የኢየሩሳሌሙ ጉባኤ ስለ ብሉይ ኪዳን ሕግ ሚናና ስለ አሕዛብ ተወያየ (የሐዋ. 15፡1-35)

በአስተምህሮ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የአሳብ ልዩነት በሚከሰትበት ጊዜ፥ ቤተ ክርስቲያን ምን ልታደርግ ይገባል? መሪዎች ችግሩ በራሱ ጊዜ ይፈታል ብለው ዝም በማለት መጠባበቅ አለባቸው ወይስ ጥቂት መሪዎች ብቻቸውን በጉዳዩ ላይ ውሳኔ መስጠት አለባቸው? የውሳኔው መሠረት ምን መሆን አለበት? የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጉዳይ ላይ ያደረገችው ምንድን ነው? በአሁኑ ጊዜ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች የሚሰጡት አስተያየት ምንድን ነው? የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የአሳብ ልዩነቶችን የፈታችው እንዴት ነው?

የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ያሳሰባት የመጀመሪያው ዐቢይ ችግር ሰው ለመዳን ምን ማድረግ አለበት? የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ አንድ ሰው ለመዳን የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ሙሉ በሙሉ መከተል አለበት? እግዚአብሔር ይቀበላቸው ዘንድ አሕዛብ መገረዝና የአይሁድን እምነት መቀበል አለባቸው? በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል በነበረው ዘመን መገረዝ ለአይሁዶች የእግዚአብሔር ሕዝብ ለመሆናቸው እንደ ትልቅ ምልክት ይወሰድ ነበር። ስለሆነም፥ አይሁዶች መገረዝ ለድነት (ለደኅንነት) አስፈላጊ ነው ብለው ያምኑ ነበር።

ቤተ ክርስቲያን እያደገች ስትመጣ ብዙ ካህናት በክርስቶስ እንዳመኑ ቀደም ሲል ተመልክተናል (የሐዋ. 6፡7)። ከእነዚህም መካከል የብሉይ ኪዳንን ሕግጋትና በየዘመኑ በአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች የተሰጡትን ደንቦች አጥብቀው የሚከተሉ ፈሪሳውያን ይገኙበት ነበር (የሐዋ.15፡5)። እነዚህ የአይሁድ ክርስቲያኖች አንድ ሰው የሚድንበት ብቸኛው መንገድ ልክ እንደ አይሁዶች በመገረዝና የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በመጠበቅ ነው ብለው ያስቡ ነበር። አሕዛብ በክርስቶስ ከማመናቸው በተጨማሪ ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ሕግጋትንም መጠበቅ እንደሚገባቸው ገለጹ። በእነርሱ አስተሳሰብ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ማድረግ የሚቻለው በክርስቶስ ከማመን በተጨማሪ የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት በመጠበቅ ነበር። ከእነዚህ አጥባቂ ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ ከኢየሩሳሌሟ ቤተ ክርስቲያን 150 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ አንጾኪያ ሄደው ነበር። የአሕዛብ ቁጥር ብዙ በሆነበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሕዛብ ሙሉ ክርስቲያኖችና እግዚአብሔር የሚቀበላቸው አማኞች ለመሆን ከፈለጉ፣ የአይሁድን እምነት ተቀብለው መገረዝና የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት መጠበቅ አለባቸው በማለት ማስተማር ጀመሩ።

ለአሕዛብ ሐዋርያ የነበረው ጳውሎስ እንዲሁም በርናባስ፥ ድነት (ደኅንነት) በክርስቶስ ብቻ እንደሚገኝ በመግለጽ ይህንን ትምህርት አጥብቀው ተቃወሙ። ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግ፥ አሕዛብ የአይሁድን እምነት መቀበል አያስፈልጋቸውም ነበር። ይህም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከፋፈልን ፈጠረ። አንዳንዶች ከአይሁድ ክርስቲያኖች ጎን ሲሰለፉ፣ ሌሎች ከጳውሎስና ከበርናባስ ጎን ተሰለፉ። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ይህ ነገረ መለኮታዊ ጉዳይ ትልቅ ችግር እንደሆነ ተገነዘቡ። ስለሆነም፥ ጳውሎስና በርናባስ በኢየሩሳሌም ወደምትገኝ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰው እግዚአብሔር ኃይልን ከሰጣቸው ሐዋርያት ጋር በመሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ እንዲወስኑ አደረጉ። ይህ የኢየሩሳሌም ጉባኤ፥ ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያዎቹ ሦስት ምእተ ዓመታት ውስጥ ካካሄደቻቸው በርካታ ነገረ መለኮታዊ ሙግቶች የመጀመሪያው ነበር። ይህ ሙግት የድነትን (የደኅንነትን) መንገድ የሚመለከት ነበር።

ጥያቄ:- ሀ) ቤተ ክርስቲያን አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ለማድረቅ የሚችልበትን መንገድ በተመለከተ፥ ግልጽ አቋም መያዝ ያለባት ለምንድን ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ በሰዎች ሕሊና ውስጥ ስለ ድነት (ደኅንነት) መንገድ፣ ስለ ተወሰኑ ሕጎችና ደንቦች ውዥንብር ይፈጠራልን? እንዲህ ዓይነቱን ውዥንብር ስለተመለከትህበት ሁኔታ አብራራ። ሐ) የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ብትሆን ኖሮ፥ ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በክርስቶስ በማመን እንጂ ባሕልን በመለወጥ ወይም የብሉይ ኪዳንን ደንቦች በመጠበቅ እንዳልሆነ የሚያመለክተውን እውነት እንዴት ታሳይ ነበር?

ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነገረ መለኮታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ አያሌ የአሳብ ልዩነቶች ይከሰታሉ። በሥላሌ፥ በመንፈስ ቅዱስ፣ በልሳን፣ በተአምራት፥ በብዝሃ ጋብቻ፥ በአምልኮ ስልቶችና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ያሉት ግንዛቤዎች የተለያዩ ናቸው። እነዚህን ልዩነቶች ቸል ከማለት ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩን በማንሣት በግልጽ መወያየት ይኖርባታል። የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን አርአያ በመከተል ነገረ መለኮታዊ ልዩነቶቻችንን ስለምናስተናግድበት መንገድ ጠቃሚ ነጥቦችን ልንመለከት እንችላለን።

ሀ. ክርስቲያኖች ሁሉ እግዚአብሔር ስለሚሠራበት መንገድ እንዲሰሙ የተደረገበት ጠቅላላ ስብሰባ ተካሄደ። ጳውሎስና በርናባስ በሄዱባቸው ስፍራዎች ሁሉ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ቤተ ክርስቲያኑን ስለሚመሠርትበት ሁኔታ ሪፖርት አቅርበዋል። በዚህ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ አንዳንዶች፣ አሕዛብ መገረዝ አለባቸው የሚል አመለካከት ሲያንጸባርቁ ነገረ መለኮታዊ ጉዳዩ በግልጽ ተብራርቷል። ጳውሎስና በርናባስ የእነዚህን ወገኖች አሳብ በመቃወም፥ አሕዛብ ለመዳን በክርስቶስ ማመን ብቻ እንደሚበቃቸው ሳይገልጹ አላለፉም።

ለ. የቤተ ክርስቲያን መሪዎች (ሐዋርያትና ሽማግሌዎች) ለብቻቸው ተሰበሰቡ፡፡ ሰፋ ያለ ነገረ መለኮታዊ እውቀት የሌላቸው ምእመናን አንዳንድ ውስብስብ ነገረ መለኮታዊ ልዩነቶችን ላይረዱ ይችላሉ። ስለሆነም፥ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ የሚያውቁና የእግዚአብሔርን መንጋ የመምራት ኃላፊነት ያላቸው ወገኖች፥ ጊዜ ወስደው ጉዳዩን በጥልቀት መመርመር ይኖርባቸዋል።

ሐ. መሪዎቹ የእግዚአብሔርን አሠራር ታሪክ መረመሩ፡፡ የቀድሞውን ተሞክር ዘወር ብለው ተመለከቱ። ጴጥሮስ እግዚአብሔርን ላመኑት አሕዛብ ሳይገረዙ መንፈስ ቅዱስን ስለተቀበሉበት ሁኔታ አብራራ። እግዚአብሔር ለአሕዛብ በክርስቶስ ማመናቸው ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ለማድረግ በቂ እንደሆነ አሳይቶ ነበር። አይሁዶችም ቢሆኑ ብሉይ ኪዳንና የአይሁድ ሥርዓት ለአንድ ሰው ሸክሙ እንጂ ወደ እግዚአብሔር እንደማያቀርቡት ያውቃሉ፡፡ ሥርዓቶቹን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም እንደማይቻል ያውቃሉ። ስለሆነም፥ ጴጥሮስ፥ «በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን» (የሐዋ. 5፡11) ሲል በሕይወቱ ያየውን እውነት ጠቅሷል፡፡

መ. ሁለቱም የወንጌል መልእክተኞች የወቅቱን ሁኔታና የእግዚአብሔርን እጅ መገለጥ ተናገሩ። ጳውሎስና በርናባስ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ተአምራት በመሥራት እምነታቸውን እንደ ተቀበለው አስረዱ። (በእናት ቤተ ክርስቲያናቸው በኢየሩሳሌም፥ ሉቃስ የበርናባስን ስም ከጳውሎስ ማስቀደሙን ልብ በል። የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በርናባስን ታውቀውና ታከብረው ስለነበርም በርናባስ ዋነኛው ቃል አቀባይ ሆነ።)

ሠ. መጽሐፍ ቅዱስን መረመሩ። የኢየሱስ ወንድም የነበረውና በዚህ ጊዜ የኢየሩሳሌሟ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ መሪ የነበረው ያዕቆብ፥ ጴጥሮስ፥ በርናባስና ጳውሎስ የተናገሩት አሳብ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተናገረው ጋር እንደሚስማማ አረጋገጠ። መጽሐፍ ቅዱስ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ስለሚመጡበትና ከአይሁድ ጋር እኩል ስፍራ ስለሚያገኙበት ዘመን ተንብዮ ነበር። ብሉይ ኪዳን አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት በመጀመሪያ የአይሁድን እምነት መቀበል እንዳለባቸው አልተናገረም።

ረ. ውሳኔው። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውሳኔ የመጣው በሁለት ደረጃ ነበር፡፡ አንደኛው፥ መሪዎቹ የቤተ ክርስቲያንን እምነት በግልጽ በመዘርዘር፣ ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በክርስቶስ በማመን እንጂ በውጫዊ የግዝረት ሥርዓት ወይም የአይሁድን እምነት በመቀበል እንዳልሆነ አስረዱ። በክርስቶስ ከማመን በተጨማሪ ሌላ ሥርዓት መደንገግ ወንጌሉን እንደሚለውጥና ይህም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መዳን ሊሆን አይችልም። ማንም ሰው በራሱ ጥረት ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለማድረግ አልቻለም፡፡ ይህ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በፈጸመው ሥራ ብቻ በመደገፍ የሚገኝ ነው። ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች በዚህ እምነት ላይ ይታገላሉ። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች ወንጌሉን እያብራሩ ሳለ «በክርስቶስ ስታምንና መጠጥ ስታቆም ትድናለህ» ይላሉ። በወንጌሉ ላይ ሰው ሠራሽ ሥርዓት በመጨመር ወደ እግዚአብሔር የሚያስኬደውን መንገድ የሰው ሥራ ያደርጉታል። አንዳንድ ወንጌላውያን ለዘላኖች በሚመሰክሩበት ጊዜ፥ «በክርስቶስ በማመን፥ ልብስ በመልበስ እንደ ሌሎች ደገኛ ኢትዮጵያውያን በመኖር፥ እርሻ በማረስና ተጨማሪ ሚስቶችህን በመፍታት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ታገኛለህ» ይላሉ። በወንጌሉ ላይ የራሳቸውን ትምህርት በመጨመር ወንጌሉን ይለውጡታል። በዚህም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኘው በሥራ እንጂ በእምነት እንዳልሆነ ያስተምራሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ብዙ ክርስቲያኖች ድነት (ደኅንነት) በክርስቶስ በማመን ሳይሆን፥ እነርሱ በሚፈጽሙት ተግባር እንደሚገኝ በማሰብ ግራ ሲጋቡ የተመለከትኸው እንዴት ነው?

ሁለተኛው፥ ሐዋርያቱ አይሁድና አሕዛብ በሚገኙበት ቤተ ክርስቲያን አንድነትን ለማምጣት አንዳንድ ደንቦችን አወጡ። እነዚህም ሁለት ዓይነት ደንቦች ነበሩ።

  1. እግዚአብሔር በየትኛውም ዘመን ከሚኖር ሕዝቡ የሚጠብቃቸው ሁሉን አቀፍ ትእዛዛት አሉ። ዝሙት የአሕዛብ ሕይወትና አምልኮ አካል ስለነበር፣ ያዕቆብ አሕዛብ የእግዚአብሔርን ሕግ በመታዘዝ ከዝሙት መራቅ እንዳለባቸው ገለጸ። ይህ ክርስቲያኖች ሁሉ ከዝሙት መራቅ አለባቸው የሚለው ጉዳይ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን የተጠቀሰ በመሆኑ፥ በየትኛውም ዘመን ያሉ ክርስቲያኖችን የሚመለከት ትእዛዝ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ታዲያ ዛሬ፥ ለዚህ የማይለወጥ የእግዚአብሔር ትእዛዝ የይገዙ ብዙ ክርስቲያኖች አሉ።
  2. አሕዛብ ከፍቅር የተነሣ አይሁዳውያን ወንድሞቻቸውንና እኅቶቻቸውን ላለማስቀየም ብለው የሚጠብቋቸው ደንቦች ነበሩ። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው።

ሀ. ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ አለመብላት። አሕዛብ በግ ወይም በሬ ወደ ቤተ ጣዖት መውሰድ፥ ለቤተ ጣዖቱ አምላክ አሳልፎ መስጠትና ማረድ ልማዱ ነበራቸው። ከሥጋው የተወሰነው ለጣዖቱ መሥዋዕት ሆኖ ሲቃጠል፥ የቀረው ወደ ቤት ተወስዶ ይበላል ወይም ሥጋ ቤት ተወስዶ ይሸጣል። የአይሁድ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ሥጋ መብላት በጣዖት አምልኮ ላይ እንደ መሳተፍ ስለሚቆጥሩት፥ ከገበያ ሥጋ የሚገዙ አሕዛብ ክርስቲያኖችን ለመቀበል ይቸገሩ ነበር። ስለሆነም፥ ያዕቆብ ከአይሁድ ክርስቲያኖች ጋር ለመተባበር ይችሉ ዘንድ አሕዛብ ክርስቲያኖች ይህን ሥጋ እንዳይበሉ ጠየቀ። ጳውሎስ ወደ በኋላ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የበለጠ ግልጽ ማብራሪያዎችን ሰጥቷል (1ኛ ቆሮ. 9፡10፤ ሮሜ 14-5)።

ለ. ከብቱ በትክክል ታርዶ ደሙ መሬት ላይ ያልፈሰሰውን ሥጋ አለመብላት። ስለሆነም፥ ታንቀው የተገደሉ እንስሳት ሥጋን እንዳይበሉ ተከልክለዋል፡፡

ሐ. ደም አለመጠጣት፡፡ (ማስታወሻ፡ ክርስቲያኖች ደም ያለመጠጣቱ ትእዛዝ ለአይሁዶች ብቻ ወይም ለክርስቲያኖች ሁሉ ስለ መሰጠቱ አንድ ዓይነት አሳብ የላቸውም። ስለሆነም፥ ዛሬ አንዳንድ ክርስቲያኖች ደም መብላት ተገቢ መሆኑን ሲያስተምሩ ሌሎች ግን ይቃወማሉ።)

መ. ውሳኔው በመሪዎች (ሐዋርያትና ሽማግሌዎች) እና በቤተ ክርስቲያን ተደገፈ፡፡

ሠ. አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የመሪዎቹን ምክንያቶች እንዲያውቁና ክርክሩ እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ፥ ውሳኔአቸው እንዲጻፍ አደረጉ። ሐዋርያቱ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የወሰኑትን አሳብ በመግለጽ ለአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ደብዳቤ ጻፉ።

ረ. ከቤተ ክርስቲያናቸው በሙግቱ ውስጥ ካልተሳተፉ ሰዎች መካከል ወኪሎች ላኩ። ከበርናባስና ከጳውሎስ (ለቤተ ክርስቲያን የላኳቸው) ጋር ይሁዳንና ሲላስን ሰደዱ። (ሲላስ በሁለተኛው የወንጌል ተልእኮ ጉዞ ከጳውሎስ ጋር አግልግሏል)፡፡ እዚህ ወኪሎች (ልዑካን) ደብዳቤውን በማብራራት ሁሉም ሰው አንድምታውን በትክክል እንዲረዳ የማድረግ ኃላፊነት ነበረባቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ነገረ መለኮታዊ ክርክር ግለጽ። የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ምሳሌን በመከተል፣ የኢትዮጵያ ወይም የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንህ ችግሩን እንዴት ልትፈታ ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading