- የጳውሎስ አገልግሎት በኢቆንዮን፥ በልስጥራንና በደርቤን (ሐዋ. 14፡1-20)
ሉቃስ ለሦስት ዓመት ያህል የዘለቀውን የጳውሎስንና የበርናባስን አገልግሎት ያቀረበው አጠር ባለ ዘገባ ነው። ኢቆንዮን ከአንጾኪያ 100 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት። ጳውሎስ በምኩራብ ለአሕዛብ ወንጌልን ከሰበከ በኋላ፥ ብዙ ሰዎች በክርስቶስ አመኑ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም ጳውሎስና በርናባስ በዚያ ለተወሰነ ጊዜ ተቀመጡ። ሉቃስ በዚህ ስፍራ ተአምራት ከተፈጸሙበት ምክንያቶች ውስጥ አንዱን ገልጾአል። “ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለመሰከረው ስለጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ተቀመጡ” ብሏል (የሐዋ. 14፡3)። ነገር ግን አይሁዶች አሁንም ከባለሥልጣናት ጋር ያላቸውን ዝምድና ተጠቅመው አሕዛብን በጳውሎስና በርናባስ ላይ አስነሡ። ስደቱ እየጠነከረ ሲመጣ ወንጌላውያኑ ከኢቆንዮን 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ልስጥራን ሄዱ።
አንዳንድ ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ ስደት ከመነሣቱ በፊት ከአካባቢው ሲርቁ፥ ሌላ ጊዜ ግን (ለምሳሌ በደርቤ) እዚያው ቆይተው ስደቱን ሲቋቋሙ መመልከት አስገራሚ ነበር። ክርስቲያኖች ስደትን የሚመለከቱት በአንድ መንገድ ብቻ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ከስደቱ መሰወር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስደቱን በጽናት መጋፈጥ ሊያስፈልግ ይችላል። መንፈስ ቅዱስ ለእያንዳንዱ አማኝ የትኛውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ይመራዋል። ስለዚህ በስደት ውስጥ በሚያልፉ ሰዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ነገር ከመናገር መጠንቀቅ አለብን፡፡ ቁም ነገሩ እግዚአብሔርን መታዘዙ እንጂ፥ በሕይወት መኖሩ አይደለም፡፡
በልስጥራን ጳውሎስና በርናባስ እንደ ልማዳቸው ወደ ምኩራብ እንደ ሄዱ ያልተጠቀሰው በአካባቢው ጥቂት አይሁዶች ብቻ ይኖሩ ስለነበር ነው። ነገር ግን አንዲት አይሁዳዊት ሴትና ጢሞቴዎስ የተባለ ሰው በልስጥራን ከተማ ውስጥ ይኖሩ ነበር። እነዚህን ሰዎች ወደ ክርስቶስ ያመጣቸው ጳውሎስ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል ጉዞው ተመልሶ ሲመጣ፥ ጢሞቴዎስን በአገልግሎቱ ረዳት እንዲሆነው ወስዶታል።
ጳውሎስ በልስጥራን ለአሕዛብ በሚሰብክበት ጊዜ አንድ ሽባ ሰውዬ በወንጌሉ እጅግ ተደንቆ ነበር። ጳውሎስ ይህን ግለሰብ ሲፈውስ ያዩ የከተማዋ ሰዎች በሙሉ ተደነቁ፡፡ በልስጥራን ከተማ “ዚዎስ” (ድያ) የሚባል የታወቀ ጣዖት ነበር፡፡ በግሪክ ሃይማኖት፥ ዚዎስ ሄርሜን የሚባል ቃል አቀባይ ነበረው። በአንድ ወቅት ዚዎስና ሄርሜን ልስጥራንን እንደ ጎበኙ የሚያወሳ አፈ ታሪክ አለ። ሕዝቡ ተአምሩን በተመለከቱ ጊዜ ዚዎስና ሄርሜን እንደገና አካባቢውን ለመጎብኘት የመጡ መሰላቸው። በርናባስ ዝምተኛና በሳል ሰው በመሆኑ እርሱን ዚዎስ አሉት። ተናጋሪው ጳውሎስ በመሆኑ እርሱን ደግሞ ሄርሜን ብለው ጠሩት። መሥዋዕት ለመሠዋት ወደ ዚዎስ ቤተ መቅደስ የመጡ ሰዎች ለበርናባስና ለጳውሎስ ለመሠዋት ተነሡ። ይናገሩ የነበሩት በገዛ ቋንቋቸው በመሆኑ፥ መጀመሪያ ጳውሎስና በርናባስ ምን ለማድረግ እንዳሰቡ አላወቁም ነበር። ነገር ቀን ሰዎቹ እንደ አማልክት እያዩአቸው መሆኑን ሲገነዘቡ፥ ወንጌላውያኑ በታላቅ ኀዘን ልብሳቸውን ቀደዱ። ለሕዝቡም እንደ እነርሱ ሰዎች እንጂ አማልክት እንዳልሆኑ ገለጹላቸው። እነዚህ ሰዎች ስለ ብሉይ ኪዳንና ስለ እግዚአብሔር ማንነት የሚያውቁት ነገር ስላልነበራቸው ጳውሎስ ምስክርነቱን ከፍጥረት ታሪክ ጀመረ። ጳውሎስ ፈጣሪው እግዚአብሔር እንጂ፥ እነዚህ ግዑዛን የሆኑ ጣዖታት ኃጢአታቸውን ይቅር እንዳላሏቸው ገለጸላቸው፡፡ እርሱም ለሰብሎቻቸው ዝናብ፥ ለእነርሱም ምግብና የልብ ደስታ የሚሰጥ ቸር አምላክ እንደሆነ አብራራላቸው። አሁን ግን ለእርሱ ምላሽ መስጠት እንደሚገባቸው አሳሰባቸው። በዚህ ጊዜ ስለ ክርስቶስና ስለ ድነት (ደኅንነት) የተናገረው ነገር የለም። ሰዎች ወንጌልን ከመረዳታቸው በፊት ስለ እግዚአብሔርና ስለ ኃጢአት፥ መዳንም እንደሚያስፈልጋቸው መገንዘብ አለባቸው። ይህ ደግሞ ጊዜ ይፈልጋል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ለልስጥራን ሰዎች ያቀረበውን ስብከት ለኢቆንዮን ሰዎች ካቀረበው ጋር አነጻጽር። ምን ልዩነቶች ይታዩሃል? ለ) ይህ ወንጌልን በሰሚዎቻችን ዳራ ላይ ተመሥርቶ ለለማቅረብ አስፈላጊነት ምን ያስተምረናል? ሐ) ለሙስሊምና ለሃይማኖተኛ ለመመስከር ከፈለግህ፥ ለሁለቱ ሰዎች የምታቀርበው ምስክርነት እንዴት ይለያያል?
ጳውሎስና በርናባስ በልስጥራን ብዙ ጊዜ ለመቆየት አልቻሉም። የኢቆንዮንና የአንጾኪያ አይሁዶች በየሄዱበት እየሄዱ ብጥብጥ አስነሡባቸው። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ከስደት አላመለጠም፤ እንዲያውም እስከ ሞት ድረስ በድንጋይ ተወገረ፡፡ እግዚአብሔር ግን ጳውሎስን ከሞት ታደገው። በዚያ በሚገኙ ጥቂት አማኞች እርዳታ በተከታዩ ዕለት ጳውሎስና በርናባስ ከልስጥራን 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ደርቤን ሄዱ።
- ጳውሎስና በርናባስ ወደ አንጾኪያ ተመለሱ (የሐዋ. 14፡21-28)
በደርቤን ብዙ አማኞች ከመኖራቸው በስተቀር በዚያ ስለነበራቸው አገልሎት ምንም የተነገረን ነገር አልነበረም። በሶርያ ወደምትገኘው አንጾኪያ መመለስ አለብን ብለው ስላሰቡ ጳውሎስና በርናባስ በመልስ ጉዟቸው ወቅት ልስጥራን፥ ኢቆንዮንና ጲስድያን ጎበኙ። (ማስታወሻ፡- አንጾኪያ የሚባሉ ሁለት ከተሞች ስላሉ በጥንቃቄ ልንለያቸው ይገባል። አንደኛዋ በትንሹ እስያ ስትገኝ፥ ሁለተኛይቱ በእስያ ውስጥ ናት)። በዚህ ጊዜ ትኩረት ያደረጉት በአማኞች ላይ ነበር። እንደ ክርስቶስ ሁሉ፥ ጳውሎስና በርናባስም ጌታን መከተል ስለሚያስከፍለው ዋጋ ከመናገር አልተቆጠቡም ነበር። ክርስቶስን ስንከተል መንገዱ የመስቀልና የመከራ መንገድ ነው። ስለሆነም፥ «ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል» ብለው አስተማሯቸው (የሐዋ. 14፡22)። የኢየሱስ ተከታዮች የሆንን ሰዎች እምነታችንን ከመደበቅ ይልቅ በእምነታችን ጸንተን መከራውንም ሆነ በረከቱን ልንካፈል ይገባል።
የውይይት ጥያቄ- ሀ) ክርስቲያኖች፥ በተለይም ወጣቶች መንግሥተ ሰማይ ከመግባታችን በፊት እኛ ክርስቲያኖች ልንቀበለው ስለሚገባ መከራ ብዙም የማይናገሩት ለምንድን ነው? ለ) ስለ መስቀሉ በረከት ብቻ መናገር ሳይሆን፥ ስለሚቀበሉትም መከራ አስቀድሞ መግለጹ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ጳውሎስና በርናባስ የወንጌል መልእክተኞች ሆነው ወንጌልን ወደ አዳዲስ አካባቢዎች እንዲያደርሱ ልከዋቸው ነበር። ምእመናንም የወንጌል መልእክተኞቹን በጸሎት ይደግፉ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስና በርናባስ እግዚአብሔር በገላትያ ቤተ ክርስቲያንን ለመመሥረት እንዴት እንደ ተጠቀመባቸው ለመግለጽ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተመለሱ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)