርስቲያኖች በፍልስጥኤም ምድር ሁሉ ተበተኑ። ሳውልም እየተከታተለ ያሳድዳቸው ጀመር።

ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠው የመጀመሪያ ስም «መንገድ» የሚል ነበር። ይህ ስም ለመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የተሰጠበትን ምክንያት ባናውቅም፥ የጥንት ክርስቲያኖች ራሳቸው ያወጡት ስም ሳይሆን አይቀርም። ምናልባትም ይህ የክርስቶስ ተከታዮች እግዚአብሔር ያዘጋጀውን የጽድቅ መንገድ እንደሚከተሉ የሚያመላክት ይሆናል። አማኞቹ እግዚአብሔር በጥንት ዘመን ለነቢያቱ የሰጣቸው ትንቢት ፍጻሜ የሆነውን መሢሕ እየተከተሉ ነበር። ምናልባትም እርሱ «እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ» (ዮሐ 14፡8) በማለት የተናገረውን ሊያንጸባርቅ ይችላል።

ደማስቆ በሶርያ አውራጃ የምትገኝ የሮም መዲና ስትሆን፥ ብዙ አይሁዶች ይኖሩባት ነበር። ምናልባትም የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች፥ ሃይማኖታዊ ጉዳዮቻቸውን ለመከታተል ከኢየሩሳሌም 180 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ደማስቆ ድረስ ተጉዘው፥ አይሁዶችን ለመቆጣጠር ከሮም ባለሥልጣናት ጋር ተስማምተው ሊሆን ይችላል።

ጳውሎስ አይሁድ ክርስቲያኖችን በኢየሩሳሌም ለፍርድ ለማቅረብ ወደ ደማስቆ በመጓዝ ላይ ሳለ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለት። ምንም እንኳ ሰዓቱ እኩለ ቀንና ጠራራ ፀሐይ ቢሆንም፥ ከዚያ የላቀ የክርስቶስ የክብር ብርሃን በሳውሉ ላይ ወርዶ ለዓይነ ስውርነት አበቃው። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ክርስቶስን ባረገበት ክብሩ ተመለከተው (1ኛ ቆር. 9፡1፤ 15፡7-8)። ጳውሎስን እጅግ ያስደነቀው የተሰቀለው ክርስቶስ ሕያው ብቻ ሳይሆን፥ በታላቅ ኃይል የሚዝ መሆኑም ነበር። ክርስቶስ ጳውሎስ ያምን ዘንድ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ አልነገረውም። ሐናንያ የተባለ ደቀ መዝሙር ስለ ክርስቶስና ስለ አዳኝነቱ ነግሮ ጳውሎስን ከክርስቶስ ጋር እንዲያስተዋውቀው ተጠቀመበት። ጳውሎስ ዓይነ ስውር እንደ ሆነ ወደ ደማስቆ ሄደ። እዚያ በቆየባቸው ሦስት ቀናት ውስጥ ስለ ብሉይ ኪዳኑ አምላክ የነበረውን ግንዝቤ በደማስቆ መንገድ ላይ ካጋጠመው ሁኔታ ጋር እንደሚያስማማው ምንም ጥርጥር የለውም።

ሐናንያ በኢየሱስ የሚያምን ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት አይሁዳዊ ነበር። በደርግ ዘመን እግዚአብሔር ወደ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሄዳችሁ ወንጌልን ስበኩለት ቢለን ኖሮ በጥያቄ ግራ እንደምንጋባ ሁሉ፥ ሐናንያም ክርስቲያኖችን በማሳደድ መጥፎ ስም ወደ ነበረው ወደ ጳውሎስ እንዲሄድ ክርስቶስ ሲያዝዘው ግራ ተጋባ። እግዚአብሔር ለሐናንያ ጳውሎስ መንግሥቱን ለማስፋፋት የተመረጠ መሣሪያ እንደ ሆነ ገልጾለት ነበር። ለአሕዛብ፥ ለነገሥታትና ለአይሁዶች ወንጌልን እንደሚሰብክ አብራራለት። ለጳውሎስም ገና ድነትን (ደኅንነትን) በተቀበለ ጊዜ ስለ ወንጌል መከራን እንደሚቀበል ነገረው።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ጳውሎስ ክርስቶስን በመከተሉና ወንጌልን በመስበኩ ከፍተኛ ሥቃይ እንደሚደርስበት የገለጸው ለምን ይመስልሃል?

ጳውሎስ አምኖ የዳነው መቼ ነበር? ጳውሎስ በኢየሱስ ማመን የጀመረው በደማስቆ መንገድ ላይ ከኢየሱስ ጋር ከተገናኘና በጸሎትና በጾም በቆየባቸው ሦስት ቀናት ውስጥ ነው። እምነቱ ሙሉ የሆነው ግን ሐናንያ ከመሰከረለት በኋላ ነው። በዚያን ጊዜ ዓይኖቹ ተከፈቱ፥ መንፈስ ቅዱስን ተቀበለ፥ ተጠመቀም።

ሉቃስ በዚህ ጊዜ በጳውሎስ ሕይወት ስለተፈጸሙት ጉዳዮች ዝርዝር ነገር አልጻፈም። በገላትያ 1፡17-18 ላይ የተጠቀሱትን ሃሳቦች ከጳውሎስ ታሪክ ጋር ስናነጻጽር፥ ከዚህ የሚከተሉት ነገሮች የተከሰቱ ይመስላል። አንደኛው፥ ጳውሎስ በደማስቆ በሚገኙ ምኩራቦች ኢየሱስ መሢሕ እንደሆነ መስበክ ጀመረ። የኢየሱስ ጠላት የነበረው ሰው፥ አሁን ኢየሱስ ራሱ መሢሕ መሆኑን ይመሰክር ጀመር። የክርስቶስ ተከታዮች የነበሩትን ያሳድድ የነበረው ሰው፥ አሁን ያን ሁሉ ተወ። ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ መሢሕነት በሚናገርበት ጊዜ ከብሉይ ኪዳን እየጠቀሰ የሚያቀርበው መረጃ እጅግ ብርቱ በመሆኑ፥ ማንም ሊቋቋመው አልቻለም። ሁለተኛው፥ ከዚያም ጳውሎስ ወደ ዐረቢያ በረሃ ተጓዘ። በዚያም ለሦስት ዓመት ያህል ተቀመጠ። ይህንንም ያደረገው አሁን ባገኘው አዲስ ብርሃን አማካይነት ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ የእግዚአብሔርን ዕቅድ ለማስተዋል ነበር። ቀደም ሲል ፈሪሳዊ ላለ የተማረውን ነገር አሁን ኢየሱስ መሢሕ ነው ከሚለው አንጻር መመርመር ነበረበት። ሉቃስ ይህን የጳውሎስን አገልግሎት በተመለከተ ምንም አልነገረንም። ሦስተኛው ለአገልግሎት ወደ ደማስቆ ተመለሰ። ሉቃስ ይህንን «ከብዙ ቀናት በኋላ» ሲል ይገልጸዋል። በዚህ ጊዜ የጳውሎስ ትምህርት እጅግ ፍሬያማ በመሆኑ አይሁዶች ሊይዙት ፈለጉ። ነገር ግን በደማስቆ በነበሩት ክርስቲያኖች እርዳታ ከደማስቆ አመለጠ።

ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ወደነበሩት ክርስቲያኖች ዘንድ ሲመጣ፥ በእርግጥ እውነተኛ አማኝ ስለመሆኑ አንዳንድ ሰዎች ጥርጣሬ ገባቸው። ነገር ግን የመጽናናት ልጅ የሆነው በርናባስ ምንም ጥርጣሬ ሳይገባው ከጳውሎስ ጋር ተገናኘ። በርናባስ ክርስቶስ ከጳውሎስ ጋር ተገናኝቷል ብሎ ስላመነ፥ ከጴጥሮስና የክርስቶስ ወንድም ከነበረው ከያዕቆብ ጋር አስተዋወቀው። እነርሱም የጳውሎስ መለወጥ እውነት እንደሆነ ተገነዘቡ (ገላ. 1፡19)። ነገር ግን በኢየሩሳሌም የነበሩት አይሁዶች ሊይዙት ይፈልጉ ስለነበር፥ ጳውሎስ ከሌሎች ሐዋርያት ጋር ከመገናኘቱ በፊት ወደ ትውልድ አገሩ ወደ ተርሴስ እንዲሄድ ተደረገ። በቀጣዮቹ ዓመታት ውስጥ በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ ስለተፈጸመው ምንም የምናውቀው ነገር የለም። ይህ «የጸጥታ ዓመታት» እየተባለ የሚታወቀው ጊዜ የአሕዛብ ሐዋርያ ለሆነው ጳውሎስ ወሳኝ የእድገት ዘመናት ነበሩ።

እግዚአብሔር አንድን ሰው በከፍተኛ ደረጃ ከመጠቀሙ በፊት ባሕርዩን መለወጥ አለበት። ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን ማወቅ ለብቻው ጳውሎስን የአሕዛብ ሐዋርያ ሊያደርገው አይችልም ነበር። ቀስ በቀስ ባሕርዩ የሚለወጥበት ሁኔታ የግድ ያስፈልገው ነበር። እግዚአብሔር ዓለምን የሚለውጥ አገልግሎት ለጳውሎስ የሚሰጠው ልቡ፥ እውቀቱና ባሕርዩ ለዚህ አገልግሎት ዝግጁ ሲሆን ብቻ ነው። ከባሕርይ ይልቅ ዕውቀት ትልቅ ስፍራ በሚሰጥበት ዘመን፥ እግዚአብሔር በሕይወታችን የሚያመጣቸውን የለውጥ እርምጃ ዎች ልብ አንላቸውም።

አንድ ጸሐፊ እንደ ተናገረው፥ እግዚአብሔር አንድን ሰው ከመስበሩ በፊት አይጠቀምበትም። «ምድረ በዳና የጸጥታ ዓመታት» እንደ ባከኑ ጊዜ የሚቆጠሩ ሳይሆኑ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመሪነት የሚያዘጋጅበት ትልቅ ስፍራዎች ናቸው። (አብርሃም፥ ሙሴ፥ ዳዊትና ክርስቶስ ለዚህ እውነት ምስክሮች ናቸው።) ወጣቶችና ምሑራን ይህን እውነታ ማወቅ አለብን። የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን ለመረከብ መጣደፍ የለብንም። ሥልጣን ተገቢው ባሕርይ ካልታከለበት አደገኛ ነው። እግዚአብሔር ለእርሱና ለቃሉ ያለንን እውቀት እንዲሁም ባሕርያችንን፥ ትሕትናችንንና ለሕዝቡም ያለንን ፍቅር እንዲለውጥ በትዕግሥት መጠበቅ አለብን። እግዚአብሔር ለመሪነት ሲያስነሣን፥ ትሑት አገልጋዮች ሆነን እንቆማለን፥ ይሁንና እንደ ክርስቶስ ሁሉ እኛም ብርቱ የእግዚአብሔር ባሪያዎች እንሆናለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ባሕርያቸው ከመለወጡ በፊት የተማሩ ሰዎች፣ የተማሩ ሰዎች በመሆናቸው ብቻ ብዙ ኃላፊነትን በመቀበላቸው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮችን ሲፈጥሩ የተመለክትኸው እንዴት ነው? ለ) ይህ እውነት ለሥነ መለኮት ትምህርት ሊኖረን በሚገባው ግንዛቤ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔር አንድን ሰው ለመሪነት ለማዘጋጀት፥ ምድረ በዳንና የጸጥታ ጊዜን እንዴት ሲጠቀም እንዳየህ ግለጽ።

ሉቃስ በዚህ ጊዜ ስለተከሰተው የስደት ዘገባ የቋጨው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየሆነ የነበረውን ነገር ጠቅለል አድርጎ በማቅረብ ነው። ሁኔታው ክርስቲያኖች ወደ ሰማርያና ይሁዳ እንዲሰደዱ ቢያደርግም፥ ጳውሎስ ከተለወጠ በኋላ ስደቱ ቀንሷል። ይህም አብያተ ክርስቲያናት በኢየሩሳሌም፥ በይሁዳና በሰማርያ (በሐዋ. 1፡8) ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲመሰክሩ የተናገራቸው የመጀመሪያዎቹ ሦስት ክፍሎች) በቁጥር እንዲያድጉ፥ ስለ ኢየሱስ ባላቸው እውቀት እንዲበስሉ፥ እግዚአብሔርንም በመፍራት በቅድስና እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። ስደት ለጥንቷ ቤተ ክርስቲያን እድገት የእግዚአብሔር መሣሪያ እንደነበረ ሁሉ፥ ዛሬም በሕይወታችንና በቤተ ክርስቲያን መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: