ጴጥሮስ በይሁዳና ቂሣርያ ያካሄደው አገልግሎት (የሐዋ. 9፡32-10፡48)

እስካሁን ወንጌል በሦስት ዐበይት የዓለም ክፍሎች ሊዳረስ ችሎአል። እነርሱም በኢየሩሳሌም የነበሩ አይሁዶች፥ በይሁዳ የነበሩ አይሁዶችና በሰማርያ የነበሩ ከፊል አይሁዶች ናቸው። አንድ የዓለም ክፍል ግን አሁንም ይቀራል፤ ይህም «እስከ ምድር ዳርቻ» ያለው የአሕዛቡ ዓለም ነው። ስለዚህ ሉቃስ በዚህ ክፍለ ዓለም ወንጌል እንዴት እንደ ተዳረሰ ይነግረናል። ምንም እንኳ አይሁዶች የሰማርያ ሰዎችን ቢጠሏቸውም፥ ቢያንስ ግማሽ አይሁዶች ነበሩ። የብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያምኑ ከመሆናቸውም በላይ፥ በአንዱ አምላክ ብቻ ያምኑ ነበር። ነገር ግን አይሁድ አሕዛብ ወደ እምነት ይመጣሉ የሚል ተስፋ የላቸውም። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ አሕዛብ በመጀመሪያ የአይሁድን እምነት ሲቀበሉ ነው። ከአይሁድ ሲሆኑ እግዚአብሔር ይቀበላቸዋል። ነገር ግን ወንጌል እስከ ምድር ዳርቻ ሁሉ እንዲዳረሰ ከተፈለገ፥ አሕዛብ ባሕላቸውን ትተው ወደ ይሁዲነት መለወጥ አያስፈልጋቸውም ነበር። ስለሆነም፥ መንፈስ ቅዱስ ይህ ክፍለ ዓለም ወንጌልን እንዲያዳምጥና በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ፥ በጴጥሮስ አማካይነት ይሠራ ጀመር። በሐዋርያት ሥራ 9፡31-11፡30 የምናገኘው ክፍል፥ ይህ አዲስ የወንጌል በር እንዴት እንደ ተከፈተ ያስረዳል። ይህ ለመጀመሪያው ምእተ ዓመት ክርስቲያኖች አስፈላጊ እውነት በመሆኑ፥ ሉቃስ ሂደቱን በዝርዝር ገልጾአል። መጀመሪያ እግዚአብሔር በጴጥሮስ ልብ ውስጥ በመሥራት እግዚአብሔር ለአሕዛብ ያለውን ፍቅር እንዲገነዘብ ማድረግ ነበረበት። አይሁዶችም አሕዛብን በእኩልነት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲቀበሉ ልባቸውን መክፈት ነበረበት። ይህ የአይሁድ ክርስቲያኖች በአሕዛብ ላይ የነበራቸው ጥላቻ እስኪወገድ ብዙ ዓመታትን ወስዷል።

ጴጥሮስ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሄዶ ወንጌልን ይመሰክር ዘንድ፥ መንፈስ ቅዱስ በጴጥሮስ ልብ ውስጥ የነበረውን የአድልዎ መንፈስ መስበር አለበት።

ሀ. የጴጥሮስ አገልግሎት በይሁዳ፡- እስካሁን ድረስ የጴጥሮስ አገልግሎት ያተኮረው በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ነበር። አንድ ጊዜ ወደ ሰማርያ ተጉዞ ከሰበከ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ እዚያው ሲያገለግል ቆይቷል። አሁን ግን እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም ውጭ መራው። ጴጥሮስ በምዕራብ ይሁዳ የሚገኙትን አንዳንድ ክርስቲያኖች ለመጎብኘት ስለፈለገ፥ በባሕር ዳርቻ ወደሚገኙት የሊዲያና የኢዮጴ ከተሞች ሄደ። በዚያም መንፈስ ቅዱስ ጣቢታን ከሞት እንዲያስነሣና ሌሎችንም በርካታ ተአምራት እንዲሠራ አደረገው።

ለ. ጴጥሮስ በአንድ ክርስቲያን ቆዳ ፋቂ ቤት ተቀመጠ፡- እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አይሁዶችም ቆዳ (ቁርበት) ፋቂዎችን ይንቋቸው ነበር። በብሉይ ኪዳን የሞተ እንስሳ የነካ ሰው እንደ ርኩስ ይቆጠር ነበር። ቆዳ ፋቂ ደግሞ የታረዱ ወይም የሞቱ እንስሳትን ቆዳ አልፍቶ ስለሚተዳደር በኅብረተሰቡ ዘንድ ሁልጊዜ እንደ ርኩስ ይቆጠር ነበር። ከእንዲህ ዓይነት ሰው ጋር የሚኖርና ወደ ቤቱም የሚገባ፥ እንደ ርኩስ ተደርጎ ይቆጠራል። ስለሆነም አይሁዶች ከቆዳ ፋቂዎች ይርቁ ነበር። ጴጥሮስ የይሁዲነት ባህላዊ አመለካከቱን ለመተው የመጀመሪያውን እርምጃ የወሰደው፥ መንፈስ ቅዱስ በሥርዓቱ መሠረት ንጹሕ ካልሆነ ሰው ጋር እንዲኖር በመራው ጊዜ ነበር። (ይህ በብዙ ኢትዮጵያውያንም ዘንድ በሚናቁ እንደ ሸክላ ሠሪ፥ ቀጥቃጭ፥ ቆዳ ፋቂ ባሉት ቤት እንደ መኖር ይቆጠር ነበር።)

ሐ. እግዚአብሔር፥ ጴጥሮስ ንጹሕ ያልሆነ እንስሳ ሥጋ በራእይ እንዲያይ አደረገ። በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት ወንጌል የዘር ልዩነት ጋሬጣዎችን ጠራርጎ በቀጥታ ወደ አሕዛብ የሚደርስበት ጊዜ ደረሰ። ይህ ሁሉ ሂደት የተፈጸመው ቆርኔሎዎስ በተባለ አንድ ሰው ቤት ነበር። ቆርኔሌዎስ በቂሣርያ የሚኖር የሮም ወታደር ነበር። ቂሣርያ በፍልስጥኤም ምድር በሮማውያን ቁጥጥር ሥር የምትገኝ ግዛት ነበረች። መንፈስ ቅዱስ ብዙ አማልእክትን ያመልክ በነበረው ቆርኔሌዎስ ልብ ውስጥ መሥራት ጀመር። ቆርኔሌዎስ ብዙ አማልእክት ማምለኩን ትቶ የብሉይ ኪዳኑን ብቸኛ እውነተኛ አምላክ ማምለክ ጀመረ። እግዚአብሔር በመልአኩ አማካይነት ቆርኔሌዎስ 50 ኪሎ ማትር ርቆ በኢዮጴ ወደሚገኘው ወደ ጴጥሮስ መልእክተኛ እንዲልክ ነገረው።

በዚያኑ ጊዜ፥ እግዚአብሔር፥ ጴጥሮስ ከአይሁድ የወረሳቸውን ሁለት ዐበይት ጥላቻዎች እንዲያስወግድ አድርጎት ነበር። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ጴጥርስ አሕዛብን እንዲቀበል ፈቅዶ ነበር። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር፥ ጴጥሮስን ሰዎች ስለሚመገቧቸውና መመገብ ስለሌለባቸው ነገሮች የነበረውን የአይሁድ ልምድ እንዲተው አግዞት ነበር። እግዚአብሔር የውሻ ሥጋና ትላትሎችን እንድትበላ ቢያዝህ፥ ምን ትሆናለህ? በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ጴጥሮስ የደነገጠው፥ እግዚአብሔር ውሻዎችን፥ ጦጣዎችን፥ ትላትሎችን፥ እባቦችንና ብዙ ዓይነት ርኩስ እንስሳትን እንዲመገብ ሦስት ጊዜ (እውነቱ በጣም አስፈላጊ ስለሆነና ለጴጥሮስም መቀበሉ በጣም ከባድ ስለሆነበት ነበር፥ እግዚአብሔር ሦስት ጊዜ ያሳየው) ስለነገረው ነው። ጴጥሮስ «እግዚአብሔር የቀደሰውን አታርክስ» የሚለውን ትምህርት የግድ መቀበል ነበረበት። በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ አሕዛብ ርኩሳን አልነበሩም። እግዚአብሔር የፈጠረው ምግብም ለእግዚአብሔር ሕዝብ ርኩስ አልነበረም፡፡ (ማቴ. 15፡11 እና 1ኛ ጢሞ. 4፡3-5 በመመልከት፥ ክርስቶስና ጳውሎስ ክርስቲያኖች የትኛውንም ምግብ ሊመገቡ እንደሚችሉ መግለጻቸውን አስተውል። ዛሬ ውሾችንና አሣማዎችን የማንበላው በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ችግር ስለሚያስከትሉ ሳይሆን፥ ከባሕላችን የተነሣ ስለማንፈቅዳቸው ነው።

መ. ጴጥሮስ አሕዛብ ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ ፈቀደ፡- በግልጽ ባይነገረንም፥ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሦስት ሰዎች አሕዛብ ሳይሆኑ አይቀሩም። ከቤት ውጭ እንዲቀመጡ በማድረግ ፈንታ፥ ጴጥሮስ ከራሱ ጋር እንዲቆዩ አድርጓል። በዚህ ጊዜ ከአሕዛብ ጋር በመኖሩ ምክንያት እረክሳለሁ የሚለው ፍርሃቱ ተወግዶአል።

ሠ. ጴጥሮስ አሕዛብ ወደ ይሁዲ እምነት ሳይለወጡ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተገነዘበ፤ መልአኩ ከቆርኔሌዎስ ጋር እንዴት እንደ ተገናኘ ሲሰማ፥ «እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ» አስተዋለ (የሐዋ. 10፡34-35)። ከዚያም ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስና በቤቱ ለተሰበሰቡት ስለ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ እንዲሁም እግዚአብሔር የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን እንዴት እንደ ፈጸመ በመግለጽ አስተማረ። ጴጥሮስ ንስሐ ገብተው እንዲያምኑ ከመጠየቁ በፊት፥ መንፈስ ቅዱስ በአሕዛብ አማኞች ላይ ወረደ። እነዚህ አሕዛብ ጴጥሮስ ካሰማው ስብከት ወንጌሉን ተረድተው በክርስቶስ ስላመኑ፥ መንፈስ ቅዱስ በፍጥነት ወረደባቸው። በቆርኔሌዎስ ቤት ከተፈጸሙት ነገሮች መካከል በርካታ አስፈላጊ ነገሮችን መማር እንችላለን፡-

  1. ጴጥሮስ የመጨረሻውን የወንጌል በር እንዲከፍት እግዚአብሔር ተጠቅሞበታል። እግዚአብሔር የወንጌልን በር ለአይሁዶች ለመክፈትና የሳምራውያኑን እምነት ለማረጋገጥ እንደ ተጠቀመበት ሁሉ፥ አሁንም የወንጌሉን በር ለአሕዛብ ለመክፈት በዚሁ ሐዋርያ ተገልግሏል።
  2. እግዚአብሔር አሕዛብ በእኔ ዘንድ ተቀባይነት የምታገኙት የአይሁድ እምነትን ስትቀበሉ፥ ስትገረዙ የብሉይ ኪዳንን የአመጋገብ ሕጎችና ሌሎች ሥርዓቶችን ስትከተሉ ነው አላላቸውም። የጠየቃቸው ነገር ቢኖር በክርስቶስ አምነው እምነታቸውን በተለወጠ ሕይወት አማካይነት እንዲያሳዩ ብቻ ነበር።
  3. አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደሚያስተምሩት፥ መንፈስ ቅዱስ የመጣው ከደኅንነት በኋላ ዘግይቶ አልነበረም። በታሪኩ ላይ እንደምናነበው ባመኑበት ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ መጣ።
  4. መንፈስ ቅዱስ የወረደው ጴጥሮስ እጁን በጫነባቸው ጊዜ እልነበረም። ገና ጴጥሮስ ሲናገር ሳለ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው። መንፈስ ቅዱስ የመጣላቸው በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ እንጂ፥ በጸሎት አልነበረም። ይህ ሁኔታ መንፈስ ቅዱስ በአንድ መንገድ ብቻ እንደማይመጣ ያሳያል።
  5. መንፈስ ቅዱስ እንደ መጣ የተረጋገጠው በልሳን በመናገራቸው ነበር። ይህ ምልክት መንፈስ ቅዱስ መጀመሪያ በኢየሩሳሌም አይሁዶች ላይ በወረደ ጊዜ ታይቷል። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፥ መንፈስ ቅዱስ በሳምራውያኑ ላይ በወረደ ጊዜ በልሳን ሲናገሩ አላየንም። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ክርስቲያኖች በደረጃ እንደማይበላለጡ ለአይሁዶች ሊያሳይ ፈለገ። ቤተ ክርስቲያን የታነጸችው በአይሁዶች ወይም በልሳን በሚናገሩ ወይም መንፈሳውያን በሚመስሉ ወይም በአሕዛብ ወይም ልሳን በማይናገሩ ወይም መንፈሳዊያን በማይመስሉ ሰዎች አይደለም። በክርስቶስ አካል ውስጥ ሊኖር የሚገባውን አንድነት ለማሳየት፥ እግዚአብሔር ለአይሁድና ለአሕዛብ እማኞች ያንኑ አንዱን መንፈስ ቅዱስ ሰጣቸው። ራሱ ጴጥሮስ ሲናገር፥ «እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ» (የሐዋ. 10፡47) ይላል። ይህ መንፈስ ቅዱስ በልሳን የተገለጸበት ሁኔታ፥ የአይሁድ ክርስቲያኖችን አስደነቃቸው።
  6. ከዚህ ነገር በኋላ መንፈስ ቅዱስ በአይሁድና በሰማርያ ሰዎች ላይ በወረደው ዓይነት በእጅ መጫን ሥርዓት፥ በአሕዛብ ክርስቲያኖች ላይ ሲወርድ የሚያሳይ መረጃ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ አናገኝም። በልሳን መናገር ለመጀመሪያዎቹ የአሕዛብ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስን ለመቀበላቸው መረጃ ነበር። በኋላ ጳውሎስ ለሌሎች የአሕዛብ ክርስቲያኖች እንደ ገለጻው፥ ይህ ከመንፈሳዊ ስጦታዎች አንዱ ስለሆነ ብዙዎቹ በልሳን አልተናገሩም (1ኛ ቆሮ. 12፡29-30)።
  7. የአሕዛብ ክርስቲያኖች ካመኑና መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ወዲያው ተጠመቁ።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እገሌ ከዚህ ጎሣ ነው፥ እገሌ ከዚያ ጎሣ ነው የሚለው አስተሳሰብ ስፍራ ሊሰጠው አይገባም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ለጴጥሮስ እንዳመለከተው፣ በዘርና በጎሣ መካከል እርሱ አያደላም። ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ በመሆናቸው፥ ሁሉም እኩል ናቸው። ክርስቶስ ሰዎችን ሁሉ እኩል ስለሚወድ፥ ባመኑበት ጊዜ ሁሉንም በእኩል ደረጃ ይቅር አላቸው። በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት፥ አማኞች ሁሉም እኩል ስለሆኑ ባሕላቸውን መለወጥ አያስፈልጋቸውም። ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አይሁድ ወይም አሕዛብ ብሎ ልዩነት እንደሌለ ገልጾአል (ቆላ 3፡11)። እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ የጎሣ ልዩነቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተው መከፋፈልን እንዳያስከትሉ ወይም የአንድ ጎሣ አባላት ተቀባይነትን እንዲያገኙ ባሕላቸውን በመለወጥ እኛን እንዲመስሉ በምናስገድድበት ጊዜ፥ ይህን የእግዚአብሔርን ቃል ትምህርት እናፈርሳለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጎሠኝነትና ጎሣዊ ትዕቢት፥ አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከፋፈልን ያስከተሉት እንዴት ነው? ለ) የጴጥሮስ ራእይና ከአሕዛብ ጋር የነበረው ግንኙነት ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እኩልነት መስፈን ስላለበት ጉዳይ ምንን ያስተምሩናል?

እግዚአብሐር፥ አይሁዶች የቤተ ክርስቲያን አካል እንዲሆኑ አይሁዳዊነታቸውንና ብሉይ ኪዳንን እንዲተው አላስገደዳቸውም። አሕዛብም በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ የራሳቸውን ባሕል ትተው አይሁዶች እንዲሆኑም በግድ አልጠራቸውም። ምክንያቱም በአንዱ የክርስቶስ አካል ውስጥ፥ ከተለያየ ጎሣ፥ ባሕልና አገር የሚመጡ ሰዎች በቂ ስፍራ ስላላቸው ነው። እግዚአብሔር «ልዩነታችንንም ሆነ አንድነታችንን» ይወድዳል። ነገር ግን በእኛ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ሌሎች እንደ እኛ እንዲሆኑ ስናስገድዳቸው ደስ አይለኝም። እግዚአብሔር የቤተሰቡ አባላት የሆኑ ሁሉ በተለያዩ ባሕሎቻቸውና ቋንቋዎቻቸው ደስ እየተሰኙ አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ይሻል። በራእይ 7፡9-10 ላይ እንደተመለከተው፥ ከተለያዩ ጎሣዎችና ቋንቋዎች የመጡ ሰዎች፥ ለክርስቶስ በዙፋኑ ፊት እንደሚሰግዱለት ተጽፎአል። ሁላችንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ምግባራዊ ሕጎች መታዘዝ ቢኖርብንም፥ ሰዎች በእግዚአብሔር ወይም በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኙ ባሕላቸውን እንዲለውጡ ማስገደድ የለብንም።

ረ. ጴጥሮስ የአሕዛብ ክርስቲያኖችን እያስተማረ አብሯቸው ሰነበተ። ጴጥሮስ በዚህ ጊዜ፥ እግዚአብሔር አሕዛብን እንደ ተቀበለና በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ አድልዎ ስፍራ እንደሌለው ተገንዝቦ ነበር።

ይሁንና ጴጥሮስ በዚህን ጊዜም ቢሆን፥ ከአድልዎ አሳብ አልተላቀቀም። አድልዎ ከሕይወታችን ውስጥ ነቅሎ ለመጣል፥ እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑ ክፉ ነገሮች አንዱ ነው። ጳውሎስ እንደ ገለጸው፥ ቆርኔሌዎስ ድነትን (ደኅንነትን) ካገኘ ከብዙ ዓመት በኋላ፥ ጴጥሮስ ከአሕዛብ ጋር የነበረውን ኅብረት አቋርጧል። ጴጥሮስ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ አይሁዳዊነትን የሚያጎሉና መከፋፈልን የሚያስከትሉ ነገሮች ክልክል መሆናቸውን የዘነጋበት ጊዜ ነበር። (ገላ. 2፡11-16 አንብብ።)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: